በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስጋት እየሆኑ ከመጡ አስር የጤና ችግሮች ውስጥ አንዱ የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ነው። የፀረ ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች እየተለመዱ መምጣታቸውን ተከትሎም በዚህ ፈርጅ የሚመረቱ መድሃኒቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። መድሃኒቶቹ አምራቾችን ለኪሳራ ስለሚዳርጉ ወደፊት ከነጭራሹ የማይመረቱበት እድል እንዳለም ይነገራል።
በቅርብ ጊዜ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ700ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ለህለፈተ ሕይወት ይዳርጋሉ። ከነዚህም ውስጥ በደቡብ ምእራብ እስያና ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። እ.ኤ.አ በ2050 ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያም የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ቀስ በቀስ አሳሳቢ የጤና ችግር እየሆነ መጥቷል።
በጤና ሚኒስቴር የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ውስጥ የአንቲ ማይክሮባያል ሬዚስታንስ ፕሪቬንሽንና ኮንቴ ይንመንት አስተባባሪ አቶ ይድነቃቸው ደገፋው እንደሚያብራሩት መድሃኒቶች ጀርሞችን ለመግደልና የጀርሞችን እድገት ለመግታት ዓላማ ይፈበርካሉ። ይሁንና ለነዚህ ሁለት ዓላማዎች መድሃኒቶች ሲፈበረኩ ጀርሞች መድሃኒቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ይላመዷቸዋል። ከዚህ አንፃር መድሃኒቶች ጀርሞችን ለመግደል ወይም የጀርሞችን ርቢ ለመግደል ሲሳናቸው የፀረ-ተህዋሲያን የመድ ሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ይከሰታል።
የመድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን በተለይ ጀርሞች የተለያዩ ነገሮችን በመጠቀም ለአብነት ኬሚካሎችን በማመንጨት የመድሃኒቱ ኬሚካል እንዳይሰራ በማድረግ፣ ቅርፃቸውን በመለዋወጥና መድሃኒቱ ወደ ሰውነት ሴሎች ውስጥ ሲገባ ተመልሶ እንዲወጣ በማድረግና ሌሎችንም ሥራዎች በመስራት መድሃኒቶች እንዳይሰሩ ያደርጋሉ። በዚህ ጊዜ የፀረ- ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች ይለመዳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ መድሃኒቶችን በአግባቡ ለታለመው ዓላማ አለመጠቀም ማለትም መድሃ ኒቶችን በሐኪም ከታዘዘው መጠን አሳንሶ መውሰድ፣ ከፍ አድርጎ መውሰድ፣ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መውሰድ የፀረ- ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድን ያስከትላል።
በተመሳሳይ እንስሳቶችን ለማደለብ ሲባል የተለያዩ መድሃኒቶች ይሰጣሉ። እነዚህ መድሃኒቶችን የተላመዱ ጀርሞች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚመጡበት እድል አለ። የመድሃኒት ፋብሪካዎች መድሃኒት በሚያስ ወግዱበት ጊዜ እነዚህ ጀርሞች ወደ እንስሳና ወደ ሰው የመተላለፍ እድል ይኖራቸዋል።
እንደ አቶ ይድነቃቸው ገለፃ የፀረ- ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ትልቅ አሳሳቢ የጤና ችግር ነው። እ.ኤ.አ በ2022 በቅርቡ የወጡ መረጃዎችም የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ከኤች.አይቪ/ኤድስና ከወባ በሽታዎች በልጦ ትልቁ የሞት ምንጭ እንደሆነ አመላክተዋል። እ.ኤ.አ በ2019 በዓመት ወደ 4 ነጥብ 92 ሚሊዮን የሚጠጉ የዓለም ሰዎች ከፀረ- ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያ ዘም በዓለማችን በደቂቃ አንድ ሰው እንደሚሞት ተረጋግጧል።
ምንም እንኳን አልፎ አልፎ የጥራት ችግር ቢኖርባቸውም በሀገር አቀፍ ደረጃም የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድን በተመለከተ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የተለያዩ ጥናቶች ይደረጋሉ። የነዚህ ጥናት ውጤቶችም ችግሩ ቀስበቀስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ብዙ መሰራት እንዳለበት ያመላክታሉ። በርካታ ሴክተሮችም በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ይጠቁማል።
አሳሳቢ እየሆነና ቀስበቀስ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ያለውን የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግርን ለመቅረፍ እንደሀገር የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱና ትልቁ ሀገሪቷ የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግርን ለመከላከል ያዘጋጀችው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ነው። ስትራቴጂክ እቅዱም እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ምን መስራት እንዳለባቸው አስቀምጧል።
ለእቅዱ ተግባራዊነትም የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴርና የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሥራ ገብተዋል። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግርን ለመቅርፍ ለህብረተሰቡ፣ ለጤና ባለሙያዎችና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
ለህክምና ባለሙያዎች፣ ለፋርማሲስቶችና ለነርሶችም በፀረ-ተዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ዙሪያ በየጊዜው ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም በጤና ተቋማት ስልጠናውን የሚሰጥ ቡድን በማቋቋም በሰላሳ ሆስፒታሎች ላይ ሥራ ተጀምሯል። ይህ ቡድን በጤና ተቋሙ ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች ስልጠናዎችን ይሰጣል። ለህብረተሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ይሰ ጣል። አግባብነት ያለው የመድሃኒት አጠቃ ቀምና አስተዛዘዝ ላይም ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨ በጫዎችን ለህብረተሰቡ ይሰጣል።
ዋናውና ትልቁ ሥራ ግን ከሚመለከታቸው ሶስቱ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በየሩብ ዓመቱ በጤና ሚኒስቴር በኩል በሚዘጋጅ መድረክ እየተገመገመ “ምን መሰራት አለበት?” በሚል ትላልቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ሆኖም ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ብዙ መስራት ይጠይቃል። ከመድሃኒት ሽያጭና አጠቃ ቀም ጋር ያለውን የቁጥጥር ሥራም ማጠንከር ያስ ፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014