እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የምርትና የፍላጎት መጠን አለመጣጣም ግን ዋነኛ ምክንያት ለመሆኑ ምስክር አያሻውም። የአቅርቦት እጥረት ካጋጠመ ምንግዜም ቢሆን የዋጋ ንረት እንደሚከሰት ይታመናል። በአገሪቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምርት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረው የዋጋ ንረት ከዜጎች አቅም በላይ እንደሆነና መቋቋም ያልቻሉት ጉዳይ እንደሆነ ሲያነሱ ይደመጣል።
መንግሥትም አልቀመስ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሚል የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። መንግሥት ከወሰዳቸው አማራጮች መካከል የህብረት ሥራ ማህበራትን በመጠቀም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከደላላ ውጭ በሆነ መንገድ ለሸማቹ ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው። ምክንያቱም ከመሰረታዊ ችግሮች በተጨማሪ ደላሎች በአምራቹና በነጋዴው መካከል ሆነው የሚፈጥሩት ረብሻ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አማካኝነት የተጀመረው የእሁድ ገበያ የዋጋ ንረትን ለማርገብ ብሎም ገበያን ለማረጋጋት ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል። ወራት ያስቆጠረው የእሁድ ገበያ ሲጀመረ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል በሚኖርበት አካባቢ ከአስር በማይበልጡ ቦታዎች ሲሆን በአሁን ወቅት የክልል ከተሞችን ሳይጨምር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 50 በሚደርሱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በቋሚነት ግብይት ይካሄዳል።
የእሁድ ገበያ ከሚከናወንበት አካባቢዎች አንዱ ጀሞ አንዱ ነው። በጀሞ አንድ አካባቢ የተጀመረው የእሁድ ገበያ በስፋት ተጠናክሮ መቀጠል የቻለና ሸማቹም ከዚሁ ገበያ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ወይዘሮ አበራሽ በቀለ በስፍራው ሲገበያዩ ካገኘናቸው ሸማቾች መካከል ናቸው። የእሁድ ገበያ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በየጊዜው መገበያየት እንደቻሉና ከሱቅ ከሚገዙበት ዋጋ በተሻለ መጠን ቅናሽ እንደሆነና ለመኖሪያ ቤታቸውም ቅርብ መሆኑ እንደልባቸው የፈለጉትን በፈለጉ ሰዓት ወጣ ብለው እየሸመቱ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ሌላኛው ስሜ ይቅር ያሉ ሸማች የእሁድ ገበያ በተለይም ለአትክልትና ፍራፍሬ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ሀሳባቸውን አጋርተውናል። ለአብነትም ሙዝ በአትክልት መሸጫ ሱቅ ውስጥ በኪሎ እስከ 40 ብር የሚሸጥ መሆኑን አንስተው በእሁድ ገበያ ግን ከ25 ብር ጀምሮ የሚሸጥ መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም ገበያው ውስጥ የተለያዩ ችግሮች የሚስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነጋዴዎች ከህብረት ሥራ ማህበራቱ በብዛት ወስደው አትርፈው የሚሸጡ መሆኑንና ይህም ተገቢነት እንደሌለው ጠቁመዋል።
እኛም ተዘዋውረን መመልከት እንደቻልነው የእህል ዘርን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች በብዛት ለገበያ ቀርበዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሸማችም በወረፋ ተሰልፎና ሰልፉን ጠብቆ ይገበያያል። ለአብነትም ጤፍ በኪሎ ከ44 ብር ጀምሮ በየደረጃው ቀርቧል። ስንዴ፣ ገብስና ሌሎች ጥራጥሬዎችም በገበያው አይን ሞልተው ይታያሉ። ምስር ክክ በሌላው የገበያ ስፍራ እስከ 130 ብር የሚሸጠው በእሁድ ገበያ ላይ ከ96 ብር ጀምሮ ይገኛል።
ከግብርና ምርቶች በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ምርቶች የዳቦ ዱቄትን ጨምሮ ፓስታ፣ መኮረኒ እንዲሁም የጽዳት ዕቃዎች ሁሉም በገበያው የቀረበ ሲሆን እያንዳንዱ ዋጋም ከመደበኛው ሱቅ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ የሚታይበት ገበያ ሆኖ ተመልክተናል። ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በእሁድ ገበያ የነበረው ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ ቢታይም የግብርናውም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች ከመደበኛው የሱቅ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ገበያ ነው።
ለዋጋ ንረቱ መባባስ የምርትና የአቅርቦት አለመጣጣም እንደመሆኑ በተለይም በበዓላት ወቅት ምርት በከፍተኛ መጠን የሚፈለግ በመሆኑ በእሁድ ገበያውም መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች አንስተው፤ ይሁንና የእሁድ ገበያውን ጨምሮ ለበዓል የተከፈቱ ባዛሮች ገበያውን ለማረጋጋት እንደሚጠቅሙ ይገልጻሉ።
መሰረታዊ ከሆነው የምርት አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ እንዳይሆን ጉልህ ድርሻ ያላቸው ህገወጥ ደላሎችና ስግብግብ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ መሥራት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል። በተለይም ወቅቱ በዓል እንደመሆኑ ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያቀርብ የተሻለ ነው። በተለይም የሥጋ ዋጋ ከአቅም በላይ በመሆኑ በህብረት ሥራ ማህበራት ሥር ያሉ ሥጋ ቤቶች ጥራት ያለውን ሥጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረብ ቢችል መልካም ነው በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ወቅቱ ሁለት ተከታታይ በዓላት የሚስተናገዱበት ከመሆኑም ባለፈ እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ እንዲሁም ወተትና የወተት ተዋጽኦ በስፋት የሚፈለግበት በዓል ነው። በቀዳሚነት የሚከበረው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች የሚያከብሩት የፋሲካ በዓል ሲሆን ቀጥሎ የሚከበረውም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኢድአልፈጥር ማለትም ከረመዳን የጾም ወቅት በኋላ የሚከበር በዓል ነው።
ቀድሞውኑ አልቀመስ ያለው የኑሮ ውድነት ታድያ በእነዚህ ተደራራቢ የበዓላት ወቅት ይበልጥ ተባብሶ እንዳይቀጥልና ሸማቹ ይበልጥ እንዳይማረር ምን አይነት ሥራዎች ተሰርተዋል ስንል ላነሳነው ጥያቄ በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
ሁለት ታላላቅ በዓላት ከፊት ለፊታችን የሚከበሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለዚህም የህብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርጓል። በተለይም ህብረተሰቡ ዕለት ዕለት ለምግብ የሚጠቀምባቸውን የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማህበረሰብ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይም ሰፊ ህዝብ በሚኖርበት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የህብረት ሥራ ማህበራት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በንቃት በመሳተፍ ገበያውን የማረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራቱ በተለይም በመደበኛ የመሸጫ ሱቆቻቸው ላይ ከመንግሥት በተመቻቸላቸው ብድር አማካኝነት እንደ ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ። ለአብነትም የጤፍ ዋጋ ልዩነትን ብንመለከት በኩንታል ከ500 ብር እስከ 800 ብር ባለው ልዩነት አለው። ሌሎች ምርቶች ላይም እንዲሁ ከመደበኛው የሱቅ ገበያ ተመጣጣኝ የሆነ ቅናሽ በማድረግ ለህብረተሰቡ የተለያዩ ምርቶችን እያቀረቡ ነው።
ህብረት ሥራ ማህበራቱ በመደበኛነት ከሚያቀርቡት ምርቶቻቸው በተጨማሪ መጪዎቹን ሁለት በዓላት አስመልክተው እንደ አትክልትና ፍራፍሬ በተለይም ሽንኩርት እንዲሁም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን ለአብነትም ቅቤ፣ አይብና ሌሎችንም ይዘው ቀርበዋል። በተጨማሪም ዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ የሆነውን እንቁላል ወደ ገበያው በማቅረብ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ በተጨማሪም በዓሉ በዋናነት ሥጋና የሥጋ ውጤቶች የሚፈለጉበት እንደመሆኑ የሥጋ ከብቶችን ከአምራች የህብረት ሥራ ማህበራቱ ጋር በመተሳሰር በቀጥታ ባሉት የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ማዕከል ለማቅረብ የሥጋ ከብት ግዢ እየተከናወነ ይገኛል።
ወቅቱ የበዓል እንደመሆኑና ሰፊ ግብይት የሚካሄድ እንደመሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የተሰራ ሥራ መኖሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም በመደበኛ የህብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ቀደም ብለው የመሸጫ ሱቆችን እንዲከፍቱና ዘግይተውም እንዲዘጉና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅትም እንዲሁ ቀልጣፋና ጥሩ የሚባል አገልግሎት እንዲሰጡ የማስቻል ሥራ ተሰርቷል።
በእሁድ ገበያም እንዲሁ ህብረተሰቡ ጋር ተደራሽ ለመሆን የህብረት ሥራ ማህበራቱ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ሲሆን የመሸጫ ቦታዎችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማስፋት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 50 በሚደርሱ ቦታዎች ላይ ሽያጭ ይካሄዳል። ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞችም እንዲሁ የእሁድ ገበያው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በተለይም ሰፊ ህዝብ በሚኖርባቸው ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ ከተሞች፣ ሀረርና በሌሎችም ከተሞች ተጀምሯል። በዚሁ የእሁድ ገበያ አምራች የህብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ ከሸማቹ ጋር ተገናኝተው የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን መገበያየት እንዲችሉ በማድረግ ገበያውን በማረጋጋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ይሁንና የምርት ዋጋ ተማኝ አርሶ አደሩ ባለመሆኑ በየቀኑ የዋጋ መቀያየር መኖሩን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ የዋጋ ተማኝ የሆነውን አካል በመቆጣጠር ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ለማስገባት የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል። ይህንን ጤናማ ያልሆነ የግብይት ሥርዓት መስመር ማስያዝ ካልተቻለ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት አይቻልም ብለዋል።
አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ከየትኛውም ነጋዴ በተሻለ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ ይገኛሉ። ለዚህም ዋናው ምክንያት የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር በመቻላቸውና በቀጥታ ሸማቹን ማግኘት ስለሚቻል ሲሆን ሁለኛው ደግሞ ማህበራቱ ለትርፍ የተቋቋሙ ሳይሆኑ ህብረተሰቡን ለማገልገል የቆሙ በመሆናቸው ጭምር ነው። በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ የትርፍ ህዳግ ሳይዙ ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ ናቸው።
የህብረት ሥራ ማህበራቱ በዋናነት የግብርና ምርቶች የሆኑትን እንደ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄትና ሌሎችንም ህብረተሰቡ ዕለት ተዕለት የሚጠቀማቸውን ምርቶች ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። በተለይም በአሁን ወቅት ለበዓሉ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ዶሮዎችን፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋጽኦዎችን እና የቁም እንስሳትን የሆኑትን የበሬ ሰንጋዎች እያስገቡ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እያቀረቡ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 50 በሚደርሱ የተለያዩ አካባቢዎች የእሁድ ገበያ የሚቆም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ አዋጭነት ኖሮት ሳይሆን ህብረተሰቡን ለማገልገል ታስቦ እንደሆነ አንስተዋል። ይህንኑ ገበያ ከእሁድ ውጪ በየዕለቱ ለማድረግም አዋጭ አይደለም ብለዋል። ይህም ለህብረተሰቡ ትልቅ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ያሳያል።
እስካሁን በነበረው ሂደት ህብረት ሥራ ማህበራቱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ተገድቦ ብድር የሚሰጣቸው መሆኑ እንደችግር ይነሳል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ከገደብ ውጭ ሆኖ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶችን ወቅቱ እንደሚጠይቀው መግዛትና ማቅረብ እንድንችል የሚል ጥያቄ አላቸው። ከዚህ ውጭ ደግሞ በተለይም የእሁድ ገበያ በተመቸ ሁኔታ ላይ የሚሰራ ሥራ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የደህንነትና የምቾች ጥያቄዎች ይነሳሉ።
እነዚህን ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ማህበራት አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማቶች በማሟላት ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ቦታዎችን ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆነና ምቾት ያላቸውን የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት የሚችልበትን ሥርዓት ለመዘርጋት የዲዛይንና የቦታ መረጣ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህ ሥራ ሲጠናቀቅም እጅግ ዘመናዊና ምቹ የሆኑ የገበያ ማዕከላት በተለያዩ የከተማ አካባቢዎች ላይ ማየት ይቻላል።
በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያለው የገበያ ሥርዓት አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ ያልሆነበት ሥርዓት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት አጠቃላይ የገበያ ሥርዓቱ ብልሽት ሲሆን ይህም በህብረት ሥራ ኮሚሽን ብቻ የሚፈታ ችግር አይደለም። ይሁንና ይህን ለማስተካከል ኮሚሽኑ በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከአምራቹ በቀጥታ ወደ ሸማቹ መድረስ የሚችልበትን ሥራ እየሰራ ይገኛል። በቀጣይም ምርትን አምራቹ በሚሸጥበት ዋጋ ለተጠቃሚው መድረስ እንዲችል በመሀል ያለውን ሰንሰለት የማቋረጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ለዚህም በርካታ ባለድርሻ አካላት ያሉ ሲሆን ከእነሱ ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ይሆናል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ ተባብሶ የቀጠለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ትልቅ አቅም ያላቸውንና ህብረተሰቡ ራሱ ያቋቋማቸውን የህብረት ሥራ ማህበራት በባለቤትነት ደግፎ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ በቅርብ ሆኖ እንዲደግፍ ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል። ተቋማቱ በሁለት እግራቸው ቆመው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ጠጋ ብሎ ምን አይነት ምርቶች ቀርበዋል? ምንስ ችግር አለ ? ብሎ በመጠየቅ ያቋቋማቸውን ህብረት ሥራ ማህበራት እንዲደግፍና ተጠቃሚ እንዲሆን ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014