ለአካባቢው ማህበረሰብ ስለ ግብርና ሥራ ማውራት ‹‹ለቀባሪው አረዱት›› እንደሚባለው አባባል ነው፡፡ ከግብርና ሥራ ጋር እንደሚተዋወቁ የሻከረው እጃቸው ምስክር ነው። በአካባቢያቸው ያለሙት አትክልት ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡ በአካባቢው ለማልማት አቅም የሌለው እንኳን ቢኖር ያለውን ቦታ አቅሙና ጉልበቱ ያላቸው እንዲያለሙበት ይፈቅዳል። ይህን አስደናቂ የከተማ ግብርና ሥራ የተመለከትነው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ውስጥ ነው፡፡
ወላጆች ለልጆች ያቆዩት መልካም ተሞክሮ ዛሬ በልጆቻቸው እግር ተተክቶ መሬቱ ለልማት በመዋል ለምግብ የሚውሉ አትክልቶች በስፋት ከመመረታቸው በተጨማሪ የመተዳደሪያ ገቢያቸውም ሆኗል፡፡ ለአካባቢ ውበትም ሆኗል። ማህበረሰቡ እያከናወነ ያለው የአትክልት ልማት በአገር ደረጃ ለተያዘው የከተማ ግብርናን የማበረታታት መርሃግብር ትልቅ እገዛ አድርጓል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በንቅናቄ እየተከናወነ ላለው የከተማ ግብርናም አካባቢው ሞዴል መሆኑም የበለጠ ትኩረት ስቧል፡፡ እኛም በስፋት አትክልት በሚለማበትና የዶሮ እርባታም በሚከናወንበት በዚህ ሥፍራ ተገኝተናል፡፡ ባየነው ልማትም የግብርና ሥራን ማነው ለአርሶ አደሩ ብቻ የሰጠው አስብሎናል፡፡ መሬቱና የመስራት ፍላጎቱ ካለ በከተማም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተጨባጭ አይተናል፡፡ ማህበረሰቡ የግብርና ሥራን የተገነዘበ መሆኑ ደግሞ ለልማቱ ውጤታማነት የበለጠ ዕድል ሰጥቷል፡፡
ከተማ ውስጥ ተወልዶና ተምሮ የግብርና ሥራ የሚመኝ ወጣት እምብዛም አያጋጥምም፡፡ ነገር ግን በተለያየ የሥራ መስክ ለመሰማራት ፍላጎት የሚያሳዩ የከተማ ልጆችን በግብርና ሥራ ላይ ማግኘት ዘመን መቀየሩን ነው የሚያሳየው።
ገቢ ካስገኘ ማንኛውም ሥራ በየትኛውም ቦታ የሚከበር መሆኑን በግብርና ሥራው ላይ ያገኘኋቸው ወጣቶች ማሳያ ናቸው፡፡ ወጣት ዘካሪያስ ቢረዳ ትዳር መስርቶ የልጆች አባት ቢሆንም በዕድሜው ወጣት ነው፡፡ በአካባቢው የሚያለማው አትክልት ዋና የገቢ ምንጩ ነው፡፡ ዛሬ አቅማቸው ደክሞ ከቤት የዋሉት ወላጆቹ ባላቸው ቦታ ላይ አትክልት አልምተው ተጠቃሚ ሲሆኑ እያየ ብቻ ሳይሆን እየሠራም በማደጉ በእነርሱ እግር ተተክቶ በግብርና ሥራው ሲሰማራ አልተቸገረም፡፡ የሥራን ባህል ያወረሱትን ወላጆቹንም ያመሰግናቸዋል፡፡
ወጣት ዘካሪያስ አትክልት የሚያለማው በመስመር ነው፡፡ አንድ አልሚ እስከ ስድስት መስመር ይኖረዋል፡፡ መሬቱ በካሬ እስከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ይሆናል፡፡ በዚህ የሚያለማው የአትክልት ዓይነቶች የተለያየ ዝርያ ያላቸው ቆስጣ፣ ጎመን፣ አበባ ጎመን፣ ሰላጣ፣ የሾርባ ቅጠል፣ ካሮት፣ ቃሪያ፣ ባሮ ሽንኩርት ነው፡፡ ልማቱ የሚከናወነው በባህላዊ መሣሪያዎች በጉልበት ነው፡፡ ለመስኖ የሚጠቀሙት ውሃም በአቅራቢያቸው ከሚገኝ ወራጅ ውሃ ነው፡፡
የአትክልት ልማቱ ምርታማ እንዲሆን ማዳበሪያና ምርጥዘር መጠቀም ያስፈልጋል። ወጣት ዘካሪያስም የመሬት ማዳበሪያ የሚጠቀመው ከከብት እዳሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በማዘጋጀት መሆኑን ይናገራል። የተፈጥሮ ማዳበሪያውን የሚያዘጋጁት በአካባቢው ከብት ካላቸው ሰዎች በግዥና አልፎ አልፎም ከአካባቢው በመሰብሰብ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መቀጠሉ አዋጭ ሆኖ አላገኙትም፡፡ ከአትክልት ልማቱ በተጨማሪ ከብትና ዶሮን በመጨመር ጥምር ግብርና ማከናወን ቢችሉ ለማዳበሪያ ግብአት የሚውለውን የከብት እዳሪ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ተመጋጋቢ የሆነ ሥራ በመስራት የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው በመተማመን ዕቅድ ነድፈው ለአራዳ ክፍለ ከተማ የግብርናውን ዘርፍ ለሚመራው ክፍል አሳውቀው ምላሽ እየጠበቁ ነው፡፡ እቅዳቸው ተቀባይነት ኖሮት የመስሪያ ቦታ ቢመቻችላቸውና ለእርባታ የሚሆን የእንስሳት ዝርያ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ቢችሉ ከራሳቸው ባለፈ የከተማ ግብርናን ዓላማ ሊያሳኩ እንደሚችሉ ያምናሉ። የክፍለ ከተማው ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸውም ወጣቱ ነግሮናል፡፡
የከተማ ግብርና ዘርፈ ብዙ ዓላማዎች አሉት፡፡ አሁን ላይ ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ አቅርቦቶች ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት በማርገብ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል አንዱ አማራጭ የከተማ ግብርናን በስፋት በማከናወን የሸማቹን የመግዛት አቅም ያማከለ ለማድረግ፣ እያንዳንዱ የከተማ ነዋሪም የዕለት ፍጆታውን በራሱ ለመሸፈን እንዲችል ለማበረታታት፣ ሥራ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም በዘርፉ ላይ በመሰማራት ገቢ በማመንጨት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ጥቂቶቹ ናቸው። ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› በሚባለው ብሂል ወጣት ዘካሪያስ እየተጠቀመ መሆኑን ነግሮናል፡፡ እርሱ እንዳለው በየቀኑ ምርቱን ለገበያ ያቀርባል፡፡ ይህም ምርት ከበቂ በላይ
መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ ግብይቱም የሚከናወነው ነጋዴዎች ከማሳው ላይ ምርቱን ለቅመው በማንሳት ሲሆን፣ ሽያጩም በግምት ነው የሚከናወነው፡፡ ከአንድ ማሳ በአንዴ ለቀማ ከ1500 እስከ 2500 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ ግለሰቦች እንደአቅማቸው መግዛት ከፈለጉም ይስተናገዳሉ፡፡ የመሸጫ ቦታ ተመቻችቶላቸው አልሚውና ሸማቹ በቀጥታ ተገናኝቶ ቢገበያይ ግን ተጠቃሚነታቸው የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ነው ወጣቱ የገለጸልን፡፡
የጋራዥና የተለያየ ስድስት ዓይነት የሙያ ባለቤት መሆኑንና ከነበረው ሙያ ሁሉ ግብርና እንደሳበው የገለጸልን አቶ ሰለሞን ገብሬ ይባላል፡፡ ከግብርና ሥራው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አካላዊና አዕምሮአዊ ጤናም ማግኘቱን ይናገራል፡፡ ያለማውን አትክልት በማየት ይደሰታል። ሲቆፍርና ሲኮተኩት አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናውን ይጠብቃል፡፡ በመሆኑም ሙሉ ጤናማ እንደሆነ ይሰማዋል። በግብርናው የሚያገኘው ገቢ ወይንም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሉት የተለያየ የሙያ ዘርፍ ከሚያገኘው የተሻለ ሆኖ ነው ያገኘው፡፡ አሁን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ነው ልማቱን እያከናወነ የሚገኘው፡፡
አቶ ሰለሞን በግብርናው ሥራ በቆየባቸው 17 ዓመታት የታዘበውን ከጥቂቶች በስተቀር የብዙዎች የሥራ ባህል ደካማ መሆኑን ነው፡፡ ጉልበት የሚጠይቅና የሚያቆሽሽ ሥራ የሚፈልግ ሰው አለመኖሩን የተረዳው አጋዥ ሠራተኞች ሲፈልግ ከሚያገኘው መልስ ነው፡፡ የግንዛቤ ችግር እንጂ የግብርና ሥራ እንደሚባለው አያቆሽሽም፡፡ ቁፋሮውም ሆነ ኩትኮታው፣ ችግኝ ተከላውም በውስን ወቅቶች ነው የሚከናወነው፡፡ እራስን ጠብቆ ለመሥራት አያግድም፡፡ ከጉዳቱ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ በሰው ኃይል እጥረት በዘር ያልተሸፈነ መሬት እንዳለውም ተናግሯል፡፡ በከተማ ግብርና ሥራ ላይ ረጅም አመት የቆየው አቶ ሰለሞን፣ የተለየ ለውጥ አላመጣም የሚል አስተያየት በአካባቢው አንዳንድ ነዋሪ ቢቀርብበትም አስተያየቱ ከግብርና ሥራው አላራቀውም፡፡ ለውጥ ላለማምጣቱ ምክንያቶቹ ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚው ማቅረብ ባለመቻሉና በመካከል በሚገቡ ደላሎች እንደሆነ ይናገራል፡፡
‹‹መሬት ቆፍሬ፣ ዘር ገዝቼ፣ ውሃ አጠጥቼና ኮትኩቼ ሦስት ወር ሙሉ ለፍቼ ያለማሁትን አትክልት በዋጋ ከነጋዴ እኩል ነው የምካፈለው›› ሲል ያማርራል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክረውን ነጋዴና ደላላ ማስወጣት የሚቻለው አልሚውና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኝበት መንገድ ሲመቻች መሆኑን ይናገራል፡፡ ክፍለከተማው ችግሩን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ለሁለት ሳምንት በፑሽኪን አደባባይ ባመቻቸው የመገበያያ ቦታ ለውጡን ማየት መቻሉንም ገልጿል፡፡ የተመቻቸው ቦታ በተለያየ ምክንያት በመከልከሉ ግብይቱ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ሌሎች የተሰጡት ቦታዎች ከሸማቹ ጋር ለመገናኘት ምቹ አይደሉም፡፡ እርሱ እንዳለው የቀጥታ ግንኙነቱ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ቢመቻች ግን ነጋዴ በ40 ብር የሚያቀርበውን አንድ እስር ጎመን በግማሽ በማቅረብ ሸማቹን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተናጠል ያነጋገርናቸው አልሚዎች የየራሳቸውን የልማት ሥራ የሚያከናውኑ ቢሆንም መሬቱ በአንድ አካባቢ በመሆኑ ብዙ ነገሮችን ተጋርተው ነው የሚሠሩት፡፡
የአትክልት ልማቱ ከሚከናወንበት ሥፍራ ሳንወጣ ተመጋጋቢ በሆነው በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማራውን የአቶ ኃይለገብርኤል ነሪ ሥራ ቃኝተናል፡፡ አምስት አመት ከሠራበት የአሽከርካሪነት ሥራ ወጥቶ ነው ፊቱን ወደ ዶሮ እርባታ ያዞረው፡፡ ለገበያ የሚበቃ ባይሆንም ለቤተሰብ የምግብ ፍጆታ የሚውል አትክልትም ባለው አነስተኛ ቦታ ላይ ያለማል፡፡ የዶሮ እርባታ ሥራ ክትትል የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ጊዜውን በአግባቡ ሥራ ላይ ያውላል፡፡ ፊቱን ወደ ግብርና ሥራ ማዞሩ አሽከርካሪ ሆኖ በሌሎች ላይ ይታዘባቸው ከነበሩ ወጣ ካሉ የሥነምግባር ችግሮችና እርሱም የመጥፎ ሥነምግባር ሰለባ ሳይሆን ቶሎ ለመመለስ ስላስቻለው የዶሮ እርባታውን ባለውለታው አድርጎ ይወስደዋል፡፡ በዶሮ እርባታው ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ጓደኞቹን በማየትና በልጅነቱም ቤተሰቡም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ዶሮ ሲያረባ እያየ በማድጉ የሥራ ዘርፉን ለመምረጥ አንዱ ምክንያት ሆኖታል። ይሄ አዋጭ የሥራ ዘርፍ እንደሆነውም አረጋግጧል፡፡ ጉልበቱንና ጊዜውን ለሥራ በማዋል ሀብት የሚያፈራበትንም ዕድሜ ለመጠቀም ጊዜው አሁን እንደሆነም ያምናል፡፡
የዶሮ እርባታውን ከቤተሰቡ ጋር በመሆን በአምስት መቶ ዶሮዎች ነው ሥራውን ዘንድሮ የጀመረው፡፡ በክፍለ ከተማው አማካኝነትም ሥልጠናዎችን ቀድሞ በማግኘቱ አልተቸገረም፡፡ በተለያየ ጊዜ ከአምስት መቶ እስከ ስምንት መቶ ዶሮዎችን በማስገባት ነው የእርባታ ሥራውን የሚሠራው፡፡ ግብይቱ የሚከናወነው ዶሮዎቹ እንቁላል መጣል እስከሚያቆሙ ድረስ እንቁላል ይሸጣል፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ እንቁላል መጣል ያቆሙ ዶሮዎችን ይሸጣሉ። ወደ ሥራው ለመግባት የሥራ ፈቃድ ማግኘት የነበረው ውጣ ውረድና ለዶሮ ቤት ለመሥራት የነበረው ወጪ ቶሎ ለውጤት የሚያበቃ ካለመሆኑ በስተቀር መስመር ከያዘ በኋላ ያለው ሂደት ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ለዶሮዎች የሚውለው የአንድ ኩንታል ዋጋ እስከ ሦስት ሺህ ብር የሚገዛ በመሆኑ ውድነቱ ተግዳሮት እንደሆነበት ይናገራል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ሥራውን ለመጀመር ወደ አራት መቶ ሺህ ብር ወጪ አውጥቷል፡፡ ወደፊት የሚያስገኝለትን ውጤት ተስፋ በማድረግ ወጪው አላሳሰበውም፡፡ ክፍለ ከተማው የብድር አገልግሎት የሚያገኝበትን ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት ያለማስያዥያ 75ሺ ብር ብድር ማግኘቱ ለሥራው ትልቅ ድጋፍ ሆኖለታል፡፡ ወደፊት የከብት እርባታንም ጨምሮ በመሥራት የግብርና ሥራውን የማስፋት ፍላጎት እንዳለው ገልጾልናል፡፡
የከተማ ግብርና ሥራ በከተማው የሚስተዋለውን የዋጋ መናር ማርገቡን የነገሩን ደግሞ የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ናቸው። የኑሮ ውድነቱን ከሚያርገበው አንዱ የከተማ ግብርና መሆኑ ስለታመነበት በንቅናቄ በስፋት በማጠናከር እየተሠራ ይገኛል። ሥራውም ሁለት ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ነው። አንዱ በከተማ ግብርና ሥራ ላይ የቆዩ ወይንም ነባር ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን፣ ግለሰቦችን፣ በአጠቃላይ በጋራና በተናጠል የሚሠሩትን የማጠናከርና የመደገፍ ሲሆን፣ ድጋፉም ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ግብአቶች በማሟላት ይገለጻል፡፡ አልሚዎቹ ከግብርና ባለሙያዎችና ከአመራሩ ጋር በቅርበት እንዲሠሩም እየተደረገ ይገኛል፡፡ በልማቱ ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ አቅርበው እየተጠቀሙ ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ግን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ አዳዲስ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴዎች በክፍለ ከተማው ወደ 25ሺ የሚሆነው ነዋሪ የቤተሰብ ፍጆታውን ማሟላት ባይችል እንኳን ቢያንስ 50 በመቶ እራሱን መደጎም እንዲችል በንቅናቄ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከታች እስከ ላይ ባለው እርከን የሚገኘው አመራር ቁልፍ አጀንዳው አድርጎ በመያዝ ኮሚቴ አዋቅሮ በእቅድ እየተመራ እየገመገመ ሥራው እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እስካሁን በተከናወነው ሥራም ከ12ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለቤተሰብ ፍጆታ የሚውሉ ልማቶች ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የጤና እና ሌሎችም ተቋማት ላይ የከተማ ግብርና ልማት እንዲሠራባቸው ጎን ለጎን ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ሌሎች አማራጮችን በመፈተሽም ሥራውን ለማስፋት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በልማቱ ሥራ አመራሩም አርአያ መሆን ስላለበት ሰፊ ግቢ ያላቸው በማልማት እንዲያሳዩም አቅጣጫ ተቀምጧል። ከአንድ ወር በኋላም ልማቱ ደርሶ ለአካባቢ ማህበረሰብ ጭምር ይሆናል የሚል እምነት የጣለበት ነው፡፡ በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብና ማርባት በተመሳሳይ ለማጠናከር ጥረቶች ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ውስጥ ያለውን ልማት በማድነቅ፣ በአካባቢው ወደ ዘጠኝ ሄክታር ላይ ከሚለማው የተለያየ አትክልት ኅብረተሰቡ እየጠቀመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014