ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሳምንቱ መጀመሪያ ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖቻችን ትንሳኤንና ረመዳንን ምክንያት በማድረግ በቤተመንግስት ባዘጋጁት ማዕድ ማጋራት ላይ ከተናገሩት ፤ “…ነገ ጥሩ ይሆናል። አሁን የገጠመንን ፈተና እናልፈዋለን፤” ያሉት አባባል ዛሬ ከሚከበረው ስቅለትና ከሁለት ቀናት በኋላ ከሚመጣውን ትንሳኤ ጋር የሚያያዝ ሆኖ ስላገኘሁት፤”ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል፤” በሚል ባለፈው አመት የጻፍሁትን መጣጥፍ ወቅታዊ አድርጌ ተመልሸበታለሁ። በነገራችን ላይ አንዳንድ ነጻ ሀሳቦቼን ወይም አጀንዳዎቼን ሀገራችን ለምተገኝበት ወሳኝ መታጠፊያ (critical juncture)እንደ አዝማች እጠቀምባቸዋለሁ። በትውልዶች መካከል ከስንት አንድ የተገኘን ለውጥ ዳር ማድረስ የሞት ሽረት ትግልና ትንቅንቅ አድርገን ካላሳካነው ከዚህ በኋላ ይሄ ታሪካዊ አጋጣሚ ከእጃችን ከወጣ መልሰን አናገኘውም የሚል እንቅልፍ የሚነሳ ስጋት አለኝ። ይሄን ለውጥ ያሳካሉ ወይም አንዳንድ ስህተቶች ይሄን ለውጥ አደጋ ላይ ይጥላሉ ብዬ በለየኋቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የጻፎኋቸውን መጣጥፎች አጀንዳ እስኪሆኑ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር እያጣጣምሁ እደጋግማቸዋለሁ። እንደ ሙዚቃ አዝማች ትኩረት እንዲስቡ ስልቱንና ምቱን እየተከተልሁ እደጋግማቸዋለሁ። አንዳንድ መጣጥፎቼ ቢደገሙ ከዚህ ቅን እምነት በመነጨ መሆኑን ልብ ይሏል።
አዎ አጀንዳዎች ስጋ ለብሰው ነፍስ እስኪዘሩ ከተለያየ ንጻሬና ማዕዘን አንጻር እደጋግማቸዋለሁ። በዚሁ ጋዜጣ ላለፉት አራት አመታት ከጻፍኋቸው በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ መጣጥፎች ደርዘኑ እንኳ አጀንዳ ሆነው ቢፈጸሙ ለእኔ ከዚህ በላይ እርካታ የለኝም። ቢቸግረኝ በአንድ መጣጥፌ፤ “እውነት እነዚህ ሰዎች(ልሒቃኑንና መሪዎቻችንን መሆኑ ነው፤) ያነቡናል!? ያዩናል!? ጀሮ ሰጠው ያደምጡናል!?” በሚል በጋዜጠኞችና በሚዲያዎቻችን ስም ጥያቄ እስከ ማንሳት ደርሼ ነበር። ዛሬም ይሄ ጥያቄዬ መልስ እስኪያገኝ ሳልታክትና ተስፋ ሳልቆርጥ በብዕሬ ደጋግሜ እጮሀለሁ። ጋዜጠኝነት በተለይ እንዲህ ባለ ፈታኝ ጊዜ ከእንጀራ በላይ ነው። በተለይ በዚህ ቀውጢ ስዓት ያሉ ማህበራዊም ሆኑ መደበኛ ሚዲያዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ከሚያስቡት ገቢና ዕውቅና ባሻገር ታሪካዊ የዜግነት ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው ተረድተው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ሁሉ፤ ለጊዜያዊ አላፊና ጠፊ ጥቅም ሲሉ ሀገርንና ሕዝብን ረስዘው የሚቆመሩ ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው ቢታቀቡ ስቅለት፣ ስቅለት እንደሆነ አይቀርም።
ትላንት ስለፓለቲካ ትክክለኝነት ደግሜና ሰልሼ ያነሳሁት አጀንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ለብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተዘጋጀ ስልጠና ላይ በተዘዋዋሪ አንስተውታል። በአንቂነት (አክቲቪዝም) እና በፓለቲከኝነትና በልሒቃንነት መካከል የሚስተዋለውን መደባለቅ እንዲሁም የብልጽግና አመራር የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከፓርቲው ሕገ ደንብ አንጻር አንስተውታል። የብልፅግና ፓርቲ አካላት የእርስ በርስ እሰጥ አገባ ለአገር ሥጋት መፍጠሩን የኢትጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ባለፈው ሀሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበዋል። እኔም ይሄን የተልኮ መደባለቅ ፓለቲካዊ ኢትክክለኝነት እያመጣና ሀገርን ለአደጋ እየዳረገ ነው ያልሁት። ይህ ችግር ከጻፍሁበት በኋላ ወይም ሳልጽፍበት ቢቀረፍ ኖሮ መልሼ አልጽፍበትም ነበር።
በዛሬ መጣጥፌም “ዛሬ አርብ ቢሆን እሁድ ይመጣል፤”ያልሁት፤ ከአምናው ይልቅ የዘንድሮው አርብ ፈታኝ ቢሆንም በጽናት እጅ ለእጅ ተያይዘን ተስፋ ባለመቁረጥ እናልፈዋለን። እሁድ ይመጣል። ስቅለት አልፎ ትንሳኤ እውን ይሆናል። የተቀበረና ያበቃ የመሰለን ነገረ ስራችን እንደ እየሱስ ክርስቶስ መቃብር ፈንቅሎ ይነሳል። ዛሬ ቢጨልምም ይነጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪቫን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም እንዳሉት። እኔም አርብን እያሰብን አንቆዝምም። አርብ፣ አርብ እንደሆነ አይቀርም። እሁድ ይመጣል፤ በሚል እሳቤ ነው።
መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ የዛሬውን ስቅለትና ትንሳኤን ታሳቢ በማድረግ፤ “ዛሬ አርብ ስቅለት ቢሆንም እሁድ ትንሳኤ ይመጣል፤” የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል። ጨለማ፣ የምድር መናዎጥ፣ ክረምት፣ ሰደድ እሳት፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ መገፋት፣ መዋረድ፣ መገረፍ፣ መቸንከር፣ መሰቀል፣ መከዳት፣ መሸጥ፣ ወዘተረፈ አርብ ቢሆንም፤ መንጋቱ፣ ብርሀን በጨለማ ላይ መንገሱ፣ እውነት ውሸትን መርታቱ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ፣ መከበሩ፣ መፈወሱ፣ ትንሳኤ፣ ቀን መውጣቱ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ ክርስቶስ ሞትን ድልነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ማንነትን ኢላማ ካደረጉ ጥቃቶች፣ ሞቶች፣ መፈናቀሎች፣ የሀብት ንብረት ውድመቶች፣ ከችግር፣ ከድህነት፣ ከተመፅዋችነት፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከፈተና፣ ከወረርሽኝ፣ ከጭቆና፣ ከአፈና፣ ከጥላቻ፣ ከሴራ፣ ከደባ፣ ከሀሰተኛ መረጃ፣ ከከበባ፣ ከውጥረት፣ ከአክራሪ ብሔርተኝነት፣ ከትህነግ ርዝራዥ፣ ከሸኔ_ኦነግና ከጉምዝ ሽፍታ ጥቃት፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ወከባ፣ ከሱዳን ወረራ፣ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጫና፣ ከአለማቀፍ ሚዲያውና የመብት ተሟጋቾች የክስ ድሪቶ፣ በገዛ የተፈጥሮ ሀብታችን የበይ ተመልካች የነበርንባቸው ዘመናት፣ ወዘተረፈ ነጻ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት፤ ትንሳኤ’ችንን፣ ህዳሴ’ችንንና አብርኆታችን የምናይበት ቀን ይመጣል። እሁድ ይመጣል። ትንሳኤ ይሆናል።” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል።” እያልን በእምነት በተስፋ እንጠባበቃለን። ደግሞም ይሆናል።
ከስድስት አመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና እክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ ቤት ለመዋል፣ ተሽከርካሪ ወንበር/ዊልቼር/፤ አጓጓዥ/ወከር/ና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር። ለመልበስ፣ ለማውለቅ ፣ ውሃ ለመጠጣት፣ ለመመገብ ፣ ለመታጠብ ፣ ለመተኛት ፣ ለመነሳት የሰው እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። ስልክ ለማነጋገር ፣ የቴሌቪዥን ቻናል ለመቀየር እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። ሁሉ ነገሬ በሰው እርዳት ላይ የተመሰረተ ነበር። መላ ህይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር። ስራዬን አጣሁ። በጋዜጠኝነትና ኮሙንኬሽን ከአአዩ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ። ህልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ። በመጨረሻም ለጭንቀትና ለድብርት ተዳርጌ ነበር። አምና ደግሞ በኮቪድ 19 ተጠቅቼ በሞትና በሕይወት መካከል ነበርሁ። አርብ ነበርና!
እንዲህ አይነት ብዙ የሕማማት “አርቦችን” በህይወቴ እንዳሳለፍሁት ሁሉ እናንተም ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በህይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን ፣ ህማማትን፣ አርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም ። በግል ህይወታችሁ፣ በትምህርታችሁ፣ በፍቅራችሁ ፣ በትዳራችሁ ፣ በንግዳችሁ፣ በሕልማችሁ ፣ በራእያችሁ ፣ በድርጅታችሁ፣ በሀይማኖታችሁ፣ በጤናችሁ፣ በቤተሰባችሁ ፣ በማህበረሰባችሁ፣ በሕዝባችሁ፣ በሀገራችሁ፣ ወዘተረፈ ላይ አርብ ሆኖባችሁ / ቀን ጨልሞባችሁ / እንደ እየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ ፣ ተገምድሎባችሁ ፣ ታስራችሁ ፣ ተገርፋችሁ ፣ ተሰቅላችሁ፣ ተቸንክራችሁ፣ ተዋርዳችሁ፣ ተፈትናችሁ፣ ባመናችሁት ተክዳችሁ፣ በባልንጀራችሁ በ’30’ ዲናር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ ወዘተረፈ ይሆናል። ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ሊሆን ይችላል።አርብ ነውና!
ካለፉት ሁለት መቶ አመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳ ብንወስድ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ሺህ አርቦችን ፣ በድርቅ ፣ በርሀብ ፣ በቸነፈር ፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 67ቱ በርሀብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት ፣ እንደ …77 … 87 … ወዘተረፈ ያሉ ጠኔዎችን ፣ ችጋሮችን አሳልፈናል ። ዛሬም ከዚህ አዙሪት በቅጡ ሰብረን መውጣት አልቻልንም። እንደ ህዳር በሽታ ፣ ፈንጣጣ ፣ ከ76 ወዲህ ደግሞ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ፣ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ደግሞ ኮቪድ – 19 የእልቂት ጥላውን አጥልቶብናል። በግብፅ ፣ በደርቡሽ ፣ በቱርክ ፣ በእንግሊዝ ፣ በጣሊያን፣ በሱማሊያ ፣ በኤርትራ ተወረናል። ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎስምብን አልጠፉም። በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች አልፈናል ። ከዘመነ መሳፍንት እንኳ ብንጀምር በመሳፍንቱ ፣ በመኳንንቱ ፣ በነገስታቱ መካከል ለስልጣን፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የእርስ በእርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል። አጼ ቴዎድሮስ ፣ አጼ ዩሐንስ ፣ አጼ ምኒልክ ፣ ልጅ እያሱ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግስቱ፤ ጉዳቱና ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በእርስ በእርስ ግጭት ፣ ጦርነት ተፈትነዋል። የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና!
ካለፉት 50 አመታት ወዲህ በተቀነቀነ የማንነት ፓለቲካ የተነሳ በሀገራችን ጥላቻ ፣ ቂም ፣ በቀል ፣ ልዩነት ተጎንቁሏል ። ጎሳን ፣ ሀይማኖትን ፣ አይዶሎጂን መሰረት አድርገን ተጋጭተናል። ተጋድለናል። አብያተ ክርስቲያናትን ፣ መስጂዶችን አቃጥለናል ። ቀይ ፣ ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል ። እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን እሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ተጠይቀዋል ። የዚችን ሀገር ታሪክ እስከወዳኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ ተጨርሷል። በርስ በርስ ጦርነት በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠር ዜጋ አጥተናል። የሀገር ሀብት ወድሟል። ሀገር አጥተናል። ዛሬ ድረስ ከዚህ ሀንጎቨር አልወጣንም። በተለይ ባለፉት አራት አመታት ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ለማየት የሚዘገንኑ ፣ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል። የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !
በተለይ በትህነግ/ኢህአዴ 27 አመታት በፓለቲካ አመለካከታችን፣ በጎሳችን በጅምላ ተገርፈናል። ተገልብጠናል። ተሰቃይተናል። ተግዘናል። ተሰደናል። ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ፣ የመናገር ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ፣ የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል። በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል። በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል። ተረግጠናል። ተገፍተናል። ሀብታችንንና ሀገራችን በቀን በአደባባይ ተዘርፈናል። ሀገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች። የድሀ ጉሮሮ ታንቆና በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ፣ በቅንጦት፣ በደስታ፣ በፍሰሐ ተንደላቀዋል። እየተንደላቀቁም ነው።አርብ ነበርና!
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ዴሞክራሲን ነጻነትን መሸከም ተስኖን ፤ የፓለቲካ ምህዳሩ መስፋትን ለእኩይ አጋጣሚ ተጠቅመን ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል፣ ገለናል፣ ሮማውያን እንኳ ያላደረጉትን ዘቅዝቀን ሰቅለናል። ከእነ ህይወታቸው በእሳት አቃጥለናል። ወደ ገደል ጥለናል። ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ህጻን ብላቴና ብልት ሰልበናል። እህቶቻችንን ደፍረናል። ዛሬ ድረስ አግተናል። በሕዝብ ፣ በክልልና በዩኒቨርስቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀጣጠልና ሀገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል። ለፍፈናል።አርብ ነበርና!
ለእሁድ መዳረሻ ፣ ለትንሳኤ ፣ ለንስህ ፣ ለጥሞና፣ ለአንድነት ፣ ለፍቅር ፣ ለሰላም ለይቅርታና ለሕዳሴ መጀመሪያ በግብፅ አንድ አደረገን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም አስቻለን ። ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ደግሞ ወደ ሰውነታችን ፣ ወደ ቀደመው ማንነታችን እንድንሸበለል ያለ ልዩነት የሰው ልጅንና ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ ቫይረስ ሰደደብን። የእሁድ አጥቢያ ነውና!
“ዛሬ ስቅለት ቢሆንም ትንሳኤ ይመጣል።” እያልሁ እጽናና ተስፋ አደርግ ነበር ። ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን ፣ የማይነጋ ፣ ዙሪያው ገደል ፣ ተራራ ፣ ተስፋ ቢስ ቢመስልም፤ ነገ ቀን ይወጣል ፣ ይነጋል ፣ ደልዳላ ይሆናል እሁድ ይመጣል እያልሁ እጽናና ነበር ። እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም ። ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ። በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ። የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች እገዛና ማበረታት በነጻነት ጀምሬ’ለሁ። ተስፋዬ ለምልሟል ። በዋሻው መውጫ ብርሀን እየታየኝ ነው። ያቋረጥሁትን ትምህርቴን አጠናቅቄ ሶስተኛ ዲግሪዬን እሰራለሁ። በዚች ሀገራ የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬ ላይ እንዲህ ህልመኛ የሆንሁት አርብ አልፎ እሁድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው። ከስቅላቱ በኋላ ትንሳኤው እንደሚከተል በማመኔ ነው። እሁድ ይመጣል!
እየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደባት ፣ ከተተፋባት ፣ ከተገረፈባት ፣ ከተቸነከረባት ፣ እንደ ወንበዴ ፣ ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍ ፣ ነቀፋ ሳይገኝበት ፣ ሞት የተፈረደበት፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለባት ፣ ጎኑ ከተወጋባት “አርብ” በኋላ እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም። የጨለማ፣ የስቃይ፣ የመከራ፣ የፈተና፣ የውርደት፣ የግፍ ፣ የበደል ፣ የመገፈፍ ፣ የራቁትነት የመሰቀል ወዘተረፈ ተምሳሌት ጭምር እንጂ ። ኤልደር “ዛሬ አርብ ነው “ ያሉት ይሄን መሰሉን ቀን ፣ አመት ፣ ዘመን ነው። ዛሬ አርብ ነውና፤ ሆኖም መግነዙን ፈቶ ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ ፣ ሞትን ድል አድርጎ ፣ በብኩርና በሶስተኛው ቀን በድል ተነስቷል ። አርጓል ። በደሙ ዘላለማዊ ድህነትን ፣ በግርፋቱ ህያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል። ሀጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል። ከኦሪታዊ ሕግ፣ ከባርነት ፣ ከሀጢያት ነጻ አውጥቶናል።እሁድ መጥቷልና!
ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ሕዝብና ሀገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ፣ ፈተና፣ መከራ፣ ቸነፈር ፣ ርሀብ፣ ስደት ፣ መፈናቀል፣ ውርደት ፣ ግርፋት ፣ መቸንከር ፣ ደም መፍሰስ ፣ ስጋ መቆረስ ፣ ጀርባ መተልተል ፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት ፣ ጎን መወጋት ፣ የሾህ አክሊል መድፋት ፣ ወዘተረፈ አልፈዋል ። እልፍ አእላፍ አርቦችን አሳልፈዋል ። ዳሩ ግን የትንሳኤው እሁድ ይመጣል። እሁድ ይመጣልና!
ከፓለቲካ ስብራት ፣ ከጥላቻ ፣ ከስግብግብነት ፣ ከደባ ፓለቲካ ፣ ከድህነት ፣ ከእርዛት ፣ ከርሀብ ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከልዩነት፣ ወዘተረፈ ወይም ከአርብ ወጥተን፤ የሀኪሞችን ምክር ፣ የመንግስትን ማሳሰቢያ በመተግበር አርብን አልፈን እሁድን እናያለን። የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን አርብን አልፈን ለእሁድ እንበቃለን ። የብልፅግና ትልማችንን ለማሳካት ሌት ተቀን በመትጋት ፣ ሙስናን፣ ብልሹ አሰራርን ፣ ስንፍናን ፣ ዳተኝነትነት በማስወገድ አርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን ። እሁድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን ። ልዩነትን ፣ ጥላቻን ፣ ጎሰኝነትን፣ የታሪክ እስረኝነትን ፣ የሴራ ፓለቲካን ወይም ብዙ አርቦችን በጽናት በብርታት አልፈን ለትንሳኤና ለህዳሴ / ለእሁድ እንበቃለን ። ደግሞም እናምናለን ይሆናል። “ዛሬ ስቅለት ቢሆንም ትንሳኤ ይመጣል !”
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም