‘’የተከሰተው የአንበጣ መንጋ አስጊ ደረጃ ላይ አይደለም’’ ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፡- በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከወዲሁ መከላከል ካልተቻለ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተልተሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ::
ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እንደባለፈው የሚያሰጋ አይደለም ሲል ም ላሽ ሰጥቷል ::
የተልተሌ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አማረ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ የአንበጣ መንጋ ወረራ ለሁለተኛ ጊዜ በወረዳው ተከስቷል:: የመጀመሪው የአንበጣ መንጋ ከሕዳር እስከ መጋቢት 28 ቀን 2014ዓ.ም ድረስ ተከስቶ የተለያዩ ጉዳቶችን አስከትሏል:: ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ በቅንጅት በተደረገው የመከላከል ሥራም 19 መንጋ ማጥፋት ተችሏል::ቀሪው የአንበጣ መንጋም ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ሀመር አካባቢ ሸሽቷል ::
ሁለተኛ ዙር የአንበጣ መንጋ ወረራም ከሚያዝያ 7ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ እየተከሰተ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የተከሰተው የአንበጣ መንጋም ለመራባት የደረሰ፣ መብረርና መብላት የሚችል በቁጥር አምስት መንጋ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የአንበጣ መንጋው እንዳይስፋፋም በየደረጃው ለሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ቶሎ መፍትሔ እንዲሰጡ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል::
ግብርና ሚኒስቴር ቀድሞ በቦታው በመገኘት የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ማረጋገጡን ጠቁመው፤መንጋውን ለማጥፋም በአይሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መካሄድ እንደሚኖርበት ተገንዝቦ በየቀኑ ክስተቱን እንደሚከታተሉ ገልጸውላቸው መመለሳቸውን ነግረውናል::
ተልተሌ ግብርና ጽህፈት ቤት የተቻለውን ያክል በጂፒኤስ (GPS) በመታገዝ የአንበጣ መንጋውን እንቅስቃሴ በመከታተል ሪፖርት እያቀረቡ እንገኛለን ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ እስካሁን የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት በአይሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት አለመጀመሩን ተናግረዋል::
ጽህፈት ቤቱ አንበጣ መጋውን መከላከል የሚያስችለው እስከ 50 ሜትር ርቀት ኬሚካል የሚረጭ መሳሪያ ከግብርና ሚኒስቴር በድጋፍ ማግኘቱን ገልጸው፤ መንገድ በሌለባቸው ረግረጋማ አካባቢዎች መድረስ አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል::
አንድ የአንበጣ መንጋ 400 ሄክታር መሬት ማውደም እንደሚችል ገልጸው፤ እስከ አሁን ድረስ በተደረገው መከላከል አንድ ጊዜ ብቻ በ30 ሄክታር መሬት ላይ በሚገኝ አንበጣ መንጋ ላይ የኬሚካል ርጭት በማካሄድ ማጥፋት ተችሏል ብለዋል::
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ በወረዳው በሚገኙ 12 ቀበሌዎች አራት ሺህ 238 ሄክታር የእርሻ መሬት፣ ሰባት ሺህ 672 ሄክታር የግጦሽ መሬት ፣ስምንት ሺህ 471 ሄክታር የደን መሬትና አምስት ሺህ የ762 አባወራ መሬት ይዞታ ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል:: እስከ አሁን ድረስ ሶስት የአንበጣ መንጋ የት እንደደረሰ ባይታወቅም ወረዳው ድንበር አካባቢ ከመሆኑ አንጻር ወደ ኬንያ ሊሄድ ይችላል::
ወቅቱ በልግ እንደመሆኑ ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት ወደፊት በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ያሉት ኃላፊው፤ ኦሮሚያ ክልል መንግሥት በስልክ ጉዳን ከመከታተል በዘለለ በአካል አልተገኘም ብለዋል::
ኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትልና እጸዋት ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሕርጳ በበኩላቸው፤ቢሮው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰው ጀርባና በመኪና ላይ ሆነው የሚረጩ ኬሚካሎችንና ቁሳቁሶችን ለወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ድጋፍ አድርጓል:: አሁን ባለው ሁኔታ የአንበጣ መንጋውን መቆጣጠር አለመቻሉን ጠቅሰዋል::
ቢሮው ችግሩን ከወዲሁ በፍጥነት ለመፍታትም ከግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር የአይሮፕላን ኪራይ ውል በመፈራረም ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል ::
በአይሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እስኪካሄድ ድረስም ሕብረተሰቡና ባለሙያዎች ችግሩን ለመቅረፍ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል::
በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ በቅርቡ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል የሚረጩ መኪናዎችና ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው በመላክ በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
የአንበጣ መንጋው በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል :: የሚታየው ስጋት ባለፈው በአንበጣ መንጋ የተከሰተውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቁመው፤አሁን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በአካባቢው በዝናብ እጥረት ስላለ የአንበጣ መንጋው መራባት በማይችልበት ደረጃ በመሆኑ የሚያሰጋ አይደለም ብለዋል::
የአንበጣ መንጋው ከተከሰተ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ክትትልም አብዛኛው የአንበጣ መንጋ የሰፈረው በደን ውስጥ በመሆኑ በአይሮፕላን የታገዘ ኬሚካል ርጭት ማጥፋት እንደሚቻል ጠቁመው፤ ይህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ገልጸዋል::
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014