በበርካታ ፈተናዎች፣ ቀውሶችና ጫናዎች ታንቆ እንዳለ ሕዝብ ፤ በአስቸጋሪ ለውጥ ሒደት ላይ እንዳለች አገር ፤ የቀደሙ ሶስት አገዛዞች እዳ ተሸካሚ እንደሆነ አገር፣ ሕዝብና አመራር ፤ ሕወሓትንና ሸኔን የመሰለ ጠላት እንዳለው አገርና ሕዝብ ፤ ጽንፍ የረገጠ አቋም በሚራገብበት ፖለቲካዊ ምህዳር እንዳለ መልክዓ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ጎሰኝነት፣ ጥላቻና ልዩነት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሲቀነቀንበት እንደ ኖረ አገር ፤ ድርቅ፣ ጦርነትና መፈናቀል እንደ ጎን ውጋት ቀስፎ በያዛት አገር፤ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አረፋ እያስደፈቀው ያለ ኢኮኖሚ ባለበት ፤ በጎሳና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ ስርዓት እንዳቆመ አገር ፤ በማንነት ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች እንደሚሳሳብ ሕዝብ ፤ የሕግ የበላይነት ክፍተት እንደሚስተዋልበት አገር፤ ያደሩና ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉት ሕዝብ ፤ የተሳሳተ ትርክት ሰለባ ያደረገውና ሆድ የባሰው ሕዝብ እንዳለበት አገር ፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከካርታ ሊፍቁን በጥፍራቸው አሰፍስፈው በቆሙበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፤ ከዚህ ሁሉ ድቅድቅ ዋሻ ባሻገር የተስፋ ጭላንጭል በምናይበት አገር፤ ወዘተረፈ. ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Political Correctness (PC) የልብ ትርታው መሆኑ ለቅፅበት እንኳ ሊዘነጋ አይገባም።
ለውጡ ከባለፉት 48 ወራት ወዲህ እንኳ ብዙ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በገለልተኛ ወገን በጥናት ባይረጋገጥም በለውጡ ተቀባይነት legitimacy ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በአብነት ማንሳት ይቻላል። የሴራ ፖለቲካና የበሬ ወለደ “ወሬ” ከፖለቲካ ትክክለኝነት ልምሻ ጋር ተጃምሎ፣ አብሮ እንደ ሰደድ እሳት ሲዛመት ታዝበናል። በሁለቱ እኩይ ኃይላት መካከል ማለትም በሴራና በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ያለውን እሳትና ጭድነት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች አኳያ ያስተውሏል። ሰሞነኛው የአማራ ብልጽግናና የኦሮሞ ብልጽግና አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ቁርቁስ እንዲሁም የአብንና የኦፌኮ እሰጥ አገባ አገሪቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ ካለመረዳትና ከሕዝበኝነት (populism) የመነጨ አደገኛ አሰላለፍ ነው።
ይህ ሕዝብ አስተዋይና አርቆ ተመልካች ባይሆን ሊያስከትለው የሚችለውን አደገኛ ዳፋ ልብ ማለት ያሻል። የሚያሳዝነው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን አደገኛ መንገድ መከተላቸው ነው። ዛሬ ባልና ሚስት እንኳ በልጆቻቸው ፊት ከረር ያሉ ቃላትን ላለመለዋወጥ በሚጠነቀቁበት 21ኛው መ.ክ.ዘ ይህን ታላቅ ሕዝብና ጥንታዊት አገር የሚመሩ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እንካስላንትያ አሽኮለል ሲገጥሙ መስማት፤ በእርግጥ ይሄ ሕዝብ የሚገባውን መሪ አግኝቷል የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል። ምንም እንኳ ጨዋና ስለሚናገሩት ነገር የሚጨነቁና የሚጠበቡ መሪዎች መኖራቸው ባይካድም። በምሳሌ ለመምራት ሌት ተቀን የሚማስኑ መሪዎች ቢኖሩም።
የፖለቲካዊ ትክክለኝነትን አንድምታዊና ታሪካዊ ዳራ በስሱ ከሸመን በኋላ ወደ አገራችን ፖለቲካዊ መልክዓ አውርደን እንከናነበዋለን። ክንብንቡን ግን ለአገራችን ለሕዝባችን ክብር ስንል መልሰን እናወርደዋለን። ፖለቲካዊ ትክክለኝነት በ1930ዎቹ ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደዋለ የተለያዩ በዘርፉ ላይ የተከተቡ ድርሳናት ያትታሉ። ወደ ኋላ ተመልሰን ይሄን ዘመን ስንቃኝ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ ሰብዓዊ መብት፣ የእኩልነት ጥያቄዎች ወዘተረፈ. ጮህ ብለው መሰማት የጀመረበት ነበር። ፅንሰ ሀሳቡ በዚህ ተመሳሳይ ዘመን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረበት መግፍኤም ይሄው ነው። በሌላ በኩል ፅንሰ ሀሳቡ ከግራ ዘመም አይዶሎጂ ማለትም ከሶሻሊስትና ኮሚኒስት ርዕዮት ጋር ተያይዞ እንደመጣ ይነገራል። ሆኖም ብያኔው ግን በርዕዮት ዓለሙ ልክ የተሰፋ ነው።
የፓርቲውን ሕገ ደንብ የሚያከብር መሪ ወይም አባል እንደ ፖለቲካዊ ትክክለኛ ይቆጠራል። በ1980ዎቹ አጋማሽ ደግሞ ሀሳቡ ከተለያዩ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራሞች እና ከአካዳሚያዊ ነፃነት ጋር ተያይዞ ይወሳ ነበር። ይሁንና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1991 ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ስለ “ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት” አሳሳቢነት ከተናገሩ ወዲህ ፅንሰ ሀሳቡ ከስርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ ከምረቃ ስነ ስርዓት ንግግር ደንብ፣ ከጾታና ዘር ጥቃት፣ ወዘተረፈ ጋር መያያዝ ጀመረ። የፅንሰ ሀሳቡ ተገዳዳሪዎች ደግሞ ከአስተሳሰብ ፖሊስነት thought police እና መልካም ስምን ዝናን ከማጥፋት፣ ከማጉደፍ (McCarthyism) ጋር ያያይዙታል። ሆኖም ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ፖለቲካን ከሁሉም ማለትም ከሰብዓዊነት፣ ከፍትሐዊነት፣ ከእኩልነት፣ ከግልፅነት፣ ከተጠያቂነት፣ ከመብት፣ ከአብሮነት፣ ከእርቅ፣ ከሰላም፣ ከመነጋገር፣ ከመቀባበል፣ ከመደማመጥ ወዘተረፈ. አስበልጦ የመመልከት መጥፎ አባዜን መሞገት ነው።
ፅንሰ ሀሳቡ ስራ ላይ ከዋለ ከ80 አመታት በኋላም ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ዛሬም አወዛጋቢ፣ አነጋጋሪ ነው። በተለይ የአሜሪካው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቲዊተርም ሆነ በመደበኛ ሚዲያዎች መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ማንን እንደሚያስቀይም ? የማንን መብት እንደሚጋፋ ? የንግግራቸው፣ የቲውታቸው ትርጉሙ፣ አንድምታው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድመው ስለማያመዛዝኑ ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት አንጻር በተደጋጋሚ ነጥብ ሲጥሉ ይስተዋላል። ቲዊት ባደረጉ ለጋዜጠኞች መልስ በሰጡ ቁጥር ፊደላቸው፣ አፋቸው ወለም እያለው ምህረት የማያውቀው ሚዲያም እግር በእግር እየተከተለ ሲያብጠለጥላቸው እሳቸውም አፋቸውን ጣታቸውን መሰብሰብ ቢቸግራቸው እውነቱን መዘርገፍ እንጂ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጉዳዬ አይደለም ማለት ጀመሩ። በእርግጥ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ማለትም ሚዲያ፣ ሕግ አውጭና ተርጓሚ፣ ሲቪል ማህበራት፣ ወዘተረፈ . ባለበት አገር የፕሬዝዳንቱም ሆነ የፖለቲከኞች፣ የጋዜጠኞች፣ የተሟጋቾች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወዘተ. የአፍ ወለምታ ሆነ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ሳይውል ሳያድር በቅቤ ስለሚታሽ ስለሚታረም ያስገምትና ያስተዛዝብ ይሆናል እንጂ ያን ያህል ዘላቂ ጉዳት አያደርስም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስልጣን ላይ እያሉ አስተዳደራቸው ከሳኡዲ አረቢያ ጎን የሚቆመው “ለምናደርግላት ወታደራዊ እገዛ እጅ በእጅ በጥሬው ስለምትከፍለን ነው።” በማለት የሳቱት ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የአሜሪካ ወታደሮች ለግዳጅ የሚሰማሩት የአገራቸውን ደህንነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና እሴት ለማስከበር እንጂ በቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይነት mercenaries አይደለም በሚል ከግራም ከቀኝም አቧራ አስነስቶ ነበር። ፕሬዚዳንቱ ትውልደ ሶማሊያዊ ሴት የምክር ቤት አባልንና ሌሎችን ሶስት ባልንጀሮቿን” የምንሰራው ነገር ካልተዋጠላቸው ወደ አገራቸው መመለስ ይችላሉ።…” ከዚያ በፊት ደግሞ ሴቶችን፣ ቀደምት አሜሪካውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አፍሪካውያንና ሜክሲኮአውያን በተመለከተ አይደለም ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትላንት ከተወለደ ብላቴና የማይጠበቅ ነውረኛ ነገር በመናገራቸው ማወዛገቡ ይታወሳል። በአሜሪካ ታሪክ እንደ ትራምፕ ደጋግሞ ነጥብ የጣለ የለም የተባለው ለዚህ ነው። የአንድ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው የቀሩትም ለዚህ ነው።
በሽግግር ወይም ገና በመሰራት ላይ ላለች እንዲሁም አንድነቷ በቋፍ ላይ ለሚገኝ አገር ግን ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የልብ ትረታዋ ነው። እንደ ‘ጥላ ወጊ’(stroke) በድንገት ሊጥላት፣ ሽባ አድርጎ አሳስሮ የአልጋ ቁራኛ ሊያደርጋት ይችላል። ለውጡን ሊቀለብሰው ከፍ ሲልም ወደለየለት ብጥብጥ ሊዘፍቀን ይችላል። ለመሆኑ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ምንድን ነው?
መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ልሒቃን፣ መምህራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ እማ ወራዎች፣ በአጠቃላይ ሰዎች አንድን ቡድንም ሆነ የሕብረተሰብ ክፍል የሚያስከፋ፣ የሚያስቆጣ ንግግርም ሆነ ሌላ ያልተገባ ድርገት መፈፀም እንደሌለባቸው የሚያሳስብ ፅንሰ ሀሳብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ይባላል።
አገራችንም በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት የምትንጠራወዝ፣ የምትላጋ፣ የምታተኩር(Obssesed) ናት ማለት ይቻላል። በተለይ ከለውጡ ወዲህ በአዳራሽ፣ በአደባባይ፣ በመደበኛ ሚዲያ፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ ወዘተ. በለውጥ ኃይሉ፣ በተፎካካሪው፣ በተሟጋቹ፣ በልሒቁ፣ በአገር ሽማግሌው፣ በሃይማኖት መሪው፣ በታዋቂ ሰው፣ ወዘተረፈ . በተደረጉ ንግግሮች፣ በተሰጡ አስተያየቶች፣ መልሶች፣ በተላለፉ ንግግሮች፣ በመግለጫዎች፣ ወዘተ. የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ልምሻዎች ተከስተው ያስከፉት ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ማንነት፣ አይዶሎጂ፣ “ መስመር “፣ ወዘተረፈ . ወገን አለ ። ይሁንና የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ሆን ተብሎም በአፍ ወለምታም ሊጣስ ይችላል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ወደ ተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ሕዝብ ባነጋገሩ ወቅትም ሆነ ከዚያ ወዲህ የተለያዩ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የሚያስነሱ ግርታዎችን ቀስቅሰው ነበር። ሆኖም በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጥያቄ ያስነሱባቸውን ሀሳቦች ያብራራሉ ። ያስረዳሉ ።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “አክሱም ‘ ለወላይታ ‘ ምኑ ነው ? “ እንዲሁም የተወለዱበትን ሕዝብ ስም ጠርተው “… ከዚህ ወርቅ ሕዝብ መፈጠሬ ያኮራኛል ። …” በማለታቸው ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት አንጻር ትልቅ ነጥብ አስጥሏቸው ነበር ። ፓርቲን ከሕዝብ ጋር ማመሳሰል፣ ገዥ መደብን ከአንድ ብሔር ጋር ማያያዝ፣ አንድን ዕምነት ከአንድ ብሔር ጋር ማቆራኘት፣ ሰንደቅ አላማን ከአንድ ቤተ ክርስቲያንና ጎሳ ጋር ማመሳሰል አንድ ማድረግ እንደ ዜጋም እንደ አገርም ሁልጊዜ የምንስታቸው የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ኢላማዎች ናቸው።
በተለይ በአዲስ አበባ የኢሬቻ በዓል በታላቅ ድምቀትና በሰላም ለመጀመሪያ ጊዜ መከበሩ የፈጠረውን ደስታ በወጉ አጣጥመን ሳንጨረስ ለአገር ግንባታ የሚኖረውን አውንታዊ አስተዋጾ አስልተን ሳናበቃ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የዛኔው ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ሳቱት የተባለው የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ኢላማ ቀደም ሲል ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነቶች ጋር ተዳውሮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው የፈጠረብንን ሀሴት በቅጡ ሳናጣጥም አዲስ አበባ ላይ የተቃውሞ ሰለፍ መጠራቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል። ከእያንዳንዱ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ጀርባ የሚከፋ፣ የሚያኮርፍ፣ የተገለለ፣ ኢላማ የተደረገ የሚመስለው የሕብረተሰብ ክፍል መኖሩን ለምን በተደጋጋሚ እንደምዘነጋ ሁልጊዜ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል።
ሆኖም የአገራችንም ሆነ የውጭ አንዳንድ ልሒቃን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የንግግርና የሀሳብ ነፃነትን እንደሚገድብ ያወሳሉ ። የሜሪ ላንድ ዩኒቨርሲቲው ዳን ሞለር ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የንግግር ነፃነት የመገደብ ጉዳይ ሳይሆን ነፃነቱ የሌላውን መብት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነት፣ ወዘተ . በማይነካ፣ በማያንቋሽሽና በማይሸረሽር መንገድ የመጠቀም አግባብ ነው ሲሉ ይሞግታሉ ። አላማውም ፦
1ኛ . ተጋላጭ፣ ተገላይ እና በታሪክ አጋጣሚ ተጠቂ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መከላከል።
2ኛ . ሕዝቡ የሚወያይባቸው፣ የሚነጋገርባቸው ርዕሰ ጉዳዮችን በማረቅ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቂ እንዳይሆኑ መስራት ።
3ኛ . በዜጎች መካከል ቁጣን፣ ግጭትን፣ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ንግግሮችን መከላከል መሆኑን ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ዳን ቀለል ባለ ምሳሌ ሲያስረዱ አንድን የሕብረተሰብ ክፍል ዝቅ የሚያደርግ የታሪክ የመማሪያ መፅሐፍት እንዲታረም መጠየቅ የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም ።
እንደ ታዋቂው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ግሌን ሎሪ ያሉም ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ሀሳብን የመግለፅና የንግግር ነፃነትን እንደሚገድብ አድርገው የሚወስዱ አሉ። ሎሪ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የሚቃወሙበት ሌላው መከራከሪያ ራስን መመርመር ማቀብ ( self censorship ) ያስከትላል በሚል ነው። የጀርመኑ (ፖለቲከኛ ፊሊፕ ጄኒንገር ስለናዚ ዘመን ጀርመናውያን በማውራቱ ብቻ የናዚ ደጋፊ ወይም ፀረ ፂወናዊ እንዳልሆነ እየታወቀ በመናገሩ ብቻ ከፖለቲካ ሕይወቱ እንዲገለል ተደርጓል። የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ በሚል መሆኑ ነው። የዋሽንግተን ከንቲባ ሹመኛም በአንድ ወቅት ጓደኞችን “niggardly “ (ቆንቋኖች) ብሎ መሳደቡ ቁጣ በመቀስቀሱ ከኃላፊነቱ በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ ተገዷ። ከዚህ ከዚህ አንፃር ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ስንመዝነው ለምዕራባውያን ለቅንጦት የቀረበ ሊመስል ይችላል እንደኛ በለውጥ በሽግግር ላይ ላለ አገር ግን የህልውና እንዲሁም የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። በተለይ አመራሩ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። አንዱ ራሱን በሌላው ጫማ አድርጎ ማየት ያሻል። ኦሮሞ ብልጽግና ራሱን በአማራ ብልጽግና ጫማ ፤ የአማራም እንዲሁ ማድረግ ይጠበቅበታል ።
እንደ መውጫ
በአገራችን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በማበረታታት ረገድ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና የአንበሳውን ድርሻ እና ቀድሞ ተነሳሽነቱን በመውሰድ አርዓያ ሊሆን ይገባል። በፓርቲው ሕገ ደንብ ላይ በማያሻማና ግልፅ በሆነ ቋንቋ ስለፖለቲካዊ ትክክለኝነት አስፈላጊነት ሊደነግግ በቀጣይም ለአባላቱና ለደጋፊዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተከታታይ መድረኮችን ሊያዘጋጅ ይገባል። በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራሮች የሚገዙበት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የስነ ምግባር መመሪያ ሊኖረው ይገባል። ይህን በሚተላለፉ አመራሮች ላይም አስተማሪና መቀጣጫ ሊሆን የሚችል እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
በከፍተኛ ትምህርትም ሆነ በሌሎች ተቋማት የሚገኙ ልሒቃን በፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ምንነትና አስፈላጊነት ላይ ሀሳብ በመለዋወጥና ችግሩን ከእነ መፍትሔው በማመላከት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የድርሻቸውን ከመወጣት ባሻገር የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጥያቄን የሚያስነሱ ጉዳዮችን በመለየት መሪዎቻቸው በመግለጫዎቻቸው በንግግሮቻቸው በቅስቀሳቸው ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ታሳቢ እንዲያደርጉ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸውም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።
ሚዲያው በአርትኦት ፖሊሲው ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በማካተት ኃላፊነቱን ለመወጣት አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል ።
እንደ ዜጋ ደግሞ ሁላችንም የምንፅፈው፣ የምንናገረው፣ የምንስለው፣ የምናዜመው፣ የምንቀርፀው፣ ወዘተረፈ የሌላውን ወገን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት፣ ሃይማኖት፣ ማንነት፣ ወዘተ . የመያናንቅ፣ የማያንኳስስ እንዲሁም በሌላው ቁስል ላይ እንጨት የማይሰድ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባናል።
የሰለጠነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እስክንጨብጥ፤ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት በአግባቡ እስኪጎለብቱ፤ በመንግስት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈፃሚው መካከል ያለው ግንኙነት ሚዛናው እስኪሆን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የሙጥኝ ብሎ መያዝ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ስንከተለው የነበረ አገዛዝ ያመጣብን መለያየትና መጠራጠር ሳያንስ በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት አገር ልትታመስ ሕዝብም ሊደናገር አይገባም ።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት አሁኑኑ ! ! !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም