እችላለሁ ብሎ ራስን እንደማሳመን ያሰቡት ግብ ላይ የሚያደርስና ለስኬት የሚያበቃ ምስጢር እንደሌለ ብዙዎች ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ሲናገሩ ይደመጣል። አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደሚለው “እችላለሁ!” ብሎ የተነሳ ማንኛውም ሰው ከሰማይ በታች ያቀደውን ከማሳካት ወደ ኋላ ሲል አልታየም። በዕቅዱም ቢሆን አፍሮ አያውቅም። ይሁን እንጂ አንዳንድ፣ እንደውም ብዙ የሚሰኙ ሴቶች “እችላለሁ” የሚል ቁርጠኝነት የላቸውም። ቢኖራቸውም በራሳቸውም ሆነ በማኅበረሰቡ አማካኝነት የተፈጠረ ተፅዕኖ ወደ ውስጣቸው ዘልቆ በመግባቱ በራስ መተማመናቸውን ሸርሽሮ ለስኬት እንዳይበቁ ያደርጋቸዋል። ቢበቁም ስኬታቸው ያሰቡበት ድረስ አስጉዞ ለግብ ሲያበቃቸው አይታይም።
እናም ‹‹የት ይደርሳል የተባለን ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው›› እንደሚሉት ዓይነት መንደርኛ አባባል በአገራችን በየሙያ መስኩ ወይም በየጥሪና ተሰጧቸው ብዙ “የት ይደርሳሉ” ተብለው ይጠበቁ የነበሩ ሴቶች በአጭሩ ሲቀጩና የት እንዳሉ ለማወቅ እንኳን በማያስችል መልኩ ደብዛቸው ሲጠፋ ይስተዋላል። የዛሬ የአምዱ እንግዳችንና ‹‹የባከነው ጊዜ›› ልብ ወለድ መጽሐፍ ደራሲዋ መጠነወርቅ ሳሙኤል ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ ላለመሆን የባከነ ጊዜያቸውን በማካካስ ሲጥሩ የነበሩ በመሆናቸው ተሞክሯቸው ለሌሎች ሴቶች ያስተምራል የሚል እምነት አለ። በተለይ ሴት ደራሲ ቀርቶ ብዙ ፊደል የቆጠሩ ሴቶች በአገራችን ባልነበሩበት በ1965 ዓ.ም ‹‹የባከነው ጊዜ›› የሚለውን የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን ለማሳተምና ለሌሎች ሴቶች አርአያ ለመሆን መብቃታቸው እጅጉን ይደነቃል።
(መጽሐፉ (ባጭሩ) በአንድ ጣራ ስር ተጋብተው ወልደው ከብደው ለመኖር ውጥን በነበራቸው ሁለት ፍቅረኛሞች ታሪክ ላይ ያጠነጥናል። በመጽሐፉ ታሪክ ወጣቶቹ ጥንዶች ይሄን ውጥናቸውን ከስኬት ለማድረስም ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። በዚህ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይባክናል። ይሄን ጊዜ ለማካካስ የራስ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ያመላክታል። በአጠቃላይ መጽሐፉ ቸኩሎ ወደ ፍቅር ሕይወት መግባትም ሆነ፤ ለረጅም ጊዜ በፍቅር ጓደኝነት መቆየት የየራሱ ጥቅምና ጉዳት ያለው መሆኑን በሚገባ ያስገነዝባል። የባከነውን ጊዜ ማካካሱ ለጉዳቱ ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም ይጠቁማል።)
ደራሲ መጠነወርቅ ሳሙኤል ዛሬ በ71 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ ሆነውም ያኔ ያልተቋጨውንና የሁለቱን ወጣቶች የፍቅር ታሪክ ያካተተ ሁለተኛ ክፍል መጽሐፍ ጽፈው ለማሳተም መንገድ ላይ መሆናቸው፣ የሌሎች ድጋፍን መሻቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ የሚበረታታና ሌሎች ሴቶችን የሚያነሳሳ ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም ሥራዎቻቸውን፣ ልምድና ተሞክሯቸውን ለአንባቢያን እነሆ ማለትን ወ’ደናል።
ደራሲ መጠነወርቅ ሳሙኤል በ1943 ዓ.ም ዱከም ከተማ ነው የተወለዱት። የተወለዱበት አካባቢ ልዩ ስሙ ዝቋላ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ይሰኛል። አባታቸው የዚሁ የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የቆሎ ተማሪ በመሆን ከድቁና እስከ ቅስና የዘለቀ የክህነት እውቀትና ሙያ የቀሰሙ ነበሩ። መነሻቸውን ወሎ አድርገው ከክፍለ አገር ክፍለ አገር እየተዘዋወሩ የቆሎ ትምህርት በሚቀስሙበት አጋጣሚ ከእናታቸው ጋር ትዳር መስርተው የወለዷቸው ወላጅ አባታቸው ለትምህርት ልዩ ፍቅር ነበራቸው። በተለይም ባህላዊ፤ ከባህላዊም የቄስ ትምህርት ለዘመናዊ ትምህርት ጥሩ መሠረት ጥሎ እንደሚያልፍ የሚያምኑ ነበሩ። በመሆኑም ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዛው የተወለዱበት ዱከም ከተማ ውስጥ ቄስ ትምህርት ቤት እንዳስገቧቸውና ፊደል እንዳስቆጠሯቸውም አጫውተውናል። ቶሎ ማንበብና መጻፍ ከማስቻል ጀምሮ ለዘመናዊ ትምህርት ጥሩ መደላድል በፈጠረላቸው የቄስ ትምህርት እስከ ዳዊት መድገም በመዝለቅ ዕውቀት ቀስመውበታል።
በወላጅ አባታቸው የሥራ ፀባይ ምክንያት ከናዝሬት ዱከም፤ ከዱከም አዲስ አበባ ከተማ መዘዋወርና ትምህርታቸውን መማር ግድ የሆነባቸው ደራሲ መጠነወርቅ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እንደሆነም አጫውተውናል። በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በፅዳትነት ተቀጥረው ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወላጅ አባታቸው እሳቸውን ዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳስገቧቸውም ነግረውናል።
‹‹ይህ ትምህርት ቤት በቄስ ተማሪነቴ የቀሰምኩት ትምህርት ብቁ እንዳደረገኝና መሠረት እንደጣለልኝ ያየሁበት ነው›› የሚሉት ደራሲዋ፣ በተለይ አንደኛና ሁለተኛ ክፍል ሆነው በክፍል ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን በፍጥነት ጽሑፍ የማጻፍና የማስነበብ ተግባር ማከናወናቸው አስደናቂ ክሂሎት አስጨብጧቸው የነበረ መሆኑንም ያስታውሳሉ። ‹‹ክፍል ውስጥ ሰርክ አርብ አርብ በነበረው የንባብ መርሐ ግብር ተማሪዎችን በማስነበብና በማጻፍ ወደር ያልተገኘልኝ ተማሪ እንድሆን ረድቶኛል›› ሲሉም ዕውቀት ያስጨበጣቸውን የቄስ ትምህርት ይመሰክሩለታል። በ1965 ዓ.ም ‹‹የባከነው ጊዜ››ን እንዲጽፉ መሠረት የጣለላቸው ይሄው የቄስ ትምህርት መሆኑንም በኩራት ይጠቅሳሉ።
‹‹ማትሪክ ብቻ ሳይሆን የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም የሠራለትን አያውቅም›› የሚሉት ደራሲዋ በዘመናዊው ትምህርት እስከ ስምንተኛ ክፍል ዘልቀው የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ሳያልፉና ሁለተኛ ደረጃ የሚያስገባ ነጥብ ለማምጣት ሳይችሉ መቅረታቸውንም በቅሬታ ይገልፁታል። ራሳቸውን በትምህርት እያሻሻሉ መጥተው ከጽዳት እስከ ሂሳብ ሹምነት በመዝለቅ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በሂሳብ ሰራተኛነት የሚሰሩት የቆሎ ተማሪው አባታቸው ፈተናውን ደግመው በመውሰድ ያሰቡበት የሚደርሱበት ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ደጋግመው ቢመክሯቸውም መጠነወርቅ በጄ አላሉም። ከጓደኞቻቸው መለየታቸው ስለቆጫቸው ፈተናውን ደግመው መውሰድ ጊዜያቸውን ማባከን ሁሉ አድርገውት ነበር። በመሆኑም በኋላ ላይ እጅግ የጓጉለትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል በመዝለቅ ለማጠናቀቅ ቢበቁም የባከነ ጊዜቸውን በአቋራጭ በመቅደም ከአሰቡት ለመድረስ ወደ ሙያው ትምህርት ማዘንበልን መረጡ።
መጠነወርቅ “ብርሃነ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ትምህርት ቤት በመግባትም በፀሐፊነትና በአካውንቲንግ ሙያ በመሰልጠን ከ10ኛ ክፍል ተመረቁ። የቀድሞው ንግድ ሥራ ኮሌጅ በመቀጠርም በጽሕፈት ሙያ (ሴክሬተሪነት) የሥራ ላይ ስልጠና ወሰዱ። ከዚሁ ጋርም በሂሳብ ሥራ መሥራት የሚያስችላቸውን ዕውቀትም አካተው ቀሰሙና በ1961 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ ዓለም ለመሰማራት በቁ። ወደ እዚህ ውሳኔ ለማምራታቸው ያኔ የነበሩበት የእሳቸውና የፍቅረኛቸው ሁኔታ አስተዋጽዖ ተፅዕኖም አርጎባቸው እንደነበረም አልሸሸጉንም ደራሲዋ። እንዳወጉን አንዳቸው ለአንዳቸው መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው እዚህ የደረሱት። መስዋዕትነቱ ትምህርት አቋርጦ ወደ ሥራ ዓለም በመግባት በትዳር ተጠቃልሎ እስከ መኖር ታሳቢ ያደረገ እንደነበርም ነግረውናል። በተለይ ባለቤታቸው 12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባት ይልቅ በሥራ ተሰማርቶ ከእሳቸው ጋር ትዳር መስርቶ እስከ መኖር የዘለቀ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ይናገራሉ። ከዚህም ጥቂቱን ለመጻፋቸው እንደማጣፈጫ መጠቀማቸውንም ገልጸውልናል።
አንጋፋ ደራሲዋ በዋነኝነት መጽሐፉን ለመጻፍ ያነሳሳቸው ፈጣንና ጥልቅ አንባቢ ለመሆን መሠረት የጣለላቸው በአባታቸው ምርጫ የቀሰሙት የቄስ ትምህርት እንደ ነበር ደጋግመው አጫውተውናል። በዚህ አነሳሸነት በተለይ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በጸሐፊነት ተቀጥረው በሚሠሩበት ወቅት ጥሩ መጽሐፍ አንባቢ ለመሆን መብቃታቸው እንደሆነም ሳይጠቅሱልን አላለፉም ደራሲዋ። ወደ ኋላ ታሪካቸው መለስ ብለው ስለ ድርሰት ፍቅር ተስጥኦዋቸው እንዳጫወቱን አብዛኛውን ደሞዛቸውን መጻሕፍት ለመግዛት ነበር የሚያውሉት። አዳዲስ መጽሐፍ በወጣ ቁጥር ቢሯቸው ድረስ ይዘውላቸው ከች የሚሉ ደንበኞችም ነበሯቸው።
ደራሲ መጠነወርቅ ‹‹የባከነው ጊዜ›› የሚል ርዕስ የሰጠሁትን ረጅም ልቦለድ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ነው›› ሲሉም ነው ያጫወቱን። በወቅቱም እጅግ ተወዳጅነትን አትርፎ እንደ ነበር፤ ገበያ ላይ ውሎም በገፍ ለመሸጥ መብቃቱን ገልፀውልናል።
ደራሲ መጠነወርቅ እንደሚሉት ከ‹‹የባከነው ጊዜ›› በኋላ ከድርሰት ዓለም ለረጅም ጊዜ ተለዩ። ይህም በአንባቢና አድናቂዎቻቸው ዘንድ መዘንጋትን አስከተለ። ይህንን ክፍተት በመጠቀምና እንደ እሳቸው መጽሐፍ ተወዳጅ ይሆንልኛል በማለት አንዲት ሴት ‹‹የባከነ ጊዜ›› የሚል የእሳቸውን ርዕስ በመስጠት መጻፍ በማውጣት አሳትማ እንደ ነበር በአግራሞት ይናገራሉ።
በወቅቱ በጥንዶች ፍቅር፣ ታሪክና ሕይወት ላይ የሚያተኩረው የረጅም ልቦለድ መጽሐፋቸው ለእሳቸውም ትልቅ ከበሬታ፣ አድናቆትና ተወዳጅነትን አስገኝቶላቸው አልፏል። በአንባቢያኑ ዘንድ “ሌሎች ረጃጅም የልቦለድ መጻሕፍቶችን ይዛ ትመጣለች” በሚል ተስፋ ሲያስጠብቃቸውም ቆይቷል። ደራሲና ገጣሚ የዝና ወርቁ የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፏን በዚህ መጽሐፍ ላይ ነው የሠራችው። ሆኖም ብዙዎቻችን እንኳን ሌሎች የደራሲዋን የረጅም ልቦለድ መጻሕፍቶች ልናይና ልናነብ እንዲህ አይነት፣ ከጊዜው የቀደመች እንስት ስለመኖሯም ሳናውቅ ቆይተናል።
ደራሲ መጠነወርቅ ሳሙኤል እንደሚሉት ሌሎች መጻሕፍቶችን ለሕትመት ያለማብቃታቸውና ደብዛቸው የመጥፋቱ ምክንያት ፈርጀ ብዙ ቢሆንም፤ ‹‹የባከነው ጊዜ›› የተሰኘውንና ታሪኩ ያልተቋጨውን መጽሐፋቸውን ተከታይ ክፍልና ሌሎች ሥራዎቻቸውን ይዘው ብቅ የማለት ውጥን እንደነበራቸው ያወሳሉ። ነገር ግን የቢሮ ሥራ ጫና፣ ትዳር መያዝ፣ ልጆች መውለድና የቤተሰብ ኃላፊነቶችን መሸከም እንዲሁም በነዚህ መካከል የሚገጥሙ መሰናክሎች ምክንያት ውጥናቸው ከግብ ለመድረስ ሳይችል ቀርቶ መኖሩንም አብራርተውልናል። ለዚህ ውጥናቸው መሰናከል ዋንኛ ምክንያት ነው የሚሉት ይህንን ሁሉ ተቋቁመው በቁርጠኝነት አለመነሳታቸውን ሲሆን፤ ሌሎች ለእንደዚህ አይነቱ ችግር እጅ እንዳይሰጡም ይመክራሉ።
‹‹ምንም እንኳን እኔ የሁለተኛ ደረጃ መግቢያ ፈተና ወስጄ ውጤት ሳይመጣልኝ በመቅረቱ ወደ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ፊቴን በማዞር ለማካካስ ብሞክርም የመጀመሪያው ተከታይ የሆነውን መጽሐፌንም ሆነ ሌሎች ልጽፋቸው የሚገቡ መጻሕፍትን ሳልጽፍ መቅረቴ እችላለሁ ብዬ ያለመነሳቴ ድክመት ውጤት እንደሆነ አስባለሁ›› ብለውናል ደራሲዋ። ይሄ ዓይነቱ ድክመት በሌሎች የእሳቸው መሰል ተሰጥኦ ባላቸውም ሆነ በሌሎች ሴቶች መደገም እንደሌለበትም ደጋግመው ያስጠነቅቃሉ።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሴቶች ያሰቡትን ዳር ለማድረስና ለስኬት ለመብቃት ‹‹እችላለሁ›› የሚለውን መንፈስ በውስጣቸው ማዳበር እንደሚገባቸው በቴሌቪዥን መስኮት ደጋግመው ሲናገሩ መስማታቸውንና ይሄም የራሳቸውን ክፍተት እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ደራሲ መጠነወርቅ ይናገራሉ። ‹‹ሰው ከስኬት ብቻ ሳይሆን ከውድቀትም ይማራል›› ሲሉም ከእሳቸው ስኬት ብቻ ሳይሆን ድክመትም ተነስተው ሌሎች ሴቶች የ‹‹ይቻላል›› መንፈስን በውስጣቸው በማዳበር ለስኬት የሚያበቃቸውን ምክር በመለገስ ያካፈሉንን ሀሳብ ቋጭተውልናል። እኛም ቀጣይ በሌላ ጽሑፍ ለመገናኘት ፈጣሪ የሳምንት ሰው ይበለን በማለት ለዛሬው ያዘጋጀነውን በዚሁ ቋጨን። ቸር እንሰንብት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014