ሕዝበ ክርስቲያኑ ለሃምሳ አምስት ቀናት በፆም በፀሎት ቆይቶ እነሆ ነገ ፆመ ልጓሙን ይፈታል። የፋሲካ በዓልም በነገው እለት በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በዓሉ በተለይ ደግሞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በኩል በተለየ ሁኔታ ይከበራል።
በዓሉ ከሚከበርባቸው መንገዶች አንዱ ሕዝበ ክርስትያኑ ዶሮ፣ በግ፣ ፍየልና በሬ በማረድ የእነዚህን እንስሳት ስጋ በተለያየ መልኩ በማብሰልና በመመገብ ሲሆን የነዚህ እንስሳት ገበያም በዚህ በዓል ወቅት በተለየ ሁኔታ ይደራል። ምእመኑ ለረጅም ጊዜያት በፆም የቆየና ከቅባታማ ምግቦች የራቀ እንደመሆኑ መጠን ታዲያ እነዚህን የእንስሳት ተዋፅኦዎች ሲመገብ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በስነ ምግብ ባለሙያዎች ይመከራል።
አቶ ቢራራ መለሰ በጤና ሚኒስቴር የስርአተ ምግብ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የፋሲካ በዓል ሲታሰብ በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከእንስሳት ተዋፅኦና ከቅባታማ ምግቦች ለረጅም ጊዜያት ታቅበው ቆይተው እነዚህን ምግቦች የሚመገቡበት ነው። ሰዎች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጥራጥሬ ምግቦችን ሲመገቡ ቆይተው የእንስሳት ተዋፅኦዎችንና ቅባታማ ምግቦችን ወደ መመገብ ሲዞሩ በሰውነት ውስጥ የምግብ መፈጨት ለውጥ ስለሚኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ምግቦች በብዛት ከመውሰድ ይልቅ በመጠኑ እንዲወስዱም ይመከራል። ቀደም ሲል ሲመገቡ የነበሩትን ምግቦች ከስጋና ከቅባት እህሎች ጋር በመቀላቀል ቢመገቡም ይመረጣል።
እንደ አቶ ቢራራ ገለፃ እንዲህ አይነቱ የአመጋገብ ስርአት ወቅታዊ ወይም ፆምን ታክኮ የሚደረግ ብቻ መሆን የለበትም። ለአብነትም በፆም ወቅት ሰዎች በየአይነት ሲመገቡ ከእንስሳት የማያገኟውና ከእህል ዘሮች የሚያገኟቸው ሰውነት ገምቢ ምግቦች አሉ። በሽታን የሚከላከሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦችም አሉ። በተመሳሳይ ኃይል ሰጪ በርካታ የምግብ አይነቶችም በስፋት ይገኛሉ።
ከዚህ አኳያ ሰዎች በፆም ወቅት የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአት ሲከተሉ ቆይተዋል ማለት ነው። በፋሲካ በዓል ወቅትም ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአትን ሊከተሉ ይገባል። አትክልትና ፍራፍሬዎችም በስርአተ ምግባቸው ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከእንስሳት ተዋፅኦዎችም በተመጣጠነ መልኩ በስርአተ ምግብ ውስጥ መጨመር አለባቸው።
ስጋን ብቻ መመገብ የራሱ ጠቃሚ የምግብ ንጥረ ነገር ያለው ቢሆንም በፆም ፍቺ ወቅት ከአትክልትና ፍራፍሬዎች ጋር በማመጣጠን መመገብ ቢቻል የተሻለ ይሆናል። በተቻለ መጠን ተፈጥሮ ባስቀመጠቸው መሰረት ሰዎች የእንስሳት ተዋፅኦዎችን ሲመገቡ የእህል ዘሮችን፣ የአትክልትና ፍራፍሬዎችን ሳይተውና በማመጣጠን መሆን ይኖርበታል። ሁሉም ነገር ከመጠን በላይ ሲሆን ትርፍ ነውና ለሰውነት ተስማሚ አይሆንም። ውፍረት ያስከትላል። ውፍረት ሲመጣ ደግሞ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል።
አቶ ቢራራ እንደሚናገሩት ሰዎች ለረጅም ጊዜ በፆም ምክንያት የእህልና የአትክልት ምግቦችን ሲመገቡ ቆይተው ወደ ስጋና ቅባታማ ምግቦችን ወደ መመገብ ሲሸጋገሩ ጊዜያዊ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል። በተለይ ደግሞ ሰውነት የለመደውና ለምግብ መፈጨት ጠቃሚ የሆኑና ቅባት የሚፈጩ ኢንዛይሞች በፆም ወቅት ስራቸው ስለሚቀንስ ሰዎች በቀጥታ ወደ ቅባታማና የስጋ ምግቦች ወደ መመገብ ሲዞሩ ድንገተኛ የጤና ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ጠቃሚ ንጥረ ምግቦች ወደ ሰውነት ሴሎች ላይገቡም ይችላሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት ታዲያ ሰዎች የስጋና የቅባት ምግቦችን በትንሽ መጠን ቀስ በቀስ እያስለመዱ መመገብ ይኖርባቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች እነዚህን የስጋ ተዋፅ ኦዎችንና ቅባታማ ምግቦችን ብሎም አልኮልን ከበቂ በላይ ሲወስዱ በሰውነታቸው ውስጥ ከበቂ በላይ ሊከማች ይችላል። ይህ ክምችት ታዲያ የደም ቧንቧዎችን ሊያጠብ ይችላል። አላስፈላጊ የሽንት ክምችትም ያስከትላል። ይህም ለደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኩላሊት፣ ካንስርና ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል።
የፋሲካ በዓል ቢሆንም፣ ዶሮው፣ በጉ፣ ቅርጫው ሁሉ የተትረፈረ ቢሆንም ይህን ሁሉ የስጋ ተዋፅኦ ከሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ፤ እንዲሁም የእህል ዘር ምግቦች ጋር አመጣጥኖ መመገብ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ቅባት በበዛባቸው ምግቦች ምክንያት የተዛባ አመጋገብ ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ በበዓል ወቅት ትልቅ የአመጋገብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014