ዋለልኝ አየለ
ዓባይ/ወንዙ/ በተለያየ ዘመን የተለያየ ስሜትን ይገልጻል። ጥንት ድልድይ ከመኖሩ በፊት በዓባይ ወንዝ ሳቢያ የተቆራረጡ የወዲያ ማዶ እና የወዲህ ማዶ ሰዎች በእንጉርጉሯቸው የሚናገሩት የዓባይን አስቸጋሪነት ነበር። ስለዚህ እነዚያ የጥንት የስነ ቃል ግጥሞች ዓባይ ምን ያህል ያስቸግር እንደነበር ይነግሩናል ማለት ነው።
ዛሬ ዓባይን ለመሻገር ያን ያህል ፈተና አይደለም። ድልድይ ተሰርቷል። ይህም በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ሲገለጽ ቆይቷል።
የአሁኑ የዓባይ ዘመን ጥበብ (ብዕር) ግን ይለያል። የአሁኑ የዓባይ ዘመን ብዕር ግንድ ይዞ ይዞር የነበረውን ዓባይ ማደሪያ ተዘጋጅቶለት ማደሪያው የታወቀውን ዓባይ የሚገልጽ ነው።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ‹‹የዓባይ ዘመን ብዕር›› የተሰኙ በርካታ የኪነ ጥበብ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄድ ቆይቷል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ደግሞ ኃይል ማመንጨት የጀመረበት መሆኑ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 11ኛ ዓመት እና ኃይል ማመንጨት የጀመረበትን ወቅት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ሲከበር ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት ሚያዚያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል የማጠቃለያ ፕሮራግሙ ተደርጓል።
ማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ በብዛት የቀረቡት ግጥሞች ናቸው። በመጨረሻም ዓባይን የሚመለከት አጠር ያለ ቴአትር ቀርቧል። ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለዓባይ ሲከራከርና የኢትዮጵያን እውነታ ሲያሳውቅ የቆየው መሀመድ አል አሩሲ አጠር ያለ ንግግር አድርጓል።
ለማንኛውም የዛሬው ጽሑፋችን ዓላማ የመድረኩን ሁነት መዘገብ አይደለም፤ ማጠቃለያውን ምክንያት በማድረግ የዓባይ ዘመን ብዕሮችን መዳሰስ ነው።
በነገራችን ላይ ‹‹የዓባይ ዘመን ብዕር የተሰኘ መጽሐፍ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ታትሟል። በመጽሐፉ 50 ወጣትና አንጋፋ ደራሲያን ተሳትፈውበታል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፤ ‹‹የዓባይ ዘመን ብዕር›› ስለ ዓባይ የተነገሩ እንጉርጉሮዎች፣ ሀዘንና መፋዘዝን በተስፋ፣ በመጪው ጊዜ ትንበያና ጥልቅ ምርምር በሚሹ ስራዎች የተካ የግጥም መድበል ነው።
የኢትዮጵያ ፀጋ የሆነው ዓባይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ምንም ሳይፈይድ ዝንተ ዓለም ወደ ባእድ አገር መፍሰሱ ያስቆጫቸው ባለቅኔና ደራሲያን፤ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎች ቁጭት አዘል ስራዎቻቸውን በሙዚቃ፣ በሥነ-ፅሑፍ፣ በስዕል በመግለጽ ወደ ቤቱ የሚመለስበትን ዘመን ሲናፍቁ ኖረዋል። መጽሐፉ እነዚያንም ይጠቃቅሳል። የዓባይን የስልጣኔ፣ የሀብት፣ የኩራት፣ የውበት ምንጭነትና የአገር ቅርስነት በቁጭት ሲያወሱ ኖረዋል፤ በእዚህ መንገድ ዓባይ ተሞግሷል፣ ዓባይ እንደ ሰው ተወቅሷል፣ ዓባይ ተሰድቧል።
የዓባይን ታሪክ የቀየረውና ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓይን እንዲመለከቱ ያደረገው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥበበኞቹንም ተስፋን የሰነቁ ስራዎች ይዘው እንዲወጡ ዕድል ሰጥቷቸዋል። እነዚህ ጥበበኞች ናቸው መጽሐፉን የጻፉት።
መጽሐፉ የተዘጋጀው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ነው። በውስጡም ዓባይን የተመለከቱ ወጥ ሥነ ግጥሞች፣ ወግና የዘፈን ግጥሞች ተካተውበታል፤ ኢትዮጵያውያን ቁጭታቸውን በብሩህ ተስፋ በማለምለም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡም ያሳስባል።
የስነ ጽሑፍ ባለሙያው ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት በአንድ ወቅት ስለዓባይና ኪነ ጥበብ በአንድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ ዓባይና ኪነ ጥበብ ለረዥም ዘመን አብረው የኖሩ ናቸው። እረኛው፣ አዝማሪው፣ አልቃሹ፣ አሚናው፣ … ይሄ ሁሉ ስለዓባይ ሲናገር፣ ሲዘምር ነው የኖረው። ጥያቄው ምን ነበር ካልን፤ ይሄ ሁሉ ዘማሪ ሊሆን የቻለው የዓባይ ጥቅም ገብቶት ብቻ አይደለም። ይልቁንም እንደ ትልቅ ክብር ስለሚያየው ነው።
እንደ ጸሐፊ ተውኔቱ ገለጻ፤ ህብረተሰቡ እየተለወጠ፣ እየተማረና እያወቀ ሲመጣ ሁኔታዎችም ተለወጡ። ከምንጭነቱና ከኩራትነቱ አልፎ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑ፣ ከሌሎች አገሮችም ተሞክሮ እየታወቀ ሲመጣ፣ የዓባይ ዘመን ጥበብም አይነቱን እየለወጠ መጣ። አሁን እየተሰሩ ያሉ ግጥሞችም የዓባይን ጠቃሚነት የሚያጎሉ ናቸው። ተውኔቶቹም አገር በቀል መፍትሔ ላይ የሚያተኩሩና መተባበርን የሚያሳዩ ናቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የግንባታው ሀሳብ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እንደነበር ይነገራል። ያንን ተከትሎም ከያኒያንም ቁጭት ማሰማት ጀምረዋል። ከጥንት ስነ ቃል ወጥተው ገጣሚያን የራሳቸውን ቅኔ ተቀኝተውበታል። በተለይም የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ተጠቃሽ ነው። ‹‹እሳት ወይ አበባ›› ከተሰኘው ከሎሬቱ መድብል ስለዓባይ ከገጠመው ረጅም ግጥም ቀንጭበን አንመልከት።
አባይ የምድረ ዓለም ሲሳይ
የቅድመ ጠቢባን አዋይ
አባይ የጥቁር ዘር ብስራት
የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት
የዓለም ስልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር አስከ ካርናክ
በእቅፍሽ ውስጥ እንዲላክ
በመመለክ በመመስገን
ጽላትሽ ከዘመን ዘመን
በአዝዕርትሽ አበቅቴሽ ሲታጠን
አቤት አባይ ላንቺ መገን።
አድርጎሽ ቅድመ ገናና
ዛሬ ወራቱ ራቀና
ምድረ ዓለም አድናቆት
ፈለጉን መሻት ተስኖት
እንዲህ ባንቺ መንከራተት
ታሪክ ወሮታሽ ጠፍቶበት
ትላንት በባዕድ ጩኸት
ዛሬም ባላዋቂ ሁከት
ቋንቋ ለቋንቋ ቢራራቅ
የቅድሚያሽ ንድፍ ላይፋቅ
እዚህ ደማም እዚያ ተማም
መበልሽ ብቻ ባይበቃም….
እያለ ዓባይንም ኢትዮጵያንም ይራቀቅባቸዋል። ዓባይን ያሞግሰዋል፤ ይወቅሰዋል። በእነ ሎሬት ጸጋዬ ጊዜ ገና ሀሳብ ላይ የነበረው ዓባይ ቁጭት ማጫር ጀምሮ ነበር። እነሆ የማይደፈር የሚመስለው ዓባይ ተደፍሮ መገደብ ሲጀመር ደግሞ የዘመኑ ከያኒያን ከቁጭት ወደ ተስፋ ተሸጋገሩ። የእነ ሎሬት ጸጋዬ ተከታይ የሆኑት እነ አርቲስት ጌትነት እንየው ዓባይን ከቁጭትነቱ ጀምረው እስከ ተስፋነቱ ገልጸውታል። እስኪ ይህን ወኔ ቀስቃሽ የጌትነት እንየው ግጥም እናንብብ!
በአገር ግፍ መዋሉን መበደሉን ትቶ
ባለፈ ተግባሩ በጎደፉ ስሙ አፍሮ ተጸጽቶ
በጊዜ ንስሃ ከዘመናት መርገምት ከበደሉ ነጽቶ
ከቆየ ልማዱ ከኖረ ምግባሩ ከባህሪው ወጥቶ
ውሃነቱን ትቶ
ወንዝነቱ ቀርቶ
እንዳንዳች ምትሀት ከቃልኪዳን ስሩ እየተመዘዘ
በአንድ የስሜት ግለት በአንድ የስሜት ሲቃ
አገር ጫፍ እስከ ጫፍ ሰቅዞ እየያዘ
ትውልድን ከታሪክ ታሪክን ከአገር ስቦ እያዋደደ
አስማምቶ እያሰረ
ስሩ የጠለቀ
ግብሩ የረቀቀ
ውሉ የጠበቀ አባይ ሀረግ ሆነ ከደም የወፈረ
ይሄው ከዓይናችን ስር ዘመን መሰከረ
ይሄው ከእጃችን ላይ ግዮን ተቀየረ…
ከእንግዲህ ባገሩ ሳቅ እና መስኖ እንጅ እንባ ሆኖ ላይገርፍ
ከእንግዲህ ላገሩ እጁ ላይታጠፍ
ጸጋው ላይገፍ
ግቱም ከቶ ላይነጥፍ
ከእንግዲህ ፍቅር እንጅ ሸፍጥ እና ድለላ ስሩን ላያስረሱት
ከእንግዲህ ምክር እንጅ ብረት እና ሴራ ውሉን ላያስረሱት
ያገር ውርስ እና ቅርስ እራት እና መብራት
ዋስ ጠበቃ ሊሆን መከታ እና ኩራት
የአገር ውርስና ቅርስ ራትና መብራት፣
ዋስ ጠበቃ ሊሆን ክብርና ኩራት፣
ይኸው በአዲስ ዘመን አዲስ ቃል ዘመረ፣
ከራሱ ታረቀ ካፈሩ መከረ፣
ለአገሩ ቆመ በአገሩ አደረ፣
ዜማና ቅኝቱ ረገደ ምቱ፣
ከጊዜ ከትውልድ ከሀቅ ሰመረ፣
ሃገርን ባንድ ነዶ ባንድ ልብ አሰረ
ይኸው ካይናችን ስር ከእውነት የነጠረ ከእምነት የጠጠረ፣
አባይ ሃረግ ሆነ ከደም የወፈረ።
የአንድ ወንዝ ልጅ ሁሉ ይህን የአባይ ሀረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ
ከጋራ አንገት መድፋት ከጋራ መሳቀቅ ከጋራ አፍረት ወጥተህ
በያለህበቱ በየዓለማቱ ጥግ በአንተነትህ ኮርተህ
አንተ ማነህ ሲሉህ
ከወዴት ነህ ሲሉህ
በሙሉ ራስነት አንገትህ አቅንተህ
ድምጽህን ከፍ አድርገህ
ደረትህን ነፍተህ
የአባይ ልጅ ነኝ እኔ
ጦቢያ ናት አገሬ በል አፍህን ሞልተህ!
የአንጋፋዎቹ ገጣሚዎች ስራዎች ብቻ አልነበሩም በየመድረኩ ይቀርቡ የነበሩት። የተለያዩ መድረኮች እየተዘጋጁ ግጥሞች ሲቀርቡ ቆይተዋል። ባለፉት 11 ዓመታት ዓባይን በተመለከተ በመድረክ የሚቀርቡ ግጥሞች ሁሉ የህዳሴ ግድቡን ተስፋ ሰጪነት የሚጠቁሙ ናቸው። ቁጭት ሳይሆን፤ ተስፋ፣ ወኔ እና የአሸናፊነት መልዕክት ያላቸው ናቸው። በእረኞችና ገበሬዎች ተወስኖ የነበረው የዓባይ እንጉርጉሮ ከተማሪ እስከ ተመራማሪ ድረስ ተቀኙበት። መድረኮች ተዘጋጅተውለት ተወደሰ።
በጽሑፋችን መግቢያ አካባቢ ስለጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ካነሳሁት አንድ ሀሳብ ቀንጭቤ ነበር። እረኛው፣ አዝማሪው፣ ገበሬው… ስለዓባይ ሲያንጎራጉር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይገደባል ብሎ አይደለም። እንዲያውም እረኛ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚገኝም ላያውቅ ይችላል። እሱ የሚያንጎራጉረው ዓባይ ማንነቱና ኩራቱ ስለሆነ ነው። ዓባይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነት ስለሆነ ነው። ክረምት ከበጋ ከዓባይ ጋር የሚያገናኘው ብዙ ማህበራዊ ሕይወት ስላለው ነው። ዓባይ ከወንዞች ሁሉ የተለየ ግዙፍ መሆኑ አንዳች ግርምት ስለሚፈጥርበት ነው።
ግብጾች ስለዓባይ ምን እንደሚሉ በምሁራን ሲተነተን ቆይቷል። ‹‹ደምና አጥንታችን ነው›› ይላሉ። ዓባይ ማንነታቸው እንደሆነ እና ለኢትዮጵያ ግን የቅንጦት መስሎ ነው የሚታያቸው። ዳሩ ግን ዓባይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነት መሆኑን የጥንት የሕዝብ ስነ ቃል እና የኪነ ጥበብ ሥራዎችም ሲመሰክሩ ኖረዋል። ታላቅነት፣ ለጋስነት፣ አይበገሬነት፣ ተጓዥነት… በዓባይ ይመሰላሉ። ተረቶች ዓባይን መነሻ ያደርጋሉ። ለዚህም ነው ዓባይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጥንታዊ ትስስር ያለው መሆኑ ሁሌም የሚገለጸው።
‹‹የዓባይ ዘመን ጥበብ›› ገላጭ የሆነ ሀሳብ ነው። የጥንቱንም የዛሬውንም ምንነቱን የሚገልጽ። በተሳተፍኩባቸው የዓባይ ዘመን ጥበብ መድረኮችም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን በተከታተልኩት የጥበብ ሥራዎች የዓባይን የጥንቱን መነሻ አድርገው የአሁኑን ይገልጻሉ። ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ የዛሬ የጥበብ ሥራዎች በዚህኛው ዘመን ያለውን ዓባይ የሚገልጹ ናቸው። ቀጣይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መደበኛ አገልግሎት እየሰጠ፣ ብርቅ መሆኑ ተለምዶ፣ ኢትዮጵያም ያሰበችው ብልጽግና ላይ ደርሳ ለማየት ያበቃው ትውልድ፤ በግድቡ ተሳትፎ ጊዜ ምን ይባል እንደነበር እነዚህ የጥበብ ሥራዎች ይመሰክራሉ።
ስለዚህ የዓባይ ዘመን ጥበብ፤ ትናንትም፣ ዛሬም ነገም ነውና ከያኒያን መጠበባቸውን ይቀጥሉ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም