የብሂሉ ዳራ፤
ሰውዬው ሹም ነበሩ አሉ። ስማቸው ማን ነበር? ጊዜውስ መቼ ነው? አድራሻቸውና የሥልጣን እርከናቸውስ? ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች ሕዝባዊው የሥነ ቃል ምንጫችን መልስ ስለሌለው ታሪኩን የምናስታውሰው ከአፍ አፍ እያቀባበሉ በነበር ያስተላለፉልንን ተራኪዎቻችንን በማመን ብቻ ይሆናል።
ታሪኩን እንደተፈጸመ ለሚያምኑ ልበ ቅኖች “እሰየው” ብለን እናመሰግናቸዋለን። “ምንጭ የሌለው አፈ ታሪክ ነው” በማለት ሙግት ለሚገጥሙትም መልሳችን “ሰውን ሰው ያሰኘው ዴሞክራሲ ነው” የሚለውን ሕግ ተጋፍተን ስለማንጋፋቸው መብታቸውን እናከብርላቸዋለን። ለማንኛውም ታሪኩን ወደመተረክ እንዝለቅ።
እኒህ ለሰማይ ለምድር የከበዱ የታሪካችን ገጸ ባሕርይ ሹም በአንድ ወቅት በግዛታቸው ውስጥ ርሃብና ችጋር ገብቶ ሕዝባቸውና ቤተሰባቸው ጭንቅ ላይ ወድቆ ነበር አሉ። ይህን መሰሉ ያልተዘጋጁበት የተፈጥሮ “በላ”(መከራ) ግራ ያጋባቸው እኒያ ጎምቱ ወንበረተኛ ቢቸግራቸውና መላው ቢጠፋቸው ለሥልጣን እርከናቸው ቁብ ሳይሰጡና በይሉኝታ ሳይግደረደሩ ጓሯቸው ያፈራውን የዱባ ምርት ገበያ ወስደው በመሸጥ ያንን ክፉ ቀን ለማሳለፍ ወሰኑ ይባላል።
ነገር ግን የዱባ ምርቱ የሚያወላዳ ስላልሆነ ምኑን ከምን እንደሚያደርጉት ግራ በገባቸው ሰዓት እኩል የተጨነቁት ባለቤታቸው በጉዳዩ ላይ አስበውበት ኖሮ “ምን ያስጨንቅዎታል? የዱባው ቁጥር ካነሰ ለምን በሀረግ ላይ የተንዠረገገውን ቅል ለቅመን “ከዱባው” ቀላቅለን አንሸጥም? ከነአባባሉም እኮ ‹በዘመነ መከራ የተፈጸመ ግፍ ከወንጀል አይቆጠርም›” በማለት ስላበረታቷቸው ባልየው እንደተመከሩ ዱባና ቅሉን ቀላቅለው ገበያ መሃል በመዘርጋት ገዢዎችን መጠባበቅ ጀመሩ ይባላል።
እውነትም ገበያው እንደደራ አንዱ ገዢ ወደተደረደሩት የዱባ ምርቶች ቀረብ ብሎ ሲያስተውል ከዱባው ጋር ቅል እንደተቀላቀለበት ያስተውላል። ይሄን ጊዜ ያ ከመታለል የዳነው ገበያተኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ “አቤቱ ፈጣሪ ሆይ ምኑ ዘመን ላይ ደረስን! እዝጊዮ አቤት! አቤት! የሕግ ያለህ የፍትህ ያለህ! የፈጣሪ ቁጣ ወርዶብን በርሃብና በቸነፈር መቀጣታችን አንሶ ምን ‹ቅል ባገኝ ብንሰኝ› (ቅል ባገኝ ማለት ሙልጭ ያለ ድሃ ማለት ነው) መንግሥት ባለበት አገር “ቅልን ዱባ” ብሎ መሸጥ ግፍ አይሆንም?” ብሎ በንዴት በመጦፍ ፊቱን ወደ ሻጩ ዞር ሲያደርግ ለካስ ተራ ነጋዴ የመሰሉት የራሱ ጉድ – የአገሩ ገዢ ናቸው። ይሄኔ በአፍ እላፊው ተደናግጦና አንደበቱን አለስልሶ፤ “ማለቴ ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል” ለማለት ፈልጌ ነው” በማለት ለሹሙ እጅ ነስቶ ራሱን ከችግር ታደገ ይባላል።
ሁለተኛው ገበያተኛም እንዲሁ ዱባውን ለመግዛት ቀረብ እንዳለ “ሻጭ ለዋጩ” እኒያው የአካባቢው ጌቶች መሆናቸውን ሲያውቅ ፍርሃት እያንዘረዘረው ቀልብ እንደነሳው ወፈፌ ወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ፡-
<<ኧረ ምረር ምረር፤ ምረር እንደ ቅል፣
ስላልኮመጠጠ ስላልመረረ ነው ዱባ እሚቀቀል።>>
በማለት ገበያውንና ገበያተኛውን በብሶት ቀረርቶ አናወጠው ይባላል። በዚያው ገበያ ላይ “ዱባ ባገሩ ጋን ያህላል አሉ።”፤ “ዱባና ቅል አብሮ ይበቅላል፤ አበቃቀሉ ግን ይለያል” በማለት የሹሙን ድርጊት በጥበበ ቃላት አራክሰው የተዘባበቱም በርካቶች ነበሩ – ይለናል ሥነ ቃላዊ ትረካው።
ዱባና ቅሉን እንዳንለይ ግራ ያጋቡን ኑሯችንና አኗኗሪዎቻችን፤
ከምንጊዜውም ይልቅ ዛሬ በኑሯችን ጅራፍ የተገረፍ ንበት ጫንቃችንና ጀርባችን ቁስሉ እያገረሸ በርትቶብናል። ማመርቀዙም ከፍቶብናል። በሁሉም የኑሯችን ዘይቤ ውስጥ “ዱባና ቅሉ” እየተቀላቀለ ሕይወታችንን መራራ አድርጎታል። የፖለቲካውና የመንግሥት ጉልበት የራደ እየመሰለን ስንባንን ውለን ማደርንም ተላምደነዋል። ሥልጣነ በትሩን የያዙት “ሙሴዎቻችን” ተደራርቦ የተጋረጠብንንና በቀይ ባሕር የሚመሰለውን ፈተናችንን በሥልጣነ በትራቸው በመምታት ከፍለው በድል ሊያሻግሩን የቻሉ አልመስል ብሎን “በኤሎሄ!” እየቃተትን ወደ ፀባኦት መቃተታችንን አላቋረጥንም።
በየደረጃው ያሉ ገዢዎቻችንና ዘመንኞቹ ሹመኞች ቀላቅለው እያቀረቡልን ያለው የዱባና ቅል ውሳኔያቸውና አተገባበራቸው እንደማያዋጣ በሕዝብ የእምባ መዋጮ ጭምር እየለወስን “አቤቱታ” ብናቀርብም ሰሚ ያገኘን አልመስል ብሎን ግራ መጋባታችን ጨምሯል።
የቢሮክራሲው ዘዋሪዎች የስብሰባ ውሎ አምሽቶማ ተነግሮም ሆነ በኡኡታ ተገልጾ ሰሚ በመጥፋቱ፤ “ምን ዕንቁላል ድፍን፤ ማያችሁን እምዬ ማርያም ድፍን” ብለን የልጅነታችንን እርግማን በማዥጎድጎድ “የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ” በማለት በሕዝባዊ ልብ ለልብ መናበብ ተግባብተን በ“ተው ቻለው ብሶት” ማንጎራጎር እንደሚሻል የጋራ ውሳኔ አሳልፈናል። “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ብሂል አርጅቶ ያፈጀው ከማእረጉና ከማእረግተኞቹ ጋር አንድ ላይ ተደምሮ ነው። በአንፃሩ ዜጎች ሁሉ እንደ አዲስ አዘውትረው የሚጠቀሙባቸው ብሂሎች “ዝም አይነቅዝም፣ ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” የሚባሉትን ዓይነቶች ነው። ተናግሮ ጥርስ ከሚነከስ ስሜትን አምቆ ውስጥ ቢነቅዝ ይበጃል።
በድምጻችን ተመርጠው በላያችን ላይ ያነገሥናቸው አብዛኞቹ ሹመኞች ውለው ሳያድሩ በሾህ ልምጭ ይጠበጥቡን ጀምረዋል። የሙስና ሰንሰለታቸውን አርዝ መው የሥልጣናቸው ጀንበር ሳትጠልቅ “ቅርሳቸውን” ለመቋጠር ደህና አድርገው መጋጡን ጀምረዋል። መቶ ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል፣ በሚሊዮን ብር ሲደራደር እየተባለ በሚዲያ የሚለፈፈው በናሙናዎቹ ላይ ካልሆነ በስተቀር ወደ ላይም ወደ ጎንም ጠለቅ ብሎ ቢፈተሽ ቅርናቱና ክርፋቱ አያድርስ የሚያሰኝ ነው። ገና ዓመት ሳይሞላ እንዲህ ካደረጉን ዘንዳ ሆዳቸውና ደረታቸው ሰፋ ሰፋ ማለት ሲጀምርማ ምን ሊያደርጉን እንደሚችሉ ለመተንበይ ነብይነት ግዴታ አይደለም። እኛ ለመኖር ወይም ላለመኖር በግብግብ ተሸንፈን ስንወድቅ፤ እነርሱ ለነገ “ቅርስ ለመቋጠር” ፍልሚያውን አጧጡፈውታል። የት ቁጭ ብለው እንደሚበሉት ግን ያሰቡበት አይመስልም።
ገበያው ሊያሳብደን ኪሳችንን መፈተሽ ገና እንደጀመረ፤ “ለከርሞ የሚያብድ ሰው በመስከረም ሱሪውን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጀምራል” እያልን በተካንንበት ብሂል “ቀንድ ማቆጥቆጥ” በጀመረው ገበያ መካከል ቆመን ታደጉን እያልን ስንጮኽ አልሰማ ብለውን ጆሯቸውን ደፍነውብን ነበር። እነሆ የፈራነው ደርሶ የኢኮኖሚው አብሾ አናታችን ላይ ወጥቶ ጨርቃችንን አስጥሎ አእምሯችንን ስለሰወረን “ዱባና ቅሉን” መለየት ተስኖን በብእራችንም በአንደበታችንም መለፍለፍን ሥራዬ ብለን ተያይዘነዋል። እንደተለመደው በድምጻችን ለወንበር ያበቃናቸው ገዢዎቻችን ዛሬም እያወቁ የደፈኑትን ጆሯቸውን አልከፍት ብለው “ይለፍልፉ ምን እንዳያመጡ ነው” የሚሉን ከሆነ “የሚመጣውን” አብረን ስለምናይ እምባችንን ወደ ፈጣሪ እየረጨን የፍርዱን ቀን በጋራ እንጠባበቃለን።
ለነገሩ በዚህች ምስኪን አገሬ ውስጥ ማን ያልባለገ ይገኛል። የሚኖር ከሆነ ሙት ተስፋችንን ስለሚያንሰራራ በግልጽ የሚያመላክቱን ብጹዓን ናቸው። ፖለቲካው ባልጓል። ያባለጉትን ባለጊዜዎች ነቅሰን በአደባባይ እንዳናጋልጥ ወይንም “ባለጌን ከወለደ የገደለ ይጽድቃል” ብለን በድፍረት እንዳንናገር “ሕጉ አሟረታችሁ” በማለት በአፍ እልፊት የክስ ቻርጅ ከፍቶ ከርቼሌ እንዳይወረውረን እንሰጋለን። “ለጥብቅና አግዘን የምንለው ዴሞክራሲውም” ሁሌም ችግር ሲገጥመን “ሥራችሁ ያውጣችሁ” በማለት ፊት እንደሚነሳን አልጠፋንም።
እንዲህ ዓይነቱን የአገር መከራ በጨዋታ እያዋዛን ብሶታችንን ስንገላለጥ አንዱ ዘመናዊ ገበሬ ነኝ ባይ ቃንቄ ጎረምሳ፤ “የባለገው መች ፖለቲካው ብቻ ሆኖ። የገበሬው ማሳም ያለ ኬሚካል ማዳበሪያ ጉቦ ምርት አልሰጥም ብሎ ካደመብን ሰነባብቷል” በማለት ከጨፍጋጋ ስሜት አውጥቶ ፈገግ እንድንል አድርጎናል። ባለሥልጣኖችም ሆኑ ተፈጥሮ ባልገው ያለ ጉቦ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ከሆነ ወደ ማን አቤት እንበል? “ግራ የገባው ግራ” አሉ ወይዘሮ ወርቄ። እያረርን እንሳቅ እንጂ ምን ማድረግ ይቻላል?
ጠቢብ ሹም ሆይ ወዴት አለህ!?
ከብሶትና እሮሮ ጨፍጋጋ ስሜት ወጣ ብለን ፈገግ የሚያደርግ አንድ አፈ ታሪክ እንከፋፈል። የአፈ ታሪኩ መነሻ ሃሳብ የተወሰደው ከቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ (1ኛ ነገሥት ምዕ. 10) ይመስላል። ታሪኩ የሚያጠነጥነው በእስራኤሉ ንጉሥ በሰሎሞንና በአበሻዋ ንግሥት በሳባ ላይ ነው። ንግሥተ ሳባን “የእኛ ናት! ማን የእነ እከሌ አደረጋት?” የሚሉ ሞጋቾች ብዙ ስለሆኑ ለጊዜው ለታሪኩ እንጂ ለእነርሱ አታካራ ፊት አንሰጥም። እንደ ወዳጅ እንምከራቸው ካልን ግን ይህቺን ታላቅ ንግሥት የምንጠራት በሦስት ስም ንግሥተ ሳባ፣ ንግሥተ ማክዳ፣ ንግሥተ አዜብ እያልን ስለሆነና ምስክርነት ደግሞ በሦስት ስለሚጸና “እመቤት ሆይ ሳባ የእኛና የእኛ ብቻ ስለሆነች” የራሳቸውን ጠበቅ የእኛን ለቀቅ እንዲያደርጉልን ማሳሰቢያ አኑረን እናልፋለን።
ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ዝና ሰምታ ልትጎበኘው ከምድረ ኩሽ ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገሰገሰች ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይተርክልናል። “የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች።…ሰሎሞንም የጠየቀችውን እንቆቅልሽ ሁሉ ፈታላት። ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።”
አፈ ታሪኩ የተቃኘው ይህንን የቅዱስ መጽሐፍ እውነታ መሰረት አድርጎ ነው። እናም ንግሥት ሳባ ወደ ሰሎሞን እንደቀረበች ሰባት ያህል እርምጃ ራቅ በማለት በቅርጽም ሆነ በይዘት ተመሳሳይ የሆኑና አንዱን ከአንዱ በፍጹም መለየት የሚያስቸግር የአበባ እምቡጦች እያሳየችው፤ “ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ! ከያዝኳቸው ከእነዚህ ሁለት የአበባ እምቡጦች መካከል የተፈጥሮው አበባ የትኛው ነው? አርቴፊሻሉ?”
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በእንቆቅልሽ ጥያቄዋ ትንሽ ግር ተሰኝቶ ከቆየ በኋላ ለፈታኟ ንግሥት እንዲህ ሲል መለሰላት። “አንቺም ንግሥት ሆይ ሺህ ዓመት ንገሺ! የተፈጥሮው አበባ የቱ እንደሆነ የምነግርሽ በእጅሽ የያዝሻቸውን አበቦች እዚያ መስኮቱ ደፍ ላይ ሄደሽ አስቀምጪ” በማለት አዘዛት። እርሷም እንደታዘዘችው አደረገች።
አበቦቹን አስቀምጣ ገና ዞር ከማለቷ አንዲት ቀሳሚ ንብ ጢዝዝዝ እያለች ሄዳ የተፈጥሮው አበባ ላይ አረፈች። ይሄን ጊዜ ንጉሥ ሰሎሞን ወደ ንግሥት ሳባ ዞር በማለት “እነሆ የተፈጥሮ አበባ የቱ እንደሆነ መልሱን አገኘሽ?” በማለት እንቆቅልሹን ፈታላት ይባላል። እርሷም ከመደነቋ የተነሳ እንዲህ አለችው ይላል የአፈ ታሪኩ መደምደሚያ ሳይሆን የቅዱስ መጽሐፉ እውነታ። “ንጉሡንም አለችው፡- ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንኩም ነበር። እነሆም እኩሌታውን እንኳን አልነገሩኝም። ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል” (1ኛ ነገሥት 10፡6 -7)።
ለእኛም ለዛሬዎቹ የሳባ ልጆች የሚያስፈልጉን መሪዎችና ፖለቲከኞች ተፈጥሯዊ ችግሮቻችንን እየነቀሱ የኢኮኖሚያችንን፣ የማሕበራዊ ተራክቧችንን ቁስልና የህመምተኛ ፖለቲካችንን እባጭ እንዲያፈርጡልን እንጂ በብልጭልጭ አርቴፊሻል ፖሊሲና መመሪያ እንቆቅል ሻችንን እንዲያወሳስቡብን አይደለም። አርቴፊሻሉንና ተፈጥሯዊውን እውነታ እያምታቱም “እሳት ካየው ምን ለየው” እያሉ እንዲፈላሰፉና እንዲመጻደቁ አንፈቅድ ላቸውም።
የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚስቶቹን ያረጀና ያፈጀ ፍልስፍና እየተነተኑ “ማልተስ እንዳለው፣ ማርክስ እንደተፈላሰፈው፣ ሚልተን ፍሬድማን፣ አስቴር ዱፍሎ እንደጻፉት ወዘተ.” እያሉ ግራ እንዲያጋቡንም ፊት ልንሰጣቸው አይገባም። ዓለም ባንክ እንዳዘዘው፣ አይ.ኤም.ኤፍ እንደተነበየው የሚለው ዲስኩርም እጅ እጅ ብሎናል። በፖለቲካው ሠፈርም ቢሆን በሕልማቸው የቃዡትን ሁሉ ማለዳ ላይ እየዘረገፉ ሸክም እንዲጭኑብን ልንፈቅድላቸው አይገባም። በየመድረኩና በየሚዲያው “ቅሉን ዱባ ነው” ሲሉን “አበቃቀሉ ለየቅል” እያልን፤ አርቴፊሻሉን አበባ የተፈጥሮ ነው እያሉ ሲደልሉንም በሕዝባዊ ጨዋነት እየገሰጽናቸው እንዲታረሙ ማድረግ ድፍረት ሳይሆን መብት ነው። “መቼስ ምን ይደረጋል” ቁዘማ የትም ስለማያደርሰን ሕዝቤ ሆይ ለራስና ለራሳችን እንወቅበት። አገሬስ ሰማሽኝ!? ሰላም ይሁን!!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014