(ክፍል ሁለት)
ትናንት በዚሁ አምድ ለንባብ በበቃው ክፍል አንድ መጣጥፌ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ሕወሓት በወልቃይት ፣ ጠገዴና ጠለምት የፈጸመውን በዘር ማጥፋትና በሌሎች ወንጀሎች ሊያቋቁም የሚችልን የጥናት ግኝት መነሻ አድርጌ የሽብር ኃይሉን የዘር ማጥፋት ያደረ ልምምድ እና ይሄን ልምምዱን ለዓለም በማጋለጥ ረገድ ያለብንን ስንፍናና ዳተኝነት ለማንሳት ሞክሬያለሁ። ዛሬም ካቆምሁበት እንዲህ ቀጥያለሁ።
ሕወሓት ከምስረታው እንደርሱ ሁሉ የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ ለመታገል ጫካ የገቡትን ኢህአፓ ፣ ኢዲዩና የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደራደር ፣ ልዩነታችንን በውይይት እንፍታ እያለ እያግባባ እውነት መስሏቸው ለውይይት ሲቀመጡ አንድ በአንድ የጨረሰ አረመኔና የዘር አጥፊ ስብስብ ነው። እነ ስሁልን ፣ ሙሴን ፣ ዩሐንስ ገ/መድህን/ዋልታ/፣ ሀይሎምንና ሌሎቹ በሃሳብ የተለዩትን እልፍ አእላፍ ታጋዮችንና ልጆቹን እንደ ድመት እንደበላ የሚነገርለት ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ፣ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈጸመ ፤ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ እንደፈጸመው ክህደት ከጀርባ ወግቶ ወይም በጥይት ደብድቦ በርካቶችን የገደለ ማህበረሰብንና ዘርን የጨረሰ አሪዮስ ነው ።
ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የሀውዜንን ሕዝብ በገበያ ቀን በአውሮፕላን አስፈጅቶ ሙሾ የሚያወርድ ፤ የአዞ እንባ የሚያነባና ሀውልት የሚያቆም የሀፍረተቢሶች ስብስብ ነው። በ77 ድርቅ ለትግራይ ሕዝብ የተላከ እርዳታን ሽጦ የጦር መሳሪያ የገዛ ትግራዋይን በርሀብ የጨረሰ ለፖለቲካዊ ቁማር ምንም ከማድረግ የማይመለስ ቡድን ነው ። ባለፉት 47 አመታት በክልሉ የሚገኙ እንደ ኩናማ ያሉ ህዳጣን ጎሳዎችን ዘር ያጠፋ ፤ ከ1972 ዓም ጀምሮ የወልቃይት ፣ የጠለምት የጠገዴ አማራዎችን ፤ እንዲሁም በኮረምና አላማጣ የራያዎችንና የአማራዎችን ዘር ያጸዳ ፤ እስከ አንገቱ በዘር ማጥፋትና በጎሳ ማጽዳት ወንጀል የተዘፈቀ የአሸባሪዎች ስብስብ ነው ።
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ሳምሪ በተባለ የአሸባሪው ወጣት ገዳይ ክንፍ (ዛሬ በስደተኝነት ስም በሱዳን የሚገኘው) ከ1 ሺህ 600 በላይ አማራዎችን በገጀራ፣ በፋስ፣ በብረት፣ በማጭድና በጩቤ በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። መንግሥት ለሰብዓዊነትና ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ በሚል ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር ዜጎችን (በተለይም አማራ እና አፋሮችን) በማንነታቸው ገድሏል። ገርፏል። ህጻናትን ፣ ሴቶችንና መነኮሳትን በቡድን ደፍሯል። ዘርፏል። አውድሟል።
በግልጽ በአደባባይ ከአማራ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ ባለው መሠረት ሒሳቡን በግፍ አወራርዷል። እያወራረደም ይገኛል። ይህ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ተላላኪና አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል ተመሳሳይ ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጭካኔዎችን እየፈጸመ ሲሆን በተለይ በፈንቲ ረሱ ዞን ጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ በወረራው ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ይገኙ የነበሩ 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ሴቶችንና አረጋውያንን በከባድ መሳሪያ በመጨፍጨፍ ጥርሱን የነቀለበትንና እንደ ልማድ የያዘውን የዘር ማጥፋት በአፋር ሕዝብ ላይ ፈጽሟል። አሁንም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ ወንጀል እየፈጸመ ነው።
ከዚህ ሁሉ ወንጀሉና ግፉ በኋላ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የአገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በእብሪት አገር ሲወርና ሲፎክር እንዳልነበር፤ ጅራፍ ራሱን ገርፎ ራሱ ይጮሀል እንዲሉ ተከበብሁ ተወረርሁ የትግራዋይን ዘር ሊያጠፉ ነው እያለ በቅጥረኛ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ፤ በእነ ማርቲን ፕላውት በአውሮፓና በአሜሪካ በኤርትራውያን ስደተኞች ስም በሀሰተኛ ማስረጃ የተሰገሰጉ የአሸባሪው ቤተሰብና ቅጥረኛ “ስደተኛ” ፤ በተከፋይ ሎቢስቶችና ውሸት ሰላቂዎች ፤ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮችና በሌሎች ባንዳዎች የድረሱልኝ እዬዬውን ያቀልጠዋል።
አሸባሪው ሕወሓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያልፈጸመበት ኢትዮጵያዊ የለም። በኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ፣ በኦርቶዶክሳውያን፣ በሙስሊሞች ፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ወዘተረፈ ላይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የዘር ማጥፋትና የጎሳ የማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል።
በትግራይ ከአንድም ሁለት ሶስት ትውልድ አጥፍቷል። የ12 ና የ13 አመት ህጻናትን በማዕበል በእሳት ከመማደግ በላይ ምን የዘር ማጥፋት አለ። ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ ሆን ብሎና አቅዶ ኢትዮጵያውያንን በማደህየት ለዘር ማጥፋት ሲያመቻቸው ኑሯል። ይህ የሽብር ስብስብ በዚህ እኩዩ ተግባሩ ሳይጸጸት በተደጋጋሚ አገርን ለማፍረስ እና እንደ ማይካድራ ጋሊኮማ ለሌላ ዙር ዘር ማጥፋት ሲዘጋጅ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲል አውጆት የነበረውን ተኩስ አቁም ተገዶ ሲያነሳ ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሊያጠፉ ነው እያለ ጡርባውን ይነፋል።
ሌላው ይቅርና የለውጥ ኃይሉ ይህ ጦርነት እንዳይነሳ በአደባባይ ከ20 ጊዜ በላይ የሽምግልና የእርቅ ጥረት አድርጓል። ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባም ንጹሐን እንዳይጎዱ ሠራዊቱ ዋጋ ከፍሏል። የተናጠል የተኩስ አቁም ያረገውም ለትግራዋይ በማሰብ ነበር። አሸባሪው ሕወሓት እንደ አጼ ልብነ ድንግል ጦር አውርድ እያለ መሬትን 40 ጅራፍ ገርፎ ፤ በዳቢሎሰኛ ጾም ጸሎት ባመጣው ጦርነት የተፈጠረውን ምስቅልቅልና ያፈረሰውን መሠረተ ልማት ለመጠገንና መልሶ ለማቋቋም በስምንት ወራት ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጓል።
ከዚህ ሁሉ በኋላም የሽብር ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች የጥፋት ስምሪቱ በአማራና በአፋር ክልሎች በብዙ መቶ ቢሊዮኖች የሚገመት መሠረተ ልማትና ፋብሪካዎችን አውድሟል። ዘርፏል። የትግራይ ክልልን የ11 ዓመታትን በጀት ዓመት ባልሞላ ለመልሶ ግንባታ ወጭ ያደረገውን የዐቢይ መንግሥት ትግራዋይን ሊያጠፋ ተነሳ ቢባል ከራሱ ከአሸባሪውና ከጭፍራው በስተቀር ሰሚ የለውም። አሸባሪው ግን ትግራዋይን ከልጅ እስከ አዋቂ በአሽሽ እያሰከረ በሕዝባዊ ማዕበልነት ለእሳት እየማገደ ትግራይን ትውልድ አልባ ምድረ በዳ ሊያደርጋት ቆርጦ ተነስቷል። እንግዲህ ዜጋ አገር ይፍረድ ! ዘር አጥፊው ማነው !? መልሱ ቀላል ነው። እሱም አሸባሪው ሕወሓት ነው ።
ሆኖም ይሄን ዘር አጥፊ አሸባሪ ዓለምአቀፍ ሚዲያው ባላየ ባልሰማ ማለፉ ሲገርመን ከእነ አመነስቲ ፣ ቴድሮስ (ዶ/ር) እና ከአንዳንድ የኮንግረስ አባላት ጋር ሆኖ ማዕቀብ ለማስጣል የተናበበ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ስንመለከት ያበግናል። በዓለማችን በጦርነት ወቅት አንድ ፎቶግራፍ ወይም አሳዛኝ የሕይወት ቅንጣት ፤ ታሪክን የመቀየር ወይም እንደ አዲስ የመበየን ኃይለኛ ጉልበት እያለው ፤ እኛ ጋ ሲደርስ ምነው ጉልበቱ ራ’ደ !? ዛለ !? ቄጠማ ሆነ !? ለዛውም በአሸባሪው ሕወሓት በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን በግፍ ተጨፍጭፈው ፤ የዘር ማጥፋት፤ የጦር ወንጀል ፤ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል ተፈጽሞ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ በቡድን አስገድዶ ደፋሪዎች ቅስማቸው ተሰብሮ።
አሜሪካውያን የቬትናም ጦርነትን ዳር እስከ ዳር ሆ ብለው እንዲቃወሙ ያደረጋቸው ጦርነቱ ፍትሐዊ ስላልሆነ ወይም ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች በመሞታቸው ብቻ አይደለም። በደቡብ ቬትናም በተፈጸመ የአየር ድብደባ የናፓል ቦንብ ፍንጣሪ ያቃጠላት የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ ፋን ቲ ኪም ቃጠሎው የፈጠረባትን ኃይለኛ የሚያነገበግብ ህመም እንዲያስታግስለት ልብሷን አውልቃ እርቃኗን እጇን ዘርግታ እየተንሰፈሰፈች ከሌሎች ህጻናት ጋር በፍርሀትና በስቃይ ከፍንዳታው ስትሸሽ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ፍቶ አንስቶ ወደ አሜሪካ ከላከው ከቀናት በኋላ ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ በሌሎች ጋዜጦች መታተሙ የአሜሪካውያንን የጸረ ጦርነት ተቃውሞ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው።
አሜሪካም ብዙ ሳትቆይ ከቬትናም በሽንፈት ለቃ ወጣች። ሰሜኑና ደቡቡ ቬትናምም ተዋሀደ ። የፎቶ ጋዜጠኛው የፑሊትዘርና የሌሎች ታላላቅ ሽልማቶች አሸናፊ ሆነ። የጦርነቱን ምዕራፍ የቀየረችው የዛኔዋ ብላቴና ኪም ዛሬ በከናዳ ቶሮንቶ የልጅ ልጅ አይታ ከመኖር ባሻገር በየአጋጣሚ የጦርነትን አስከፊነት ትገልጻለች።
ታሊባን ሴቶች እንዳይማሩ እስከግድያ ይደርስ የነበረን አፈናውን ለዓለም ያሳወቀችው ከታሊባን ጥይት በተአምር የተረፈችው የሴቶች የመማር መብት ተሟጋቿ የኖቤል ተሸላሚዋ ብላቴና ማላላ ዮሱፍዚ ናት ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆኖ ፤ የሕዝብን ይሁንታ ለማግኘትና አስተያየቱን ለማስቀየር ትናንትም ሆነ ዛሬ ሀሰተኛ ሁነቶችንና ምስክሮችን ሲዘጋጁ ተመልክተናል። ጆርጅ ቡሽ የኢራቅን የኩየት ወረራ ለመቀልበስ ሕዝባዊ ድጋፍና የኮንግረስ ይሁንታ እንዲያገኝ ደጋፊዎቹ እረጅም ርቀት ሄደዋል ።
በኩየት የአሜሪካ አምባሳደር ልጅ የሆነችው የ15 ዓመቷ ናይራህ አልሳባብ በሀሰት በጎ ፈቃደኛ ነርስ እንደሆነችና የኢራቅ ወታደሮች በምትሰራበት የኩየት ሆስፒታል መጥተው 312 በህጻናት ማቆያ (ኢንኩቤተር) የነበሩ ጨቅላዎችን አውጥተው ቀዝቃዛ ወለል ላይ ስላስቀመጧቸው ሕይወታቸው ወዲያው ማለፉን አሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርባ እንባ እየተናነቃት በሀሰት በመመስከሯ ጦርነቱን ይቃወሙ የነበሩ የኮንግረስ አባላት ደግፈው ድምጽ እንዲሰጡ ፤ ጦርነቱን ይደግፉ የነበሩ አሜሪካውያን ቁጥርም ከ17 በመቶ ወደ 41 በመቶ ከፍ ሊል ችሏል።
ሕወሓት በዘረፈው ዶላር የቀጠራቸው ሎቢስቶች እየታገዘ ሀሰተኛ የዘር ማጥፋት ፤ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምና አስገድዶ መድፈር የሚሉ የፈጠራ ክሶችን በመደረት እያወናበደ ይገኛል። እነዚህ በአብነት ያየናቸው ሁነቶች ታሪክን እስከ መቀየር የደረሰ ተጽዕኖ ማሳደር የቻሉት ለሰው ልጆች ስሜት የቀረቡ እንዲሆኑ ተደርገው በመቀረጻቸው ነው። የእኛ የሚዲያዎቻችንም ሆነ የመንግሥት የኮሙኒኬሽንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የጎደላቸው ይህ ነው ። በዋናነት ተግባቦታችን በሚጠበቅበት ደረጃ ውጤታማ ሊሆን ያልቻለው በዚህ የተነሳ ነው ።
ለቀደሙት 21 ዓመታት የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር እየተፈራረቀበት ፤ በቀበሮ ጉድጓድ የዕድሜውን ሲሶ ገብሮ ሲጠብቀው ፤ በትግራይ ሕዝብ ደስታና ኀዘን ተካፋይ ፤ በእርሻው በዘሩ በአረሙ በአጨዳውና በበራዩ እንዲሁም አንበጣን በመከላከል እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ (ቀንጃ )ተለይቶት በማያውቀው ፤ ከሬሽኑ እየቀነሰ ለልጆቹ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም ሲገነባ ፤ በኮቪድ 19 ለችግር ለተጋለጡ አሁንም ከእጅ ወዳፍ ከሆነች አበሉ ያካፈለ እሩህሩህና ለወገኑ ሟች የሆነ ሠራዊት በአረመኔውና ጉግማንጉጉ የትህነግ እፉኝት ቡድን ለማየት የሚዘገንንና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ ተፈጽሞበታል። በዚህም ከ6ሺህ በላይ የሠራዊቱ አባላት በተኙበት በውድቅት ሌሊት በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ስንቁ ትጥቁ ከባድ መሳሪያው ተዘርፏል። ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓም ከ1600 በላይ ንጹሐን በማይካድራ በማንነታቸው ሳምሬ በተባለ የሕወሓት ወጣት ገዳይ ቡድን ተጨፈጨፉ።
ሆኖም ይህን የዘር ማጥፋት ፣ የአገር ክህደትና የጦር ወንጀል ጊዜ ወስደን ለሕዝባችን ለወዳጅና ጎረቤት አገራት ፤ ለአፍሪካ ሕብረት ፣ ለኢጋድ ፣ ለመንግሥታቱ ድርጅት፣ ለአሜሪካና ለምዕራባውያን በልኩና በአግባቡ ባለማሳወቃችን የሕግ የበላይነት የማስከበር እና የሕልውና ዘመቻችንን ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ እጅን በአፍ በሚያስጭን ወታደራዊ ድል ብንቋጭም፤ በአሸባሪው ሕወሓት መሰሪና ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ትግራዋይም እነ አሜሪካም ስለተነሱብን የሠራዊታችንም ሆነ የመንግሥታችን መልካም ስም ከመጠልሸቱ ባሻገር ፤ በዘር ማጥፋት ፣ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም፤ በአስገድዶ መድፈርና በዘረፋ የፈጠራ ክስ ተፈርጀን ጫናው በመበርታቱ እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ሰለባ ሆነን ሳለ እንደ ወራሪና ወንጀለኛ በመታየታችን በተናጠል የተኩስ አቁም ከትግራይ ልንወጣ ችለናል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014