አዲስ አበባ፡- የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ብርሃን የላኪውንም የተላላኪዎቹንም ተንኮል ያፈረሰ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለእየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው፤ የትንሣኤው ብርሃን የላኪውንም የተላላኪዎቹንም ተንኮል አፈረሰው። ወጥመዳቸውንም በጣጠሰው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስናና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። የዲያብሎስና የሦስቱ የጥፋት ተላላኪዎች ተንኮል የተሳካው ለሦስት ቀናት ብቻ ነው ብለዋል።
ይሁዳም 30 ብሩን ሳይጠቀምበት ታንቆ ሞተ። የአይሁድ ካህናትም እንኳንስ ሊሳካላቸው በ70 ዓመተ ምሕረት ሀገራቸውን ጥለው ለሺህ ዓመታት ተሰደዋል። ሮማውያንም ቀስ በቀስ ግዛቶቻቸውን እየለቀቁ ሄደዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዛሬም አለ። የትንሣኤው በዓል ይሄንን ነው የሚመሰክርልን ሲሉ ገልጸዋል።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤው ተበስሮ እውነትና ደግነት ድል አድርገው እስኪታዩ ድረስ፣ ክፋትና ውሸት እንደ ቋጥኝ ገዝፈው ታይተዋል፣ እንደ ተራራ የማይነቀነቁ ሆነው መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ትንሣኤ የአራት ወገኖችን ሤራ ያፈረሰ ነው። በቃሉ ትምህርት በእጁ ተአምራት ያልተደሰቱ፤ የአዳምን ጥፋት እንጂ የአዳምን ድኅነት የማይፈልጉ፤ በእነርሱ መንገድ ካልሆነ በቀር ምንም ነገር ለመቀበል ፈቃደኞች ያልሆኑ አራት ወገኖች የሠሩት ወጥመድ በትንሣኤው ተወግዷል ብለዋል።
የሤራው ጠንሳሽ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ነው። ምንም ቢሆን በሰው ልጆች ላይ ያለውን አቋም የማይቀይር የጥንት ጠላት ነው። የሰው ልጆች እርሱ በሚፈልገው የክፋትና የስሕተት መንገድ ቢሄዱለት እንኳን፣ ጠላታቸው መሆኑን አይቀይረውም። ዓላማው የሰውን ልጅ ማጥፋት እንጂ ከሰው ልጅ ጋር ወዳጅነት መፍጠር አይደለምና ሲሉ አስረድተዋል።
አሠራሩንና አካሄዱን የሚያውቁ፤ የሐሰትና የክፋት አባት መሆኑን የተረዱ፤ የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት መሆኑን የተገነዘቡ ብቻ ተንኮሉንና ክፋቱን ያውቁበታል። ሌሎች ግን እርሱ ባጠመደው ወጥመድ ወድቀው ከገዛ ወገኖቻቸው ጋር ሲጋጩና ሲፋጩ ይገኛሉ ብለዋል።
ዲያብሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሦስት ተላላኪዎችን አሠማርቶ ነበር። እነዚህ ሦስት ተላላኪዎች ከዚያ ቀን በፊት እርስ በርሳቸው የማይስማሙ፤ አንድ ዕቅድ ዐቅደው፣ አንድ ሥራ ሠርተው፣ ለአንድ ግብ ሊሠማሩ የማይችሉ ናቸው። ዲያብሎስ ያደረገው አንድ ነገር ነው። የጋራ ጠላት ፈጠረላቸው። የጋራ ዓላማ ግን አልፈጠረላቸውም ሲሉ ገልጸዋል።
ጠላታቸውን የሚያጠፉበት ምክንያት የተለያየ ነው። ጠላታቸውን ለማጥፋት ያላቸው ፍላጎት ግን አንድ ነው። ዲያብሎስ ሦስቱን ሲያሠማራ የያዘው አላማው የሰው ልጅን እንዳይድን ማድረግ ነው። ሦስቱም ተላላኪዎች ሳያውቁት የዚህ ዓላማ ፈጻሚዎች ናቸው። እነርሱ ግን ለየራሳቸው ዓላማ የተሠማሩ መስሏቸው ነበር ብለዋል።
የሚገርመው ነገር፣ በመጨረሻ ሦስቱም ተላላኪዎች ጠፍተዋል። ቢሸነፍም ያልጠፋው የላካቸው ዲያብሎስ ነው። ምንጊዜም የጥፋት ተላላኪ ዕጣ ፈንታው ይሄ ነውና ሲሉ ገልጸዋል።
ዲያብሎስም የአዳምን ድኅነት ለማስቀረትና በምድር ላይ ብቸኛ ገዥ ሆኖ ለመኖር ለጥፋት ያሰማራቸው ሦስት አካላትን ይሁዳ፣ የአይሁድ ካህናትና ሮማውያን ናቸው። ይሁዳ ዓላማው ገንዘብ ነው። ለገንዘብ ራሱንም ጭምር ለመሸጥ ዝግጁ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው የሐዋርያነት ክብርና ሥልጣን ለእርሱ ምኑም ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የአይሁድ ጥያቄ ደግሞ የጥቅም ጥያቄ ነው። ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን እየበዘበዙ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ሮማውያን ደግሞ በዚያን ጊዜ መካከለኛው ምሥራቅን በቅኝ ይገዙ ነበር። ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን እየበዘበዙ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ የነጻነትን ወንጌል አስተማራቸው። አዲስ ሕይወትና አዲስ መንገድ አሳያቸው ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ፤ ይሄን ነገር ከኢትዮጵያ አንጻር መመልከቱ መልካም ነው። ዛሬም ከኋላ ሆኖ ሀገራችንን ለማፍረስ ወጥመድ የሚያጠምድና ተንኮል የሚሠራው ጠላት ማነው? ምንም ብናደርግለት ይህችን ሀገር ካላጠፋ በቀር የማይረካው ማነው? ብሎ መመልከት ይገባል።
ይህ ጥንተ ጠላት የሚያሠማራቸው የጥፋት ተላላኪዎቹስ እነማን ናቸው? አንዳንዶቹ ለገንዘብ፣ ሌሎቹ ለጥቅም፣ ሌሎቹም ለሥልጣን ብለው ከዚህ ጥንተ ጠላት ጋር የሚሠሩት እነማን ናቸው? እነዚህ የጥፋት ተላላኪዎች የራሳቸውን ፍላጎትና ዓላማ የሚያሳኩ መስሏቸው ይሆናል፤ ይሁንና አይሳካላቸውም ብለዋል።
ይሁዳም ከሥሯል፤ የአይሁድ ካህናትም ከሥረዋል። ሮማውያንም ከሥረዋል። የጥፋት ተላላኪዎች መጨረሻ እንደዚህ ነውና። ለጊዜው የማይገናኙ ተገናኝተው፤ የማይተባበሩ ተባብረው፤ አጥፊና ጠፊ ተወዳጅተው፣ በክርስቶስ ላይ ሲነሡ፤ ለጊዜው የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር። መጨረሻው ግን ኪሣራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሡ ሁሉ ለጊዜው የሚሳካላቸው ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻቸው ኪሣራ ነው። ጥቂት ቀናት የተሳካላቸውና ያሸነፉ ቢመስላቸውም ኢትዮጵያ ሞተው እንደሚቀሩ ሀገራት አይደለችም። ጠላቶቿንም ታሳፍራለች፤ አሳፍራም ታከሥራቸዋለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም