የዛሬው የዘመን እንግዳችን ምስራቅ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ አውራጃ ጊዳ አያና ሲርበቡልቱም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው የተወለዱት። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ጊዳ አያና ፤ ገሊላ ፣ ሻምፖ በተባሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል።
ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ ግን በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የሶስት ቀን የእግር መንገድ በምታስኬደው ሻምቡ ከተማ ለመሄድ ተገደዱ። ይሁንና ወላጅ እናታቸው የሚቋጥሩላቸውን እህል ጭነው እየተመላለሱ ቂጣ እየጋገሩ በብዙ መከራ ውስጥ መዝለቅ ከበዳቸው። በመሆኑም ትምህርታቸውን አቋርጠው አዲስ አበባ ለሥራ መጡ። እንዳሰቡት ግን ሥራ ማግኘት ባለመቻላቸው ወታደር ቤት ተመልምለው ተቀጠሩ። የውትድርና ስልጠናውን ባጠናቀቁ ማግስት ወደ ኤርትራ ተመድበው ለሁለት ዓመታት በጦር ሜዳ አሳለፉ። ይሁንና በሻቢያ ወታደሮች ተማርከው ሳህል በርሃ ውስጥ በእስር ለአምስት ዓመታት ቆዩ።
ለትምህርት ልዩ ፍቅር የነበራቸው እኚሁ እንግዳችን በወህኒ ቤትም ሆነ ከእስር ከተፈቱ በኋላ እንደእርሳቸው በምርኮ የሚኖሩ አግኝተዋል። በዚህ ብቻ አላበቁም፤ ከ15 ያላነሱና በትግርኛ የተፃፉ የመማሪያ መጽሐፍትን ወደ አማርኛ በመተርጎም ታሪካዊ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያውያን ከቀለም ትምህርት እስከ ፖለቲካ ድረስ በማስተማር ንቃተ ህሊናቸውን የማሳደግ ሥራ በራሣቸው ተነሣሽነት ሰርተዋል። ለሁለት ዓመታትም በምርኮ በሄዱባት አገር አካውንቲግ ሰልጥነው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማምጣታቸው ይጠቀሳል።
በምርኮ በቆዩባቸው 18 ዓመታት ከኤርትራውያን ጋር በፍቅርና በሰላም የኖሩት እኚሁ ሰው አንዲት ኤርትራዊ ወታደር አግብተው አራት ልጆችን አፍርተዋል። ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ እናት አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሚወዱትን ትምህርታቸውን በመቀጠል ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ማግኘት ችለዋል።
እንግዳችን ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሬዲዮ ፋና ኦሮምኛ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ አዘጋጅ ሆነው ከመስራት ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት እየተዘዋወሩ አገልግለዋል። በተለይም ሬዲዮ ፋና በነበሩበት ወቅት አጫጭር ድራማዎችን በመፃፍ ከፍተኛ እውቅና ማግኘት ችለውም ነበር። አሁን ደግሞ በገምሹ በየነ ህንፃ ተቋራጭ ድርጅት ውስጥ የሰውኃይል አስተዳደር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በቅርቡ በኤርትራ በርሃ በምርኮ ያሳለፉትን ውጣ ውረድና በአጠቃላይ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት የሚዳስስ #አንቱ በእናት$የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። በዚህ መጽሐፍና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ማሞ አፈታ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንዲህ አሰናድተናል።
አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሚማሩበት ወቅት የተለየ ገጠመኝ እንደነበሮት ሰምተናል። እስቲ ስለዚህ ገጠመኝ ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
አቶ ማሞ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለን እኔና ጓደኛዬ በወቅቱ በትምህርታቸው ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዱ ስለነበርን በአንድ ዓመት አምስተኛንና ስድስተኛ ክፍልን ለመማር ጥያቄ አቅርበን ነበር። ሆኖም ይህ ‹‹ደብል ፕሮሞሽን›› የተባለው ስርዓት በዚያ ትምህርት ቤት ስለማይሰጥ ጥያቄያችን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። በመሆኑ ሌላ ሊሙ በተባለ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ገሊላ በተሰኘ ትምህርት ቤት ለመማር አመለከትን። ይሁንና የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እኔ ከነበርኩበት ትምህርት ቤት ጋር ክስ ላይ ስለነበሩ አናስገባም ብለው ብዙ አጉላሉን። እኛ ግን ተስፋ ሳንቆርጥ የግል መኖሪያ ቤታቸው ድረስ እየተመላለስን ጭቅጨቃችንን ቀጠልን።
ከብዙ መመላለስ በኋላ ግን አንድ ቀን በአጋጣሚ ከተማ መሃል ላይ አንድ ባላባት የሆኑ አጎቴ መጥተው ተገናኘን። የሚገርመው ቆመን ከእሳቸው ጋር እያወራን የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በአጠገባችን አለፉ። በዛ ጊዜ ወደ እርሳቸው እየጠቆምኩኝ ያደረጉኝን ሁሉ ለባላባቱ ዘመዴ ወቀሳ አቀረብኩኝ። እርሳቸውም ደግሞ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ይፈሩና ይከበሩ ስለነበር የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ከእርሳቸው ጋር ሲያዩን ተደናገጡ። እርሳቸውም ጠርተውት እኔንም ሆነ ጓደኛዬን እንዲመዘገቡን ትዕዛዝ ሰጡልንና ከሳምንታት መንከራተት በኋላ መመዝገብ ቻልን። ነገር ግን ያን ቀን ባይመዘግቡን ኖሮ እኔና ያ ጓደኛዬ እቅዳችን ወደ አባይ ተሻግረን ጎጃም ልንጠፋ ነበር። ምክንያቱም ከመጀመሪያው ትምህርት ቤት መልቀቂያ አስገብተን ደብዳቤ ተሰጥቶን ስለመጣን መመለስ አንችልም ነበር። ሌላው የጓደኞቻችን መሳቂያ እንሆናለን የሚል ስጋት ስለነበር ወደማናውቀው አገር ለመጥፋት አስበን ነበር። ግን ተፈቀደለንና እንዳሰብነው በአንድ ዓመት ውስጥ አምስተኛና ስደስተኛ ክፍል ማለፍ ቻልን።
ይሁንና በአቅራቢያችን ሰባተኛ ክፍል ባለመኖሩ ሶስት ቀን በእግር በሚፈጀው የሆረጉድሩ አውራጃ ዋና ከተማ በሆነው ሻምቡ ድረስ ሄዶ መማር ግድ ሆነብን። የምንማረው ከቤተሰብ ርቀን ቤት ተከራይተን ቂጣ እየጋገርን ነበር ። እህል የሚጫነው ከወላጆቻችን ነው ። የእኔ ደግሞ ወላጆች ተለያየተው ስለነበር እኔ ከእናቴ ጋር ሆንኩኝ። አባቴ ሌላ ሚስት አግብቷል። ስለዚህ እናቴ ለእኔ ቀለብ እየጫነች ለማስተማር በጣም ተቸገረች። የምታስተምረኝ ብዙ ጊዜ ሰው እየለመነች፤ እምቢ ሲሏት እያለቀሰች ነበር ። ለእኔ ይህንን ለመቀበል በጣም ከባድ ሆነብኝ። እናቴን ለመርዳት ስል ስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ ሁሉንም ዝግጅት ካጠናቀቅኩኝ በኋላ ሁለት ወር ሲቀረኝ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ፖሊስነት ለመቀጠር ወደ ነቀምቴ ተያይዘን ጠፋን።
ስንደርስ ምዝገባው ከአንድ ቀን በፊት መጠናቀቁን ሰማን። በዚህም ምክንያት ዳግመኛ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ነውር ሆኖ ተሰማን። ጓደኛዬ ተስፋ ቆርጦ ወደ አገሩ ለመመለስና ቡና ለመትከል ወሰነ። ለጓደኛዬ እኔ ግን ወደ ገጠር ተመልሼ ከእኔ ኋላ ላሉ ልጆች ተስፋ እንዲቆርጡ ምክንያት አልሆንም ብዬ እንደማልመለስ ነገርኩት። እናም አንገር ጉትን በተባለ የሆላንዶች እርሻ ልማት ወዛደር ሆኜ ተቀጠርኩኝ። እስከ ሰኔ ድረስ በቁፈራ ሥራ ቆየሁ። ሰኔ ላይ የፈተና ወቅት ሲደርስ ማልቀስ ጀመርኩኝ። የሚገርምሽ እዛ የሚቀጠረው ባለትዳር ብቻ ነበር፤ እኔም የተቀጠርኩት ቡቱቱ ለብሼ ባለትዳር ነኝ ብዬ ነበር። አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ሳለቅስ የሚያሰራን ካቦ አየኝና ምን ሆኜ እንደሆነ ጠየቀኝ። አንድ ባልደረባዬ ተማሪ መሆኔና የሚኒስትሪ መውሰጃ ጊዜ ስለደረሰ እንደማለቅስ ነገረው። ዋናው ሥራ አስኪያጅ አስፈቅዶልኝ ተፈተንኩ።
የሚገርመው ያንን ፈተና ለመፈተን በጣም የሚያስፈራውን እና ዘወትር በማዕበል የሚናወጠውን አንገር የተባለውን ወንዝ በዋና ለማቋረጥ ተገድጄ ነበር። ሁለት ጊዜ ለሞት አፋፍ ደርሼ የነበረ ቢሆንም፤ ከሌላው እኩል ቁጭ ብዬ ለመፈተን የበቃሁት ትምህርቴን ለመቀጠል ከፍተኛ ቁጭትና እልህ ስለነበረኝ በፅናት ከማዕበሉ ጋር ተፋልሜ ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በዚያው ሰሞን ወባ በሽታ ይዞኝ ሁለት ቀን ተኝቼ ነበር ሄጄ የተፈተንኩት። ግን በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበርኩኝ በዚያ ውጣ ውረድ ውስጥ ባልፍም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ተሸጋገርኩ።
አዲስ ዘመን፡- እንደዚያ ዋጋ የከፈሉለት ትምህርትዎን አቋርጠው ደግሞ ወደ ውትድርና ገብተውም ነበር። ወደ ውትድርና የገቡበት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ ማሞ፡- እንዳልኩሽ በነበረብኝ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ዘጠነኛ ክፍል ከገባሁኝ በኋላ መቀጠል የበለጠ ከባድ እየሆነብኝ መጣ። በተለይም እናቴን እያሰቃየሁ መኖር አልፈለኩም ነበር። እየሰራሁኝ ለመማር ስል የተላከልኝን እህል ሽጬ ወደ አዲስ አበባ ኮበለልኩኝ። አንድ የአክስቴ ልጅ ጋር ባርፍም እርሱም ተማሪ ስለነበር ያለሥራ እዛ መቆየት ከባድ ሆነብኝ። የገጠሩ ባህል ገና ያለቀቀኝ በመሆኑ እንዳሰብኩት ቶሎ ሥራ ለማግኘትና ለመማር አልቻልኩም።
በመጨረሻ ከዘመዴ ጋር ተማክረን ለውትድርና ለመመልመልና ለመቀጠር ወሰንኩኝ። የሚገርመው ልክ እኔ እንደተመዘገብኩኝ ምልመላው ተጠናቀቀ። ደብረብርሃን ላይ ስድስት ወር ከሰለጠንኩኝ በኋላ አስመራ ተመድቤ ስለነበር አንድ ሌሊት ብቻ አዲስ አበባ አድረን በአውሮፕላን በቀጥታ ወደ አስመራ ሄድኩኝ። ሁለት ዓመት ካገለገልኩኝ በኋላ በ1969 ዓ.ም አፋቤት የሚባለው ካምፕ ሲደመሰስ ከ165 ሰዎች ጋር ተማረኩኝ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለ18 ዓመታት ኑሮዬ ከሻቢያዎች ጋር ሆነ።
ለአምስት ዓመታት እስር ቤት ቆይቻለሁ። ቀሪውን ጊዜ ያሳለፍኩት እንደማንኛውም ሰው ከጠመንጃ አፈሙዝ ጥበቃ ውጭ ነው። በእስር ቤት ቆይታችንም ቢሆን የተለያዩ ሥራዎችን እንሰራ ነበር። ከጉልበት ሥራ በተጨማሪ እርስ በእርስ የቀለም ትምህርት እንዲሁም የፖለቲካ ትምህርት እንማማር ነበር። በዚህ ምክንያት እስር ቤቱ ለእኛ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሆነልን እንደ ኮሌጅ ነበር። በኢትዮጵያ መንግሥት ወንበዴና መቀነት በጣሽ የሚባለውን የሻቢያን ታጋይ ቡድን ለመግደል ሄደን የጠበቀን መስተንግዶ የሚገርም ነበር። እኛ አዕምሮ ላይ የተቀረፀው ከአረቦች ጋር ያበረ እና ወንበዴ ቡድን ነው የሚለው አስተሳሰብ ነበር ። እኛ እንዳውም ስንሰለጥን ጀምሮ እንፎክር የነበረው ‹‹ምንአለ ደርጉ ምን አለ፤ አገሬን ለአረብ አልሰጥም አለ፤ ኤርትራን ለአረብ አልሰጥም አለ›› እያልን ነበር። የደርግ ስርዓት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ ‹‹የኤርትራ ወንበዴዎች›› የሚል ስያሜ ነበር የሰጣቸው። እንደአንድ ትልቅና በዲሲፕሊን የሚመራ ድርጅት ተደርጎ አይቆጠርም ነበር።
ያገኘነው ግን በተቃራኒው ሆኖ ነው። እኛ ልንገድላቸው ሄደን በእጃቸው ላይ ስንወድቅ ሊገድሉን ሲችሉ፤ አላደረጉትም። የወንድማቸውን ሬሳ አስቀምጠው እኛን ‹‹እንኳን ፈጣሪ አተረፋችሁ›› አሉን። እኛም በሕይወት ያቆዩናል የሚል እምነት አልነበረንም። እንደውም ለተወሰነ ጊዜ እንጠራጠራቸው ነበር። እነሱ ግን ከጭቁን ኢትዮጵያውያን ጋር ምንም አይነት የጠላትነት ስሜት እንደሌላቸው ደጋግመው ይነግሩን ነበር። ነፃነታቸውን ብቻ የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ይነግሩን ነበር። ያንን ሁሉ ዓመት ያቆዩንቃላቸውን አክብረው ነው። ከ10 ሺዎች በላይ ኢትዮጵያውያን ምርኮኞችን ያስተናገዱት በዚህ መልክ ነው። በጊዜ ሂደት ምርኮኛው እየባዛ ሄዶ የሳህል በርሃ የአማርኛ ተናጋሪዎች መንደር ወደ መሆን ሄዶ ነበር።
የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ምርኮኛ የለኝም ብሎ ክዶን ነበር። ስለዚህ የእኛ እጣፈንታ የወደቀው በፈጣሪና በኤርትራ ታጋዮች እጅ ነበር። ቤተሰቦቻችን ሳይቀር በጦር ሜዳ እንደሞትን ተረድተው እርማቸውን አውጥተው ነበር። እኛ ግን በዚያ በርሃ የኖርነው የህዝባችን ናፍቆት እያቃጠለን ነበር። በዚያ ላይ እነሱም ትግል ላይ ስለነበሩ ለእኛ በቂ ምግብ ማቅረብ አይችሉም ነበር። የምንበላው የጫካ ጎመን ነበር ። ስለዚህ ከረሃቡ ባሻገር ወባ፤ ታይፎይድና መሰል በሽታዎች በተደጋጋሚ እንጠቃ ነበር። ብዙ መከራና ውጣ ውረድ አሳልፈናል። እንዲያም ሆኖ በሕይወት ቆይተን ዛሬ እንደታሪክ ለማውራት በመብቃታችን ፈጣሪዬን ላመሰግን እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ምርከኞችን የቀለምና የፖለቲካ ትምህርት ወደ ማሰልጠን ገብተውም እንደነበር ይታወቃል፤ እስቲ ይህ አጋጣሚ እንዴት እንደተፈጠረ ያስታውሱን?
አቶ ማሞ፡- እንዳልኩሽ እነሱ ነፃነታቸውን ከመፈለግ ውጭ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የጠላትነት ስሜት እንደሌላቸው በተግባር አሳይተውናል። በጣም የሚገርመው ‹‹ዳግመኛ እንኳን ተማርከን ብንሄድ ይዘን እናስተምራችኋለን እንጂ አንገላችሁም›› ይሉን ነበር። እንዳሉትም ተመሳሳይ እጣ የገጠማቸውን ሰዎች በፍቅር ተቀብለው አኑረዋቸዋል። እዛም ሆነው ‹‹ኤርትራ መገንጠል የለባትም!›› ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ነበሩ። ይህንን በማለቱ ጥቃት የሚደርስበት የለም። ከአምስት ዓመት እስር በኋላ መጀመሪያ ላይ የተማረክነው ሰዎች በነፃ ተለቀቅን። ይህም ማለት ያልታጠቀ፤ በጠመንጃ አፈሙዝ የማይጠበቅ ማለት ነው። እንቅስቃሴያችን በዲሲሊን ስር ያለ ቢሆንም ዝም ብሎ መሄድ አይቻልም።
ለእስረኞች ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን የፖለቲካ ትምህርት አስተምር ነበር። በነገራችን ላይ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ መማር አለብን ብዬ ጠፍጣፋ ድንጋይ ከወንዝ አምጥቼ፤ ባትሪ ድንጋይ ከታጋዮች ለምኜ ፊደላትን በመፃፍ ያልተማሩ ምርኮኛ ወገኖቼን በጋዛ ፍቃዴ አስተምር ነበር። እነሱም የሚፅፉበት ወረቀት ስላልነበር ሰፋፊ ቅጠል በጥሰን እንደ ደብተር፤ አፈርን በጥብጠን ደግሞ እንደብዕር እንጠቀም ነበር። የቤት ሥራቸውን የሚሰሩት ቅጠል ላይ ነበር። ብዙዎቹ ግን ይነቅፉኝና ያሾፉብኝ ነበር። እኔ በዚህ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ እንዳውም በዚህ መልኩ የተጀመረው ትምህርት እየሰፋ ሄደ። ከፊደል አልፈው ቃላት ማንበብ ሲጀመር ግን ችግር ሆነብን። በኋላ ላይ ድርጅቱ የውጭ ሚዲያዎች ጋብዞ በቪዲዮ እንዲቀረፅ በማድረጉ በዓለምአቀፍ ቀይመስቀል መታወቅ ጀመርን።
በዚህ ምክንያት የዱቄት ወተት መጣልን። ወተቱን ከጠጣን በኋላ የታሸገበትን ወረቀት ሰፍተን እንደደብተር መጠቀም ጀመርን። ከዚያ ደግሞ ከቃላት አልፈው አጫጭር ታሪኮችንና መግለጫዎችን እየፃፍኩኝ እንዲያነቡ አደርግ ነበር። ያቺን አጭር መግለጫ ደጋግመው ከማፃፌ የተነሳ ያልደረሰችው ሰዎች ጥቂት ነበሩ። ተማሪው ቁጥሩ እየበዛ በሄደ ቁጥር ግን መጽሐፍ ማግኘት የግድ ሆነብን። ስለሆነም ከትግርኛ መጽሐፍ ጋር መታገል ያዝኩኝ።
የትግርኛ መጽሐፍ ከታጋዮቹ እየተዋስኩኝ እየተተረጎምኩኝ ማቅረብ ጀመርኩኝ። ከዚህ በመነሳት በርካታ መማሪያ መጽሐፍቶችን ተርጉሜ ለህትመት አብቅቻለሁኝ። የድርጅቱ ታዋቂነት በዓለም ላይ እየጎላ ሲመጣ የምርከኞችም ታዋቂነት በዚያው ልክ ጨመረ። በዚህ ምክንያት በዓለም ቀይ መስቀል ማህበር አማካኝነት አልባሳትና ደብተር በገፍ መጣልን። ከዚያ በኋላ የወተት ወረቀቱን መጠቀም አቆመ። በፊት ሲያሾፉብኝ የነበሩ ሰዎች ራሳቸው መማር ጀመሩ።
ፊደል ከመቁጠር የጀመሩ ሰዎች ደግሞ ሰባተኛ ክፍል ደረሱ። ከዚያም አልፈው ግጥምና ድረሰትም የሚፅፉ ነበሩ። እኔ ብቻዬን እንኳን 15 መጽሐፍትን ተርጉሜያለሁ። በሌላ በኩል በምርኮ የሄድን ሁሉ ስንተሳሰብ የነበረው እንደአንድ ሆነን ነው። ይህም እዚህ አሁን እርስ በርስ የምንገዳደልበትን የጎሳ ልዩነት አጥፍተን ትንሿን ኢትዮጵያ መስርተን ነበር ማለት ይቻላል። አንዳንዴ እንደውም የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት መማረክ ይኖርብናል እንዴ? እያልኩኝ ራሴን እጠይቃለሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- ምንአልባት ሁላችሁም በችግር ውስጥ በባዕድ መካከል መሆናችሁ ይሆን አንድ ያደረጋችሁ?
አቶ ማሞ፡– በዚህ ምክንያት አይመስለኝም። ሲጀመር እንደተናገርኩት ሻቢያዎቹ ምንም እንኳን የአመለካከት ልዩነት ቢኖረንም ያደረሱብን ጉዳትና ጫና አልነበረም። በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንም ኢትዮጵያኖች በፍቅርና በመከባበር ለመኖር ወሰነን ይህንንም በመተግበራችን ይመስለኛል ህብረታችንን ያጠናከረው። በነገራችን ላይ አሁንም ድረስ በርሃ አብረን ከነበሩት ጓደኞቼ ያለን ግንኙነት ጥብቅ ነው። ለእኔ እንደውም ከዘመድ በላይ የሚረዱን የበርሃ ጓዶቼ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ደግሞም ውስጣችን የገባው ንቃተ-ህሊና ለየት ያለ ስለሆነ እንደሆነም እረዳለሁ።
ኤርትራውያን እዛ በርሃ ላይ ለየት ያለ ትውልድ ፈጥረዋል። ከህዝብ አስተሳሰብ ወጣ ያለ ግንኙነት፤ እርስ በርስ መተሳሰብ፤ መከባበር፤ የሴቶች እኩልነት የተረጋገጠበት ነበር። በዲሲፕሊን የታነፀ ሰራዊት ነበረ፤ በዚያ ላይ በሂስና ግለሂስ የምንወቃቀስበት መድረክ መኖሩ ራሳችንን ለማረቅና በትክክለኛው መንገድ እንድንቀረፅ አድርጎናል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በምርኮ በተሰደዱበት አገር ደግሞ ትዳር መስርተው ልጆችም አፍርተዋል፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
አቶ ማሞ፡- ነፃ ከተለቀቅኩኝ በኋላ በሥራ አጋጣሚ ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር የመተዋወቅ እድል ገጥሞኝ ነበር። እሷ ታጋይ ነበረች፤ እኔ ደግሞ ምርኮኛ። ፍቅር ስንጀምር ግን እኔ ከእስር ተፈትቼ ነፃ ሰው ነበርኩኝ። የምኖረው ከብዙሃኑ ጋር ተዋህደን ነበር። ብዙዎች የማደርገውን ጥረት ያደንቃሉ፤ እሷ ግን ከሌላው በተለየ ታበረታታኝ ነበር። ቀስ በቀስ ግን ቅርበታችን ወደ ፍቅር ተለወጠ። እኔ በወቅቱ አፍር ነበር፤ ምክንያቱም አንደኛ እኔ በእነሱ እጅ የወደኩኝ ምርኮኛ መሆኔና እሷ ታጣቂ ሆና ሳለ ግንኙነታችን በዚህ መልክ መቀየሩ ያስፈራኝ ነበር። ሁለተኛ ህብረተሰቡ ራሱ አይቀበለንም የሚል ስጋት ነበረኝ።
የታጋዮቹ ንቃተ-ህሊና ከፍተኛ ነው። ብዙዎቹ ታጋዮች እሷን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጠላት አይደለንም የሚለው አመለካከት ይዘው ነበር። አንዳንድ ጠማማ አስተሳሰብ የነበራቸውም ነበሩ። ሊያስፈራሯት የሚሞክሩ፤ በጥላቻ የሚያዩን ነበሩ። እንዴት ጠላት ከነበረ ጋር ትወግኚያለሽ? ብለው የሚሞግቷት ነበሩ። እሷ ግን ይህንን ሁሉ ዛቻና ማስፈራሪያ ከምንም አልቆጠረችውም። ‹‹እኔ ያፈቀርኩት የሰውን ልጅ ነው ፤ ድርጅቴ የህንን አስተሳሰብ ቀይሮታል፤ ግንኙነታችንን እስከተቀበለው ድረስ ማንም ሊያግደኝ አይችልም›› አለች። ምክንያቱም በወቅቱ የሴቶች መብት ሻቢያ ውስጥ የተከበረ ነው። ስለዚህ መብቷን ተጠቅማ ግንኙነታችንን ቀጠለን። ግን ደግሞ ግንኙነታችን የቀጠለውበዲሲፕሊኑ መሰረት በማመልከቻ ለድርጅቱ ፈቃድ ጠይቀን ነው ።
ከሁለት ዓመት የእጮኝነት ጊዜ በኋላ የፖለቲካ ድርጅቱ ራሱ ሞቅ ያለ ሠርግ ደግሶ 36 ጥንዶች ጋር በአንድ ቀን ዳረን። ከእዚያ ሁሉ ውስጥ ግን ኢትዮጵያዊው እኔ ብቻ ነበርኩኝ ። በሰርጋችን ላይ ደግሞ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጀምሮ ፤ በርካታ ምርኮኞችና ተፈናቃዮች በሙሉ ታድመውበታል። በሠርጉ ላይ የታደሙት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በህዝባዊ ሃርነት ኤርትራ ታሪክ ውስጥ በዚህ ያህል መጠን ሰዎች የተጋቡበት ትልቅ ሰርግ መሆኑና ከሁሉ በላይ ሰርጉን ታሪካዊ የሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ምርኮኛ ኤርትራዊ ታጋይ መጋባታቸው መሆኑንና ድርጅታቸው በዚህ ታሪክ እንደሚኮራ ተናግረዋል።
አንድ ሊገድል የመጣ ወታደር ማርኮ፤ አስተምሮ፤ ንቃተ ህሊናውን አሳድጎ፤ አመለካከቱን ቀይሮ ከወገናችን ጋር መቀላቀሉ ድርጅቱ የሚኮራበት መሆኑንም ገልፀዋል። ህዝቡም የዳረን ቆሞ አጨብጭቦ ነበር። የተጋባነው ናቅፋ በምትባል ታሪካዊ ቦታ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ በርሃ ላይ ሁለት ልጆች አፈርተን ነበር፤ ደርግ ወድቆ አስመራ ከገባን በኋላ ደግሞ አንዴት ሴት ልጅ ወልደን፤ ቤተሰቤን ይዤ ወደ አገሬ ከገባሁኝ በኋላም ተጨማሪ ሴት ልጅ ወለደን።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶና የባለቤትዎ ታሪክ ለሁለቱ ህዝቦች አንድነት ማሳያ ነው ማለት አንችልም?
አቶ ማሞ፡– እንዳልሽው በጦርነት ታሪክ ውስጥ በፍቅር የተጣመርን ከጥቂቶቹ አንዱ ብንሆንም፤ ብዙዎች ከዚያም በፊትም ሆነ በኋላ ተጋብተው ተዋልደዋል። ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት የበለጠ እንዳጠናከረው አምናለሁ። በነገራችን ላይ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጥላቻ እንደሌላቸው በደንብ ያውቃሉ። አሁን በደንብ ያልተነገረው የሚመስለኝ በኢትዮጵያ በኩል ነው። እነሱ ለነፃነታቸው የታገሉበት ትክክለኛ ምክንያት በእኛ በኩል ይታወቃል ብዬ አላስብም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በደንብ ያልተነገረ የሚመስለኝ ስለኢትዮጵያ ሰራዊት ጀግንነት ነው። በወቅቱ ሰራዊቱ አቅም ስላልነበረው የተሸነፈ እንደሆነ የሚያስቡ ብዙዎቹ ናቸው። እውነታው ግን ይህ አልነበረም። ሰራዊቱ ከየትኛውም ኃይል የላቀ አቅምና ብቃት እንዲሁም ወኔ የነበረው ነው። ኤርትራውያን ራሳቸው ይመሰክሩለታል። ወታደራዊ ሳይንስን አኝከው የበሉ መኮንኖች የነበሩት ሰራዊት ነው። የተሸነፉበት ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳለው እሙን ነው።
ከዚያ ባሻገር ኤርትራውያን በንጉሱ ጊዜ ነፃ ሆነው የኖሩበት ታሪክ ተገልብጦ ለአረቦች አሳልፎ ለመስጠት ተደርጎ ይወራ የነበረውም ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነበር። ኤርትራ የአፍሪካ አገራት በአውሮፓውያን ሲቃረጡ አገር ሆና ተመስርታለች። አሁን ይህንን ታሪክ የኢትዮጵያ ህዝብ በብዛት አያውቅም። ከዚያ በኋላ ደግሞ በ1945 ዓ.ም ከእናት አገሯ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቀለች። ይህንን የነፃነታቸውን ታሪክ መቀበል ብዙዎቻችን አንፈልግም። እኔ ለአገሬ አንድነት ብታገልም እዛ በኖርኩበት ጊዜ የኤርትራውያን ስነልቦና በደንብ ተረድቻለሁ። እንዳልኩት ለእኛ ምንም አይነት ጥላቻ የላቸውም፤ ግን ደግሞ ነፃነታቸውን እንድናከብርላቸውም ይፈልጋሉ። ስለዚህ እኛ ባይዋጥልንም፤ ሁለት አገራት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ የሚያቀራርባቸው የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር ቢኖራቸውም ጎረቤት መሆናቸው እሙን ነው።
ግንኙነታችንን ማጠናከር የምንችለው ሉዓላዊነታቸውን አክብረን በሰላምና በፍቅር ስንኖር ነው። እንደጎረቤት አገራት የንግድ ልውጥ ማድረግ፤ ማዳበር ያለብን የባህር ወደቦችን በጋራ የመጠቀም ልምድ ነው። ምክንያቱም ከየትኛውም ባህር በላይ ቀይባህር ለእኛ ይቀርበናል። በመሆኑም በሁለቱ አገራት መካከል የተዘራውን ጥላቻ እንዴት ማስወገድ እንደምንችል መወያየት አለብን። በተለይም የሁለቱም አገራት ምሁራን ተቀራርበው መወያየት አለባቸው። በነገራችን ላይ በቅርቡ ለንባብ ያበቃሁት ‹‹አንቱ በእናት›› የተባለው መጽሐፍ ሙሉ ታሪኩ የሚያጠነጥነው በእኔ የሕይወት ታሪክ ላይ ቢሆንም ስለሁለቱ ህዝቦች ጠንካራ ግንኙነት የሚዳስስ ነው። ይህ መጽሐፍ አሁንም የሁለቱ አገራትን ህዝቦች ይበልጥ እንዲቀራረቡ ያግዛል ብዬ አምናሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገርዎ የተመለሱበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ከተመለሱ በኋላ ደግሞ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ጦርነት ማምራቱ የፈጠረበትን ስሜት ያስረዱን?
አቶ ማሞ፡- በመሰረቱ እኔ ከአገሬ ርቄ የኖርኩት ህዝቤንና አገሬን ጠልቼ አልነበረም፣ ተገድጄ እንጂ! በሌላ በኩል ለእናቴ አንድ ልጅ እንደመሆኔ ለእናቴ መኖር ነበረብኝ። ወደ አገሬ የተመለስኩት ህዝቡም ደግሞ በጣም ናፍቆኝ ስለነበር ነው ። ከምንም በላይ ደግሞ 18 ዓመት ሙሉ ‹‹ልጄ ሞቷል›› ብላ ስታለቅስ የኖረችውን እናቴን በእድሜ እየገፋችና እየደከመች በመምጣቷ መደገፍና መንከባከብ ስላለብኝ ነው የመጣሁት። እኔ በሕይወት ስለመኖሬ እናቴም ሆነች ሌላው የቤተሰብ አካል አያውቅም ነበር። እዚህ ስመጣም አዲስ አበባን በቅጡ ስለማላውቅ ወደ ወለጋ የሄድኩት አንድ ሌሊት አድሬ ነው ።
መኪና ውስጥ ሆኜ እጅግ በጣም የምወዳት እናቴ ሞታ ብትቆየኝ ምን አደርጋለሁ የሚል ጥያቄና ስጋት ተፈጥሮብኝ ነበር። እዛ ከደረስኩኝ በኋላ ደግሞ ቤታችን ጠፋኝ። ምክንያቱም በከተሞች መስፋፋት ዳር የነበረው መሃል ሆኗል። ቤታችን ፊት የነበረው ፖሊስ ጣቢያ ፈርሶ መናሃሪያ ሆኗል። እንግዳ መሆኔን የተረዳች አንዲት ልጅ ጠይቄ ቤቱን ካሳየችኝ በኋላ ግን ዘው ብዬ ድንገት ብገባ እናቴ በድንጋጤ ትሞትብኛለች ብዬ ሰጋሁ። ብዙዎቹ ጓዶቼ እንደእኔ ቆይተው ሲመለሱ በድንጋጤ የሞቱባቸው መኖራቸውን ስለሰማሁ ወደ ቤት የገባሁት በጥንቃቄ ሌላ ሰው መስዬ ነው። እናቴ ስታየኝም አላወቀችኝም፤ እኔም የልጇ ጓደኛ መሆኔን እንጂ ልጇ መሆኔን አልነገርኳትም። ምክንያቱም የእኔ ዋና አላማ በሕይወት መኖሯን ማወቅና ስትረጋጋ ማንነቴን መንገር ብቻ ነው። ጓደኛው ነኝ ብዬ ነግሪያት እንኳን በጣም አለቀሰች። በኋላ ከሰዎች ጠይቄ እንደተረዳሁት በሄደችበት ሁሉ ስሜ ሲጠራ ስታለቅስ ነው የኖረችው። ደግሞም እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቹ ሞተዋል ተብለው ተስካራቸው ተበልቷል።
የኋለኛው ጦርነት ለእኔ እጅግ አሳዛኝ ነበር። ምክንያቱም እዛም እዚህም ለኖረ ፤ ለተዋለደ ሰው ህመሙ ከባድ ነው። ያንን ሁሉ ዓመታት በጦርነት መቆየታችን አልበቃ ብሉ እንደገና አዲሱ ትውልድ እንዲያልቅ መደረጉ ያሳዝናል። እውነቴን ነው በዚህ ደረጃ ደም መቃባታችን አሁንም ድረስ የሚፈጥርብኝ ትልቅ ቁስል ነው። ምክንያቱም ልዩነቶች ቢኖሩም በሰላም መፍታት የሚቻልበት እድል ነበር። ይህንን ደግሞ ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞ እንደሚቻል አይተናል። በዚህ ረገድ ዶክተር ዐቢይ በሁለቱ አገራት መካከል እርቅና ሰላም እንዲወርድ ላደረጉት ጥረት ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በፊትም ይቻል ነበር።
በተለይም የኤርትራውያንን ስነልቦና ስለማውቅ ለእርቅ በራቸውን ማንኳኳት ከባድ አልነበረም። ለፍቅር ልባቸውን የከፈቱ መሪ መጡና የዘመናት ቁጭታችንን ፈቱልን። ተነፋፍቆ የኖረን ማህበረሰብ እምባ ጠረጉ። ኤርትራውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ መንገድ የተቀበሏቸው ለዚህ ነው ። ያ ፍቅር እኛ ለዓመታት ያየነው እንጂ አዲሳችን አይደለም። ግን ደግሞ የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ እንደአንድ ህዝብ መኖራቸው ለእኔ ዳግም እንደመወለድ እቆጥረዋለሁ። አሁንም ይህንን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ጎሳን፤ ቋንቋንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች መበራከታቸው ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ? መፍትሄውስ?
አቶ ማሞ፡- አስቀድሜ እንዳልኩት አንድነት ለመፍጠር ፍቅር ያስፈልጋል። ፍቅር ደግሞ ከንቃተ ህሊና ጋር ይሄዳል። አንዱ መሰረታዊ ችግር ብዬ የማምነው የማህበረሰቡን ንቃተ-ህሊና ማሳደግ ያለመቻሉ ነው። ያወቅን እየመሰለን መድረኮችን እየዘለልን ሄድን እንጂ ብዙ ያላወቅነው ነገር አለ። ዓለም አሁን ወደ አንድ መንደር በመጣበት ጊዜ እኛ በሰበብ በአስባቡ እርስበርስ እየተገዳደልን በመሆናችን በእውነት ከልብ ያሳዝናል። ከግድያ ምንም አይገኝም። ከግድያ ምንም የማይገኝ መሆኑን፤ ታግሶ ማለፍንና ሆደ ሰፊ መሆኑን ከኤርትራውያን መማር እንችላለን። እንዳልኩሽ እንደእኔ አይነቱን ገዳዮቻቸውን በፍቅር ተቀብለው ማኖር የሚችሉ ሰዎች መሆናቸውን በሕይወት ያለሁ ምስክራቸው ነኝ። እኛ ደግሞ ከእነሱ በላይ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች በመኖራቸው እርስ በርስ መከባበርና መፈቃቀድ አለብን። ስለዚህ ለግጭት መነሳትም ሆነ መባባስ ተጠያቂ የማደርገው ምሁራኑን ነው።
ለምሳሌ አንድ ገበሬ አማራና ገበሬ ኦሮሞ ፊት ለፊት አስቀምጠው እረሱ ብትያቸው አብረው ሰርተው በጋራ ለመብላት አያናቸውን አያሹም። አይገዳደሉም። ምክንያቱም ቁርሾውና ጥላቸው ያለው በምሁራኑ መካከል እንጂ ተራው ህዝብ ጋር ባለመሆኑ ነው። የቅራኔውን እርሻ የሚያርሱት ምሁራኑ ናቸው። ምሁራኑ አውቀናል የሚሉት እንደየመሰላቸው እየፃፉና እንደመሰላቸው እየተናገሩ ህዝቡን ያቃርኑታል። እዚህ አገር ውስጥ ምሁራኑ እየፈጠሩ ያሉት ችግር ሊተኮርበት ይገባል። ያልተማረው ህዝብ እየተመራ ያለው በእነዚህ ጨለምተኛ አስተሳሰብ ባላቸው ምሁራን ነው። ወጣቱም ቢሆን የሚከተለው እነሱን ነው። እነሱ የተናገሯት ትንሽ ሃሳብ ብዙ ነገር ታቀጣጥላለች። ስለዚህ እዚህች አገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ እነዚህ ምሁራን ከጥፋት ጎዳናቸው ሊመለሱ ይገባል።
የምናድገው ህብረት ስንፈጥርና አንድነታችንን ስናስጠብቅ ነው ። ተከፋፍለን የተለያዩ አገሮችን ብንፈጥር ማደግ አንችልም። ንግድ እንኳን የተሳለጠ የሚሆነው በጋራ ስንኖር ነው። ለምሳሌ ወለጋ የሚኖር አንድ ገበሬ ምርቱን የፈለገውን ያህል ቢያበዛ በሰላም ጊምቢ ማድረስ ካልቻለ ምርቱ ይባክንበታል እንጂ ተጠቃሚ አይሆንም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ለደረሰው ጥፋት ሁሉ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ቆመው ይቅርታ መጠየቅ ያለባቸው ምሁራኑ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ደፋሮች መሆን አለባቸው። በንፁህ ልቦና ካሰብንበት የምንመኘው ሰላምና ልማት እናመጣዋለን።
ልባችን ካሰፋነው የማይመጣ አንድነትና ፍቅር አይኖርም። ፍቅር ቋንቋ የለውም፤ ጎሳ የለውም። ስለዚህ ሁሉም ሰው ልቡን ክፍት አድርጎ ወንድማማችነትን ሲያስብ ሁልም ነገር ሩቅ አይሆንም። የእዚህች አገር ሰላም እርግጥ ነው፤ ውይይት ይፈልጋል። ከልብ የመነጨ መቀራረብ ይፈልጋል፤ በብስለት መመካከርን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ከራስ ጋር መታረቅና ውስጥን ማዳመጥ ይጠይቃል። ምክንያቱም ከራሴ ጋር ካልታረቅኩኝ ከጎረቤት ጋር መታረቅ አልችልም። መጀመሪያ ውስጤ የሚንተገተገውን ቅራኔና ጥላቻ ልቤ ውስጥ መግደል አለብኝ። ይህንን ማድረግ ሲቻል ዘላቂ ሰላምና ልማት ማምጣት ይቻላል። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በያለበት ከራሱ ጋር መታረቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ማሞ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014