‹‹ጓደኛህን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ›› ሆነና ጋዜጠኛ ሲታማ እበሳጭ ነበር(ወገንተኝነት ተሰምቶኝ ማለት ነው)። በተለይም የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ እንታማለን። ሀሜቶቹ ብዙ ዓይነት ቢሆኑም ዋናው ግን የእውቀትና የብቃት ጉዳይ ነው። ዛሬ እንደጋዜጠኛ ሳይሆን እንደሌላ ወገን ሆኜ ነው ምታዘበው።
123ኛውን የዓድዋ ድል ለማክበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወደ ዓድዋ የጉዞ ፕሮግራም አዘጋጀ። ለጉዞው ድፍን ሰባት ቀን ተይዟል። ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ተራራ ድረስ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎች ይጎበኛሉ። መታደል ነበር አይደል? የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚታሙት ለእንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ቦታዎች ትኩረት ባለመስጠታቸው ነበር አይደል? ዳሩ ግን ትኩረት ሲሰጡም ለካ ጋዜጠኛ የለም፤ ያ ስማቸውን ሲያብጠለጥል የነበረው ሁሉ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ በስልክ ጠይቆ ነው የሚደነፋ፤ ወይም የአንድ ታክሲ ጉዞ ሄዶ ነው። ወደ ዓድዋው ጉዞ እንመለስ!
ከአዲስ አበባ የተነሳው ጉዞ የአዳር ፕሮግራም የተያዘለት ደብረብርሃን ነው። የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የንግስና እና የትውልድ ቦታዎች አንጎለላና አንኮበር ሲጎበኙ ውለዋል። እንግዲህ የአገራችን ጋዜጠኞች እስከ አፍንጫቸው መወቀስ አለባቸው ብዬ ያመንኩት ከዚህ ጀምሮ ነበር። ከአርባ ምናምን ጋዜጠኛ ውስጥ የሙያው ፍቅርና ትጋት ኖሮት የሚሠራው ከአራት አይበልጥም። መጀመሪያ ላይ የተጭበረበርኩት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስላዩት ይሆናል ብዬ ነበር። እነዚያው ሲበጠብጡ የነበሩ ጋዜጠኞች ግን ለቦታው አዲስ መሆናቸውን ሲናገሩ ስሰማ ግርምቴ ባሰብኝ። ለመሆኑ ምን አሉ? አስቡት! እነዚህ ሰዎች ጋዜጠኛ ተብለው ነው የሄዱት፤ ዳሩ ግን እነዚህን ታሪካዊ ቦታዎች ለማየት እንሂድ አንሂድ ክርክር ተፈጥሮ ነበር።
አካባቢዎቹ በእርግጥም አድካሚ ናቸው፤ የእግር ጉዞም አለባቸው። ቢሆንም ግን በጣም ቢበዛ ከ10 ደቂቃ በላይ የሚወስድ የእግር ጉዞ አላጋጠመንም። ወደነዚያ ቦታዎች ስንሄድ ምን ያደርግልኛል ብሎ መኪናው ውስጥ የሚጠብቀን ጋዜጠኛ ነበር! ሌላው የታዘብኩትን ደግሞ ልንገራችሁ። ግዴታ ሆኖባቸው የሄዱት እንኳን የሙያውን ምንነት አያውቁትም፤ ወይም ቢያውቁትም ግዴለሽነት በልጧል። በታሪካዊ ቦታዎች ላይ የሚቀረጹ ነገሮች ብዙ ናቸው። እዚህ ላይ ነበር የቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና የፎቶ ካሜራ ባለሙያዎች በጣም የተቸገሩት። ልክ የሚቀረጸው ነገር ላይ ‹‹ሰልፊ›› ፎቶ ለመነሳት የሚንጋጋው መዓት ነበር። እሺ ሲጨርሱ ይሁን ብለው የካሜራ ባለሙያዎች ትንሽ ይታገሳሉ። ኧረ ወዲያ እቴ! ጭራሽ አቅጣጫ እየቀያየሩ ተደጋጋሚ ፎቶ መነሳት ሆነ። ይህኔ የካሜራ ባለሙያዎች ትዕግስት ያልቅና መጨቃጨቅ ይመጣል። ይህን የሚያደርጉት እንግዲህ ጋዜጠኛ ተብለው የተላኩ ናቸው። ሌላ ሰው ቢያደርገው አይደንቀኝም፤ ምክንያቱም ስለሙያው ባህሪ ስለማያውቅ።
እንዴት ጋዜጠኛ ተብሎ እንደ ሕፃን በካሜራ ሥር አትለፍ እየተባለ ይነገራል? በግድ በጭቅጭቅ የቀረጸው ቀርጾ ያልቻለም ትቶት ወደ መኪና ግቡ ይባላል። እነዚያ መሄድ የለብንም ሲሉ የነበሩ ጋዜጠኞች ይጠፋሉ። አንድ ቦታ ተጎብኝቶ ሳይመሽ ወደ ሌላ ቦታ መኬድ አለበት፤ ዳሩ ግን የሉም። የተገላቢጦሽ ሥራ የሚሠሩት ጨርሰው ሲመጡ ድንጋይ ላይ እና ዛፍ ላይ ፎቶ ለመነሳት የሄዱት ይጠፋሉ። እነርሱን ፍለጋ ብዙ ደቂቃ ይባክናል። ከሌላ አካላት የመጡ ተጓዦችን የያዘው መኪና ጭኖ ሲሄድ ጋዜጠኞችን የያዘው መኪና ግን ገና አይታሰብም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ይሁን።
የጋዜጠኞች የተለየ ነው። ቀረጻ አለ፣ ቃለ መጠይቅ አለ፣ የቀረጻ ዕቃዎችን ማሰባሰብ በራሱ ጊዜ ይወስዳል። ከሌላ አካል የመጡት መጎብኘት ብቻ ነው። ይሄን አውቃለሁ። ዳሩ ግን ስንዘገይ የነበረው ሥራ በሚሠሩ ጋዜጠኞች ምክንያት አልነበረም! ኧረ ቆይ ሌላም የባሰ አለ! ከሁለተኛው ቀን የጉብኝት ቦታዎች አንዱ የውጫሌ ውል የተፈረመበት ይስማ ንጉሥ ነው። የዓድዋ ጦርነት ምክንያትም ያቺ መዘዘኛ አንቀጽ 17 አጼ ምኒልክን እና ኮንታንቶሎኒን ውረድ እንውረድ ያባባለችበት ቦታ ነው። ወደዚች ታሪካዊ ቦታ ስንሄድ ነበር በጋዜጠኞች መካከል ዱላቀረሽ ክርክር የተፈጠረው! ‹‹መሄድ የለብንም›› ያሉትን ሰዎች ምክንያታቸውን ሳልጠቅስላቸው አላልፍም። አጼ ምኒልክ ‹‹ወረኢሉ ላይ ከተህ ጠብቀኝ›› ያሉበትን የወረኢሊ ቤተ መንግሥታቸውንና የጦር ማዘዣ ሥፍራዎችን ስንጎበኝ ውለን ከፍተኛ ድካም ነበር። አካባቢውም የእግር ጉዞ ይበዛዋል፤ የሚጎበኙ ቦታዎችም ብዙ ነበሩ። እናም ወደ ውጫሌ ስንሄድ ከፍተኛ ድካም ነበር፤ በዚያ ላይ ወልዲያ ለማደር ሰዓቱም እየመሸ ነበር።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን የውጫሌ ውል የተፈረመበት ታሪካዊ ቦታ ከዋናው የአስፋልት መንገድ 9 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚርቀው። ጠጠር ቢሆንም መኪና እስከቦታው ድረስ ይገባል። ከዋናው የአስፋልት መስመር ወደውጫሌ ሊታጠፍ ሲል ከፍተኛ ጫጫታ ተፈጠረ። መኪናው ቆመ። አስተባባሪው ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹ይሄ የተያዘ ፕሮግራም ነው፤ ድካም ቢኖርብንም ብናየው ይሻላል!›› አለ፤ አስተባባሪው አማራጭ መስጠቱን ሲያውቁ ‹‹ማየት የለብንም›› የሚሉ ወገኖች ጠንከር ብለው «ማየት የለብንም» አሉ። ከሁለቱም ወገን የየራሳቸውን ምክንያት እያመጡ ክርክሩና ጭቅጭቁ ጠነከረ። የዚህን ጊዜ ከልባቸው ጋዜጠኛ የነበሩ ሰዎች አስተባባሪውን በከፍተኛ ቁጣ ተናገሩት! ያልፈለገ ይቅር እንጂ ምን ልናደርግ ነው ታዲያ የመጣን? የሚል አቋም ያዙ። መሄድ የለብንም የሚሉትም እየከፋቸው ሄድን! አንድ ጋዜጠኛ ቃል በቃል የተናገረውን ልንገራችሁ! ‹‹ውሉን እኮ አሁን እየተፈራረሙ አይደለም፤ ምኑን ነው ምናየው?›› ነበር ያለ። ይሄ ጋዜጠኛ ነው እንግዲህ ታሪክን የሚያስተዋውቅ? ይሄ ነው መቶ ሚሊዮን ሕዝብን የሚያስተምር? እዚህ ላይ አንድ ሃሳብ እናንሳ። ይሄ ጋዜጠኛ የውጫሌን ታሪካዊ ቦታ የማየት ግዴታ የለበትም እንበል፤ ታሪክን የመውደድ ግዴታም የለበትም እንበል። ታዲያ ዓድዋ የሚሄደው ለምንድነው? የዓድዋ ድል ታሪኮች ምንም ትርጉም ካልሰጡት ያን ያህል የሳምንት ጉዞ ምን አደከመው? እንዲያውም እኮ ጋዜጠኛ ማለት እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የሚያልፍ ነበር፡፡
የነገሩን ተቃርኖ ደግሞ ልንገራችሁ! እነዚህ ይመሽብናል ማየት የለብንም የሚሉ ሰዎች ቁርስ ለመብላት ብቻ ሁለት ሰዓት የሚጠቀሙ ናቸው። ቁርስ በልተው ሰው መኪና ውስጥ እነርሱን እየጠበቀ የከተማዋ ዳር ድረስ እየዞሩ የማይገዙትን ዕቃ የሚጠይቁ፣ በየአጥሩ ሥር ፎቶ የሚነሱ፤ ከየመጠጥ ቤቱ እየተጠሩ የሚመጡ ናቸው። መጠጥ ከተነሳ አይቀር የሱሷንም ነገር እናንሳት! አብዛኛው ጋዜጠኛ ይጠጣል፣ ይቅማል፣ ያጨሳል። ስለዚህ ጋዜጠኞች ራሳቸው ሱሰኛ ናቸው ሚባለው ወቀሳ ትክክል ነው። የብቃት ነገርም ሌላው የብዙ ጋዜጠኞች ችግር ነበር። ዓ
ድዋን ያህል ትልቅ ታሪክ ያላወቀ ጋዜጠኛ ሌላ ምን ሊያስተምር ይችላል? እውቀቱ ከማህበረሰቡ በታች ከሆነ ለማን ነው ሚናገረው? አጼ ምኒልክ እና ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሲምታቱበት የነበረ ጋዜጠኛም አጋጥሞኛል። ማንም ሰው የትኛውንም ነገር አውቆ አይጨርስም፤ ቢሆንም ግን ለዚያ ለሚሄዱበት ሥራ ደግሞ ዓውዳዊ መሆን የግድ ነው። ለምሳሌ ወደ ዓድዋ የሚሄድ ሰው ስለዓድዋ ታሪክ የተጻፉ መጽሐፎች መያዝ፣ እሱ እንኳን ባይቻል በይነ መረብ ላይ መፈለግ ይገባ ነበር! ‹‹በማን ይፈረድ?›› ከተባለ በመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለቤቶች! በስነ ምግባርም ሆነ በዕውቀት ማስተካከል አለባቸው። በስነ ምግባርም ሆነ በዕውቀት ከማህበረሰቡ በታች የሆነ ጋዜጠኛ ሲፈጠር ለምን ዝም ይላሉ? ጋዜጠኝነት ትልቅ ጥንቃቄና በትኩረት ማስተዋልን የሚጠይቅ ሙያ ነው።
እስኪ ሁላችንም እናስብበት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ዋለልኝ አየለ