ድጎማ የሚል ቃል ሲነሳ ተደጋግሞ የሚነገረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በድጎማ ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑ ነው። በእርግጥም ድጎማ እንደኪሣራ መታሰብ ባይኖርበትም መንግሥት በሁሉም ነገሮች ላይ ድጎማ ማድረጉ ተገቢ ስላለመሆኑ ይገለፃል። ምክንያቱም በመንግሥት ላይ ጫና በርትቶ ሲያንገዳግደው ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ስለሚወድቅ አደጋው የከፋ እና የሰፋ ስለሚሆን። ይህንን መነሻ በማድረግ መንግሥት ከድጎማ ወጥቶ ኢኮኖሚውን ለገበያ ክፍት ለማድረግ ጥናት ከማካሔድ ጀምሮ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት አለበት የሚለውን ሃሳብ መሠረት በማድረግ መንግሥት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየገባ ስለመሆኑ እየተገለፀ ይገኛል።
መንግሥት ጫናው ሲበዛበት እያቃተው ማራገፍ ሲጀምር በጥንቃቄ ካደረገው ጉዳቱ አነስተኛ ጥቅሙ ደግሞ ከፍተኛ ይሆናል። በትክክል መደጎም ያለበት ኅብረተሰብ ጉልህ ጫና እንደማይደርስበት ተደርጎ እንዴት እንደተደጎመ ለማሳየት ያህል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድጎማ መቀነስን ተከትሎ ከ12 ዓመታት ቆይታ በኋላ የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ በመጥቀስ ድጎማ በዝርዝር ታይቶ በጥንቃቄ ከተነሳ የከፋ ጉዳት አያስከትልም የሚሉ ወገኖችም አሉ። የመንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድጎማ መሳሳት ለጊዜውም ቢሆን ብዙ የኅብረተሰብ ክፍልን ያነጋገረ እና በወቅቱ ፈጥሮት የነበረው ጫጫታ የሚዘነጋ ባይሆንም በዓመታት ተከፋፍሎ ከታኅሣሥ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማሻሻያው ሲተገበር ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ተገልጋይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥንቃቄ በመደረጉ መደጎም ያለበት ኅብረተሰብ ተደጉሞ የመንግሥት ጫናም ቀንሶለታል።
መንግሥት ብዙኃኑን ሕዝብ ለመጥቀምና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በሚል ከልክ ያለፈና በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ ድጎማ ማቅረብ ምንም እንኳ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጉዳት ለመቀነስ የሚያግዝ ቢሆንም መንግሥት የሚያጣው እና መደጎም ያለበት ኅብረተሰብ የሚያገኘው ጥቅም ሲነፃፀር ውጤቱ ሰፊ ልዩነት እንዳለው በመጥቀስ በኤሌክትሪክ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሌሎች ድጎማዎችንም መቀነስ እና ማንሳት እንደሚኖርበት የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ይናገራሉ። በምሳሌነት ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ የሕፃናት ምግብን በመደጎም እና ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግም ኅብረተሰቡ ግን መንግሥት ከሚያጣው ጋር የተመጣጠነ ጥቅም እያገኘ አይደለም። እነዚህ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ በማስገባት መንግሥት ብዙ መሠረተ ልማቶችን የሚሠራበትን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያጣ ይገኛል።
በዋናነት ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነው ነዳጅም ቢሆን ነዳጅ አምራች አገራት ሳይቀሩ በዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲመሩ ኢትዮጵያ ግን የሕዝቡ የገቢ አቅም አነስተኛ ነው በማለት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ በነዳጅ ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ጉድለት በመንግሥት እየተሸፈነ መቆየቱ በአጠቃላይ የአገሪቷ ወገብ እንዲጎብጥ በማድረጉ ከጥቅል ድጎማ ይልቅ ወደ ዝርዝር ድጎማ መግባት አስፈላጊ መሆኑ ተገልፆ ሥራዎች መሠራት ጀምረዋል። በተቃራኒው ነዳጅ ከአጠቃላይ ሊባል ከሚችል ምርት ጋር የተገናኘ በመሆኑ ድጎማ መቀነስም ሆነ ማንሳት አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል የሚል የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች አስተያየትም እየተስተጋባ ነው። ይህን እያሉ ካሉ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች መካከል ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ አንዱ ናቸው። ከድጎማ ጋር ተያይዞ እርሳቸውን ጠይቀን የመለሱልንን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ድጎማ ምንድን ነው ከሚለው እንጀምር?
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡– ድጎማ ሕዝብን ለመደጎም የሚሰጥ ነው። ድጎማ አንዳንድ ችግሮች ሲመጡ ሰዎች እንዳይቸገሩ ታስቦ የሚሰጥ ድጋፍ ነው። አሁን በቅርቡ ለምሳሌ የኮቪድ -19 መከሰቱን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች የአውሮፓ ሁሉም አገራት ዜጎቻቸው ሥራ ስላልሠሩ በማለት በየሂሳብ ቁጥራቸው በርከት ያለ ገንዘብ ልከዋል። በትሪሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተዋል። ይህ በአውሮፓም ሆነ በሰሜን አሜሪካ የተፈፀመ ነው። ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች በተለያየ መልኩ ሕዝባቸው እንዳይጎዳ በማሰብ ይደጉማሉ። ለምሳሌ መንግሥታት ከውጭ የሚመጣ ነዳጅን ይደጉማሉ። ምክንያቱም ነዳጅ የልማት ሞተር ነው።
ነዳጅ ሲጨምር ትራንስፖርት ስለሚጨምር የሁሉም የሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል። ሕዝብ የሚንቀሳቀስበት ዋጋ ይጨምራል። ስለዚህ እኛም አገር ለረዥም ጊዜ ነዳጅ በድጎማ ላይ ነበር። በተጨማሪ አስፈላጊ የሚባሉ ሰዎች በየቀኑ የሚጠቀሟቸው ምግቦች ይደጎማሉ። ለምሳሌ ግብፅ፣ ሱዳን እና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ምግቦች እንዳይወደዱ እና ሕዝቡ እንዳይቸገር ይደጉማሉ። በግብፅ ለ50 ዓመታት የዳቦ ዋጋ አልተቀየረም። ሱዳን ለረዥም ጊዜ የዳቦም ሆነ የሌሎች ምግቦች ድጎማ ነበር። ልክ ድጎማው ሲነሳ አልበሽርን ሕዝቡ ‹‹ሆ›› ብሎ አባርሮታል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ድጎማ ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ሲባል የሚካሔድ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡- በትክክል ድጎማ ለሕዝብ ብቻ አይደለም፤ ለመንግሥትም የሚጠቅም ነው። ምክንያቱም ድጎማ ሰላም እና ደህንነት ላይ የራሱ ሚና ይኖረዋል። ድጎማ ሲቀር ሰላም ይጠፋል። ይሔ ደግሞ ለመንግሥትም አደጋ ይሆናል። ምክንያቱም ሕዝብ ተጎዳሁ ብሎ ሲያምን ወደ ሌላ ነገር ይገባል። በአብዛኛው በተለይ የኑሮ ውድነት ሲያጋጥም ድጎማ ከሌለ ችግር ይፈጠራል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ በ1980ዎቹ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ብለው በሚያስተገብሩበት ጊዜ ወደ 40 አገሮች የመንግሥት ግልበጣ ተደርጓል። ይህ የሆነበት ምክንያት ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ የሚሉት መንግሥታት ድጎማ እንዲያነሱ ሲገፋፉ፤ ሕዝቡ ሠርቶ መክፈል ካልቻለ የመንግሥት የገንዘብ ቋት ባዶ ይሆናል በማለት ነበር። በተጨማሪ ልማት አይኖርም፤ ስለዚህ ሰፊ ልማት እንዲኖር እና ሕዝቡ እንዲንቀሳቀስ ድጎማ አንሱ ይሉ ነበር። ነገር ግን መንግሥታቱ ድጎማ ሲያነሱ እነርሱ እንዳሉት አልሆነም። እንዲያውም ሕዝቡ ተነሳ።
ድጎማ የተነሳበት ሕዝብ ወደ ልማት ከመግባት ይልቅ ወደ አመፅ ሔደ። የሚያሳዝነው ሕዝቡ ሲነሳ ደግሞ ምንም እንኳ ወጣቱ እና ሌላ ሌላውም በሙሉ በአንድነት ‹‹ሆ›› ብሎ ቢወጣም ተደራጅቶ ያለው ወታደር ብቻ በመሆኑ ወታደሩ ስልጣኑን ይረከባል። ለዚህ በምሳሌነት ማሊ፣ ጊኒ እና ሌሎችንም አገሮች መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ አገራት ያ ሁሉ ችግር የተከሰተው ከድጎማ ጋር ተያይዞ ነው። ድጎማዎች በአጠቃላይ በበጀት ተይዘው ለሕዝብ የሚሰጥ ሲሆን በተለይም ምግብ ነክ ነገሮች ተራው ኅብረተሰብ መጠቀም እንዲችል ማድረግ ትክክል ነው። በተቃራኒው ከሆነ ችግሩ ቀላል አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ድጎማ መሰጠት ያለበት በትክክል ለማን ነው?
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡- አንዳንድ በኅብረተሰቡ ውስጥ በደል የደረሰባቸው ናቸው የሚባሉ ቡድኖች እንዲደገፉ መደረግ ይኖርበታል። ለምሳሌ የሴቶች ፖሊሲ ሲወጣ ፣ የሕፃናት ፖሊሲ ሲወጣ፣ የአቅመ ደካሞች ፖሊሲ ሲወጣ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በሙሉ የሚጠቀሙባቸው ነገሮች ድጎማ የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል። ሌላው ደግሞ በጤናው ረገድ የሆስፒታል የአገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ዜጎችን እንዳይጎዳ፣ የመድኃኒት ዋጋ እንዳይንር በብዙ አገሮች ድጎማ ይደረጋል። ለምሳሌ አውሮፓ ለዜጎቻቸው በነፃ ሕክምና ይሠጣሉ። መድኃኒት በሙሉ ነፃ ነው። በሌላ በኩል የርዕዮተ ዓለም ጉዳይም አለ። ሶሻሊስት ዘመም የሆኑ ክርስቲያን ዴሞክራቶች፣ ሶሻሊስት ዘመሞች ዋናው ትኩረታቸው የሕዝባቸው ደህንነት ነው። ስለዚህ ድጎማን ያበረታታሉ።
በሌላ በኩል ሕዝባዊ ነን ባይ መንግሥታት እየተነሱ ድጎማዎችን እያነሱ ሕዝቡ በውድድር መኖር አለበት በማለት አቋም ይይዛሉ። እነኚህኞቹ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚሉት ከአፍሪካ የመጡ ስደተኞች ሥራችንን ወሰዱ፤ ለምሳሌ ከሶሪያ በስደት የሔዱትን በመጥቀስ ሙስሊሞች አገራችን ውስጥ ገቡብን ይላሉ። ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ግን ኢኮኖሚውን ያደቃሉ። ለምሳሌ ከዩክሬን ጋር ተያይዞ ፑቲን ከምዕራቡ ዓለም ጋር የገቡበት ጭቅጭቅ ሕዝባዊ ናቸው የሚባሉትን ሊያጠፋቸው ይችላል። ምክንያቱም አሁን ቀኝ ዘመም የመንግሥት አስተዳደር ሳይሆን የድሮዎቹ አገር በመጠበቅ የሕዝብን ደህንነት በማረጋገጥ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣን ላይ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።
አዲስ ዘመን፡- የሱዳንን የአልበሽርን ተሞክሮ በማየት ድጎማ ድሃውን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን መንግሥትንም ይጠቅማል ብለዋል። እስኪ በደንብ አብራርተው ድጎማ በትክክል ማንን ይጠቅማል?
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡– ድጎማ ተብሎ ሲነሳ ዋነኛው ትኩረቱ የሰዎች ደህንነት ነው። እዚህ ላይ የመንግሥት ደህንነት እና የአገር ደህንነት ሁሉ የሚካተቱበት ነው። የሰዎች ደህንነት ሲባል የእያንዳንዱ ግለሰብ ደህንነት ነው። ግለሰቦች ደህና ካልሆኑ በተለይ እንደአፍሪካ ባለች ከፍተኛ ቁጥር ባለባት አህጉር ውስጥ ያሉ አገራት የወጣቶች ደህንነት ትልቅ ጉዳይ ነው። ወጣት ተምሮ ሥራ የሚያገኝበት ዕድል ከሌለ የራሳቸውን ሥራ የሚፈጥሩበት ሁኔታ ላይ ፖሊሲዎች እና የመንግሥት የአስተዳደር ሥርዓት ሲታይ አስቸጋሪ ካልሆነ ድጎማ ሲነሳ ተያይዞ አመፅ ይቀሰቀሳል። በዚህ ጊዜ ወጣቱ ወደ መበጥበጥ ይገባል። ነገር ግን ወጣቱ ሥልጣን አይይዝም። ስልጣን የሚይዘው ወታደር ይሆናል። ወታደሩ ደግሞ ካለፈውም መንግሥት የባሰ ይሆናል። ለዚህ ማሳያው የደርግ ዘመንን እንደምሳሌ ማቅረብ ይቻላል።
በወታደር አገዛዝ ሕዝብን መግደል እና መጨረስ ታይቷል። በሌላ በኩል ከወታደሩ ውጪ ደግሞ የሽምቅ ተዋጊዎች ወደ ስልጣን የሚወጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለምሳሌ ኢህአዴግን መጥቀስ ይቻላል። በሌሎች አገሮችም እንደታየው የሽምቅ ተዋጊዎችም ሆኑ ወታደሮቹ የሚታያቸው ጠላትን ማጥፋት ብቻ ነው። ምክንያቱም የሚሠለጥኑት ጠላት ሲታይ መግደል ላይ ብቻ በመሆኑ ጠላትን በማነጋገር የሚያምኑ አይደሉም። ስለዚህ መንግሥታት ለራሳቸው ሲሉ ድጎማ ማድረግ አለባቸው። ዋናው ነገር ግን የኢኮኖሚ ፖሊሲው መልክ መያዝ አለበት። አሁን ዚምባቡዌ ገንዘቡ ዋጋ አጥቶ የገንዘብ ግሽበቱ ሰማይ ወጥቶ መጨረሻ ላይ ብዙ ዓመት የቆዩ ሰውዬን ፕሬዚዳንት ሙጋቤን ከስልጣናቸው ያወረዳቸው የራሳቸው ፓርቲ ነው። በሽርም የራሳቸው ወታደሮች ናቸው ያወረዷቸው። ስለዚህ ይህ ሲታይ ድጎማ ለመሪዎችም ሆነ ለአጠቃላይ የአገሪቱ ባለስልጣናት የሚጠቅም ነው።
ድጎማ ሲነሳ ሁሉንም የሚጎዳ ይሆናል። ለምሳሌ ላይቤሪያ ላይ ፕሬዚዳንቱንም ሚኒስትሮቹንም ገድለው አስክሬናቸውን ሕዝብ እንዲያየው ብለው በአደባባይ ፀሐይ ላይ ያዋሉት በዚሁ ምክንያት ነው። አብዛኛውን ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የመንግሥት ግልበጣ የሚካሔደው በዚሁ ምክንያት ነው። እኛም አገር በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ነዳጅ በሳንቲም ቤት ትንሽ ጨመረ ተብሎ ነገር ተንቀሳቀሰ። ታክሲ በጠበጠ ተማሪም ሲናገር ኖሯል። መሬት ላራሹ እና የብሔር ብሔረሰብ መብት ተባለ፤ የደርግ ወታደራዊ አስተዳደር ተቋቋመ። ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ መጀመሪያ 60ዎቹን አረደ። ይህን ተከትሎ በነጭ ሽብር እና በቀይ ሽብር እንዲሁም በረሃብ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ አለቀ። 28 ነፃ አውጪ ግንባሮች ተቋቁመው ደግሞ ደርግ ሲወድቅ የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ። ስለዚህ መንግሥት ድጎማን በሚመለከት በሚወስደው ርምጃ ጥናት ላይ ተመስርቶ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- የድጎማ መነሳት የሚጠቅመው ማንን ነው?
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡– የድጎማ መነሳት የሚጠቅመው መንግሥትን ብቻ ነው። መንግሥት ምናልባት በጀቱን ለማስተካከል ያግዘዋል። ነገር ግን ድጎማ የሚደረገው በሁለት መንገድ ነው። አንዱ ለምሳሌ ነዳጅን መጥቀስ ይቻላል። እኔ ወደ 26 አገራት ሠርቻለሁ። በአፍሪካ አገር በሙሉ ከአንድ ዶላር በታች ቤንዚል የለም። ይሔ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ነው። በአገራችን ግን ነዳጅ ለረዥም ጊዜ ሲደጎም የኖረ ነው፤ ምክንያት አለው። አንደኛው የኅብረተሰቡ ገቢ ዝቅተኛ መሆን ሲሆን፤ ሌላው በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ደረጃ እየሔደ ያለ እንደኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ ነዳጅ መደጎሙ መጨረሻ ላይ ኅብረተሰቡ ሠርቶ አምጥቶ በሚከፍለው ታክስ አገሪቱ ላይ በሚያመጣው የኢኮኖሚው ጥቅም ይሸፈናል ተብሎ ታስቦ ነው።
ይሔ ድጎማ ሲነሳ የመንግሥት ጫና ይነሳል። ነገር ግን መንግሥት ድጎማውን በሚያነሳበት ጊዜ ሌሎቹ የኢኮኖሚ አውታሮች እየሠሩ ነው ወይ ሕዝቡ በዚህ ሊንቀሳቀስ ይችላል ወይ የሚለው በደንብ መታየት አለበት። ለምሳሌ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ቢያነሳ ሕዝቡ እንዴት ይንቀሳቀሳል የሚለው ሊጤን ይገባዋል። ድጎማ ከሰብአዊ ዕርዳታ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። አገራችን ውስጥ ብዙ ግጭቶች አሉ። በሌላ በኩል በድርቁ ምክንያት ብዙ የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉም አሉ። ምግብ፣ መጠለያ እና መድኃኒት ይፈልጋሉ፤ የሚሰጣቸው በነፃ ነው። ድጎማ ከዚያ ትንሽ ከፍ ያለ እንጂ ያነሰ አይደለም። ድጎማ በቋሚነት ማድረግ ሳይሆን ጥናት እየተጠና ዩኒቨርሲቲዎች በየክልሉ በየአካባቢው በሚያርጉት ጥናት ላይ በመመስረት በተለያየ መልኩ ድጎማ ማድረግ ይቻላል። በመጨረሻም ይሔ የአገሪቱን ደህንነት እና የውስጥ መረጋጋትን የሚያረጋግጥ ነው።
የኢኮኖሚ ችግር ሁልጊዜ ለሕዝቦች መነሳሳት ዋና ምክንያት ነው። ሕዝቦች በሚነሳሱበት ጊዜ ደግሞ መሪ የሌለው የሕዝብ መነሳሳት ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ምክንያቱም መሪ ቢኖራቸው ከመሪዎቹ ጋር ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት ይቻላል። መሪ ከሌለ ግን በየቦታው የሚነሳው የሕዝብ ብሶት ወደ ፅንፈኝነት አምርቶ እርሻ እና ፋብሪካ ወደ ማቃጠል ገብቶ አገር ያፈርሳል። አገራችንም ውስጥ ብዙ አይተናል። መኪና ማቃጠል፤ ምግብ ወደ ከተማ እንዳይገባ መከልከል እና ሌሎችም ጥፋቶች ነበሩ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ማነጋገር የሚቻልበት ሁኔታም አይኖርም። የፀጥታ ኃይሎቹ ደግሞ በጉልበት ፀጥታ ለማስከበር ሲሞክሩ ሌላ ቀውስ ይፈጠራል። ስለዚህ ጥንቃቄ ያሻል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014