ከአነስተኛና ጥቃቅን ስራዎች ተነስተው ወደ መካከለኛ ብሎም ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮችን ለመፍጠር የተለያዩ ማኑፋክቸሪንጎች ተቋቁመው ወደ ስራ ከገቡ አመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ለበርካቶች የስራ እድል ከመፈጠሩም ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል። በርካቶች ስኬታማ ሆነው የእድገት ደረጃቸውን ጠብቀው እየተጓዙም ቢሆንም ጥቂት የማይባሉቱ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ ቀርተው እንመለከታለን።
ተሳክቶላቸው ለአመታት በስራው ላይ የቆዩት የያሬድ ብረታ ብረትና እስፔር ፓርት ማሽነሪ ማምረቻ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ እስጢፋኖስ ራሳቸውን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ካሳደጉት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ትላልቅ የሚባሉ ዘመናዊ ማሽኖች በማምረትና በስፋት በማከፋፈል ላይ ናቸው። የግል ጥረታቸው ከመንግስት ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል። ለብዙዎች እንጀራ ከመክፈት በተጨማሪ ለነገ የሚሆናቸው የሙያ ባለቤት ጭምር አድርገዋል። እዚህ ደረጃ የደረሱት ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም። እርሳቸውም ስራው ፈታኝ ቢሆንም የስራው ፍቅር በዚህ ዘርፍ እንዳቆያቸው ይናገራሉ። ወደ ስራው የገቡት በ2003 ዓ.ም ሲሆን ፋብሪካቸው ከመቋቋሙ ቀደም ሲል በመኪና ጥገና ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ያስታውሳሉ። ወደዚህ ስራ ለመግባት ያነሳሳቸው የቀድሞ ስራቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ያሬድ በአገሪቱ የሚነዱ መኪኖች የምርት ዘመናቸው ከመቆየቱ የተነሳ መለዋወጫ የማይገኝላቸው ሲሆኑ ለምን ለእነዚህ መኪኖች የሚሆኑ መለዋወጫዎችን በራሳችን አናመርትም በሚል መነሻ ድርጅታቸውን መክፈታቸውን ይናገራሉ።
አስመስለው የተሰሩ (ሞዲፊክ) የመኪና መለዋወጫዎችን በመስራት ችግርን በአገር ውስጥ ምርት ለማቃለል በሚል የተጀመረው ስራ ሙሉ ለሙሉ መለዋወጫዎችን ወደማምረት ስራ ካደገ በኋላ ለስምንት አመታት ከውጭ የሚመጡ የተለያዩ ማንኛውም አይነት ማሽነሪዎች፤ የአዳራሽ ወንበሮች፤ የመኪና መለዋወጫ እቃዎችን ያመርታሉ።
የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ማለትም እንደ ደቡብ ግሎባል ባንክ አይነቶቹ፤ የተለያዩ በእቃው መጠቀም የፈለጉ ግለሰቦች፤ የአዳራሽ ወንበር የሚፈልጉ ተቋማት ደንበኞቻቸው መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ያሬድ ለምሳሌ የዳቦ ማሽኖች፤ የእህል ወፍጮዎች፤ የሳሙና ማምረቻ፤ የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖች፤ ትናንሽ የቤት ውስጥ መገልገያ የዳቦ መጋገሪያዎች፤ ቡና ማድረቂያ፤ ቆሎ መቁያ፤ ቡና መፍጫ በአጠቀላይ ደንበኞች ለሚፈልጉት ግልጋሎት ሊያውሉት የሚችሉት ማንኛውም ማሽን የማምረት ስራ የሚሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
“የእያንዳንዱ ስራ ትእዛዝን ስንቀበል የደንበኛውን ፍላጎት በመረዳት በጥንቃቄ ዲዛይን ተደርጎ ወደ ምርት ይገባል።” የሚሉት አቶ ያሬድ ከሁሉም በላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያሰችል ምርቶችን በብዛትም ሆነ በተናጠል ለሚያዙ ደንበኞች እንደየ ፍላጎታቸው አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ይናገራሉ።
ማሽኖቹን ለመስራት የተለያዩ ጥሬ እቃዎችን ይጠቀማሉ። እንደ ብረት፤ አለሙኒየም፤ እንጨትና የተለያዩ ለማሽን መስሪያ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ተጠቅመው ያመርታሉ። አዳዲስ ጥሬ እቃዎችን ከመጠቀመም በላይ የማይፈለጉ ተብለው የወዳደቁ ብረታ ብረቶችን እንደ አዲስ በማቅለጥ ግልጋሎት ላይ የሚያውሉ መሆኑን ይናገራሉ። የወዳደቁ እቃዎችን፣ የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ የመኪና መለዋወጫዎች፤ ከየአካባቢው የወዳደቁና ቁርጥራጭ ከሚሰበስቡ ብረቶች፤ ተረፈ ምርቶችን በኪሎ በመግዛት አንድ ላይ በመሆን የሚያቀልጡ ሲሆን ሞልድ በማዘጋጀት ወደ ተፈለገው ማቴሪያል የሚቀየር መሆኑን አቶ ያሬድ ያስረዳሉ።
ሀዋሳ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ያሬድ በፈጠራ ላይ የተመሰረተውን ድርጅታቸውን ከመክፈታቸው በፊት በአውቶሞቲቭ የትምህርት ዘርፍ ስልጠናን ወስደዋል። ለረጅም አመታት በፍቅር የቆዩበት ሞያም በመሆኑ ክፍተቶቹን እየተመለከቱ ስራ ፈጣሪ ለመሆን መቻላቸውን ይገልጻሉ። የመኪና ጥገና ስራ ላይ ይህ ቀረሽ የማይባሉ ባለሞያ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ያሬድ በመኪና ስራ ላይ ከኤሌክትሪክ እስከ ሞተር፤ ከሞተር እስከ ቦዲ ስራ እያንዳንዱን ነገር የሚሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
“ስፈጠር ጀምሮ ለፈጠራ ስራ ነው “ የሚሉት አቶ ያሬድ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ የተለያዩ ነገሮችን መሞከር ያስደስታቸው እንደነበር ይናገራሉ። አንድ ነገር ሲመለከቱ ከዚህ በተሻለ እንዴት አድርጌ ልሰራው እችላለሁ የሚል ሀሳብ በውስጣቸው እንደሚፈጠር የሚናገሩት አቶ ያሬድ ህይወትን ቀለል ለማድረግ የሚያስችሉ በተለይም ከውጭ በውድና በውጪ ምንዛሬ ወደ አገር ቤት የሚገቡ ቁሳቁሶችን ለመተካት ማሰብ ሀሳብን ደግሞ ወደተግባር ከዚያም ወደስኬት መቀየር የዘወትር ስራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን በተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት ቢያደርጉም በቀጣይ በኤክስፖርት እስታንዳርድ በማምረት ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ አላቸው። ሆኖም ግን አሁን ካለው የአገሪቱ ሁኔታ አንፃር የገንዘብ አቅም ማነቆ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ። የአቅም ውስንነት ባይኖር ግን በፍጥነት የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። በድርጅቱ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በመተካት የውጭ ምንዛሪን የማስቀረት ስራን ከመስረታቸው ባሻገር አሁን ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚሰሩበትን ሁኔታ ማቀዳቸውን ያስረዳሉ።
ምርቶችን የማምረት ሂደት ውስጥ አንድ አይነት አካሄድ ብቻ እንደማይከተሉ የሚናገሩት አቶ ያሬድ፤ በርከት ያሉ ትእዛዞች ወደ ድርጅቱ ሲመጡ ሌሎች በአካባቢው ያሉና በሙያው ብቁ ለሆኑ አጋር ድርጅቶች የተለያዩ ክፍሎችን ድርጅቱ በሚፈልግው የጥራት ደረጃ መሰረት ጥሬ እቃ በማቅረብ እንዲሰሩ የሚደረግበት አግባብ መኖሩን ገልፀዋል። ስራውን የተቀበሉት አካላት የእውቀታቸውንና የማሽናቸውን በቂ ክፍያ የሚያገኙ ሲሆን ድርጅታቸው በስራ ብዛት እንዳይጨነቅ ያደርጋል። ይህን ከማድረጉም ባሻገር በአካባቢው በርካታ የበቁ ሞያተኞች እንዲኖሩ እድል የሚሰጥ መሆኑን ያብራራሉ።
በስራ እድል ፈጠራ ረገድ በድርጅቱ የሚሰሩ ሀምሳ አራት ሰራተኞች መኖራቸውን ገልፀው ስራው በሚፈለገው መልኩ ቢገኝ ከዚህ ተጨማሪ የሰው ሀይል ለመቅጠር ያስባሉ። ስራ በአግባቡ ላለመገኘቱ እንደማነቆ የሚያነሱት ስራ ለመስራት ጨረታዎች ሲወጡ ለሚፈለገው ሰው ብቻ ለመስጠት አጥር የሚቀመጥበት አሰራር መኖሩን ነው። ይህም ሁሉም አምራች በተገቢው መልኩ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንዳደረገው ያስረዳሉ። ለዚህም መፍትሄ ነው ያሉት ሀሳብ የመወዳደሪያ ሜዳውን እኩል ክፍት በማድረግ በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት የግድ መሆኑን ያስረዳሉ።
“መንግስት ማኑፋክቸሪንጎች ይደጉ ካለ፤ ምርቶቻችን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ከቻለ፤ ለአገር ኢኮኖሚ ደጋፊ ስራ መስራት ከቻልን ሙሉ አቅማችንን የምንጠቀምበት አሰራር መዘርጋት አለበት” የሚሉት አቶ ያሬድ ስራው በተጀመረበት ልክ መሄድ እንዲችል ሰራተኞች እንዳይበተኑ መንግስት ድጋፉን እኩል ማድረግ የሚገባው መሆኑን አሳስበዋል።
አቶ ያሬድ እንደሚሉት፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጥራት ያለው እቃ በአገር ውስጥ ማምረት እየቻሉ በጣም በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ እቃዎችን ከውጭ የማስመጣት ፍላጎት በመንግስት ተቋማት መኖሩ አሳሳቢ ነው። መንግስት የስራ እድሎችን መፍጠር የስራ አጥ ቁጥር መቀነስ የሚሉ ሀሳቦችን እያነሳ ስራ ውስጥ ያሉ አካላት አቅም ሳያንሳቸው በገበያ እጦት የተነሳ ስራ እንዳይቆሙ ማድረግ እንዳለበት ይናገራሉ። ይህም ሲባል አምራቾች ተገቢው የጥራት ደረጃ ተቀምጦላቸው ጥራቱ ከውጭ ከሚመጡት ጋር በማወዳደር ቅድሚያ ለአገር ውስጥ አምራቾች መስጠት ይበልጥ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የራሱን አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ማምረት መሸጥ ከሚለው እሳቤ ባሻገር እውቀት ያላቸው ሙያተኞችን በማፍራት ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ያሬድ፤ በድርጅታቸው ስልጠና ከመሰጠቱ ባሻገር አሁን ላይ ስርዓተ ትምህርት በማሰቀረፅ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ባደራጁት ኮሌጅ ውስጥ እስከ ድግሪ ደረጃ የሚደርስ ስልጠና እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፅንሰ ሀሳብ ትምህርትን በኮሌጅ ከተማሩ በኋላ ልምምዳቸውን በወርክ ሾፑ በመስጠት ምርቱን ለገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን ተማሪዎቹም ልምድ ካለው ባለሙያ ጋር በመጣመር በተግባር የተደገፈ ትምህርት በማግኘት ብቁ የሰው ሀይል የማፍራት ስራ ላይ መሰማራታቸውን ያስረዳሉ።
በኮሌጁ ለጊዜው ወደ አንድ መቶ ሰማኒያ አካባቢ የድግሪ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪዎች በኮሌጁ አራት አመታትን ይቆያሉ። ይህ ሲባል ግን በክፍል ውስጥ አመት ከቆዩ በኋላ እጅ ከማፍታቻ ጀምሮ ብቁ ባለሙያ እስኪሆኑ ድረስ በወርክ ሾፕ ውስጥ የሚቆዩ ሲሆን ስልጠናው 30 በመቶ በንድፈ ሀሳብ 70 በመቶው የተግባር ሆኖ ይጠናቀቃል ብለዋል።
የሙያ ስልጠና በድግሪ ደረጃ የሚያስተምር በደቡብ ክልል ብቸኛው ተቋም መሆኑን ገልፀው በኮሌጁ የሚሰጡት የስልጠና ዘርፎች አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፤ ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ፤ ሜታል ፋብርኬሽን፤ ማሽን ቴክኖሎጂ፤ የትምህርት ዘርፎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፤ ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ፤ በድግሪ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በሌቭል ደረጃ የሚሰጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ቀደም ሲል ዲፕሎማ ይዘው በድርጅቶችና በተለያዩ ቦታዎች ተቀጥረው የነበሩ የሞያ ብቃታቸውን መሻሻል ሳይችሉ ቀርተው ተቸግረው የነበሩ በርካታ ሰዎች ትምህርታቸውን ከፍ ለማድረግ ከሚኖሩበት ሀዋሳ የግድ መልቀቅ ነበረባቸው የሚሉት አቶ ያሬድ፤ አሁን ግን በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ የትምህርት ፍላጎትን ሊያሟላ የሚችል ኮሌጅ በአቅራቢያው ለመክፈት መቻሉ መማር ለሚፈልጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በማህበራዊ አገልግሎት ረገድ የሰው ሃይል ማምረት ከማህበራዊ አገልግሎቱ አንዱ ሲሆን፤ በዚህም በማሰልጠኛ ኮሌጁ ውስጥ ነፃ የትምህርት እድል ለዘጠኝ ልጆች መሰጠቱን ነው የገለጹልን። አገራዊ ጥሪዎችም ሲኖሩ በንቃት በመሳተፍ አገልግሎት የመስጠት ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተው ወደ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ደረጃ ሲያድጉ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እንዳደረገላቸው ይናገራሉ። ከዚህም ውስጥ 800 ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን ምርቶቻቸውን ለማሳየት የሚያስችል አዳራሽ ተከራይተዋል። በቀጣይም ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ይናገራሉ። በቀጣይ ስራው ሲሰፋ የፕላስቲክ ምርቶችን እስፖንጅና ሌሎችን ለመስራት የሚያስቡ ሲሆን ለዚህም የሚሆን የስራ ትስስሩ ላይ ትኩረት ቢደረግ ውጤታማ ያደርገናል ይላሉ።
“ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር መሸጋገር አለብን ሲባል በተደጋጋሚ ጊዜ ይነገራል። ይሄንን ከወሬ ባለፈ በተግባር ማየት ብንችል፤ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ በቂ የብድሮች ሁኔታዎች ቢመቻቹ፤ ስራውን የምናሳድግበት ከዛም አልፎ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ቢኖር ስራውን ለማሳደግ ምንም እንደማይከለክለን አስባለሁ” ይላሉ።
ብልሹ አሰራሮችን በማጥራት ሰው በሙያው ብቻ መመዘን ቢችል የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት የሚቻል መሆኑን ይናገራሉ። በአጠቃላይ በስራቸው ውጤታማ የስራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት የተሻለ ስራዎችን እንዲሰሩ ድጋፍ ቢደርግላቸው መልካም መሆኑን አንስተዋል።
ፍሬህይወት አወቀና አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም