በ2002 ዓ.ም የስፖርቱን መቀዛቀዝ ተከትሎ የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አነሳሽነት ‹‹ኦሮሚያን የአትሌቶች ምንጭ ብቻ ሳይሆን ጎርፍም እናደርጋታለን›› በሚል መርህ በርካታ ክለቦች እንዲቋቋሙ መደረጉ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ከተመሰረቱ 20 ክለቦች መካከል እስካሁን በሥራ ላይ ያሉት ከአምስት ያልበለጡ ሲሆኑ፤ የኦሮሚያ ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት የአትሌቲክስ ስፖርት ክለብ አንዱ ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ጾታ 46 አትሌቶችን በማቀፍ እንደ ሳሙኤል ተፈራ፣ ጭምዴሳ ደበሌ፣ ትዕግስት ከተማን የመሳሰሉ ታዋቂ አትሌቶችን በማፍራት ላይ ይገኛል።
የኦሮሚያ ደን እና የዱር እንስሳት ድርጅት ከሚያበረክታቸው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች መካከል አንዱ የአትሌቲክስ ክለብን ማቋቋሙና በስፖርቱ ዘርፍ ውጤታማ መሆኑ ነው። ክለቡ በዚህ ዓመት ብቻ በተካሄዱ የተለያዩ አገር አቀፍ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎዎቹ 8የወርቅ፣ 8የብር፣ 9የነሃስ ሜዳሊያዎችን እንዲሁም 10 ዲፕሎማዎችን አስመዝግቧል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለሚወክለው ብሄራዊ ቡድን ሰባት የሚሆኑ አትሌቶች በእጩነት ቀርበውም ነበር። ክለቡ ከመሃል ከተማ ወጣ በማለት የአየር ሁኔታውና የቦታ አቀማመጡ ለስፖርቱ በእጅጉ ጠቃሚ በሆነው እንጦጦ ካምፕ አስገንብቷል። ይኸውም አትሌቶቹ በስፖርቱ ለውጤታማነት እንዲያተጉ ምክንያት በመሆኑ ያስመሰግነዋል።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የአትሌቲክስ ውድድር ርቀቶች መካከል በ1ሺ500ሜትር አስደናቂ አቋማቸውን እያሳዩ ካሉ ወጣቶች መካከል አንዱ ሳሙኤል ተፈራ ነው። እ.አ.አ 2018 በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሳይታሰብ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌቱ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት ከውድድር ርቆ ቆይቷል። ከጉዳቱ አገግሞ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ ቢሆንም ውጤታማ ለመሆን ግን አልቻለም። በመጨረሻም በኦሊምፒክ ማግስት በተካፈለበት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናም በድጋሚ ቻምፒዮን በመሆን አድናቆትን አግኝቷል።
በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 4 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሃስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም በቀዳሚነት ውድድሩን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በዚህ ውድድር የመጨረሻውን የወርቅ ሜዳሊያ በእጁ በማስገባት ሃገሩን ከዓለም አንደኛ በማድረግም የስፖርት ቤተሰቡን አኩርቷል። ይህንን ተከትሎም ክለቡ የኦሮሚያ ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት የሽልማት መርሐ ግብር አዘጋጅቷል። ክለቡ ለአሰልጣኞች እና ሁሉ በዓለም አቀፍ ውድድር ውጤታማ ለሆነው ሌላኛው አትሌት ጭምዴሳ ደበሌ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።
የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አራርሳ ረጋሳ ይጠቁማሉ። በእውቅና መርሐ ግብሩን በሁለት ምክንያቶች የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከክለቡ አልፎ የሃገሩን ስም ለማስጠራት የበቃው አትሌት ሳሙኤል ተፈራን ማመስገን ቀዳሚው ነው። ሌላው ደግሞ በክለቡ የታቀፉ አትሌቶችም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዛቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም አትሌቶቹ ውጤታማ በመሆን የሃገራቸውን ስምና ሰንደቅ ለማስጠራት መትጋት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ የቤት ውስጥ ውድድር ቻምፒዮን ለመሆን የቻለውና ከጉዳት መልስ ብቃቱን ያስመሰከረው ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል፤ ድርጅቱ የእውቅና መርሐ ግብር በማዘጋጀቱ ምስጋናውን አቅርቧል። ሽልማቱ ለተቀሩት አትሌቶች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ሲሆን፤ በቀጣይም ከሞራል ጀምሮ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
መካከለኛና ረጅም ርቀት አሰልጣኝ ብርሃኑ መኮንን በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ለአትሌቶች ምሳሌ የሚሆነውን የሽልማት መርሐ ግብር በማዘጋጀቱ አመስግነዋል። ክለብ ከማቋቋም ባለፈ ካምፕ በመክፈትም ጭምር እስከ አሁን ድረስ መቆየቱም ያስመሰግነዋል። ክለባቸው ከ14 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን በተለያዩ ስፍራዎች በመገኘት መልምሎ ወደ ክለቡ ይቀላቅላል። እስካሁንም በርካታ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ለሌሎች ክለቦችም ጭምር ግብዓት ለመሆን ችሏል።
ይሁንና ክለቡ ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ አንጻር መቀዛቀዝ ይስተዋልበት ነበር፤ ይኸውም ከዚህ ቀደም ካምፑ ባለበት ስፍራ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ይገነባል ቢባልም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።
በመሆኑም ለወደፊት አሁን የተፈጠረውን መነሳሳት ተከትሎ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ይሟላሉ የሚል ተስፋውን አንጸባርቋል። ከዚህ ባለፈ እንደ ሃገር ክለቦችን አቋቁመው ያፈረሱትን ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም እስካሁን የቀጠሉትን ደግሞ ማበረታታት የሚቻልበት አሰራር ሊፈጠር እንደሚገባም አሰልጣኙ ጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014