በአትሌቲክስ ስፖርት ይህ ወቅት የቤት ውስጥ ውድድሮች ተጠናቀው የውጭ መም ውድድሮች የሚጀመሩበት ነው። ዛሬ በሁሉም አህጉራት በ12 ዙር የሚደረገው የአህጉር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በቤርሙዳ ሲከፈት፤ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ደግሞ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ይጀመራሉ። ከሶስት ወራት በኋላ ደግሞ በስፖርቱ ታላቅና ለአትሌቶችም የላቀ ክብር የሚያጎናጽፈው ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ18ኛ ጊዜ ይካሄዳል። የተለመደው የውድድሩ መርሃ ግብር ከኦሊምፒክ አስቀድሞ የሚካሄድ ቢሆንም የመላው ዓለም ስጋት በነበረው የኮቪድ ስርጭት ምክንያት ከአንድ ዓመት መራዘም በኋላ ነው ለማካሄድ ቀን የተቆረጠለት።
በአሜሪካ አፈር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ውድድር በዓለም አትሌቲክስ ባለቤትነት ለአስር ቀናት በአጭርና ረጅም ርቀት የመም፣ በጎዳና ውድድሮች እንዲሁም በሜዳ ላይ ተግባራት አገራትን ያወዳድራል። 214 አገራት የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ 49 ውድድሮች ይከናወናሉ።
በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ አትሌቶች የሚፎካከሩበትና ያሉበትን ደረጃም ለሚፈትሹበት ለዚህ ውድድር አገራት አስቀድመው ዝግጅት እንደሚያደርጉ ይታወቃል። ውድድሩ በኦሊምፒክ ማግስት፤ ከዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና መልስ የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ በቶኪዮና ቤልግሬድ የታዩ ድንቅና እውቅ አትሌቶች ራሳቸውን ለውድድሩ ዝግጁ ማድረጋቸውን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስነብቧል።
በእርግጥ ኢትዮጵያዊያኑን አትሌቶች ጨምሮ በርካታ የኦሊምፒክ ተሳታፊ የነበሩ አትሌቶች በወራት ልዩነት በቤት ውስጥ ቻምፒዮናው ድንቅ አቋማቸውን አሳይተዋል።
በቀጣይም አብዛኛዎቹ በአህጉር አቀፉ የዙር ውድድር እንዲሁም በዳይመንድ ሊጉ ተሳታፊ እንደሚሆኑ እርግጥ ነው። ይህም የውድድር መደራረብ አትሌቶቹን ለጫና የሚያጋልጣቸው እንደሚሆን ቢገመትም፤ የዓለም ቻምፒዮናው ግን እንደቀደመ ክብሩ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ከጉዳት አገግመው በቻምፒዮናው ደግም ወደ ውድድር የሚመለሱትን ጨምሮ በዓመቱ አስደናቂ አቋም ላይ ያሉ አትሌቶች ክብረወሰኖችን በማሻሻልና ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ እንደሚያደምቁት ይጠበቃል።
ከነዚህም መካከል በቶኪዮ ኦሊምፒክ ስኬታማ የሆኑ አሜሪካዊ አትሌቶች በአጓጊው ቻምፒዮና ላይም የበላይነቱን ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል። በአፍሪካም በአትሌቲክስ ስፖርት ታዋቂ ከሆኑት የምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል በውጤታማነቷ ተጠቃሽ የሆነችው ኬንያም ከምትሳተፍባቸው ርቀቶች መካከል በተወሰኑት የሚሳተፉትን አትሌቶች ማንነት አሳውቃለች።
በዚህም መሰረት ረጅሙ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር በሆነው ማራቶን ቡድኗ በወንዶች ጄዮፍሪ ካምዎረር፤ በሴቶች ደግሞ ሩት ቼፕጌቲች የሚመሩ ይሆናል። በርቀቱ ሰባት አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ አራቱ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል።
በስፖርቱ በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ስኬታማ የሆነችው ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ አገር ኢትዮጵያ፤ በአትሌቶቿ አማካኝነት በርካታ ክብሮችን ካስመዘገበችባቸው መድረኮች መካከል አንዱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው። በቅርቡ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በሰበሰበቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት አንደኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ሲሆን፤ ይኸውም በዓለም ቻምፒዮናውም ብርቱዎቹ አትሌቶቿ እንዲጠበቁ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ለውድድሩ አስቀድሞ ዝግጅት በማድረግ ወደ ኦሪገን ለመጓዝ እየተደረገ ያለው መሰናዶ ምን ይመስላል የሚለውን ጥያቄ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቅርቧል።
በፌዴሬሽኑ የተሳትፎና ውድድር የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ፤ ለቻምፒዮናው ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች እየተመረጡ ሲሆን፤ ውድድሩ የራሱ የሆነ ዓለም አቀፍ የመወዳደሪያ መስፈርት (ሚኒማ) አለው።
ይህንንም ተከትሎ በተቀመጠው ጊዜና መስፈርት መሰረት መሳተፍ የሚያስችላቸውን ሚኒማ የሚያሟሉ አትሌቶች በቻምፒዮናው አገራቸውን የሚወክሉ ይሆናል። የቅድመ ዝግጅት ጊዜው ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ይጠናቀቃል በሚል ይጠበቃል። አትሌቶች በቻምፒዮናው ተካፋይ ለመሆን በራሳቸው በዝግጅት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በተያዘው የጊዜ ገደብ ብሔራዊ ቡድኑ ታውቆ ወደ ልምምድ የሚገባ መሆኑን የስራ ሂደት መሪው ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014