ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬም እንደመሰንበቻው በአውቆ አበድ ስም የባጥ የቆጡን እየረገጠ ይጮህ ይዟል፡፡ የዛሬው ጩኸቱ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ ይለያል፡፡ በተለይ በባለፈው ሳምንት የእድራችን እና የሰፋራችን ሃላፊ አቶ መሃመድ ይመርን በፖለቲካ ንግግር ከረታ ወዲህ ይልቃል አዲሴ ንግግር ባደረገ ቁጥር የሰፈራችን ሰዎች እየተሰበሰቡ በጥሞና ያዳምጡታል።
በእኛ ሰፈር የፖለቲካዊ ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ለለውጡ መሳካት እና ለውጡን ወደፊት በማራመድ ረገድ እኔ እበልጣለሁ እኔ እበልጣለሁ የሚለው ግብግብ ከግብግብነት ባለፈ አንዱ በአንዱ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አዘል ንግግር ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በሰፈራችን አመራሮች ንግግር እና እሰጣ ገባ የተናደደው ይልቃል አዲሴ ብሶቱን ለመወጣት በጠዋቱ ተነስቶ ከዋርካው ስር በሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ መጮህ ሲጀመር የሰፈሩ ሰው በሙሉ ተሰበሰበ፡፡
ይልቃል ለተሰበሰበው እንዲህ አለ …. በአጋጣሚ ቤትህ ቀዳዳ ከበዛው ቤትህን ከእነጭራሹ ሊያጠፋው የማይፈልግ ፍጡር አይኖርም፡፡ አይጡም፣ ፍልፈሉም፣ አውሬውም፣ ሌባውም በቀዳዳው እየገባ አላስቀምጥ አላስቆም ማለቱ የማይቀር ነው፡፡ የእኛ እድር ድንኳንም ቀዳዳው ሲበዛ አላፊ አግዳሚው ካልገባሁ እያለ ቁም ስቅላችንን እያሳየን ነው፡፡
ከድንኳኑ ቀዳዳ ብዛት የተነሳ የእድራችን አባላት ሳይቀሩ የእድሩን ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ ማን ምን ይለናል ሳይሉ ያለምንም ሃፍረት እና ይሉኝታ ሲዘርፉት እና ሲያዘርፉት እያየን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በእኛ አገር ባህል የእድራችን ድንኳን ቢቀደድ የእድሩ አባላት ነጋሪት ጎስመው፣ እምቢልታ ነፍተው፣ የእድሩን መለያ እያውለበለቡ ሁሉም የእድሩ አባላት ድንኳኑን ከጠላት እንዲጠብቁት ይደረግ ነበር። አሁን ግን ሁሉም የተገላቢጦሽ ሲሆን እያየን ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በእድራችን አሰራር እና አመራር ለውጥ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በለውጥ ማግስት በለውጥ አምጭዎች መከካል መከፋፈል እና ግጭት እንደሚኖር በለውጥ ወስጥ ካለፉ አገራት ታሪኮች ተምረናል፡፡ ለውጥን በተወሰኑ ሃይሎች ጥምረት ማምጣቱ የሚከብድ አደይደለም፡፡ ችግሩ በለውጡ ማግስት ያለውን የለውጥ ሂደት ለውጡ ከተያዘለት ግብ እና አላማ አኳያ በትክክለኛው ጎዳና ማስቀጠል መቻል ነው ፡፡
በእኛ ሰፈር እና እድር ውስጥም የገጠመን ችግር ይኸው ነው፡፡ ለውጡን ለማምጣት ከከፈልነው ዋጋ በላይ ለውጡን ለማስቀጠል እየከፈልነው ያለው ዋጋ እጅጉን ከባድ ሆኖብናል፡፡ በፈረንሳይ፣ በራሺያ፣ በቻይና ወዘተ አገራት የተካሄዱትን አብዮቶች ተከትሎ የአገዛዝ ለውጥ ባደረጉ ማግስት አገራቱ ከፍተኛ ችግር ማሳለፋቸው የሚታወቅ ነው። በአሜሪካ የነጻነት ትግል ታሪክ ውስጥ የታየውም ተመሳሳይ ነው።
አሜሪካ ነጻነቷን ለማግኘት ተዋድቃ ነጻነቷን ከተቀናጀች በኋላ ለአሜሪካ ነጻነት ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ሃይሎች ከነጻነት እና ከለውጥ በኋላ አገሪቱ ያገኘችውን ነጻነት እና የፖለቲካል ኢኮኖሚ አካሄድ ለውጥ ማስቀጠል ተስኗቸው ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ጦርነት ማካሄዳቸውን የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡
በራሽያ የሮማኖቭ ሥርወ-መንግስትን በመገርሰስ ራሽያን ለለውጥ ካበቁ ቡድኖች መካከል የራሽያ ሶሻል ዴሞክራሰቲክ ፓርቲ አንዱ ነበር፡፡ ይህ ፓርቲ ከለውጡ በኋላ ለውጡን በተፈለገው ልክ ማስቀጠል ተስኖት ቦልሼቪክ እና ሜንሼቪክ ተብሎ ለሁለት ተሰንጥቆ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ቦልሼቪኮች ለለውጡ ምክንያት የሆኑ መነሻዎችን ዘንግተዋል ፤ ለላባደሩ እና ለአርሶ አደሩ መወገን ሲገባቸው ለቡርዣው በመወገን ለውጡን ሊያደናቅፉት ነው ሲሉ ሜንሼቪኮችን ይከሱ ነበር፡፡
ሜንሼቪኮችም አርሶ አደሩን እና ወዛደሩን እንደ ለውጥ መዘወሪያ ሃይል መጠቀም ከአብዮቱ በፊት አንግበን የተነሳንለትን አላማ ለማሳካት የሚያስችል አይደለም በማለት ቦልሼቪኮችን ይከሱ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ቦልሼቪኮች ሜንሼቪኮችን የለውጡ ደንቀራ አድርገው ለህዝብ አሳዩ፡፡ ሜንሼቪኮችም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አጡ፡፡ ቦልሼቪኮችም መሄድ ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ተጉዘው ራሽያን ሊዚህ ክብር አበቁ፡፡
ከራሽያ እና ከላይ ከተጠቀሱ አገራት ተሞክሮ እንደተረዳነው ከለውጥ ማግስት በለውጥ አምጭዎች መካከል አለመግባባት እንደሚፈጠር እና አለመግባባቱም ወደ ውይይት አምርቶ የአገራቱ የወደ ፊት እጣ ፈንታ መወሰን ያስቻሉ መሰረቶች የተገነቡበት መሆኑን ነው፡፡
በእኛ እድር እና ሰፈር የገጠመን ይሄው በለውጥ ማግስት እርስ በእርስ መካሰስ የሚሉት የፖለቲካ በሽታ ነው፡፡ ግን በእኛ አገር የትኛው ቦልሼቪክ የትኛው ሜንሼቪክ መሆኑን መረዳት አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም የእኛን አገር ለውጥ ለየት የሚያደርገው ለውጡን ማስቀጠል የተሳናቸው ሃይሎች ጥረት የሚያደርጉት በአስተሳሰብ እና በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይሆን በክልል፣ በጎሳ እና በማንነት ውስጥ እየተደበቁ እድራችን እና ሰፈራችንን እየበጠበጡ ነው። ይህ በጎሳ እና በማንነት የተነሳ ብጥብጥ በጊዜ ማስቆም ካልተቻለ አገሪቱን ወደ መጥፎ አዙሪት ውስጥ እንደሚከታት እሙን ነው፡፡
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጠለ…….የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የተሳነው አንድ የሰፈር መሪ ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ምክንያት ህዝብ እንዳይጠይቀው በመፍራት አጀንዳ ለመፍጠር ሲል አጎራባች ሰፈር አስተዳደሮችን እንደሜንሴቪኮች የለውጥ ጋሬጣ ናቸው ብሎ በሃሰት ይከሳል፡፡ ራሱንም እንደቦልሼቪክ የለውጥ ሃዋሪያ አድርጎ ይስላል፡፡ ራሱን እንደቦልሼቪክ ያደረገው አስተዳዳሪ እሱ የሚያስተዳድረው ጎሳ በደል እንደተፈጸመበት ያስመስላል፡፡ የውሸት አጀንዳ የተፈጠረለት ጎሳም የሰፈሩ መሪው ያለው እውነት መስሎት መሪውን ተከትሎ ወደ ጥፋት ጎዳናው ዘው ብሎ ይገባል፡፡ ይህን አሁን ላይ በእኛ ሰፈር በብዛት የሚስተዋል የፖለቲከ ጉንፋን ነው፡፡ ሲል ሁሉም በዋርካው ስር የተሰበሰበው ሰው ጭብጨባውን አቀለጠው ፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች አቅም አልባ ሆነው ገዥውን ፓርቲ በሃሳብም ሆነ በሁለንተናዊ መልኩ መፎካከር ስላቃታቸው የክልል ገዥ ፓርቲዎች እርስ በእርስ እየተፎካከሩ እና እየተነቋቆሩ አንዱ በአንዱ ላይ መግለጫ እያወጡ እያየን ነው፡፡ ህዝብን እያተራመሱ መፎካከር ምን አይነት የለውጥ ወቅት ፖለቲካ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም፡፡
የክልሎች ፉክክርን ስመለከት ማን ነው የምዕራባዊን ተላላኪ? ጋሼ ጃልመሮ ወይስ አይተ ጭሬ ልድፋው? ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው እና አገሪቱን ወደ እንጦሮጦስ ለመክተት እየሰራ ያለው የምዕራባዊያን ተላላኪ በእድራችን አስተዳደር ውስጥ ትልልቅ ስልጣን ያላቸው አካላትም ሊሆኑ እንደሚችሉ የሰፈራችን እና የእድራችን አባላት እየታዘቡት ያለ ሃቅ ነው፡፡
ክልሎች በሚያደርጉት አገር አፍራሽ ፉክክር እና በሚያወጡት መግለጫ ላይ ከአሁኑ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ምዕራባዊን ባጠመዱት የክፋት ወጥመድ መግባታችን አይቀሬ ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል መሆኑን ከዚህ በፊት የተናገርኩትን አንድ ምሳሌ ተጠቅሜ ላስረዳ ብሎ ንግግሩን በድጋሚ ቀጠለ ……
በድሮ ጊዜ ከእኔ ዝርያ ውጭ ጎበዝ፣ ጀግና እና ሁሉን ማድረግ የሚችል የለም የሚል የሚታበይ አንድ ንጉስ ነበር፡፡ ከባለቤቱም አንድ ሴት ልጅ ብቻ ይወልዳል፡፡ ንጉሱ እና ንግስቲቱም ልጃቸው አድጋ እስከሚድሯት እና እሯሷን እስከምትተካ ያለውን ጊዜ በጉጉት ይጠብቁ ነበር፡፡ ከጠሩት ውሻ የቀጠሩት ቀን ቀድሞ ይደርሳል እንዲሉ፤ ልጃቸውን ለማደር ሲጠባበቁ የነበሩ ወላጆች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ቀን ደረሰላቸው፡፡ ሙሽሪት የንጉስ ልጅ አይደለች፤ በአገሪቱ አለ የተባለ የንጉስ ልጅ ተፈልጎ ተዳረች፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው ! የሙሽሪት ጥጋብ « ሰማይን በእርግጫ! » ሆኖ ያገባቸውን ልጅ በሰርጋቸው ማግስት ፈታችው፡፡
እናት እና አባት የመጀመሪያ ባሏን ብትፈታም ልጅ አንድትወልድላቸው ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ሁለተኛ ባል አጋቧት፡፡ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም እንዲሉ፤ አሁንም ሙሽሪት ባሏን ደብድባ በሰርጓ በበነጋታው ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ አምስት ጊዜ አገባች፡፡ አምስቱንም ባሎች ከሰርጓ በበነጋታው እየጣላቻቸው መጣች፡፡ በዚህም የሙሽሪት እናት እና አባት ክፉኛ አዝነው እሳት እንደገባ ጅማት እርር ድብን ብለው ተቀመጡ፡፡ ራሷን ተክታ ዘራችንን ታበዛልናለች ብለው ተስፋ የጣሉባት አንዲት ልጃቸው በጋለ ብረት ምጣድ ላይ እንደተቀመጠ ቅቤ የቤተሰቦቿን ተስፋ ከንቱ አደረገችው፡፡
በዚህም እናት እና አባት ክፉኛ አዝነው እየኖሩ ሳለ አንድ ገበሬ ልጅ «ልጃችሁን ስጡኝ?» ሲል ንጉሱን ጠየቀ፡፡ ንጉሱም ልጄን ለገበሬ ልጅ አልድርም አላሉም፡፡ ይልቁንም ልጃቸው ለሚስትነት የማትበቃ፣ ስንት የተከበሩ የነገስታት ልጆችን እንኳን አላገባም ብላ ያስቸገረች ለሱ ለገበሬው እንደማትገዛለት እንጂ ልጃቸው አግብታ ብትወልድ እንደሚደሰቱ ይንገሩታል፡፡ ገበሬውም እርስዎ ይፍቀዱልኝ እንጂ እርሷን ለማስተካከል ሌላውን ነገር ለእኔ ተውት ሲል ለንጉሱ ተናገረ፡፡ ንጉሱም አንተ ቻል እና አስተካክላት እንጂ እኔማ ልጄ አግብታ ወልዳ ባያት ምንኛ ደስተኛ በሆንኩ ሲሉ ለገበሬው ልጅ ይነግሩታል፡፡
የገበሬው ልጅም ልጅዎትን ለማጨት ስመጣ በማደርገው ነገር ቅር እንዳይሰኙብኝ፡፡ የማደርገው ነገር በሙሉ እርሷን ወደ መስመር ለማስገባት መሆኑን ይወቁልኝ ይላቸዋል፡፡ ንጉሱም ብቻ ልጄ አግብታ ልጅ ለመውለድ ትብቃልኝ እንጂ የፈለገውን ብታደርግ አልቀየምም ይሉታል፡፡
ባልም ልጅቷን ለማጨት ሲመጣ ጓደኞቹን በግ እያስጎተተ መጣ፡፡ የጋብቻው ውል ከተጻፈ በኋላ ባል ያመጣው በግ ሊታረድ በቀረበ ጊዜ በግ እያሰቡ የመጡ ጓደኞቹን ያለምንም በቂ ምክንያት አንገታቸውን እቆርጣለሁ ብሎ በስንት መከራ ተገላገለ፡፡ የተናደደ በመምሰልም ሊታረድ የቀረበውን የበግ አንገት በጎራዴ ቀላው፡፡ የታጨችው ሙሽሪትም ያጫትን ሙሽራ ኃይለኝነት በተመለከተች ጊዜ ደነገጠች፡፡
ሰርጋቸውም ደረሰ፡፡ የሰርጉ እለትም ሙሽሪት እያያች ሰዎችን በጎራዴ ካልቆረጥኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል ያዘ፡፡ ይሄን የተመለከተችው ሙሽሪትም በፍርሃት መግቢያ ቀዳዳው ይጠፋታል፡፡ ወዲያውኑም ለሙሽሪት እና ለሙሽራው ምግብ ይቀርብላቸዋል፡፡ ምግቡ በቀረበ ጊዜም ሙሽራው ጎራዴውን ከሰገቡ ወጣ፤ ገባ እያደረገ በጣም እያጮኸ ሙሽሪትን አጉርሽን ሲል አዘዛት፡፡ በባሏ ሃይለኛነት በፍርሃት ቆፈን የተዘፈቀችው ሙሽሪትም ሰው ምን ይለኛል ሳትል ባሏን እስኪበቃው ድረስ እንደህጻን ልጅ አጎረሰችው፡፡
በማግስቱ ለምላሽ ወደ አባቷ ቤት በተመለሱ ጊዜም ምግብ ይቀርብላቸዋል፡፡ ሙሽሪት ፍጹም ተረጋግታለች፡፡ እናት አባቷ ቤትም ምግብ እንደቀረበላቸውም ሙሽሪትን አጉርሽኝ ብሎ አዘዛት፡፡ ሙሽሪትም ከዚህ ቀደም ያገባቻቸውን ባሎቿን እንደማትማታ ሁሉ ዛሬ ላይ ግን ባሏ ያዘዛትን ትእዛዝ ትፈፅም ገባች፡፡ ይህን የተመለከቱ አባት እባክህ ልጄ እንዴት አድርግህ ነው ያስተካከልካት? ሚስቴ እኔን በጣም እያስቸገረችኝ ነው፡፡ ዘዴውን አሳውቀኝ ? ይሉታል፡፡
የልጅ ባልም ንጉሱን እርጥብ እና ደረቅ የሆኑ ሁለት ጠማማ እንጨቶች እንዲያመጡ ያዝዛቸዋል፡፡ ንጉሱም የተባሉትን ሁለት ጠማማ እንጨቶች አመጡ፡፡ የልጅ ባልም ንጉሱ ያመጧቸውን ጠማማ እንጨቶች እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ትንሽ አቆይቶም ከእሳት ውስጥ አወጣቸው፡፡ መጀመሪያ እርጥቡን ጠማማ እንጨት ለማቃናት ሞከረ፡፡ ተቃና፡፡ ቀጥሎም ደረቁን ሊያቃና ሞከረ፡፡ ደረቁ ግን ተሰበረ፡፡ በዚህ ጊዜ የልጅ ባል ለአባትየው እኔ ያገባዋት ልጅ ገና እርጥብ ልጅ ናት ወይም ለጋ ስለነበረች ተቃናች፡፡ የእርስዎ ግን እድሜአቸው የገፋ እና ችግራቸው ለእርጅም ጊዜ አብሯቸው የኖረ ለማቃናት ቢሞክሩ እንደ ደረቁ እንጨት ይሰበራሉ፡፡ ሁሉም ነገር በለጋነቱ ነው መስተካከል የሚችለው ሲል መለሰላቸው፡፡ በማለት ይልቃል አዲሴ ደጋግሞ የሚናገረውን ተረት እንደለመደው ለተሰበሰበው ሰው ተናገረ፡፡ እባካችሁ ደጋግሜ አንድን ነገር የምናገረው ወድጄ አይደለም በደንብ አስቡበት ብሎ በድጋሚ ንግግሩን ቀጠለ፡፡
ይህን እንድል ያስገደደኝ ዋናው ምክንያት ችግሮችን በጊዜአቸው መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ችግርን እያለባበሱ መሄዱ አዋጭ አይደለም፡፡ ችግርን እያለባበሱ መሄድ የሚለውን ስናገር አንድ ነገር አስተዋሰኝ፡፡ ብሎ አሁንም አቶ ይልቃል ቀጠለ..ከሰሞኑ ለፋሲካ ዶሮ ልገዛ ወደ ገበያ በወጣሁበት ቀን አንድ ሰው አሞራ ሊሸጥ ወደ ገበያ ማምጣቱን ተመለከትኩ፡፡ አሞራ ገበያ ወጥቶ ለፋሲካ የሚሸጠው ከመቼ ወዲህ ነው? ስል ጠየኩ፡፡ ሰውየውም ምን ቢል ጥሩ ነው፤ የግድ ዶሮ ካልሆነ ተብሎ ፋሲካን ስጋ ሳይበሉ አይዋል፡፡ ስለዚህ ዶሮ ከሌለ አሞራን አርዶ መብላት እንደሚገባ ለማስገንዘብ ነው፡፡ ቻይናውያን ለዚህ ደረጃ ያበቃቸውም ሳይመርጡ መብላታቸው ነው ብሎኝ አረፈው፡፡ አለ አቶ ይልቃል፡፡
ለውጥ ማለት አንዱን ያለምክንያት እያፈናቀሉ አንዱን ምክንያት ፈልገው የህዝብን መሬት እንዲወር እየገፋፉ መምራት ከሆነ ያጠያይቃል ብሎ በአሽሙር ሲናገር የተሰበሰበው ሰው ንግግሩን በጭበጨባ አቋረጠው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ንግግር ለሚቀጥለው ሳምንት ይዘን እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ቸር እንሰንብት !
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014