ከለውጥ ማግስት በተለያዩ ኃይሎች መካከል መከፋፈል እና ግጭት እንደሚኖር የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎች ያመላክታሉ። የዓለም አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የለውጥ ኃይሎች የሕዝብን ድጋፍ እስካገኙ ድረስ ለውጥን ለማምጣት ብዙም ሲከብዳቸው አይታይም። ችግሩ ከለውጡ ማግስት ያለውን የለውጥ ሂደት ለውጡ ከተያዘለት ግብ እና አላማ አኳያ በትክክለኛው ጎዳና እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? የሚለው ላይ ነው። ይህን ሃሳብ ለማጠናከር ከበርካታ አገራት የለውጥ ታሪኮች መካከል የራሽያ እና አሜሪካን ታሪክ በወፍ በረር ማየቱ ተገቢ ነው።
አሜሪካውያን ነፃነታቸውን ለማግኘት ተዋድቀው ነፃነታቸውን ከተቀናጁ በኋላ ለአሜሪካ ነፃነት ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ኃይሎች ከነፃነት እና ከለውጥ በኋላ አገሪቱ ያገኘችውን ነፃነት፤ እንዲሁም የፖለቲካል ኢኮኖሚ አካሄድ ለውጥ ማስቀጠል ተስኗቸው ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ጦርነት ማካሄዳቸውን የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።
አሜሪካውያን የብሪታኒያን የቅኝ ግዛት ሴራ በመበጣጠስ ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ ነፃነታቸውን ማግኘት የቻሉ ቢሆንም፤ ከነፃታቸው ማግስት ግን የቅኝ ገዥዎችን ሴራ መበጣጠስ የቻሉት ኃይላት ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ተብለው ለሁለት ተከፍሉ። የመከፋፈላቸውም መነሻ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋነዎቹ ግን ሁለት ናቸው። አንደኛው ኢኮኖሚ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካ ነበር።
ኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ፣ የደቡቡ የአሜሪካ ክፍል ባርነት በአገረ አሜሪካ እንዲቀጥል ይፈልጉ ነበር። ደቡብ አሜሪካዎች ይህን እንዲሉ ያስቻለው ዋና ምክንያት የደቡብ አሜሪካ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተንጠለጠለ እና ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ መመስረቱ ከፍተኛ የባሪያ ጉልበት እንዲፈልጉ አድርጓቸው ነበር። በመሆኑም ባርነት በአገረ አሜሪካ መቀጠል አለበት ሲሉ ተደመጡ። በአሜሪካ የሰሜኑ ክፍል ደግሞ ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተው ስለነበር የሰው ኃይልን በማሽን መተካት ችለው ነበር። በመሆኑም ሰሜኖቹ ባርነት በአገረ አሜሪካ መኖር የለበትም ሲሉ የደቡቡን የአሜሪካ ኃይሎች መሞገታቸው ነው።
ሌላው ልዩነታቸው ፖለቲካ ነበር። ከዚህ አንጻር የደቡቡ የአሜሪካ ክፍል አሜሪካ በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል ኮንፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ይሻላታል የሚል ሲሆን፤ የሰሜኑ አሜሪካ ክፍል ደግሞ አሜሪካን ማሻገር የሚችለው ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶች ማዋሃድ ሲቻል እንጂ በኮንፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር አይደለም ሲሉ በጽኑ ሞገቱ። ይህም ልዩነታቸው አሜሪካኖችን እጅግ ለከፋ እና አውዳሚ ጦርነት ዳረጋቸው። በጦርነቱም በንግግር መፍታት ያልቻሏቸውን የለውጥ ጋሬጣዎች መንጥረው እና አስተካክለው አዲስ እና ኃያል የሆነችን ዩናይትድ ስቴስ ኦፍ አሜሪካ የተባለችን አገር መሠረቱ። አገራቸውንም አሁን ላለችበት የዓለም ቁጥር አንድ ልዕለ ኃያልነት ደረጃ አበቁ።
ሌላው ከለውጥ ማግስት ግጭቶች እንደሚከሰቱ ሁነኛ የዓለም ተሞክሮ የታየው በራሽያ ነው። በራሽያ የሮማኖቭ ሥርወ-መንግሥትን በመገርሰስ ራሽያን ለለውጥ ካበቁ ቡድኖች መካከል የራሽያ ሶሻል ዴሞክራሰቲክ ሌቨር ፓርቲ አንዱ ነበር። ይህ ፓርቲ ከለውጡ በኋላ ለውጡን በተፈለገው ልክ ማስቀጠል ተስኖት ቦልሼቪክ እና ሜንሼቪክ ተብሎ ለሁለት ተሰንጥቆ አረፈው። በዚህ ወቅት ቦልሼቪኮች ለለውጡ ምክንያት የሆኑ መነሻዎችን ዘንግተዋል፤ ለላባደሩ እና ለአርሶ አደሩ መወገን ሲገባቸው ለቡርዣው በመወገን ለውጡን ሊያደናቅፉት ነው ሲሉ ሜንሼቪኮችን ይከሱ ነበር። ሜንሼቪኮችም አርሶ አደሩን እና ወዛደሩን እንደ ለውጥ መዘወሪያ ኃይል መጠቀም ከአብዮቱ በፊት አንግበን የተነሳንለትን አላማ ለማሳካት የሚያስችል አይደለም በማለት ቦልሼቪኮችን ይከሱ ነበር። የኋላ ኋላ ቦልሼቪኮች ሜንሼቪኮችን የለውጡ ደንቃራ አድርገው ለሕዝብ አሳዩ። ሜንሼቪኮችም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አጡ። ቦልሼቪኮችም መሄድ ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ተጉዘው ራሽያን ለዚህ ክብር አበቁ።
እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር የተለያዩ አገራት ከለውጥ ማግስት ለውጥ ያመጡ ኃይሎቻቸው የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ ነው። ከለውጥ በኋላ ለሚከሰቱ የግጭት መንስኤዎች በአብዛኛው ጊዜ በሁለት ናቸው።አንደኛው፣ ትክክለኛውን የለውጡን አላማ ለማስቀጠል ከሚመጣ ፍላጎት ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ደግሞ የለውጡ አካላት የሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከለውጡ በኋላ እናገኘዋለን ብለው ያቀዱት ሁለንተናዊ ጥቅም በሆነ ምክንያት የሚያጡት መስሎ ሲሰማቸው የሚፈጠር ነው። ከላይ ከተጠቀሱ አገራት ተሞክሮ እንደተረዳነው ከለውጥ ማግስት በለውጥ አምጪዎች መካከል የሚፈጠረው አለመግባባት ከሁለቱ ምክንያቶች የመነጨ ነው።
በእኛም አገር በ1966 ዓ.ም፣ በ1983 ዓ.ም እና በ2010 ዓ.ም ለሦስት ጊዜያት አስተዳደራዊ ለውጥ ቢደረጉም ከላይ እንደተጠቀሱት አገራት ከለውጥ ማግስት የሚነሱ ጥያቄዎች መፍታት አቅቶን እስካሁን ድረስ እየተነታረክን እንገኛለን። ሆኖም የእኛ ችግር ከላይ በማሳያነት ካቀረብናቸው አገራት በእጅጉ ይለያል። ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱት አገራት ከለውጥ ማግስት ለጸብ ያመሯቸውን አጀንዳዎቸ የፈጠሯቸው ራሳቸው ሲሆኑ፤ በእኛ አገር ግን ከለውጥ ማግስት ለሚፈጠሩ የጸብ መነሻ የሆኑ አጀንዳዎችን የምንቀበለው ኢትዮጵያን ጠል ከሆኑ አገራት እና ቡድኖች በመሆኑ ነው።
ይህን ስል በአመክንዮ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት ላለመሆኑ በርካታ አመክንዮችን ማቅረብ ቢቻልም ለዛሬው ግን ሁለት ማሳያዎችን እነሆ ብያለሁ።
አንደኛ፣ በ1966 ዓ.ም የመጣው አብዮታዊ ለውጥ የእውነተኛ ለውጥ እና ኢትዮጵያን ሊቀይር የሚችል የነበረ ቢሆንም አወቅን እና ተማርን የሚሉ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሌት ከቀን ከሚታትሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል የኢትዮጵያን ጦር በግንባር እስከመፋለም የደረሱ እና የኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠል ህልውናዋን አደጋ ውስጥ የጨመሩበት ነበር። ሕወሓት እና መሰሎቹ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናቸው።
እነኝህ ኃይሎች ከለውጡ መንግሥት ጋር ያደረጉት ግብግብ የኢትዮጵያን የባህር በር ያሳጣ እና አገረ መንግሥቱንም አደጋ ውስጥ የጨመሩ ነበሩ። እዚህ ጋ የብርጋዴል ጄኔራል ተሾመ ተሰማን ሃሳብ ልዋስ፤ እንደሚታወቀው አንድ ቤት ሲሠራ በርም መስኮትም ይሠራለታል። ለመቃብር ቤት ግን በርም መስኮትም አያስፈልገውም። ባህር በር የሌለው አገርም መስኮት እና በር የሌለው ቤት ነው። ይህ ማለት መቃብር ውስጥ ያለች አገር ናት።
ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር ያስቀሯት የለውጥ ደንቃራዎች ወይም ጋሬጣዎች የውጭ ተላላኪዎች ሕወሓት እና መሰሎቹ ነበሩ። እነኝህ አካላት ለውጡን ሲያደናቅፉ እና የኢትዮጵያን አገረ መንግሥትነት ጥያቄ ውስጥ ሲጨምሩ አገር የማተራመስ አጀንዳውን የፈጠሩት በራሳቸው ሳይሆን ኢትዮጵያን ከሚጠሉ ምዕራባውያን አገራት ነበር። በዚህም በ1966 ዓ.ም የተፈጠረው አብዮት ወይም ለውጥ አብዮትነቱ ሳይታወቅ እስከ 2010 ዓ.ም አደረሰን።
ሁለተኛ፣ በ2010 ዓ.ም የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፣ ቀድሞ የተሠራበት እና በዚህ ወቅት ጎልተው እንዲወጡ የተደረገባቸው በተለያዩ ቦታዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በመስፋፋታቸው ኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት በአስቸጋሪ የለውጥ ጉዞ ውስጥ እንድትጓዝ ተፈረደባት። ለዚህም ዋናው ምክንያት በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ በገዥው መንግሥት ውስጥ የሚገኙ አካላት ኢትዮጵያን ከሚጠሉ አካላት አጀንዳ ወስደው ስለሚንቀሳቀሱ ነው። በዚህም በመዋቅሩ ውስጥም ሆነ ከመዋቅሩ ውጪ ባሉ ኃይሎች በመታገዝ ጭምር አገር የመገንጠል አጀንዳ፣ የሽግግር መንግሥት የመመስረት አጀንዳ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም የሚል አጀንዳ፣ ወዘተ. ከውጭ ኃይሎች እየተቀበሉ አገርን ለትርምስና ጦርነት በመዳረግ እረፍት የመንሳት፣ የማዋከብና ሕዝቡ ተረጋግቶ ሳያስብ ለውጡ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ለማድረግ ሲሠሩ ቆይተዋል፤ እየሠሩም ናቸው።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ የኢትዮጵያን እድገት እንደ ስጋት የሚመለከቱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አማካኝነት ነው። እነሱ ውጭ ሆነው እኛ የእነሱን ጦርነት ተረክበን ስንዋጋ፤ ከጉዞችን ስንስተጓጎል፤ እነሱ ይሳለቁብናል። ስለሆነም የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከተፈለገ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና ገዥው መንግሥት በሥሩ ያሉ ባንዳ ተላላኪዎችን ከመዋቅሩ ያስወጣ፣ በተፎካካሪ ፓርቲ ስም የጠላትን አጀንዳ አዝለው አገር ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም አደብ ይያዙ፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ሰከን ብሎ የሚሆነውን በማስተዋል ማጤን ይኖርበታል። ሰው ከራሱም ከጎረቤቱም ይማራልና፤ ሌላ ለውጥ ሳንጠብቅ በዚህኛው ልንጠቀም፣ ከለውጥ ማግስት ከሚፈጠሩ ችግሮችም አገራችንን ልንታደግ ይገባል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014