ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ሳምንት በወዳጅነት አደባባይ መካሄዱ ይታወቃል፡፡ ይህ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በብዛት የተሳትፉበት ዝግጅት ስኬታማ መሆኑ ይገለጻል፤ ደቡብ ክልል ብቻ ወደ 100 ተሳታፊዎችን ይዞ መገኘቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ይህን የኢትዮጵያ ሳምንት ዝግጅትን ከፍ ባለ መልኩ ለማካሄድ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የምስራቅ አፍሪካና ታላላቅ ሀይቆች አገሮች የባህልና የኪነጥበብ ሳምንት በሚል በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አባል አገሮችን ጨምሮ ሌሎች የታላላቅ ሀይቆች አገሮችም የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የቀጠናውን የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት አስመልክቶ በቅርቡ በአዳማ ከተማ ከመገናኛ በዙሃን ባለሙያዎች ጋር በመከረበት ወቅት የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ መሀመድ የበአሉን እቅድ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንዳመለከቱት፤ ምስራቅ አፍሪካ ሲባል የኢጋድ አባል አገሮችን ጨምሮ ወደ አስራ ስምንት አገሮች ያሉበት ነው፡፡ በበአሉ ይሽፈናል ተብሎ እየተሰራ ያለውም ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን እስክዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው የአህጉሪቱ ክፍል ነው፡፡
ይህ ቀጠና ሰፊ እምቅ ሀብት አለው፡፡ 270 ሚሊየን አካባቢ ህዝብም ይኖርበታል፤ ይህ አሀዝ ከአሜሪካ ህዝብም ብዛት የማይተናነስ ነው፡፡ 6ሺ 600 ኪሎ ሜትር የባህር ዳርቻ ያለው ሲሆን፣ ይህ በራሱ ለቀጠናው ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በከብት፣ በተፈጥሮ እና በዱር እንስሳት ሀብቱና በአየር ጸባዩ ምቹነትም ይታወቃል፡፡ ይህ አካባቢ ቢቀናጅ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ አንደሚችል በዚህ በአል ዝግጅትም ታምኖበታል፡፡
አካባቢው ከሌሎች በአፍሪካ ካሉ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች አኳያ ሲታይ ግን በተለይ በኪነጥበብ በኩል አልተሰራበትም የሚባልና የተዘነጋ አካባቢ ነው፡፡ በባህልና በኪነጥበብ ዘርፍ ቢሰራበት ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ታምኖበትም ጭምር ነው የባህልና የኪነጥበብ ሳምንቱ የሚካሄደው፡፡
የምእራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብና የደቡብ አፍሪካው ተመሳሳይ ተቋም በኪነጥበቡም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከምስራቅ አፍሪካው አካባቢ አንጻር ሲታይ ብዙ እንደተሰራባቸው በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ ያልተካተተችበት የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በዚህ በኩል ተጠቃሚ መሆኑ ይገለጻል፡፡ በመሆኑም ይህ ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ቀጠናዊ የባህልና ኪነጥበብ ዝግጅት እርሾ በመሆን ቀጠናውን በማስተሳሰር በኩል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ለአገራችን ደግሞ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ አገራችን በጦርነት ውስጥ አንደመቆየቷ በአለም ስሟ እየተነሳ ያለውም ከዚሁ ጋር ሆኗል፡፡ ይህን ገጽታ መቀየር የግድ ያስፈልጋል፤ ለእዚህ ደግሞ ይህ ክፍለ አህጉራዊ ዝግጅት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡ መድረኩን አስመልክቶ እየተካሄደ ባለው ዝግጅትም ሆነ ዝግጅቱ በሚካሄድበት ወቅት በመገናኛ ብዙሃን ሰፋፊ ስራዎች እንዲሰሩም የሚጠበቅ በመሆኑም ነው ሚኒስቴሩ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ሰፊ ምክክር ያደረገው፡፡
የባህልና የኪነጥበብ ሳምንቱ ለስድስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፤ አስር አገሮችም ይሳተፉበታል፤ ተሳታፊ አገሮችም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲና ታንዛኒያ ናቸው፡፡ አገሮቹም አስፈላጊነት ላይ አዎንታዊ መልስ መስጠታቸው በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከሆነ የተሳታፊ አገሮች አምባሳደሮች ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በቅርቡ ውይይት በተደረገበት ወቅት ይበልጥ ተረጋግጧል፤ አምባሳደሮቹም ግብዣውን ተቀብለውት ለዝግጅቱ በቂ ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑን በመጥቀስ የሚካሄድበት ቀን እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡ ለአንድ አመት ብቻ ተዘጋጅቶ መቆም እንደሌለበትም ነው ያስገነዘቡት፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ተቀብሎ፤ ሚያዚያ 28 ሊጀመር ታስቦ የነበረው መድረክ በፈረንጆቹ ግንቦት አጋማሽ አንዲጀመር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በዝግጅቱ ልዩ ልዩ ፌስቲቫሎች፤ ሲምፖዚየምና ኢግዚቢሽኖች ይካሄዳሉ፡፡ ሲምፖዚየሙ ለየት ባለ መልኩ የሚዘጋጅ ነው፡ በሙዚቃ ኮንሰርት በጣም ብዙ ሰው እንዲሳተፍ ለማድረግ ታቅዷል፤ በተቻለ መጠን በዩቲዩብም በምንም አርገን የአስሩም አገሮች አርቲስቶች አንዲሳተፉበት ይደረጋል ሲሉ አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም አሁን በአገራችን ያለውን ድባብ የምንቀይርበት ሁኔታ ላይ እንሰራለን ያሉት አቶ አህመድ፣ በአገራችን በአፋርና አማራ ክልል በባህልና ኪነጥበብ ዘርፉ ተቋማት ላይ የደረሰ ውድመት እንደመኖሩም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለመልሶ ማቋቋሙ የሚጠቅሙ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
የስነ ጥበብ ኢግዚቢሽን፣ የፊልምና የሙዚቃ ፌስቲቫል፣ የመጻህፍት እንዲሁም የእደ ጥበብ አውደ ርእዮች ይኖራሉ፤ ሲምፖዚየሙ በአፍሪካ ህብረት ወይም በኢሲኤ ይካሄዳል፤ ወዳጅነት አደባባይና የእንጦጦው የአርት ጋላሪም ዝግጅቱ ከሚካሄድባቸው ቦታዎች መካከል ናቸው፡፡
የሙዚቃ ፌስቲቫሎቹ በሁለት መልኩ ነው የሚካሄዱት፡፡ አንደኛው የባህል ሙዚቃ ሲሆን፣ ሌላው ዘመናዊ ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ኮንሰርት ይሆናል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ይዘት ምን መሆን አለበት በሚለውም ላይ ተሰርቷል፡፡
እንደ 1977ቱ የህዝብ ለህዝብ አይነት የኪነጥበብ ዝግጅትም ይካሄዳል፤ ይህም በተዋቂ ከያኒያን ድንቅነሽ ኢትዮጵያ በሚል እየተዘጋጀ ነው፡፡ የዚህ ዝግጅት አንዳንድ ስራዎች ተጠቀናቅቀው ወደ ልምምድ መገባቱን አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዝግጅት ኢትዮጵያ ላይ በደንብ ከታየ በሁዋላ በምስራቅ አፍሪካ እንዲዞር አንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ የአገሮች ባህልና ስፖርት ሚኒስቴሮች ይሳተፋሉ፤ ቢቻል ቢቻል የምስራቅ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በዚህ በኩል ትኩረት ተደርጎ የሚሰራውም የምስራቅ አፍሪካ አገሮችን ማስተሳሰር ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፤ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩል ኪነጥበብ የሚኖረው ሚና ላይ ይሰራል፡፡ በመድረኩም ኢትዮጵያዊነትን ተይዞ ነው የሚቀረበው፡፡
የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት ዝግጅት መርሀ ግብሩን ዝርዝር እቅድ እንዲሁም ቀጣይ ክንውኖች በማስተዋወቅና በመዘገብ በኩል ሚዲያዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አጽንአት ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ሚኒስቴሩ ታሳቢ ባደረጋቸው ወደ 11 በሚደርሱ ቋንቋዎች የሚፈጸም እንዲሚሆን ተገልፃል፡፡ የቋንቋ ፖሊሲው በሚፈቅደው መሰረት በአማርኛ፣ በኦሮምኛ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ ዘገባዎች ይሰራሉ፤ በአለም አቀፍና በክፍለ አህጉሩ ቋንቋዎች በእንግሊዝኛ፣ በስዋህሊ፣ ሶማሊኛ፣ በፈረንሳይኛ አረብኛ የሚሰራባቸው ይሆናል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ፣ ስነጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሀዲ መገናኛ ብዙሃን ይህ የባህልና ኪነጥበብ መድረክ ሰፊ ሽፋን እንዲኖረው በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፤ የቱንም ያህል ትልቅ ጉዳይ ቢኖር መገናኛ ብዙሃን ካልያዙት ተደብቆ እንደሚቀር የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በአንጻሩ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን የያዙት ጉዳይ በስፋት እንደሚዳረስ ጠቁመዋል፡፡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃንም ለእዚህ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ለሆነ ክፍለ አህጉራዊ የባህልና ኪነጥበብ ድግስ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አገራችን ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ የምታዘጋጀውን የምስራቅ አፍሪካና የታላላቅ ሀይቅ አገሮች የባህልና የኪነጥበብ ሳምንት በማዘጋጀትም የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን ጠቅሰው፣ በዚህ ዘርፍ እንደ ክፍለ አህጉር ይህን አይነት ክፍለ አህጉራዊ መድረክ እስከ አሁን ተሰርቶ እንደማያውቅም ጠቁመዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ በአላት ሲከበሩ ከሚሰራው ውጪ በዚህ መልኩ ተሰርቶ አያውቅም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አገራችን ካለችበት ችግር አኳያ ሲታይ ይህ የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት ትልቅ የገጽታ ግንባታ ያመጣል ብለን አስበናል ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ሁሌም በጦርነት የምትታወቅ አርገው የሚመለከቱ አሉ፡፡ ይህ በአል በተለያዩ ቋንቋዎች በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ በአገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ አገሪቱ ከጦርነት ወጥታ በልማቱ መስክ ላይ አተኩራ እየሰራች ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ትልቅ የገጽታ ግንባታ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ከኪነጥበብ ዘርፉ መጠቀም ያለብንን ያህል ተጠቅመናል ወይ የሚለውንም ስንመለከት አገራችን በኪነጥበብ ዘርፉ በአጠቃላይ በጥበብ የተጠቀመችው የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ባለሙያውም ህዝቡም መጠቀም ባለባቸው ልክ አለመጠቀማቸውን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች አገሮች ግን በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው በሚገባ እየተጠቀሙበት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ይህን በአል ብቻ አክብረን አንለያይም፤ እዚህ መድረክ ላይ የተገኛችሁ ሁሉ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት አንደመሆናችሁ በቀጣይ አገሪቱ ከዚህ ዘርፍ መጠቀም አለባት በሚለው ላይ ትልቅ ውይይት ማድረግ አንዳለብን ይታሰበኛል›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያው የሆነ ችግር ሲደርስበት እርዳታ ሲጠየቅ ነው እያየን ያለነው ሲሉ ገልጸው፣ የራሳቸው የተሻለ ቤት እንኳ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡ ከኪነጥበቡ አንደኛ የጥበብ ሰዎች መጠቀም አለባቸው፤ ጥበቡን ከምናባቸው አውጥተው ነው የሚፈጥሩት፤ ማግኘት የሚገባቸውን ማግኘት አለባቸው፤ ማግኘት ያለባቸውን ማግኘት እንዳይችሉ ያረገው ምንድን ነው የሚለው መታወቅ አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ሰዎች ሙዚቃ እያዝናና ያስተምራል ብቻ ብለው ነው የሚያስቡት፤ እያዝናና ያስተምራል ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ወደሚለው ወስደን በዚህ ላይ በደንብ መስራት አለብን፡፡ ወደ እዚህ መስሪያ ቤት ከመጣሁ በሁዋላ እንደምመለከተው የሚታየው በዙም የሚያስደስት አይደለም፤ ያመኛል›› ሲሉም አመልክተዋል፡፡ መሰራት ያለበት አንዳለ እረዳለሁ ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ መንግስትም ይህንን አስቦ ነው የኪነጥበብና ስነጥበብ ክፍሉ ራሱን ችሎ በሚኒስትር ዴኤታ እንዲደራጅ ያደረገው፡፡ ሰዎች የሚያነሷቸውን እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ነው በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ በአዋጅ የተቀመጠው፡፡ ከዚህ አንጻር ምቹ ሁኔታ አለ ብለን መጠቀም አለብን፤ አደረጃጀቱ በባህል ስር ነበር፤ አሁን ራሱን ችሏል፡፡ አደረጃጃቱ አለ፤ በሙያው የሰለጠኑ ሰዎች አሉ፤ ጥበቡን የሚፈልጉ ማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ስራው ከኛ ነው የሚጠበቀው፤ ሁሉም ነገሮች አሉ፡፡
ይህን በአል ውጤታማ ለማድረግ ይህን ስሩ ለማለት አይደለም የጠራናችሁ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ነፊሳ፣ እያንዳንዱ ከእኔ ምን ይጠበቃል ብሎ እንዲሰራ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡ ተግባርና ሃላፊነትን፤ ቆጥረን ተረካክብን መለያየት አለብን፤ አገራዊ ጉዳይ ነው፤ ጉዳዩ የሁላችንም ነው፤ ከልባችን እንደ ሚዲያ ከእኔ ይህ ይጠበቃል እንደ ኪነጥበብ ባለሙያም ከእኔ ይሄ ይጠበቃል፣ እንደ አዘጋጅ እንደ ባህልና ስፖርት ምን ይጠበቃል ብለን መስራት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሁሉም እንደ አዘጋጅ ዝግጅቱን ውጤታማ ለማድረግ መስራት ይጠበቅበታል፤ እንግዶች ጠርቶ ማፈር አይገባም፤ እንግዶች ከመስተንግዶ ከሚቀርቡ ነገሮች አንስቶ ተደስተው መመለስ ይኖርባቸዋል፤ አገራችንን በደንብ ስለው ነው መመለስ ያለባቸው፡፡ ነገ ደግሞ እኛን ወደ እነሱ አገር ሲጠሩ የሚሰሩበት ተሞክሮ ይዘው መመለስ
ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገር ሄዳ ተሞክሮ ተቀባይ መሆን የለባትም፤ እኛም ተሞክሮ የሚገኝብን መሆን አለብን፡፡ ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014