አዲስ አበባ ሀና ማርያም አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ማገዶ ሲፈልጉ ጫካ መውረድ፤ ገበያ መሄድ አያሻቸውም። ቤታቸው ድረስ፣ ከመንደራቸው የሚያቀርቡ ደንበኞች አሏቸው። ደንበኞቻቸው የቡና ገለባን ከሌሎች ገዝተው ለእነሱ በጥሩ ዋጋ የሚሸጡ ናቸው።
የእዚህ መንደር እናቶች ገለባውን ለማገዶ በፈለጉት ጊዜ ጆንያ ተሞልቶ፣ ማዳበሪያ ተጠቅጥቆ ይመጣላቸዋል። ለሚያመጡላቸው ባለገለባዎችም የዋጋውን ከፍለው፣ ለሌላ ቀን ቀጥረው ይሸኛሉ። የቡና ገለባው እንጀራን በእሳት ለሚጋገሩ ሴቶች ሁነኛ መፍትሄ ነው። ከጥቂት እንጨት ተዳምሮ፣ ብዙ ግልጋሎት እየሰጠ አመታትን አሻግሯል።
በሀና ማርያምና አካባቢው የቡና ገለባን ሽያጭ እንጀራቸው ያደረጉ በርክተዋል። ገለባውን ቡና ከሚፈለፍሉ ድርጅቶች ተረክበው ማገዶ ለሚያደርጉት ደንበኞች ያከፋፍላሉ። ደንበኞቻቸው የእነሱን ገለባ ወስደው በሚከፍሏቸው ገንዘብ ኑሯቸውን ይመራሉ።
የገለባው ጉዳይ…
ጌታቸው የተባለው ወጣት የቡና ገለባን ከአንድ ድርጅት እየገዛ ለሚፈልጉ ጠያቂዎች ያከፋፍላል። ጌታቸው እስከዛሬ ራሱን ለማስተዳደር ብዙ ሥራዎችን ሞክሯል። የቡና ገለባውን ማከፋፈል ከጀመረ ወዲህ ሥራው እንደሚያወጣው ገምቶ የራሱን ደንበኞች አፍርቷል። እየተዘዋወረ በሚሠራባቸው መንደሮች ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው።
ወጣቱ የቡና ገለባን ከሚወስድበት ድርጅት ጥሩ መቀራረብ ፈጥሯል። የእጁን ሸጦ ሲጨርስ ሌላ ጆንያ ይረከባል። የጆንያውን ሲያጠናቀቅ የተጠየቀውን ሊያመጣ ይሮጣል። ጌታቸው አብሮት ከሚሠራ ባልንጀራው ጋር ተሳስበው ያድራሉ። ነገን የተሻለ ለማድረግ፣ ሕይወትን በጥሩ ለመምራት በጋራ ይሠራሉ።
ለጓደኛሞቹ የቡና ገለባው እስከዛሬ ከሞከሩት ሥራ የተሻለ ነው። ውሎው ድካምና ልፋት እንዳለው ያውቃሉ። ያም ሆኖ ከሌላው ገቢ መልካም የሚባል ነው። እኩል ሠርተው በሚያገኙት ገቢ የድርሻቸውን ይወስዳሉ። ሁለቱም ዛሬን ብቻ አያስቡም። ሁለቱም ስለነገ ህልም አላቸው። አርቀው ያልማሉ። ከፍ ብለው ያስባሉ።
ሁለቱ ሳሪስ አካባቢ ከሚገኝ የግል ማከፋፈያ ገለባውን ሲረከቡ በክፉ የሚያይዋቸው ዓይኖች አልጠፉም። ሥራውን መተዳደሪያ ያደረጉ ጥቂቶች በእንጀራቸው የመጡ፣ በሕይወታቸው የገቡ ያህል ይቆጥሩታል። ከድርጅቱ እነሱ ብቻ መጠቀም የሚሹ አንዳንዶች ወጣቶቹን በርቀት እየቃኙ ጥርስ ይነክሱባቸዋል። እንጀራቸውን እንደነጠቁ፣ ሕይወታቸውን እንደተጋሩ ቆጥረውም ይገላመጣሉ።
ጌታቸውና ጓደኛው በሚኖሩበት አካባቢ የአንድ ሰው አስተያየት በተለየ ይረብሻቸው ይዟል። ሰጠኝ ልክ እንደነሱ ወጣትና በቡና ገለባ ሽያጭ የሚተዳደር ነው። እሱም በሥራው አመታትን ገፍቶ ደንበኞችን አፍርቷል። ገለባውን ሸጦ በሚያገኘው ገቢ ራሱን እየመራ ፍላጎቱን እየሞላ ነው። ገለባውን ከሚረከብበት ድርጅት ጓደኛሞቹ መገኘታቸውን ካወቀ ወዲህ ሰላም ተሰምቶት አያውቅም።
ሰጠኝ ባልንጀሮቹ የእሱን ደንበኞች፣ ደንበኛ ማድረጋቸውን ካወቀ በኋላ ቂም ይዞ ጥላቻ አፍርቷል። ሁለቱን በርቀት ካያቸው ደሙ ይፈላል። አጠገቡ ካሉ ሊጣላቸው ሊነቁራቸው ይፈልጋል። ሰጠኝ ሁሌም ልጆቹ ገለባውን ከድርጅቱ መረከባቸው ያስቀናዋል። ፍላጎቱ ይህ ብቻ አይደለም፤ ገዢዎችም ገለባውን ከእሱ እጅ ብቻ እንዲረከቡ ነው። ይህን ቢያደርግ ፣ የተሻለ ትርፍ ያገኛል። ገቢው ጨምሮ ሥራውን ያሰፋል።
አሁን ሰጠኝ ስሜቱ ከጥላቻ ተሻግሯል። ጓደኛሞቹን በግልጽ አግኝቶ መጣላት እየፈለገ ነው። እንጀራውን፣ መኖሪያውን እንደነጠቁት ተሰምቶታል። ይህ ስሜቱ ጫፍ በነካ ጊዜ ለድብድብ ይጋበዛል። ጓደኛሞቹ የሰጠኝ ሀሳብ ገብቷቸዋል። እሱ እንዳሰበው ገለባውን ከእጁ ተረክበው ለሌሎች ማስረከብ አይፈልጉም።
ሰጠኝ የጓደኛሞቹን ውሳኔ ካወቀ ወዲህ ማስፈራራትና መዛት ጀምሯል። ባገኛቸው ቁጥር ለድብድብ ይጋበዛል። አንዳንዴ የውስጡን ሀሳብ የሚናገረው በእርግጠኛነት ነው። እነሱን ገድሎ ሰላሳ ሺህ ብር ካሳ መክፈል እንደሚችል ሰው እየሰማው ጭምር ይናገራል።
ባልንጀሮቹ የቡና ገለባ ሥራቸውን አላቆሙም። ሰጠኝ ትጋታቸውን ባየ ጊዜ እልሁ ጨምሯል። ዛቻና ማስፈራራቱን፣ ልደባደብ፣ ልግደል ማለቱን ቀጥሏል።
ምክክር …
ሰጠኝ አብሮት ከሚያዘወትረው ጓደኛው ጋር ስለቡናው ገለባ እያወራ ይገባበዛል። የገለባው ነገር ከተነሳ የባልንጀራሞቹ ጉዳይ ሳይወራ አያልፍም። ዘወትር ስማቸውን እየጠራ የሚብከነከነው ሰጠኝ በእንጀራው እንደመጡበት የሚናገረው በተለየ ብሶት ሆኗል። ስሜቱን በወጉ የሚረዳው የቅርብ ጓደኛው በጉዳዩ እንዳይበሳጭ እየነገረ አብሮነቱን ያሳየዋል።
የሰጠኝ ጓደኛ በሰማው የገለባ ታሪክ ብስጭት ይዞታል። ጓደኛሞቹ ከፋብሪካ ብቻ ሳይሆን እርሱን አልፈው ከሌላ ሰው ላይም በተጨማሪነት እየገዙ መሸጣቸው እያናደደው ነው። ይህን ለማድረጋቸው የእጃቸውን እንዲያገኙ ጓደኛውን ማነሳሳት፣ ማደፋፈር ይዟል። ሰጠኝ ጓደኛው የሚለውን አምኖ ተቀብሏል። ሁለቱ ሰዎች ላደረጉት ድፍረትና ንቀት የእጃቸውን ሊያገኙ ይገባል።
ሰጠኝና ጓደኛው ብርጭቆ ይዘው በሚዝናኑበት ግሮሰሪ ሁሌም የሚያነሱትን ጉዳይ አይዘነጉም። በተለይ ጌታቸው የተባለው ወጣት ድርጊት ከልብ እያናደደ አልህ አስይዟቸዋል። የሰጠኝ ጓደኛ መፍትሄውን አመላክቶ መሆን የሚገባውን ጠቁሟል። ሰጠኝ እሱ ባለው ተስማምቶ ቀንና ጊዜ ለይቷል። ማድረግ ያለበትን፣ መሆን የሚገባውን አውቆ ራሱን አዘጋጅቷል።
ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም…
ምሽቱ ገፍቷል። ወቅቱን ጠብቆ መጣል የጀመረው የነሐሴ ዝናብ አሁንም አላባራም። የሀና ማርያም ሰፈርና አካባቢው ነዋሪዎች በጊዜ ወደ የቤታቸው ገብተዋል። እንዲህ ጨለማና ዝናብ በሚሆን ጊዜ ለደህንነታቸው የሚሰጉ እግረኞች ጥቂቶች አይደሉም። ዝናብ ሲመጣ ጨለማው ይበረታል። ይህኔ ጊዜና ቦታ መርጠው ፣ የሰውን ብቸኝነት ለሚሹ ዘራፊዎች አጋጣሚው ያመቻል።
የሁለቱ ጓደኛሞች ልብ ግን ከዚህ ዓይነቱ ስሜት ርቋል። እነሱ ጨለማና ዝናቡን የፈለጉት ለተለመደው ዓላማ አልሆነም። ሰጠኝና አብሮት ያለው ሰው ወዳሰቡት ሰፈር ሲቃረቡ ውስጣቸው ብዙ እያቀደ እጃቸው ላሰቡት ድርጊት እየተዘጋጀ ነው። ምሽት ሦስት ሰዓት ሆኗል። እግራቸው የቆመበት ስፍራ እነሱ የሚፈልጉት ቤት ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
ከአንድ ግቢ ደርሰው የሚሹትን ሰው በዓይናቸው ፈለጉት። የጨለማው ብርታት የሚፈልጉትን አላሳጣ ቸውም። የመጡበትን አግኝተዋል። ተፈላጊው ሰው ከቤቱ ተቀምጧል። አዩት፣ አላያቸውም። ከዓይናቸው ሳይርቅ ወደ ፊት ገሰገሱ።
ግቢውን አቋርጠው ወደ ክፍሉ አመሩ። ተፈላጊውን ፊት ለፊት ተቀምጦ አገኙት። ማንነታቸውን እንዳወቀ ከልቡ ደነገጠ። በዚህ ሰዓትና በራሱ መኖሪያ ምን ሊያደርጉ እንደመጡ ግራገባው። ጥያቄ እስኪያቀርብላቸው አልጠበቁም። ያሰቡትን ፈጽመው፤ የልባቸውን ከውነው ከቤቱ ሲወጡ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከሰላሳ ሆኖ ነበር።
ድንገቴው ጥሪ …
ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በድንገት የደረሰው የስልክ ጥሪ የዕለቱን የምሽት ተረኞች ጆሮ ያነቃው በፍጥነት ነበር። የስልክ ጥሪው መልዕክት የደረሰው ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01 ልዩ ስሙ ሀና ማርያም ከተባለ አካባቢ ነበር። ፖሊስ በስፍራው ሲደርሰ የተባለው ግቢና አካባቢው በሰዎች አጀብ ተሞልቶ ነበር።
የምርመራ ቡድኑ አባላት ቦታውን እያስለቀቁ ወደ ተባለው ቅጥር ግቢ አመሩ። ወዲያው ከፊት ለፊት ያለው ክፍል በር በግማሽ ገርበብ ብሎ ተመለከቱ። ጥቆማውና ዋና ጉዳዩ የሚመለከተው ቤት ከፊት ለፊት የሚታያቸው ክፍል መሆኑን አውቀዋል።
የምርመራ ቡድኑ አባላት በሩን በርግደው ወደ ውስጥ ዘለቁ። ከቤቱ ወለል ላይ በስለት ተወግቶ በደም የተነከረው ወጣት በሕይወት አለመኖሩን ለማወቅ አልተቸገሩም። ስፍራውን በጥንቃቄ ከበው ምርመራቸውን ቀጠሉ። በዕለቱ በስፍራው የተገኙ ባለሙያዎች አስፈላጊውን አጠናቀው አስከሬኑን አነሱ።
ፖሊሶቹ የሟችን ማንነትና የተገደለበትን ምክንያት ለማወቅ መረጃዎችን ማሰበሳብ የጀመሩት ወዲያውኑ ነበር። ሟቹ በአካባቢው የቡና ገለባን እየሸጠ የሚተዳደር ወጣት ጌታቸው ስለመሆኑ ታውቋል። ከእሱ ጋር የሚሠራው ባልንጀራው አብሮት ባለመሆኑ የሆነውን ማስረዳት አልቻለም። ያም ሆኖ ለጉዳዩ ተጠርጣሪ የሚያደርገውን ግለሰብ ለማወቅ ጊዜ አልፈጀም።
ፖሊስ የጌታቸውን ባልንጀራና ሌሎች እማኞችን በማስረጃነት መዝግቦ ድርጊቱን ይፈጽመዋል የተባለውን ሰጠኝ ታደሰን ማፈላለግ ያዘ። ሰጠኝ ወጣቱ ከተገደለበት ምሽት አንስቶ በአካባቢው አልታየም። አብዛኛው ጠቋሚ ተጠርጣሪው ሰጠኝ እንደሚሆን ገምቷል። ፖሊስ እሱን ጨምሮ አብሮት ነበር የተባለውን ግለሰብ ማፈላለጉን ቀጥሏል።
በምርመራው ወቅት ለፖሊስ የደረሰው አዲስ መረጃ ተጠርጣሪውን በጥብቅ እንዲፈለግ አድርጓል። የአንደኛው ተጠርጣሪ የቅርብ ጓደኛ ነው የተባለና ከዚህ ቀደም በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተፈርዶበት ዓመታትን በማረሚያ የቆየ ስለመሆኑ ተሰምቷል። ድርጊቱን ከሰጠኝ ጋር ሊፈጽሙት እንደሚችሉ የጠረጠሩ ጠቋሚዎች በየአቅጣጫው በፍለጋ፣ በክትትል ማሰስ ይዘዋል።
ዋና ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የወንጀል ምርመራውን ሊያሳዩ የሚችሉ መረጃዎችን ማጣራት ይዟል። ወንጀሉ በማንና ለምን ተፈጸመ? በድርጊቱስ ማን ተጠቃሚ ይሆናል የሚሉትን ወሳኝ ሀሳቦች በተግባር ለመፈተሽ ጥረቱ ተጠናከረ።
የምርመራ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ይገኙባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች በህግ ጥላ ስር ለማዋል ክትትሉን አጠናክሯል። ወንጀሉ በተፈጸመ በአራተኛው ቀን ለፖሊስ አንድ ጥቆማ ደረሰ። ዋናው ተጣርጣሪ ሰጠኝ ታደሰ በአንድ ጫካ ተደብቆ አምልጦ ለመውጣት መሞከሩ ተሰማ።
ፖሊስና የአካባቢው ነዋሪ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አድርጎ በህግ ጥላ ስር አዋለው። ፖሊስ ሰጠኝን ለጥያቄ ሲያቀርብ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸም ያለመፈጸሙን እንዲያረጋግጥለት ጠየቀው። ተጠያቂው ለምላሹ አላንገራገረም። ድርጊቱን በትክክል ለመፈጸሙ በሰጠው ቃል አረጋገጠ።
ፖሊስ ጥያቄውን አላበቃም። ለግድያው መፈጸም ምክንያትና ሰበቡን እንዲያስረዳ ዕድል ሰጠው። ሰጠኝ የጌታቸውን ሕይወት ለማጥፋት መነሻ የሆነው የቡና ገለባው ንግድና ያስከተለበት የቅናት መንፈስ ስለመሆኑ አስረዳ። ተጠርጣሪው በዚህ አላበቃም፤ ድርጊቱን የፈጸመው ሲሳይ ከተባለ ጓደኛው ጋር ስለመሆኑ አረጋገጠ።
የፖሊስ ፍለጋ…
ፖሊስ የተጠርጣሪውን ሙሉ ቃል መዝግቦ እንደጨረሰ ሁለተኛውን ተጠርጣሪና ለወንጀሉ ተባባሪ ነው የተባለውን ግለሰብ ማሰስ ጀመረ። ሰጠኝ ድርጊቱ ከተፈጸመ ምሽት በኋላ ግለሰቡን እንዳላየው አረጋግጧል። ከአካባቢው በተገኘ መረጃ መሠረት ሲሳይ ይገኝበታል ከተባለው የሀና ማርያም አካባቢ ፍለጋው ተጠናከረ። በተፈላጊው ስምና አድራሻ የተገኘ ሰው አልነበረም።
ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ምርመራና አሰሳ ሲሳይ የሚባል ግለሰብ ያለመኖሩን አወቀ። ሰጠኝ የሕግን አቅጣጫ ለማሳት የፈጠረው ስያሜ መሆኑ ተረጋገጠ። የተፈላጊው ትክክለኛ ስም ሲሳይ ሳይሆን አበበ መርኔ ነው። ይህ ሲታወቅ የፖሊስ ዓይኖችና ጆሮዎች ነቁ። በተፈላጊው አበበ ላይ የሚደረገው ፍለጋ በተለየ ጥንቃቄ ተጠናከረ። ከፖሊስ እጆች የገቡት የአበበ ፎቶግራፎች ፍለጋውን ለማፋጠን አገዙ።
ጥቂት ቆይቶ ፖሊስ ግለሰቡ ከዚህ ቀድሞ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሶ አስራ ስድስት ዓመት እንደተፈረደበትና ስምንት ዓመት ታስሮ በምህረት እንደተፈታ ደረሰበት። የእሱም መተዳደሪያ የቡና ገለባ ሽያጭ እንደነበር ታወቀ።
የሁለተኛውን ተጠርጣሪ ዱካ ለማግኘት ፍለጋውን የጀመረው ፖሊስ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ቀድሞ ታስሮበት ነበር ወደተባለው የደብረብርሀን ከተማ አቀና። በአካባቢው የተገኙት የምርመራ ቡድኑ አባላት ከስፍራው ደርሰው መረጃዎችን ሰበሰቡ። ግለሰቡ ወንጀሉን በፈጸመ ሰሞን በሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር እጅ ከፍንጅ ተይዞ በጊዜ ቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ታወቀ።
የምርመራ ቡድኑ አባላት በእጃቸው ያለውን ፎቶግራፍ ከፍርድቤት ማዘዣ ጋር ይዘው ደብረብርሃን ማረሚያ ቤት ደረሱ። እንደተባለው ሆኖ ተፈላጊው አበበ ከማረሚያ ቤቱ በእስር ላይ ሆኖ ተገኘ። ፖሊስ ህጋዊ አካሄዱን ተከትሎ ተጠርጣሪውን በእጁ ለማስገባት ጥረት አደረገ። የወንጀሉ ክብደትና ያለው መረጃ ሚዛን ደፍቶ ቡድኑ ተፈላጊውን ተጠርጣሪ ወደ አዲስአበባ ይዞ እንዲሄድ ተፈቀደለት።
አበበ በምርመራው ሂደት ቃሉን ሲሰጥ ከሟች ጌታቸው ጋር ከዓይን እይታ በቀር ትውውቅ እንዳልነበረውና ወንጀሉን የፈጸመው ለጓደኛው ሲል እንደሆነ ተናገረ። ፖሊስ የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ቃል በበቂ ማስረጃዎች ሰንዶ በፎረንሲክና በቴክኒክ ማስረጃዎች በማጠናከር አዘጋጀ። ተጠርጣሪዎቹ ክስ ይመሰረትባቸው ዘንድም መዝገቡን ወደ ዓቃቢ ሕግ አስተላለፈ።
ውሳኔ…
በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ክስ ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት አራዳ ምድብ ችሎት በተከሳሾቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷል። ሁለቱም ተከሳሾች ስለ ወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበሉም።
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ሁለቱ ባልንጀሮች በቂም በቀል ተነሳስተው ላጠፉት የሰው ሕይወት እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሃያ ዓመት ጽኑ እስራት ‹‹ይቀጡልኝ›› ሲል ውሳኔውን በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014