በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ፣ የመንግሥትንም ጨምሮ፣ በአጠቃላይ 1ሺህ 522 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ንብረትነታቸው ይለያይ እንጂ እነዚህ ሁሉ ለአንድ አላማ የሚሰሩ ናቸውና ከትምህርት ጥራት አኳያ መለኪያቸው፣ መስፈሪያ ሚዛናቸው አንድ ነው (ወይም፣ መሆን ይጠበቅበታል)። በመሆኑም ባለፉት ሳምንታት ከመንግሥት፣ በተለይም ከላይ ከጠቀስነው ባለስልጣን አኳያ አንዳንድ ሀሳቦችን አንስተን ተወያይተናል። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ከትምህርት ባለ ሀብቶች አኳያ ስለ ግሉ የትምህርት ዘርፍ እናወራልን።
ከግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ90 በመቶ ያላነሱት ቤት ተከራይተው የሚሠሩ በመሆናቸው፣ መንግሥት ያስቀመጠውን የትምህርት ቤት ግቢ ስፋት አያሟሉም፤ በመምህራን በኩልም መንግሥት የሚጠይቀውን መሥፈርት የሚያሟሉ ማግኘት አይቻልም፤ መንግሥት የሚጠይቀውን መሥፈርት ለማሟላት ሲባል ተማሪዎች የሚጠየቁት ክፍያ ከወላጆች አቅም በላይ ነው፤ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ናቸው፤ አላማቸው ትርፍ ማግበስበስ ነው፤ ትውልድ መቅረፅ ላይ መስራት አይፈልጉም፤ ትምህርትን እንደ ማንኛውም በገንዘብ እንደሚገዛ ሸቀጥ ነው የሚያዩት … እና የመሳሰሉት በግሉ የትምህርት ዘርፍ ላይ የሚሰነዘሩ ያልተቋረጡ ወቀሳዎች ሲሆኑ፤ እነዚህን ወቀሳዎች የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር እንዴት ይመለከታቸዋል? የሚለውን ከማህበሩ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከአቶ አበራ ጣሰው የምረዳው ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በእስከ ዛሬ የግል/የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውዝግብ ውስጥ የመንግሥት መምህራን ማህበር (ኢመማ)፣ ወላጅ ተማሪ ማህበርና የመሳሰሉት መኖራቸው እንጂ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ስለመኖሩ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። በመሆኑም ስለ ትምህርት ጥራትም ሆነ መምህራን ተጠቃሚነት ጉዳይ ከእነዚህ አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ አይስተዋልም። ከዚሁ አኳያ የዛሬው እንግዳችን ከሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትን አድርገናልና አብራችሁን ትዘልቁ ዘንድ እንጠይቃለን።
ሁሌም የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት የአገሪቱን የትምህርት ፖሊስ ተከትለው እንዲሠሩና ብቁ ተማሪ እንዲያፈሩ ከማድረግ አንፃር፣ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተባብረው መሥራት እንደሚገባቸው ሲነገር ቢሰማም ዳር ሲደርስ ታይቶ አይታወቅም። “አሁንስ?” ለሚለው ጉዳዩ አሁን እንደ አዲስ የተቀሰቀሰ ሲሆን ውጤቱንም ወደ ፊት የምናየው ሆኖ አዲስ ነገር ካለ ከማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋር የምናደርገው ውይይት የሚነግረን ይሆናል።
አቶ አበራ ጣሰው ይባላሉ። የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። ያገኘናቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በዲኦፖል ሆቴል አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት (ለትጉህ መምህራንና ትምህርት አመራሮች እውቅና የመስጠት ፕሮግራም) መድረክ ላይ ነው። ከመድረኩ ብቻም ሳይሆን ስለሚመሩት ማህበርና አጠቃላይ አላማው፤ እንዲሁም ስለ ትምህርት ጥራት ጉዳይ አነጋግረናቸዋል። “መድረኩን እንዴት አገኙት?” ለሚለው ጥያቄያችን ከሰጡት መልስ ጀምረንም እንደሚከተለውም አቅርበነዋል።
መድረኩ ጥሩ ነው መወያየት ያስፈልጋል፤ ተገቢም ነው። እኛም መተንፈሻ እናገኛለን። ግን ለውይይት የቀረበው ሰነድ አስቀድሞ ደርሶን ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። አልደረሰንም። የደረሰን አሁን ነው። አይተነው፣ አስበንበት፣ ተዘጋጅተንበት፣ ጥሩ የሆነ ግብአት ይዘን እንመጣ ነበር። ምንም እንኳን ውሳኔው የእነሱ፣ የመንግሥት ቢሆንም ለእሱም ግባት ይሆናቸው ነበር። ይሄ ነው እንጂ ችግሩ መድረኩ ጥሩ ነው።
የትምህርት ጥራትን በተመለከተ በእኛ በኩል፤ በግል ትምህርት ቤቶች በኩል ችግር የለም። በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ካሉት ተማሪዎች ከ65 በመቶ በላይ ማንበብና መፃፍ አይችሉም ያለውን በተመለከተ ለጠየከኝ በእኛ በኩል ምንም ችግር የለም። በራሱ፣ በግል ችግር ካልሆነ በስተቀር ማንበብና መፃፍ የማይችል ተማሪ በግል ትምህርት ቤት ውስጥ የለም። በተለያዩ ምክንያቶች ግን እንደ አገር ሊኖር ይችላል።
አዲስ አበባን በተመለከተ ከአጠቃላይ ተማሪው 72 በመቶ የሚሆነው እኛ ጋ (የግል ትምህርት ቤት) ነው የሚማረው። የትምህርት ጉዳይ የመንግሥት ጉዳይ ነው ብለን ዝም አላልንም። የመንግሥትን ሸክም ለመጋራት፤ ለማገዝ በሚል ነው ወደ እዚህ ዘርፍ የገባነው። በመሆኑም ያለብን ኃላፊነት ቀላል አይደለም። የከተማውን 72 በመቶ ተማሪ ማስተናገድ ቀላል አይደለም።
ያሉብንን ችግሮች በተመለከተ በርካታ ናቸው። ያሉብንን ችግሮች ሁሉ እንግለፅ አንልም። ከሁሉም የባሰው ግን ትምህርት ቤት ለመገንባት የሚያስችለው የመሬት ጉዳይ ነው። በተደጋጋሚ ለግንባታ የሚሆን መሬት እንዲሰጠን ጠይቀን ሊሳካልን አልቻለም። “ይሰጥ አልነበረም ወይ?” ላልከው እሱ በፊት ነበር። በፊት ከባለቤቶቹ 20 በመቶ ከመንግሥት 80 በመቶ ተሸፍኖ በሊዝ ይሰጥ ነበር። አሁን እሱ ቀርቷል። እናም ትልቁ ችግራችን የመሬት ጉዳይ ነው። የትምህርት ባለሀብቱ እኮ በግለሰብ ቤት ነው ተከራይቶ እያስተማረ ያለው።
የስፖርት ሜዳ የለ፣ ምን የለ ላልከውም ይሄ እኮ በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ነው። ምንም የለም። የቱ ጋ ሊኖር ይችላል። ለዚህ እኮ የግንባታ ቦታ እንዲሰጠን እየጠየቅን ያለነው። መንግሥት ለትምህርት ቤት መገንቢያ የሚሆን መሬት ለባለ ሀብቱ ቢያመቻች (ቢሰጥ) የግል ትምህርት ቤቶቹ ሌላውን ለማሟላት አይቸገሩም ነበር። ቦታ በሌለበት ግን እንዴት አድርጎ ነው አሁን ያልካቸውን ማሟላት የሚችሉት፤ አይቻልም። ትምህርት ቤቶቹ መጀመሪያ ከግለሰብ ቤት መውጣት አለባቸው።
ትምህርት ቤት ማለት ክፍል ብቻ ማለት አይደለም። ትምህርት ቤት ማለት ብዙ ነገር ማለት ነው። ልጆቹ መጫወቻ ቦታ ይፈልጋሉ። የሚሯሯጡበት ሜዳ ያስፈልጋቸዋል። ሌላም ሌላም። ስለዚህ፣ ይህ ሁሉ ግንዛቤ ተወስዶበት ለትምህርት ባለ ሀብቱ በቂ የሆነ የመገንቢያ ቦታ ሊሰጠው ይገባል።
የዋጋ (የትምህርት ቤት ክፍያ) ጭማሪን በተመለከተ አዎ ብዙ ጊዜ አለመግባባት ይነሳል። ተቃውሞም ግጭትም ይታያል። ግን ምን ማድረግ ይቻላል። ትምህርት ቤቶች የክፍያ ዋጋን የሚጨምሩት እኮ ወደው አይደለም። የትምህርት ግብአት ጉዳይ እየሆነባቸው ነው። የትምህርት ግብአት (የቤተ ሙከራ ኬሚካል ወዘተ) ዛሬ በገዛህበት ነገ አትገዛውም። ጨምሮ ነው የምታገኘው። በየጊዜው ሲጨምር ነው የሚታየው። ታዲያ ትምህርት ቤቶች ያላቸው እድል እኮ ክፍያ መጨመር ነው። የትምህርት ቤቶቹን ችግር የሚረዳ ይረዳዋል። የማይረዱም አሉ። የትምህርት ጉዳይ የሰው ልጅ ጉዳይ ነው። በሌላ ነገር መቀለድ ይቻላል። በልጆች ግን መቀለድ አይቻልም። በመሆኑም ትውልድ እንዲገነባ ካስፈለገ፣ ልጆቹ በሚገባ ሊማሩ፤ ማግኘት ያለባቸውን ትምህርት በሚገባ ሊያገኙ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ክፍያ የግድ ነው።
በነገራችን ላይ የግል ትምህርት ቤቶች አኮ ተመራጭ ናቸው። ባይሆኑ ኖሮ እኮ ይሄ ሁሉ (ወላጅ) ወደ እኛ ዘንድ እየመጣ ልጆቹን አያስገባም ነበር። ትምህርት በአግባቡ እንደሚሰጥ፤ ክፍያውም ተገቢ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ ነው።
“በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አማካኝነት ለውይይት በቀረበው ሰነድ ላይ አዳዲስ አሰራሮች ለታዳሚው ተዋውቀዋል። ለምሳሌ ’ግብረ ኃይል ማቋቋም …’ እና የመሳሰሉት። በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?” ለሚለውም ፕሬዚዳንት አበራ ጣሰው አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን “እኔ በበኩሌ ’ግብረ ኃይል ማቋቋም …’ ወይም ’… ይቋቋማል’ የሚለው ብዙም አያስደስተኝም። በሀይራርኪ አላምንም። በእንደዚህ አይነቱ መመሪያ ብዛት ምንም አይገኝም። የሚበጀው መነጋገር፣ መወያየት . . . ነው። ምንም እንኳን ወሳኙ ባለስልጣኑ፤ መንግሥት ቢሆንም ከእኛም ቢሆን ግብአት ስለማይታጣ መነጋገሩ ጥሩ ነው።” ነበር ያሉት።
በመጨረሻም “የሚያስተላልፉት መልእክት ካለዎት” ለሚለውም፤ እኛም ሆንን ባለስልጣኑ፤ ሁላችንም ተማሪዎቻችንን ማእከል አድርገን ነው የምንሄደው፤ መሆን ያለበትም ይኸው ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ከባድ ጉዳይ ነው። ዛሬ ተንበርከክ፣ እንዲህ ሁን … የምንላቸው ተማሪዎቻችን ነገ አለቆቻችን ናቸው። መሪዎቻችን ናቸው። ነገ የእነሱ ነው። በመሆኑም ዛሬ በአግባቡ እነሱን ልናበቃቸው ይገባል። በመሆኑም እኛ፣ እንደ ትምህርት ቤት እነዚህን ልጆች፣ የነገ መሪዎች ከማብቃት አኳያ ትልቅ ኃላፊነት ነው ያለብን። የምንንቀሳቀሰውም ከዚሁ አኳያ ነው። እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደግሞ ምን ጊዜም እኛንም በማይጎዳ፣ ተማሪዎችንም በማይጎዳበት ሁኔታ ቢሰራ፤ እኛንም እየመከረ፣ እያሳተፈ … ቢመራን ጥሩ ነው የሚሆነው።
ወላጆችም ልክ ክፍያ ተጨመረ ብለው እንደሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ወደ ትምህርት ቤቶች ብቅ እያሉ ልጆቻቸውንም መከታተል ይገባቸዋል። ምን ሲሰራ ዋለ፣ እየተማረ ነው ወይ፤ የመማር ማስተማሩ ሁኔታ ምን ይመስላል፤ ትምህርት ቤቱ ውሎው እንዴት ነው? …. የሚለውን ሁሉ መከታተል፤ ማወቅ አለባቸው። ትምህርት ቤት ብቻውን ምንም አያመጣም። የወላጆች ክትትል የግድ ያስፈልጋል። ወላጆች ይሄንን ማወቅ አለባቸው። የጎደለ ነገር ካለ … ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ቀረብ ብሎ በመመካከር ልጆቹን ተገቢ ቦታ ላይ ማድረስ ይገባል። አገሪቱን የሚረከቡት እንግዲህ እነሱ ናቸው።
በመሆኑም እነሱን ማብቃት አለብን። አንዳንድ ወላጆች ዝም ብለው ከፍለው ልጃቸውን መላካቸውን ብቻ ነው የሚያዩት። ምንም አይነት ክትትል የማያደርጉ አሉ። ትምህርት ቤቱ ያስተምረው አያስተምረው፤ ግብአት ያቅርብ አያቅርብ … ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ትምህርት ቤቱ እግዚአብሔርን ካልፈራ በስተቀር የሚከታተለው ወላጅ የለም። ይህ ደግሞ ስህተት ነው። ይህን ሁሉ ትቶ፣ ከትምህርት ቤቶችና አመራሮቻቸው ጋር በቅርበት ሆኖ፤ እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ነው የታሰበው ሁሉ የሚሳካው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014