የአውሮፓ ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች የሚፋለሙበት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በአዲስ አበባ የነበረውን የአንድ ቀን ቆይታ አጠናቆ ወደ ቀጣይ መዳረሻው አምርቷል:: በመላው ዓለም በሚገኙ 31 አገራት እየተዘዋወረ በደጋፊዎች ሲጎበኝ ቆይቷል፤ ዋንጫው በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባም ሰሞኑን ተገኝቷል::
ከዋንጫው ጎን ለጎን በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ከሶስት የተለያዩ ክለቦች ጋር አራት (ከአያክስ እና ሪያል ማድሪድ አንድ አንድ እንዲሁም ከኤሲሚላን ጋር ሁለት) ዋንጫዎችን በማንሳት ስሙን በስኬት መዝገብ ያጻፈው የቀድሞ ተጫዋችና አሰልጣኝ ክላረንስ ሴዶርፍ ከዋንጫው ጋር በአዲስ አበባ ተከስቷል፤ተጨዋቹ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረትም በእግር ኳስ ሕይወቱ የተገነዘበውንና ያገኘውን ልምድ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጠቁሟል::
ሆላንዳዊው ተጫዋች ለበርካታ ጊዜያት ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወር ኢትዮጵያን እንደመሸጋገሪያ ሆና እንደሚያውቃት ተናግሯል፤ አሁን ደግሞ አገሪቱን በአካል ለመጐብኘት በመብቃቱ የተሰማውን ደስታ አስታውቋል::
እግር ኳስንም ሆነ በየትኛውም ዘርፍ ሌሎችን ከመመልከት ይልቅ ራስን መሆንና በራስ መንገድ ለስኬታማነት ለመብቃት መጣር አስፈላጊ መሆኑን የተናገረው ተጫዋቹ፣ ሁሉም አገር የራሱ ባህልና ልምድ እንዳለው ሁሉ ክለቦችም የየራሳቸው መለያ እንዳላቸው ያመለክታል፤ እርሱ በጣሊያኖቹ ተቀናቃኝ ክለቦች ኢንተርሚላን እና ኤሲሚላን ክለቦች የተጫወተ ቢሆንም ሊያነጻጽራቸው እንደማይችል ግን ይጠቁማል:: በመሆኑም በራስ መንገድ ጥረት በማድረግ ስኬታማነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ነው አጽንኦት ሰጥቶ የገለጸው::
22 ዓመታትን በስድስት የሆላንድ፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና የብራዚል ክለቦች ተዘዋውሮ በመጫወትና በሆላንድ ብሔራዊ ቡድንም ይታወቃል:: በአንድ ወቅትም ከዓለም ስመጥር የመሐል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እና ከሻምፒዮንስ ሊጉ ምርጥ 20 ተጫዋቾች መካከል የነበረው ሴዶርፍ፤ በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ለመጫወት ለሚሹ ወጣቶች መልዕክት አስተላልፏል::
በስፖርቱ ከፍተኛ ሕልም ያላቸው ወጣቶች ግባቸውን ለማሳካት እስከሚችሉ ማለማቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ነው ያሳሰበው:: ይህም ብቻ ሳይሆን ከታላላቆቻቸው ድጋፍን መጠየቅና በሕይወታቸው ከሚገጥማቸው ልምድ መማር እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል:: ህልምን እንደ መኖር መልካም ነገር የለምና ወጣቶች አላስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች በመራቅ ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ጠንክረው መሥራት አለባቸው ሲል አሳስቧል::
የተጫዋቹንና የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ መልዕክት አስተላልፈዋል:: በንግግራቸውም ሃይንከን የቻምፒዮንስ ሊጉ ስፖንሰር መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም የአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ጠንካራ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: እንደማሳያም በአራት ዓመት ውስጥ 56ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን ስፖንሰር ማድረጉን ጠቅሰዋል:: አሁንም ታች ወርዶ በተለይ በታዳጊዎች ላይ በሚሠራበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረው፣ ተቋሙ ከፌዴሬሽኑ ጋር በሚሠራው በዚህ ሥራም ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይገባዋል::
የተጫዋቹን መምጣት ተከትሎ ከተያዘው መርሐ ግብር መካከል አንዱ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር በመሆን መጫወት ነበር:: ፕሬዚዳንቱ፤ እግር ኳስ መጫወትን ራዕያቸው ያደረጉ ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ እንደ ክላረንስ ሲዶርፍ ካሉ ተጫዋቾች ጋር ሲገናኙ እንዲሁም ለጥቂት ደቂቃዎች አብረው የመጫወት ዕድል ሲያገኙ ተስፋን ይጭርባቸዋል ይላሉ:: በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ እነ ኃይሌ እና ደራርቱን የመሳሰሉ አትሌቶችን እያዩ ሌሎች እንደወጡት ሁሉ ምሳሌ የሚሆናቸው ሰው መሆኑንም በመጥቀስ፣ በየዓመቱ ተቋሙ ለሚያደርገው ለዚህ ተግባሩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስም አመስግነዋል::
አቶ ኢሳያስ የአፍሪካ ዋንጫ እንደ ሻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ ሁሉ በመላው ዓለም የሚታይበትን ጊዜ እንደሚናፍቁም ጠቁመዋል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ አፍሪካውያን ጠንክረን መሥራት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ኮከብ ለማየት ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ነው የጠቆሙት::
ሃይንከን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ስኬታማ የሆኑ ተጫዋቾችን እንደ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጠቢብ ሮናልዲኒሆ ጎቾ እንዲሁም ፈረንሳዊውን የቀድሞ ተጫዋች ክላውድ ማካሌሌን ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ከአድናቂዎቻቸው ጋር ማገናኘቱ ይታወሳል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014