ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ የካቲት 6 ቀን 1924 ዓ/ም ከአባቱ ከመምሬ ገብረ ዮሐንስ ተሰማና ከእናቱ ከወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተ ወልድ አዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ አጥቢያ ተወለደ:: ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በዚሁ ደብር ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሟል:: ዳዊቱን በቃሉ ጭምር ያውቀው ስለነበረ የዳዊት መጽሐፍ ባላገኘ ጊዜ በዓቢይ ጾም ዳዊት በሚተዛዘልበት ወቅት በቃሉ ያስተዛዝል ነበረ።
ቀጥሎም የዜማ ትምህርት ከመሪጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ወንበር ዘርግተው ከሚያስተምሩት ዘንድ ገብቶ ጾመ ድጓን ዘልቋል:: በዚያን ጊዜ ከየደብሩ 2:2 ልጆች እየተመረጡ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ጥሪ ስለደረሰ ከሁለቱ ተመራጮች አንዱ ሆኖ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ገብቶ በዘመናዊ ትምህርት ስምንተኛን ክፍል አጠናቅቆ ሁለተኛ ደረጃ እንዳለ ወደ ግሪክ አገር እንዲሄድ ተመረጠ። በ1943 ዓ/ም ወደ ግሪክ አገር ሄዶ ቆሮንጦስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቋል::
እዚያ በነበረ ጊዜ ዝንባሌው ግልጽ እየሆነ ሄደ:: ፍልስፍና ትምህርት ላይ ትኩረት ስለአደረገ የፍልስፍናን መጽሐፍት በብዛት እየገዛ ያነብ ነበር::
የቆሮንጦስን ትምህርት ቤት ሲጨርስ ንግግር እንዲያደርግ የተወሰነው እርሱ ላይ ነበር:: ንግግሩ ቅደም ተከተሉ የሠመረ ብቻ ሳይሆን ለለጋ ዕድሜው ጥልቅ የፍልስፍና ሐሳብን ያዘለ ሆነ:: በዚያን ጊዜ በወቅቱ የአቴን ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ መምህራን እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር:: እጓለ ንግግሩን ሲጨርስ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ከመቀመጫው ተነሥቶ ሒዶ ስሞ አመስግኖታል::
አቴን ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ ትምህርትን ከፍልስፍና ጋር አዛምዶ አእምሮውን ያንጽ ጀመር:: ለትምህርት የነበረው ፍቅር በአርዓያነት የሚጠቀስ ነበር:: የተወሰነውን የአራት ዓመታት ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ጀርመን አገር ሄዶ ቦን ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና ፉክልቲ ተመዝግቦ ያ የሚጓጓለትን ፍልስፍና ይዋኝበት ጀመር::
በዘመኑ ከቦን ዩኒቨርሲቲ በዓለም መድረክ የታወቁ መምህራን ያስተምሩ ነበር:: የእነርሱን ትምህርት ሳያስታጓጉል በጥንቃቄ ያዳምጥ ነበር:: በግልም እያነጋገረ ስለ ፍልስፍና ትምህርት አጠናንና አቀራረብ መመሪያ ይቀበል ነበር:: ይህም አልበቃ ብሎ በሌላ ዩኒቨርሲቲ አንቱ የተባሉና በዓለም መድረክ ያንጸባረቁ ለምሳሌ ፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ Martin Heidegger ሀይደልበርግ ዩኒቨርሲቲ Karl Jaspers ያስተምሩ ስለነበር እዚያ ያሉበት ድረስ እየሄደ ትምህርታቸውን አዳምጧል::
ሁለቱም እንደሚታወቀው Existentalist Philosophers ናቸው:: የ Martin Heidegger የታወቀው ሥራ “ጊዜና መሆን” Time and Being የሚለው ምን ያህሉንም እጓለን ያረካ አልመሰለኝም የ Jaspers ን “እውነት” Von der Wahrheit የሚለውን ግን ከአንደበቱ የማይለየው ነበር: ሁሉንም ባይሆንም እንኳ አብዛኛዎቹን የዚህን ፈላስፋ ድርሰቶች ገዝቶ ከግል ቤተ መጻሕፍቱ አከማችቷል:: ምናልባት ወደዚህ ፈላስፋ መንፈሱ ያጋደለው ሚዛናዊና ኃላፊነት የተሞላ አስተሳሰብ ስላለው ሳይሆን አልቀረም::
ቀደም ካሉት ፈላስፋዎች የሚያደንቃቸው አፍላጦንን ፕሌቶንና ኢማኑኤል ካንትን ነበር:: የአፍላጦን “ሪፑብሊክ” የካንትን “የንጹሕ አእምሮ ሒስ” Critique of Pure Reason የሚባሉትን አዘውትሮ ደጋግሞ አንብቧቸዋል:: መጽሀፍቱ ምናልባትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ለጥቆ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደቡ ሳይሆኑ አልቀረም::
ቦን ዩኒቨርሲቲ የዶክተር ማዕረግ ካገኘ በኋላ ምኞቱ በከፍተኛ ተቋም ለማስተማር ስለነበረ የማስተማርን ዘዴ ለማጠናከርና የእንግሊዝኛ ዕውቀቱን ለማጎልበት እንግሊዝ አገር በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ቆይቶ በ1953 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ:: ወዲያው ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመድቦ ፍልስፍናን ማስተማር ጀመረ::
በዚያን ጊዜ ነው ፍልስፍና ለበስ ንግግሮችን በተከታታይ በሬዲዮ ለሕዝብ ያሰማ የነበረው:: እነዚህንም ኋላ አሰባስቦ “የከፍተኛ ትምሀርት ዘይቤ” በሚል ርእስ አዲሰ አበባ በ 1956 ዓ/ም መጽሐፍ አሳትሟል:: በዚህም በኢትዮጵያ አስተሳሰብና በምዕራብ አስተሳሰብ መካከል ድልድይ ሠርቷል::
ይህም በአገሩ በዘመናዊ አዋቂዎች ታሪክ ግንባር ቀደም እንዲሆን አስችሎታል :: ከዚሁ ጋር መጥቀስ የሚገባው በአስተማሪነቱ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የታወቀውን መምህር አብራራው በመባል የሚታወቀውን ፕሮግራም ስያሜውንም የሰጠ ፕሮግራሙንም የጀመረ ዶ/ር እጓለ መሆኑን ነው::
በ1956 ዓ/ም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውሮ በቦን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖ ሠርቷል:: እዚያም 6 ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ተዛውሮ በአማካሪነት ማዕረግ የክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግሏል:: በ 1965 ዓ/ም የመምሪያ ኃላፊ ሆኗል::
ከኅዳር ወር እስከ ሰኔ ወር 1970 ዓ/ም በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካሪ ሆኖ ሠርቷል:: ከጥር 1 ቀን 1972 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ተገለለ:: ከዚያን ጊዜ እስከ ዕለተ ሞቱ ባለው ዕድሜ ከፈጸማቸው ሥራዎች በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱሰ ማኅበር አማካይነት የግዕዙን ሐዲስ ኪዳን ለማሻሻል በተቋቋመው ቡድን ያደረገው አስተዋፅኦ ጎላ ብሎ የሚታይ ነው:: ሐዲስ ኪዳንን በተለይ ጳውሎስን በእናቱ በግሪኩ ዘር በቃሉ ጭምር የሚያውቀው በመሆኑ የእርሱ ድርሻ የላቀ እንደነበር ይገመታል::
1983 ዓ/ም እንደሚባለው ለእጓለ ጎደሎ ዓመት ነው:: ይህ ዓመት ከገባ አንሥቶ ፈጽሞ ጤና አልነበረውም:: ዓመቱ ሲጋመስ እንዲሁ ጤንነቱ ተጋመሰ:: እዚሁ አዲስ አበባ ሐኪም ቤት ገባ፤ ግን ሕመሙ አልተሻለውም:: ለተሻለ ሕክምና ናይሮቢ ኬንያ ተላከ:: ሕክምናው አሁንም ውጤት አላሳየም:: መጋቢት 23 ቀን 1983 ዓ/ም በናይሮቢ ኬንያ ዐረፈ:: አስከሬኑ በአይሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተጓጉዞ መጋቢት 26 ቀን 1983 ዓ/ም ሥርዓተ ቀብሩ በቀራንዮ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ:: ወሩ ይለያይ እንጂ ወር በገባ በ23 አባቱ ያረፉበቱ ዕለት ነው:: አባት ልጃቸውን ጠሩ ልጅም ለአባቱ ታዘዘ::
ዶ/ር እጓለ ሚያዝያ 8 ቀን 1964 ዓ/ም ከወይዘሮ እህትአፈራሁ ተስፋዬ ጋር በቁርባን ታጋብቶ 3 ልጆችን አፍርቷል:: (የቅርብ ጓደኛቸው ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ እንደጻፉት)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም