
በኢትዮጵያ በየክልሉና ከተማ አስተዳደሮቹ በርካታ ስታዲየሞች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ። ሁሉም ስታዲየሞች ግን የፊፋን መስፈርት በጠበቀ መልኩ የተገነቡ አይደሉም። ይህን ተከትሎም እገዳ ተጥሎባቸዋል። በእዚህ የተነሳም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ አልቻሉም። ደረጃቸውን ለመጠበቅና ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ እየተሞከረ ቢሆንም፣ አገሪቱ ላሉበት ወሳኝ ግጥሚያዎች ሊደርሱላት አልቻሉም።
እንደ አዲስ አበባ ስታዲየም ያሉትም እድሳታቸው ሊጠናቀቅ አልቻለም። ሌሎች ስታዲየሞች የማጠቃለያ ስራ ይቀራቸዋል፤ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉት የግንባታ መሳሪያዎችና ግብአቶች የሚመጡት ግን ከውጭ አገራት መሆኑና ይህን ማግኘት ደግሞ ከክልሎቹ አቅም ጋር ሲዳመር የማጠናቀቂያ ጊዜያቸውን ሊርቅ የግድ ሆኗል።
የስታዲየሞቹ ጉዳይ በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው እንግዲህ የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከተፍ ያሉት። በችግሩ ላይ ችግር። ይህ ኮትዲቯር አስተናጋጅ የሆነችበት የአፍሪካ ዋንጫ ሊካሄድ አንድ ዓመት ብቻ ነው የቀረው። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) በውድድሩ ተካፋይ ለመሆን የሚችሉ አገራትን ለመለየት የሚያስችለውን የማጣሪያ ውድድር ለማድረግ የምድብ ድልድል ከሰሞኑ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ጥቂት ሳምንታት ብቻ በሚቀሩት መጪው ግንቦት 2014 ዓ.ም እንደሚጀመሩ አሳውቋል። ይኸውም በስፖርት ቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ጉዳይ ሆኗል።
የስጋት ምንጭ የሆነው ይኸው ጉዳይም ኢትዮጵያ ከወራት በፊት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተቀመጠውን የስታዲየም መስፈርት ባለማሟላቷ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ውድድር ማስተናገድ እንደማትችል ማሳወቁ ነው። ባለፉት ጊዜያትም እገዳውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በሌሎች አገራት ሜዳ በመከራየትና ልዩ ልዩ ወጪዎችን በማድረግ መጫወታቸው ይታወቃል። ይህም ሁኔታ አገሪቱን ውድ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እንድታወጣ አስገድዷታል።
በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ የውጪ ምንዛሬ እጥረት በስፋት አጋጥሟታል። በእዚህ የተነሳም በርካታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወኑ አይደሉም፤ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ አንዱ የስታዲየም ግንባታ ነው።
በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ሁለተኛ ምዕራፍ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖትም በሚገባው ፍጥነት ሊሄድ አልቻለም። ይህም የሆነበት ምክንያት አንደኛ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ነው። ለግንባታው ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎችን ከውጪ ለማስገባት እንዲሁም ለተቋራጩ በውጪ ምንዛሬ የሚከፈለውን ገንዘብም እስካሁን መክፈል እንዳልተቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔ መውሰድ እንዳለበት በቅርቡ አስታውቋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከስታዲየሞቹ የግንባታ ችግር ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብለት ቆይቷል። ለዚህም ቁርጠኛ መሆኑን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ስታዲየሞቹ ካፍ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች አሟልተው ወደ ውድድር እንዲገቡ ለማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጾ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጉብኝቶችን ብሔራዊ ስታዲየሙ በሚገነባበት ስፍራ በመሄድ አድርገዋል። በክልሎች የሚገነቡና በተለያየ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ነገር ግን ግንባታቸው ያልተጠናቀቀና የቆመ ስታዲየሞችን በሚመለከትም ግንባታው ለምን እንዳልተጠናቀቀና እንደ ቆመ ምክክር በማድረግ የመፍትሄ ሀሳብ እንደሚወሰድም አስታውቆ ነበር።
በእርግጥ ሚኒስቴሩ በዚህ ላይ እየሰራ ይገኛል፤ ጨዋታዎች ግን በተለያዩ ምክንያቶች ቀድሞ በተያዘላቸው መርሃ ግብሮች መሰረት ሊቀጥሉ አለመቻላቸውን ታሳቢ ያደረገ አስቸኳይ ስራ መከናወን ነበረበት ።
ተጫዋቾች በራሳቸው ሜዳ አለመጫወታቸው ብዙ ችግር ያስከትላል። የአየር ጸባዩንና ደጋፊውን ማጣታቸውም ብዙ እድሎችን የሚዘጋባቸው መሆኑ ጉዳዩን አሁንም በእጅጉ አሳሳቢ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው ያላት ተሳትፎ እጅግ የዘገየና በረጅም ዓመታት ልዩነት የሚሳካ መሆኑ ይታወቃል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከካሜሮኑ ውድድር በአንድ ዓመት ልዩነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ችግሮቹን በመቅረፍና ጥንካሬው ላይ በመስራት በድጋሚ የመድረኩ ተሳታፊ ለመሆን የሚችልበት ምቹ ሁኔታም አለው። ይሁንና በሜዳው ሊያገኝ የሚችለውን መልካም አጋጣሚ በስታዲየሞች አለመኖር ምክንያት ሊያጣ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ግን ያሳስባል። ፌዴሬሽኑም ቢሆን በተጋጣሚዎቹ ሜዳ ለሚያደርገው ጨዋታ ከሚያወጣው ወጪ ባለፈ፤ በራሱ ሜዳ ለሚከናወን ጨዋታ ለሜዳ፣ ለተጫዋቾች መጓጓዣ እና ቆይታ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የሚከፍለውን ገንዘብ የሚሸፍንበት አቅም ይኖረዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ሌላኛው ራስ ምታት ነው።
ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ መፍትሄ መፈለግ ወቅቱ የግድ ይላል። ጨዋታዎች የግድ መካሄድ ይኖርባቸዋል። ግንቦት ነገ ነው። የሚመለከታቸው የስፖርቱ አካላት እና መንግስት ለእዚህ አስቸኳይ መፍትሄ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም