የእውነት የልቤን ሀሳብ በአጭሩ የገለፀልኝ ስለሚመስለኝ ከልቤም ከአፌም አላጠፋውም “ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም፤ ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፤” የሚለውን የከያኔውን ግጥም። እንዲህ በዓል ደርሶ ፤ አገራችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ታምሳና ተመሰቃቅላ ባለንበት በዚህ ወቅት ደግሞ ፅድቁን ፈልገን ሳይሆን እንደው ለራሳችን ለውስጣችን እርካታ ብለን ደግ ደጉን ማሰብና ደግ ስራ መስራት እንዳለብን ይሰማኛል። ስለዚህ በዚህ ወቅት ይሄንኑ ለማለት ተነስቻለሁ።
እንዲህ የበዓል መዳረሻ ላይ ስንደርስ በልባችን ብዙ ሀሳቦች ይመጣሉ። በተለይ አብሮነቱ፤ ሰብሰብ ብሎ በዓልን ማክበር ከልብ የማይጠፋ ትዝታን አዝለን በየሄድንበት ይከተለናል። ተካፍሎ ተሰጣጥቶ ያለው ለሌለው አካፍሎ ማለፍን የመሰለ ፍፁም ደግነት የተሞላበት ኢትዮጵያዊነት ውስጥ የመኖር ለልብ የሚሰጠው ሀሴት በምንም አይለካም። ለመሆኑ ደግነት ራሱ ምን ያስገኝልናል? ምናልባት ደስ የሚል ስሜት? ወይስ ሌላ? በእርግጥ መልካምነት በሕይወታችን ጥሩ ነገሮችን ያስከትላል። ደግነት ከሚፈጥርልን አወንታዊ ስሜት ባሻገር እድሜያችንንም እንደሚያረዝም አንድ ጥናት ላይ በአንድ ወቅት ማንበቤን አስታውሳለሁ።
ደግነት ዋጋ ኖረውም አልኖረውም ለሌሎች ተስፋ ከመሆን የሚልቅ ምን ጉዳይ አለ? ጠያቂ ደጋፊ የማግኘትን ያህል ተስፋ የሚሰጥ ነገር እንደማይኖር ልቤ ይነግረኛል። ደግፎ የሚያቆመኝ ወገን አለኝ ብሎ ማሰብ፤ እገሌ ለኔ ይቆማል፤ ወገኔ ጨክኖ ትቶኝ አይበላም፤ ሁሌም ተካፍለን ተረዳድተን ነው የምንኖረው የሚለው ከልጅነት እስከ እውቀት ስሰማው ያደኩት እውነት የአብሮነት ማሰሪያው ገመድ፤ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት የሚያስተሳስረው ፍቅር ደግንትን ይወልዳል። የደግነት ዋጋ ደግሞ በልብ መስፈሪያ እንጂ በምን ይለካ ይሆን?
እንዲህ ሰው ከቤት ንብረቱ ከቀዬው ተፈናቅሎ፤ ከሞቀ ቤቱ ብርድና ጸሀይ እየተፈራረቀበት ዓመት በዓልን በመጠለያና በጎዳና ማሳለፍ ግድ ሲለው እኛ ደግሞ የፍቅራችንን ልክ የደግነታችንን ጥግ የሚጠይቅ እውነት ከፊታችን ድቅን ይላል። አሁን አሁን ፍቅር ፈርተን መቀራረብ ሸሽተን ሌሎች ለኛ የሚያወጡልን ስም እያሳሰበን፤ ወቅቱን እያየን የንፋሱን አቅጣጫ እየተመለከትን ደግ ለመሆን የምንነሳው በበዛንበት ወቅት፤ የደግነት ዋጋ ሳይጠይቅ እኔ ከገዛኋት አንድ ኪሎ ስጋ ላይ በሯን ዘግታ ከልጆቿ ጋር ለተቆራመደችው እናት ከፊሉን ባካፍል ውስጤ የሚያገኘውን እርካታ ማን ያገኘዋል?፤ ማንም!
ደግነት ካሜራ ፊት በሆነበት፤ ወገን ተረስቶ እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን ደስ በማይል ስሜት በጥርጣሬ እየተያየን፤ መዋደድን ፈርተን፤ ጉርብትናን ንደን እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን፤ መካፈል መሰጣጣት ለታይታ የሆነብንና ተመልካች ሳናገኝ በር ቀርቃሪ ሆነን በግለኝነት ውስጥ ተዘፈቅን። ቀደም ቀኝህ የሰጠውን ግራህ አይመልከት በሚባልበት ዘመን እናቶቻችን በጉያቸው ወሽቀው ሲከፋፈሉ፤ ከቅመም አንስቶ እስከ ሽሮ በርበሬ፤ ከእንጀራ አንሰቶ እስከ ጠላ፤ ቤቷ ባዶ የሆነውን ጎረቤታቸውን ከየጓዳቸው አውጥተው ከነሱ እኩል ሲያደርጉት የትኛው ተመልካችስ ተጠርቶ ነበር ብዬ እጠይቃለሁ? ይሄን ማለት ባልወድም ልለው ተገድጃለሁ፤ ፍቅር መከባበር ደግነት ድሮ ቀረ በደጋጎቹ ዘመን ልል ከጅያለሁ።
ዘንድሮማ ፍቅርን ፈርተን የጥላቻ ስራን እየሰራን በኛ ሳያበቃ ወደ ትውልዱ እያመራን አብሮነታችንን ትተን ብቸኝነት ጠራን። አብረን መኖር ሲገባን መደጋገፍ መከባበሩ አንተ ትብስ አንቺ መበባሉን ትተን በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር አቆምን፤ በልዩነት ውበት ደምቀን ያልኖርን ያህል አንድም ቀን አብሮ እንዳላደረ እንዳልተዋለደ እልህ ተናነቅን መቻቻልን ናቅን። አንተም ተው አንችም ተይ የሚል ሽማግሌ አጥተን ፀብን አሟሟቅን፤ እኔ የጠላሁትን ጥሉ በሚመስል አድመኝነት ለአመፅ ስንነሳ ለሰላም እራቅን። በክፉ ስራችን በእኩይ ተግባራችን እሳት ለኩሰን ከዳር ሆነን ሞቅን።
ደግ ለመሆን መንገድ ዘጋን፣ ፍቅር አጣን፤ መወያየት ጠላን መነጋገር ተፀየፍን፤ መደማመጥ ጠፍቶ መነቋቆር በዝቶ ሁሉ ተናጋሪ አንድም አድማጭ ጠፍቶ፤ መከበር ያለበት ትልቅ የተባለው የእንጨት ሽበት ሆኖ መናናቅ በርክቶ መመካከርን ስንረሳ መከባበርን ስንተው ያኔ ትናንት የነበረው እሴታችን፣ የሚያምርብን የአብሮነት ውበታችን ደብዝዞ እኛ በሞቀ ቤታችን አድረን በየጥጋጥጉ የወደቀውን ረስተናል። የወገናችንን በር ያንኳኳው የእኛ ቤት ላለመግባቱ ምን ዋስትና ይዘናል።
እጃችንን ለወገናችን ከመዘርጋት ይልቅ በወንድማችን ላይ ዱላ አነሳን፤ የቃየል ምቀኝነት በልባችን ላይ አንግሰናል፤ የወገናችን ረሃብ የአዞ እንባ እያስነባን ለደግነታችን ዋጋ መተመናችን ይብቃ፤ ዛሬ ላይ የዳገቱ ግማሽ ላይ ደርሰናል። ወደ ላይ ወደ ከፍታው ለመውጣት መያያዝ እንጂ መጓተት አያዋጣንም፤ የደከመውን እያበረታን፣ የዛለውን እያነቃን ዳገቱ ጫፍ ላይ መውጣት ይገባናል።
አሁን የምናከብረው በዓል ትንሳኤ ነው፤ የዓለም መድኃኒት ሞቶ የተነሳበትን፣ ከጨለማ ወደ ፍፁም ብርሃን የተሻገርንበትን ታላቅ በዓል፤ እናም በዚህ ቀን ከማንኛውም ጊዜ በላይ የተቸገሩትን መደገፍ ይገባናል፤ መደጋገፋችን መረዳዳታችን የግድ የሆነበት ሰዓት ላይ ደርሰናል። አንዳችን የሌላችን እንባ መፍሰስ እንደቀልድ የምንመለከትበትን ጊዜ አብቅቶ እንባ አባሽ፤ ለታረዘ አልባሽ፤ ለተራበ አጉራሽ መሆን የሚገባን ጊዜ ላይ ነን።
የደበዘዘው እሴታችን ሳይጠፋ፣ ያለው የሌለው ሳይል ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ለችግሮቻቸን መፍትሄ እስክንሰጥ ጊዜ ለማይሰጠው ረሀባችን እጃችንን እንዘርጋ፤ በዚህ የኑሮ ውድነት፤ በዚህ ጦርነቱ የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ባለበት በዚህ ጊዜ ተመልካች አዛዥ ሳያስፈልገን በልባችን ልብ ብለን እጃችንን እንዘርጋ።
ድቅድቁን ጨለማ የሚገፋ የተስፋ ሻማችን ተለኩሶ ወጋገኑ መታየት ሲጀምር የጨለመውን አድማሱን ጥሶ እኛ ወደኋላ መራቃችንን ትተን ወደ ብርሃኑ መጠጋት ያሻናል፤ በማይረባ ወሬ፤ እዚህ ግባ በማይባል ትርክት ወደ ብርሃኑ መሻገር ሲኖርብን ዛሬ ላይ ተጣብቀን ትናንትን እየናፈቅን ነጋችንን አናጨልም። ነገ አዲስ ቀን ነው አዲስ ተስፋ።
ሼህ ሰኢድ የሚባሉ ጎረቤታችን፣ “ልጄዋ እንደው የክርስቲያኑና የእስላሙ ጦም ሲገጥም አላህ በሙሉ እጁ ዱኣችንን የሚቀበል ይመስለኛል” ይላሉ። እንደ ሼህ ሰኢድ ቃል ይሁንና ክርስቲያኑ በሁለት ወር ፆም ያቀረበው ልመና፤ ሙስሊሙም በዚህ በቅዱሱ የረመዳን ወር ያቀረበው ዱኣ በአንድ ተሰምቶልን የአገራችን ሰላም ይብዛ፤ ልባችንን ለሰላም ክፍት ያድርግልን፤ ፈጣሪ የፈቀደው መልካሙ ቀን እስኪደርስ እርስ በእርስ እንደጋገፍ ብዬ አበቃሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም