
የዛሬው እንግዳችን መልሰው ደጀኔ (ዶ/ር) በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና ልማት፣ ጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ናቸው። በኢትዮጵያ ማሕበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ዙሪያ የተለያዩ ምርምሮችን አካሂደዋል። የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸውንም ያከናወኑት በኢትዮጵያ ማሕበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ላይ ነው። ብዙ በተመራመሩበት ማሕበራዊ ጥበቃ ላይ በሚያተኩረው ቃለመጠይቅ ዘርፉን የተመለከቱ ጥልቅ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፤ መልካም ቆይታ!
አዲስ ዘመን፡- ማሕበራዊ ጥበቃ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ምንድን ነው ?
መልሰው (ዶ/ር)፡– ማሕበራዊ ጥበቃ ወይም ማሕበራዊ ዋስትና የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ሰዎች በሕይወት ዑደቱ ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው አደጋዎች (ሥራ አጥነት፣ አካል ጉዳተኝነት፣ እናትነት ወዘተ) እና በአጠቃላይ ድህነት እና ማሕበራዊ መገለል ለሚሰቃዩ ሰዎች ጥቅማ ጥቅሞች የሚሰጡበት ማሕቀፍ ነው።
ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም. ያጸደቀችው የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ማሕበራዊ ጥበቃ በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን፣ የዜጎችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ተጋላጭነትንና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የተመጣጠነ እድገትን በማረጋገጥ ላይ የሚያተኩር የማሕበራዊ ፖሊሲ ማሕቀፍ አካል መሆኑን ይገልጻል።
አዲስ ዘመን፡- በማሕበራዊ ጥበቃ ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ተሞክሮዎች በስኬት የሚነሱ ሀገራት እዴት ያለ ውጤት አግኝተዋል ?
መልሰው (ዶ/ር)፡- ስዊዲን፣ ኖርዌይ እና ፊላንድን የመሰሉ የስካንዲኔቪያን ሀገሮች የማሕበራዊ ጥበቃ ሞዴል እጅግ ተራማጅ የሚባል ነው። ፊላንድን በአብነትነት ብንጠቅስ ስርዓቱ ሥራ መፍጠር ላልቻለለት ዜጋ መሰረታዊ ፍላጎቱን ማሟላት እንዲችል ከመንግሥት መውሰድ አለበት ብለው ያስቀመጡት የፈንድ መጠን አለ። ፈንዱ መሰረታዊ መጠለያ፣ መሰረታዊ ምግብ እና መሰረታዊ ጤና ማሟላት እንዲያስችል ብቻ ታስቦ የተበጀተ ነው። መሰረታዊ የሚለው ቃል ትኩረት የተሰጠው ከመሰረታዊ ፍላጎት በላይ የሆኑትን ፍላጎቶች ዜጎች ሰርተው ማምጣት አለባቸው በሚል እሳቤ ነው። ስርዓቱ በማሕበራዊ ጥበቃ ሰበብ ጠባቂነት እንዳይኖር ያደርጋል።
በፊላንድ ማንኛውም ሥራ ያጣ ዜጋ በወር 1600 ዶላር ከመንግሥት መውሰድ ይችላል። ይህ ለሁሉም ዜጎች ስር ነቀል ማሕበራዊ ጥበቃን ለማድረስ ያለመ ሥራ ነው። 1600 ዶላር ከፊላንድ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በጣም ያነሰ ነው። ዜጎች ሥራ አጥተው መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ባለመቻል ጎዳና እንዳይወጡ የሚያደርግ ስርዓት ነው የዘረጉት።
ሌላኛው በጥሩ ምሳሌነት የሚነሳው የብራዚል ማሕበራዊ ጥበቃ ስርዓት ነው። ብራዚል ቦልሳ ፋሚሊያ የሚባል የቤተሰቦችን ተጋላጭነት በመቀነስ እና በማሕበራዊ ጥበቃ ተደራሽ የማድረግ ትልቅ ፕሮግራም ነበራት። ፕሮግራሙ የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን ዜጎቿ እንዲያገኙ ስርዓት የተፈጠረበት አካሄድ ነበር። ስርዓቱ በምሳሌነት ተወስዶ ሌሎች የላቲን አሜሪካ እና እኛን ጨምሮ የደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ሀገራት ሄደው አይተው እንደ ልምድ በመውሰድ የሴፍቲኔት ፕሮግራምን እንዲያስቡ እና እንዲያቅዱ ያደረገና የተጽዕኖ አድማሱ የበረታ ነው።
በአፍሪካ የተሻለ ተሞክሮ ያላት በደቡብ አፍሪካ ናት። በሀገሪቱ ሕጻናት ላይ እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ አለ። አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው ዕደሜዬ ደክሟል፤ አቅሙ የለኝም ካለ ሰራተኛ ነበረ አልነበረ እንዲሁም ሥራ አጥ ነው አይደለም የሚል መመዘኛ ሳይኖር ያለፍረጃ ይስተናገዳል። ዜጎች አቅም በከዳቸው ወቅት ጎዳና ላይ ወድቀው ለስርዓቱ ሸክም እንዳይሆኑ መሰረታዊ የማሕበራዊ ጥበቃ እንዲያገኙ ይደረጋል። በኢትዮጵያ መደበኛ የማሕበራዊ ጥበቃ ዋስትና ያለው በጡረታ ዘመን የመንግሥት ሰራተኛ ወይም በግል መንግሥት ድርጅት ውስጥ ተቀጣሪ የነበረ ሰው ብቻ ነው። በሌላ በኩል መደበኛ ገቢያቸው በተጨባጭ ስለሚታወቅ ጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ ሕጻናትን ትምህርት ቤት ለመላክ አቅም ያነሳቸው ወላጆች ተለይተው የጤና እና የምግብ ፍላጎታቸው እንዲሟላ የማሕበራዊ ጥበቃ ሽፋን ያገኛሉ። ዓላማውም ልጆቻቸው መሰረታዊ የምግብና የጤና ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሕበራዊ ጥበቃ ሥራዎች በኢትዮጵያ ያላቸው መሰረት ምን ይመስላል ?
መልሰው (ዶ/ር)፡- ከልማት አጋሮች እና ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት መንግሥት የሚያደርገው መደበኛ የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ከዘመናዊት ኢትዮጵያ በተለይም ከአጼ ኃይለሥላሴ ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው። ሕገመንግሥታዊ መሰረት ተሰጥቶት በ1955 ቱ የንጉሡ ሕገመንግሥት ላይ ተካትቶ ይገኛል።
አጀማመሩ በወሎ እና ትግራይ አካባቢዎች የዝናብ እጥረትን ተከትሎ ከተከሰቱ ቀውሶችና የረሃብ አደጋዎች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በጣም ጠባብ የሆነና አደጋ ላይ ትኩረት አድርጎ እሳት የማጥፋት አይነት ሚና የነበረው ነው። እያንዳንዱ ነገርም ሙሉ በሙሉ በንጉሱ በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ነበር። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ንጉሱ የምግብ እጥረት ኮሚቴ አቋቁመዋል። ሰባት አባላት የነበሩት ይህ ኮሚቴ በወቅቱ የነበረው ድርቅ ካደረሰው አደጋ አንጻር የሚመጥን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም አልነበረውም።
በደርግ መንግሥትም የነበረው የማሕበራዊ ጥበቃ ጉዳይ ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ በመስጠት የቀጠለው ነው። ደርግም በበኩሉ የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አቋቁሞ የነበረ ሲሆን ኮሚሽኑ ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ የመንደር ምስረታ ማካሄድ ነበር። የመንደር ምስረታው ወታደራዊው ሥርዓት ያከናወነው ትልቁ የማሕበራዊ ጥበቃ ሥራ ነው። ነገር ግን የማሕበራዊ ጥበቃ በመጀመሪያ ደረጃ በተጠቃሚው ማሕበረሰብ ይሁንታ ላይ መመስረት አለበት። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመንደር ምስረታው አስገዳጅ እና በደምብ ያልታሰበበት ነበር። በወቅቱ በድርቅ ተጠቅተው ከነበሩት የወሎ እና የትግራይ አካባቢዎች በዘመቻ መልኩ በአስገዳጅ ሁኔታ ሕዝብን በማንሳት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማስፈር ሥራ ተሰርቷል።
ሰፈራ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ሰፋሪዎቹን ለወባ እና ለተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ያጋለጡ ናቸው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች በሚያሳዝን ሁኔታ የአንድ ቤተሰብ አባላት በመበታተን ግማሹ አንድ ቦታ ግማሹ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ጭምር ያደረገ አካሄድ ነበር። በዚህም ምክንያት ወታደራዊው አገዛዝ በብዙ የተወቀሰበት ድርጊት ሆኗል።
ደርግ ሰዎች በቀጥታ እርዳታ ተሰጠን ብለው እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ሥራ እንዳያቆሙ ምግብ ለሥራ በሚል አካባቢያቸው የሚፈልገው የልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ክፍያ እንዲያገኙ ያደርግ ነበር። አካሄዱ በማሕበራዊ ጥበቃው የታቀፉት ሰዎች ራሳቸውን እንደተረጂ እንዳያዩና የተረጂነት አስተሳሰብ እንዳያዳብሩ ለማድረግ ያለመ ነው።
ከደርግ በኋላ የተከተለው ኢሕአዴግ በመደበኛ ፖሊሲ ደረጃ የመጀመሪያ የሚባለውን የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ አውጥቷል። ከሕገመንግሥቱ በዘለለ ለማሕበራዊ ጥበቃ ሥራ ፖሊሲ በመቅረጹ ትልቅ እምርታ ነው ማለት ይቻላል። ፖሊሲው ማሕበራዊ ጥበቃን ሳይንሱ በሚለው እና አሁን ባለው እሳቤ ሰፋ አድርጎ ከልማት ጋር አስተሳስሮ ያየ ባይሆንም የማሕበረሰብን ደህንነት እንዴት አድርገን እንከላከል እንዲሁም እንዴት ድርቅን እንቋቋም ከሚል እይታ የተነሳ ነው። የፖሊሲው እይታ በጣም አጭርና በማሕበራዊ ጥበቃ የምርምር አይንሲታይ ፈራጅ የሆነ ነበር። ለአነብነትም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ብሎ በሌሎች አካባቢዎች ምንም ችግር እንደሌለ አድርጎ ይወስዳል እንዲሁም አካል ጉዳተኞች ብሎ ከአካል ጉዳት ውጪ የተፈጥሮ ጉዳቶች እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ማሕበራዊ ጥበቃ የማግኘት ሕገመንግሥታዊ መብት ያላቸውን ሰዎች የሚያገል ፍረጃ የነበረው ነው።
አዲስ ዘመን፡- 2007 ዓ.ም የጸደቀው አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የማሕበራዊ ፖሊሲ ከቀደሙት የተለየ ነው ?
መልሰው (ዶ/ር)፡- በ2007 ዓ.ም የጸደቀው አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ አዋጅ በተለየ መልኩ ተራማጅ ሆኖ የወጣ ነው። አደጋን መከላከል እና መልሶ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ልማትን በማረጋገጥ በቋሚነት የማሕበረሰብን የኑሮ መሰረት መቀየር ላይ ትኩረት አድርጓል።
ፖሊሲው በድህነትና በተጋላጭነት ውስጥ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚዘረጉ አገልግሎቶች አቅርቦትና ተደራሽነት በተፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያግዷቸው በርካታ መሰናክሎች በመኖራቸው ፍላጎትንና አቅርቦትን በማመጣጠን ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የማሕበራዊ ጥበቃ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢና ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ያነሳል።
መሰረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠትና በወቅታዊ ድጋፍ ላይ ብቻ ሳይወሰን የማሕበረሰብ ተሳትፎንና ንቅናቄን በማጠናከር እና የተቀናጀ ሥርዓት በመዘርጋት በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈሩትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ባሕላዊና ሰብዓዊ መብቶች ከማስጠበቅ ባሻገር የተሸጋጋሪነት ባሕርይ ያላቸውንና በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚታዩትን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ተጠቃሚነት ልዩነቶችንና አለመመጣጠንን ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንደተካተቱበት ይገልጻል፡፡
ማሕቀፉ በዋናነት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ፣ በኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ለመከላከል፣ ዘርፈ ብዙ የማሕበራዊ ዋስትና ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ የዜጎችን ሰርቶ የማግኘትና ጥሪት የመያዝ አቅምን ለማጎልበት፣ የሥራ እድልንና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የተዘጋጀና ለጥቃትና በደል ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሕግ ጥበቃና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በ2007 ዓ.ም በጸደቀውና አሁንም በሥራ ላይ ባለው የማሕበራዊ ፖሊሲ አዋጅ በማሕበራዊ ጥበቃ ሥራዎች የታዩ እምርታዎች ምንድን ናቸው?
መልሰው (ዶ/ር)፡- “Policy Coherence and Social Protection in Ethiopia: Ensuring No One Is Left Behind” በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 2019 ባካሄድኩት ጥናት የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን በመቅረጽ ማሕበራዊ ጥበቃን ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን ገልጫለሁ።
የኢትዮጵያ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በአፍሪካ ሁለተኛው ትልቁ የማሕበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ የተጀመረው አሁን ሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ገና ጠረጴዛ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። መንግሥት እርዳታ ላይ ብቻ ማተኮር ጠባቂነት እንዲመጣ ያደርጋል የሚል ስጋት ስለገባው ከርዳታ ወጥተን ልማታዊ እናድርገው የሚል ውሳኔ ላይ በመድረሱ የተገባበት አካሄድ ነው።
ከአምስት ዓመታት በፊት እኔ ባጠናሁት ጥናት እንዳረጋገጥኩት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ሰዎች፤ ቀጥተኛ ድጋፍ ከሚያገኙት አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ አጥቢ እናቶች እና ነብሰ ጡሮች ውጭ ያሉት በዕለታዊ ሥራ ተሰማርተው ሰርተው ነው የሚከፈላቸው። ሰዎቹ በቀን 39 ብር አካባቢ እየተከፈላቸው በሳምንት አራት ቀን ነበር የሚሰሩት። በወቅቱ በአካባቢው የቀን ሥራ የሚሰራ አንድ ሰው በቀን የሚከፈለው 60 ብር ነበር። መንግሥት በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉት ዜጎች 60 ብር የሚከፈላቸው ከሆነ ሥራ የመሥራት ፍላጎት አይኖራቸውም በሚል የ21 ብር ልዩነት እንዲኖረው አድርጓል። ይህም መንግሥት የሴፍቲኔት ፕሮግራሙን ሲተገብር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን የሚያመላክት ነው።
ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ሥራ ፈጥሮ ሰዎችን በማቋቋም ዘለቄታ ያለውና ከአጭር ጊዜ ድጋፍ አስተሳሰብ የወጣ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና እንደ ዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም ዩኤስ ኤይድ ያሉ ታላላቅ የልማት አጋሮችን በአንድነት ያጣመረ ስኬታማ መሆን የቻለ ነው።
በኢትዮጵያ የማሕበራዊ ጥበቃ ሥራን ማን ነው መሥራት ያለበት የሚለው የባለቤትነት ችግር ነበረበት። የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ባለቤት የነበረውና በዋናነት ሥራውን መምራት አለበት ተብሎ የሚታሰበው በወቅቱ የነበረው የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር። ነገር ግን ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙን አስፈጽም ተብሎ ተልዕኮ የተሰጠው ለግብርና ሚኒስቴር ነበር። በዚህ ምክንያት የአፈጻጸም ብዥታዎች እና የተለያዩ እጥረቶች የነበሩበት ነው። በኋላ ግን መንግሥት ለማሕበራዊ ጥበቃ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ብቻውን አቋቁሞ መንቀሳቀሱ ከፍተኛ ውጤት እንዲመጣ አድርጓል።
በብዙ ጥናቶች እንደተመላከተው ድህነት የገጠር ብቻ ሳይሆን የከተማም ችግር ነው። ከተማ ውስጥም የድሃ ድሃ የሚባሉ ማሕበረሰቦች አሉ። ልማትን ማረጋገጥ ካለብን እነሱን ዘንግተን መሆን የለበትም የሚል ምልከታ እየዳበረ መጥቷል። አስተሳሰቡ በመሻሻሉ በ2008 ዓ.ም ከተማ አቀፍ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጀምሯል። ቀደም ሲል የተዘነጉ አካባቢዎችን በማካተት በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አበባን ጨምሮ በስምንት ዋና ዋና የክልል ከተሞች ልማታዊ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በፓይለት ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ ወደ መደበኛ ሕይወት በመመለስ በሠራው ሥራ ሚኒስትሯ ኒውዮርክ ድረስ ተጠርተው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። መንግሥት በዚህ ረገድ ትልቅ ሥራ ነው የተሠራው። በቀጣይ ወደ ነበሩበት እንዳይመለሱ እንዲሁም ሌሎችም ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ስር ነቀል የሆነ ሥራ መሥራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የማሕበራዊ ጥበቃ ሥራዎች ያጋጠማቸው ተግዳሮቶች እንዴት ያሉ ናቸው ?
መልሰው (ዶ/ር)፡- እኛ ባጠናነው ጥናት የአሁኑ ልማታዊ ሴፍቲኔት እጥረት ተብሎ የሚጠቀሰው ያገለላቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ተመልክተናል። ልየታው አካባቢን መሰረት ያደረገ መሆኑ አንዱ ክፍተቱ ነው። ሳይንሱ እንደሚለው ድህነትና ተጋላጭነት አካባቢያዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው። ለምሳሌ እንደ ክልል ካሰብን ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ማሕቀፍ ውስጥ አልነበሩም። ፖሊሲው ለድርቅ ወይም ለምግብ እጥረት ተጋላጭነት አለው በሚባል አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው በሴፍቲኔት እንዲታቀፍ ሲያደርግ፣ በአንጻራዊነት የዝናብ እጥረት የሌለበትና ምርታማ ነው ተብሎ በታሰበ አካባቢ የሚኖር ድሃ በአካባቢው በመኖሩ ብቻ ለችግር አልተጋለጠም ብሎ የሚያስብ ነው።
ሁሉንም አካባቢ በአንድ ጊዜ መድረስ ባይቻልም እንኳን የዝናብ እጥረት ያለባቸው እና የሌለባቸው ብሎ ፈርጆ የተነሳ ነው። ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፈጥሮ ሰዎችን በማቋቋም ዘለቄታ ያለው ከአጭር ጊዜ ድጋፍ አስተሳሰብ የወጣ በመሆኑ ስኬታማ ቢሆንም በአፈጻጸሙ ከአቅም ውስንነት እና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የተነሳ የራሱ እጥረቶች ነበሩበት።
በሌላ በኩል ማሕበራዊ ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብኣዊ መብት ነው። መሰረታዊ የማሕበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ማግኘት ሕገመንግስታዊ ነው። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ማሕበራዊ ጥበቃን ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል። እኛ ሀገር ማሕበራዊ ጥበቃ የዲሞክራሲዊ መብት ተደርጎ ነው የተቀመጠው። አቅም በፈቀደ መጠን የሚለው አገላለጽ ለመንግሥት ግዴታ አለመሆኑን የሚገልጽ ነው። በሌሎች ሥርዓቶች ግን መንግሥት መሰረታዊ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ካቃተው መንግሥት ግዴታውን እንዳልተወጣ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው።
አዲስ ዘመን፡- የማሕበራዊ ጥበቃ ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት ?
መልሰው (ዶ/ር)፡- 130 ሚሊየን ከሚጠጋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ የማሕበራዊ ድጋፍ እያገኘ የሚገኘው 10 በመቶ እንኳን አይሆንም። የማሕበራዊ ጥበቃ ሽፋን ባለማድረግ ምክንያት የሚመጣው ቀውስ ማሕበራዊ ጥበቃ ለማድረግ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በአንድ ዓመት ውስጥ 10 ሚሊዮን ተጋላጭ ወገኖች ያሉት አንድ መንግሥት የማሕበራዊ ጥበቃ ሽፋን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ካለ፣ ድጋፉን ባለመስጠቱ ምክንያት በቀጣዩ ዓመት የተጠቀሱት ዜጎች ይበልጥ ተጋላጭ ሆነው፤ ሌሎች 10 እና 20 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ አዲስ ተጋላጭ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። ችግሩን ገና ሳያገነግን እልባት ለመስጠት ጥረት ባለማድረግ ምክንያት ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ለነብስ አድንም ሆነ ለሌሎች ድጋፎች የሚወጡት ወጪዎች እጥፍ ድርብ ይሆናሉ።
አትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጅት አባል በመሆኗ ምክንያት የማሕበራዊ ጥበቃ ወለልን የተመለከተ ስምምነት ፈርማለች። ወለል ማንኛውም ሀገር ማሕበራዊ ጥበቃን ለመስጠት ማሟላት ያለበት ዝቅተኛው ደረጃ ነው። ብዙ ሀገራት ዝቅተኛ ወለሉን ለማሟላት ኢኮኖሚያቸው በፈቀደላቸው መጠን እየጣሩ ነው። መንግሥታዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ የወጣቶች ሥራ አጥነት 22 በመቶ አካባቢ ነው። ኢኮኖሚው ይህን ያህል ቁጥር ላለው ወጣት ሥራ መፍጠር ካልቻለ በማሕበራዊ ጥበቃ በኩል ሽፋን መሰጠት አለበት ማለት ነው። በኢትዮጵያ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙን ግጭቶች ጋር በተያያዘ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። በተበታተነ መልኩ ቢሆንም በየቦታው በስፋት የተጀመሩ የማሕበራዊ ጥበቃ ሙከራዎች አሉ። ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌውን እና መሰረታዊ የማሕበራዊ ጥበቃ ፍላጎትን ባሟላ መልኩ ወደፊት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ለዚህ ድግሞ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገራት ልምድ መውሰድ ይገባል። አሁን ባለን የኢኮኖሚ ደረጃ እንደ ስካንዲኔቪያን ሀገሮች ወይም እንደ ብራዚል አይነት ማሕበራዊ ጥበቃ ይኑረን ማለት አንችልም። በአንድ ሌሊት እንደ ደቡብ አፍሪካ መሆንም ሊከብደን ይችላል። ነገር ግን ቢያንስ አሁን መጀመር ይቻላል።
በኢትዮጵያ የጤና መድህን ሽፋን ብዙዎችን እየጠቀመ ነው። ማሕበረሰቡ አነስተኛ መዋጮ እያደረገ የማሕበራዊ ጥበቃው አካል ሆኖ ድጋፍ እያገኘ በጤና ረገድ ያለበትን ችግር እየቀረፈ ነው። ይህ አበረታች ውጤት ቢሆንም የመድህን ሽፋኑ ተስፋፍቶ ሁሉም የመንግሥት ሰራተኞች እና የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያገኙበት ሁኔታ ገና አልተፈጠረም። በፖሊሲ ደረጃ በጥሩ ሁኔታ የተቀመጡ ነገር ግን በአፈጻጸም ረገድ ውስንነቶች አሉ።
ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ለምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ። በተጠቀሰው ቁጥር ደረጃ ያሉ ሰዎችን በየዓመቱ በመደገፍ መጓዝ ያስቸግራል። እንዲህ አይነቱን ችግር ለማስወገድ አማራጭ የሚሆነው ማሕበራዊ ጥበቃን ሥርዓታዊ መልክ እንዲይዝ በማድረግ ከትምህርት፣ ጤና እና ሥራና ክህሎት ፈጠራ ጋር በማያያዝ አካታች አድርጎ መሥራት ነው። መንግሥት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን አቅሙ በፈቀደ መጠን ለእነዚህ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ ነው። ነገር ግን ይህ እሳት የማጥፋ አካሄድ ነው። አካሄዱን ማቆም የሚቻለው አቅም በፈቀደ መጠን የተሟጠጠ ጥረት በማድረግ የማሕበራዊ ጥበቃ ሽፋንን በግሉ ዘርፍ፤ በመንግሥትም፤ በዜጋም ደረጃ በማድረስ ነው።
በእኛ ሀገር ትልቁ የመንግሥት ፈተና መደበኛ ያልሆነው ኢኮኖሚ ግዙፍ መሆኑ ነው። መንግሥት በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ዜጎች የማሕባራዊ ዋስትና ቁጠባ ስለማያደርጉ አይመለከተኝም የሚል አመለካከት ማዳበር አይችልም። ይህን መደበኛ ያልሆነውን ኢኮኖሚ ጭምር ግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሰጠው የፖሊሲ ጥቁምታ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች የማሕበራዊ ዋስትና አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ መሰረታዊ ምህዳር መፍጠር የሚል ነው። ለምሳሌ የነዳጅ ሽያጭ ሲደረግ በበጎ ፈቃድ ላይ በመመስረት ከእያንዳንዱ ሌትር ከገዢው እና ሻጩ አስርና ሃያ ሳንቲም እንዲሰበሰብ ተደርጎ ለማሕበራዊ ጥበቃ ሥራ እንዲውል ማድረግ ይቻላል።
ማሕበራዊ ጥበቃ በሆነ አካል ላይ ብቻ የሚጣል ኃላፊነት አይደለም። ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው በተፈጥሮ ተጋላጭ ነው። የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን፣ የእለት ደራሽ እርዳታ፣ ሥራ የማግኘትና የመፍጠር እድል የሚያገኙበት ማሕቀፍን የያዘ ፖሊሲ ነው። የማሕበረሰቡን የተጋላጭነት መጠን በመቀነስ የማሕበረሰቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል እሳት ከማጥፋት ባሻገር ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ቀድሞ የመከላከል ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል አንድምታ ያለው ነው። በሂደትም ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ማሕበራዊ ጥበቃ እስከመሆን ደረጃ ይጓዛል። ስርነቀል ማሕበራዊ ጥበቃ ማለት ችግርን በራሱ የሚቆም ማሕበረሰብ መፍጠር የሚል እይታ ያለው ነው። ይህ መንግሥት በማሕበራዊ ጥበቃ የተጣለበትን ማሕበራዊ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት የመወጣት ተግባር በደምብ እንዲያሻሽል በቀጣይ ብዙ ሥራዎች እንዳሉበት ያመላክታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን!
መልሰው (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ !
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም