ኢትዮጵያ ሁሉን አይነት ሰብል ለማብቀል የሚያስችላት የአየር ፀባይ የታደለች ሀገር ናት። ከጤፍ እስከ ስንዴ፣ ከስንዴ እስከ ገብስ፣ ከገብስ እስከ ጥራጥሬ እህሎች፣ ከጥራጥሬ እህሎች እስከ ቅባት እህሎች ድረስ ምድሯ ያበቅላል። አያሌ አትክልትና ፍራፍሬዎችም በኢትዮጵያ ምድር ይበቅላሉ። ለምግብነት የሚውለው የእንስሳት ሀብቷም ቀላል የሚባል አይደለም። እንደውም በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ናት።
ይህን ሁሉ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ የማብቀል አቅም ያላትና ለምግብነት በሚውሉ የእንስሳት ሃብት የታደለች ሀገር በምግብ እጥረት ዜጎቿ ሲጎዱ ማየት ታዲያ በእጅጉ ያሳዝናል። ህፃናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉ ማየትም ያማል። እናቶች ለጨቅላ ህፃናቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን አጥተው ጡታቸው ሲደርቅ ማየት ይዘገንናል።
ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ወደ ምግብነት ሊቀየር የሚችለውን ሃብቷን በሚገባ ከተጠቀመችበትና በዚህ ላይ ህዝቦቿ ጠንክረው ከሰሩ ከራሷ አልፋ ለሌሎችም እንደምትተርፍ ብዙዎች ይስማማሉ።
ዶክተር መሰረት ዘላለም በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የህፃናት፣ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና እና የስረዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። የብሄራዊ የምግብና ስረዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ሴክሬታሪም ሆነው ይሰራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት በአሊያንስ /alliance/ 2015 በተሰኘውና የዘንድሮውን ጨምሮ ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት በተካሄደው ጉባኤ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሀገራትን እየደገፉ የምግብና የስረዓተ ምግብን ጉዳይን በመዳሰስ ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ሪፖርት ያወጣሉ።
በዚህ ሪፖርትም ሶስት ዋና ዋና ቁልፍ ጉዳዮች የሚካተቱ ሲሆን እነዚህም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ የህፃናት ሞት፣ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት የምግብ እጥረትና የምግብ አቅርቦት ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት በየዓመቱ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶችን፣ የዓለም የህፃናት አድንና የህፃናት አድን ድርጅትና ሌሎችም በሀገር ውስጥ ያሉ ድርጅቶችን ያሚያወጣውን መረጃዎች ተንተርሰው የሀገራትን ዓመታዊ የምግብ እጥረት ደረጃ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ይፋ ያደርጋሉ። ለዚህም የደረጃ መለኪያዎችን ያስቀምጣሉ። በዚህም በርካታ ሀገራት ልኬታቸው ይቀመጣል።
በፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ በወጣው ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ሪፖርት መሰረትም ኢትዮጵያ ሙሉ መረጃ ከሰጡ 116 ሀገራት መካከል በ90ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በተቀመጠው መስፈርት መሰረትም ኢትዮጵያ 24 ነጥብ 1 ላይ ትገኛለች። ይህም በተቀመጠው አራት የደረጃ መስፈርት ውስጥ ኢትዮጵያ በምግብ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያሳያል። ይህ ደረጃ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲወዳደር ጥሩ መሻሻሎች እንዳሉ የሚጠቁም ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቅ ይናገራል።
በተለይ ምርታማነትን ከመጨመር፣ ከምርት አቅርቦት ማሻሻልና ከአምስት ዓመት በታች ያሉ የህፃናት የምግብ እጥረትና ሞትን መቀነስ ጋር በተያያዘ፤ የሀገሪቱን የምግብና የስረዓተ ምግብ ማሻሻል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
የምግብና የስረዓተ ምግብ ጉዳይ ለአንድ ሴክተር የሚተው ባለመሆኑ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል። አጠቃላይ የሚሰራው ሥራ ደግሞ ከጤና ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የሁሉንም ህብረተሰብ ጤና ለማሻሻል የምግብና የስረዓተ ምግብ ጉዳይን ማሻሻል ይገባል።
የምግብና የስረዓተ ምግብ ጉዳይ የጤና ብቻ ሳይሆን የሀገር እድገት፣ የብልፅግናና አጠቃላይ እንደ ሀገር ማምጣት ለሚፈለገው ውጤት ለመድረስ የሚያስችል ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሰፊ ሥራዎችን መስራት ይጠይቃል። ከሀገር ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናንና የአፍሪካ አህጉርን የስረዓተ ምግብ ጉዳይ ለመለወጥና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ለመሆን በዚህ ላይ መስራት በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
እንደ ዶክተር መሰረት ገለፃ በአስራ ስድስት ዓመታት ውስጥ ያሉትን መረጃዎች መተንተን ቢቻል የምግብ እጥረትን ከመቀነስ አኳያ በኢትዮጵያ ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ያሳያል። አሁንም ቢሆን ሀገሪቱ ከ116 ሀገራት መካከል 90ኛ ደረጃ ላይ ያለች በመሆኗ ይህን ደረጃ ማሻሻል ያስፈልጋል። ለዚህም በተለይ ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል አንፃር ብዙ መስራት ይጠይቃል። የህፃናትን የምግብ እጥረትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ሞት መቀነስም የግድ ይላል። ይህም ኢትዮጵያን ወደሚፈለገው ደረጃ የሚያደርስ ትውልድ መፍጠር ይቻላል።
የምግብና የስረዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ንቅናቄ ጀምሯል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የተጀመረ ከፍተኛ ንቅናቄ አለ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለምን የምግብ ስረዓት ለመቀየር ትልቅ አጀንዳ በመያዙ እ.ኤ.አ በ2022 የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይም ዓመቱ የምግብና የስረዓተ ምግብ ዓመት እንዲሆን ተወስኗል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ንቅናቄ ተቀላቅላለች።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን የምግብ ስረዓት ለመቀየር 22 ጌም ቼንጀር የተሰኙ አመላካቾች አሉ። ይህንኑ ለማሳካትም የጤና ሚኒስቴርና የግብርና ሚኒስቴር ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ሆነው ሥራውን አስጀምረዋል። ይህንንም በስፋት መስራት ከተቻለ በርካታ ነገሮችን መለወጥ ይቻላል። እንደ ሀገርም ከተረጂነት በማለፍ የተወሳሰበ የምግብ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች የኢትዮጵያ መገለጫዎች ሳይሆኑ ኢትዮጵያ እነዚህን ችግሮች ታሪክ አድርጋ ለሌሎች ሀገር የምትተርፍ ትሆናለች ተብሎ ይታሰባል።
ኢትዮጵያ ሰብል ለማምረት የሚያስችል ሰፊ መሬትና ምህዳር አላት። በቀንድ ከብት ሀብቷም ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት። ይህን ሀብት ወደ ውጤት ለመቀየር ጠንካራ ሥራዎችን መስራት ከተቻለ ሀገሪቷ በብዙ ነገር ራሷን መቻል ትችላለች። ለዚህም እንደ መንግሥት የኢትዮጵያ የምግብ ስረዓትን የመቀየር ከፍተኛ አጀንዳ ተይዟል። በዚህ ውስጥ ሁሉም ተሳትፎ አድርጎ ውጤት ማምጣት ይቻላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014