ስፖርት በዘመናችን ብዙ ነገር ነው። በተለይም በዓለም ሕዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የእግር ኳስ ስፖርት ለአንድ አገር፣ ማህበረሰብና ግለሰብ ተዘርዝሮ የማያልቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የማይስማማ አለ ተብሎ አይታሰብም።
ዓለማችን ከቅርብ አመታት ወዲህ በየአቅጣጫው ከገባችበት የፖለቲካ ውጥረት፣ የተለያዩ አይነት ጦርነቶች አኳያ እግር ኳስ ተጽእኖውን ከሚያሳርፍባቸው ጉዳዮች አንዱን የሰላም ጉዳይ መዘን ብንመለከት ስፖርቱ ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው መረዳት ይቻላል። በእርግጥ እግር ኳስ ለሰላም ያለውን ትልቅ አስተዋጽኦ አሁን ለስፖርት ቤተሰቡ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም ማስታወሱ ጉዳት የለውም።
በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም የቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ትልቁን አህጉራዊ ውድድር በቀጣይ አመት የምታዘጋጀው ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ኮትዲቯር ከሁለት አስርት አመታት በፊት ገብታበት ከነበረው የእርስበርስ ጦርነት ለመውጣት እግር ኳስ የነበረውን ሃይል የሚያስታውስ ይሆናል።
እኤአ በ2000 የበርካታ ከዋክብት እግር ኳስ ተጫዋቾች አገር የሆነችው ኮትዲቯር በከባድ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር። በዚህ አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ህጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ነፍሰ ጡሮች በአጠቃላይ የአገሪቷ ንጹህ ዜጎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት ጊዜ ነበር። በዚህም ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር በቀላሉ ወደ ማትወጣው ቅርቃር ውስጥ ለመዘፈቅ ተገዳለች።
በወቅቱ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት እንደታየው በኮትዲቯር ፖለቲከኞች ዘንድም ከልክ ያለፈ የስልጣን ጥማት፣ አፍቃሪ ንዋይና እና ዝና እንጂ ፈጽሞ ለሰዎች ሕይወት ቅንጣት ታህል የማያስቡ ልባቸው የስልጣን ወንበርን ብቻ የተጠማ ባለስልጣናት ለስልጣን እና ለሆዳቸው ይሻሙ ነበር፤ በመሃል ንጹሃን፣ ለነገ ተስፋ ያላቸው ህጻናት እንዲሁም በርካታ ዜጎች በእርስ በርስ ጦርነቱ ሕይወታቸው ተቀጠፈ።
ደም አፋሳሹ የእርስ በእርስ ጦርነት መፍትሄ አግኝቶ የንጹሃን ሕይወት መቀጠፉ አንድ ቦታ መቋጫ ከማግኘት ይልቅ እየቀጠለ ሄደ። ለአምስት አመት በተካሄደው ከባድ ጦርነት ሳቢያ የኮትዲቯር በርካታ ዜጎች የሚበላ ቀርቶ የሚቀመስ ብርቅ እየሆነባቸው ሄዶ ብዙዎች ተራቡ።
መፈንቅለ መንግስት ሊያደርግ ያሰበው አሸባሪ ቡድን ተደብቆ መላ አገሪቷን ያሸብራትም ነበር። በዚህ ነገሮች ከመርገብ ይልቅ እየተባባሱ በሄዱበት ወቅት ዝሆኖቹ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ብርቱካናማ ማልያ ለባሹ የአገሪቱ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለፍ የሱዳን አቻውን ገጥሞ ድል ቀናው።
ዝሆኖቹ በወቅቱ ሱዳንን ሲያሸንፉ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የአገሪቱ የምንጊዜም ኮከብ ተጫዋችና በዓለም እግር ኳስ ላይ ተጽእኗቸው ጎልቶ ከሚነገሩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዲዲየር ድሮግባ የአገሪቱ እርስ በእርስ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን እና በብሔራዊ ቡድኑ ድል ሁሉም እንዲደሰት ቢናገርም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሽኩቻው ቀጠለ። ነገሮች ከመስተካከል ይልቅ ተባባሱ። የስልጣን ጥማቱ እና የወንበር ሽሚያውም ቀጥሎ ንጹሃን መቀጠፋቸው ቀጠለ።
እኤአ በ2007 በዲዲዬር ድሮግባ የሚመራው የኮትዲቫር ብሔራዊ ቡድን ከማዳጋስካር ጋር ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ በወቅቱ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ካፍ በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ ወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ ድሮግባ ደጋግሞ ባደረገው ጥረትና ልመና ከኮትዲቫር ውጭ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በኮትዲቫር እንዲደረግ ተወሰነ። በወቅቱ ካፍ በውሳኔው ተቃውሞ የነበረው ቢሆንም ድሮግባ ጨዋታው በአገሩ መደረግ የፈለገበትን አላማ ነግሮ የካፍን ባለስልጣናት በማሳመን ጨዋታው በዝሆኖቹ ሜዳ ሊካሄድ ቻለ።
ጨዋታውን ኮትዲቫር ስታሸንፍ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረውም የቁርጥ ቀን ልጇ ዲዲዬር ድሮግባ ነበር። ይህ ታላቅ ኮከብ በወቅቱ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአገሩ ኮትዲቯር በሁለት ወገን እየተደረገ የሚገኘው እና ብዙዎች እየሞቱበት የነበረውን ጦርነት እንዲቆም ተማጸነ። ከጨዋታው በኋላም በድሮግባ አማካይነት ተጫዋቾች ተሰባስበው “እኛ ብዙ ሀብት አለን፤ ለምን እርስ በእርስ እንገዳደላለን፤ ንጹሃን ለምን ይገደላሉ፤ ምርጫ አድርገን ሰላም እንድናሰፍን በፈጣሪ ስም እንለምናችኋለን” በማለት ተማጸኑ።
ይህ የዝሆኖቹ ተማጽኖ ኮትዲቯርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን አስለቀሰ ፤ ሁለቱ ወገኖችም ይህንን አይተው አዘኑ። በፖለቲካ ልዩነቶቻቸው ዙሪያ ለመነጋገር ወሰኑ። ተነጋግረውም ጦርነቱን በመግታት እና ተኩስ አቁም በመፈራረም ዓለም ቢለምናቸው አልሰማም ያሉ በሁለት ጽንፍ የቆሙ የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች በእግር ኳስና እግር ኳስ ተጫዋቾች ተማጽኖ በአካል ተገናኝተው ተመካከሩ።
ምርጫ እንዲያደርጉ ወሰነም ሂደቱ በሰላም ተጠናቆ ያ ሰላም የናፈቀው ሕዝብ ፤ ያ የተራበ ሕዝብ ዳግም ሰላምን አገኘ። የዓለም ሃያል መንግስታት የተሳናቸውን እግር ኳስ ሰላምን ፈጠረ። አሁን ላይም ኮትዲቯር ከዚያ አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ከአመታት በኋላ የ2023 ታላቁን የአፍሪካ ዋንጫ ለማሰናዳት ሽርጉዷን የጀመረች አገር ሆናለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም