ጦርነት በሰዎች ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ከሕይወት መስዋዕትነት ጀምሮ ማህበራዊና ስነልቦናዊና ቀውስ ይፈጥራል። በአገሪቱ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነትም በዜጎች ሕይወት ላይ እጅግ አስከፊ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
በጦርነት ቀጠና አካባቢ የነበሩ በርካታ ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። ከቤት ንብረታቸውና ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ስደት፣ ረሃብና ጉስቁልናም ደርሶባቸዋል። ዜጎች በጦርነቱ ከደረሰባቸው ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ባለፈ በአካባቢው የደረሰው የንብረት ውድመት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በነበሩ አካባቢዎች በርካታ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወድመዋል። በውድመቱ ግንባር ቀደም ተጠቂ ከሆኑት ተቋማት መካከልም መኖሪያ ቤቶች፤ ፋብሪካዎች፤ የህክምና ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የዕምነት ቦታዎችና ሌሎችም ይገኙባቸዋል። የጦርነቱ ሰላባ ከሆኑት መካከልም የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ሲሆን የዛሬው ቅኝታችን ትኩረቱን በአሁኑ ወቅት ፓርኩ ከደረሰበት ጉዳት ለማንሰራራት እያደረገ ባለው ጥረት ላይ ያተኩራል።
ፋብሪካው ከደረሰበት ውድመት መልሶ ለማገገም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ገበያ የማጣት ስጋት ከፊት ለፊቱ ተደቅኗል። በፓርኩ የሚገኙ ካምፓኒዎች፤ አብዛኛው ምርታቸውን በአጎዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ ገበያ ይልኩ የነበሩ በመሆናቸውና በአሁን ወቅት ደግሞ ዕድሉ የተዘጋ በመሆኑ የገበያ ስጋት ስለመኖሩ በቅርቡ በኢንዱሰትሪ ፓርኩ በተደረገው ጉብኝት ተገልጿል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸመውን ወረራ ተከትሎ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ባደረሰበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። እስካሁን በተደረገው ጥናትም ፓርኩ በወረራው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን አጠቃላይ ውድመት እንዳደረሰበት ጥናቶች ያሳያሉ።
ጥናቱ አሁንም ያልተቋጨና የቀጠለ በመሆኑ የደረሰው ጉዳት ከፍ የማለት እድሉ ሰፊ ነው። በጦርነቱ ተንቀሳቃሽ የሆኑ ንብረቶች በሙሉ የተዘረፉ ሲሆን፤ ማንቀሳቀስ ያልቻሉትንም በማውደም እንዲሁም ለዘራፊዎች ክፍት በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት መደረጉን የፓርኩ ሥራ ኃላፊዎች አስረድተዋል።
በአሁን ወቅት አካባቢው ከቡድኑ ወረራ ነጻ መውጣቱን ተከትሎ በተሠራው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ፓርኩ ወደ ሥራ የተመለሰ ሲሆን፤ አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ ከሰባት ነጥብ አራት ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱን የገለጹት የፓርኩ ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ አህመድ ሰኢድ፤ ከተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላሩ ፓርኩ በመልሶ ማቋቋም ወደ ሥራ ከተመለሰ በኋላ ያገኘው መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ፓርኩ በ2014 በጀት ዓመት 13 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅዷ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ በሚገኝበት ወቅት ጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰበት ቢሆንም ካለፉት ሦስት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ችሏል። ከዚህም ባለፈ የተቀመጠውን ዓመታዊ የኤክስፖርት እቅድ ለማሳካት በቀሪ ጊዜያት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።
ፓርኩ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገባና ውጤታማ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ካምፓኒዎች በጎ ምላሽ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ያስታውሱት አቶ አሕመድ፤ መንግሥትና ሌሎችም ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስፈላጊውን እገዛ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል። ፓርኩ ከጦርነቱ አስቀድሞ ሶስት ሺ ሁለት መቶ ሰራተኞች የነበሩት ሲሆን በጦርነቱ ማግስት ወደ ሥራ የተመለሱት ግን ሁለት ሺ አንድ መቶ ያህሉ ሠራተኞች ብቻ ናቸው። ቀሪ ሠራተኞችን ወደ ሥራ ለመመለስም ካምፓኒዎች በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ ይገኛሉ።
አካባቢው ከአሸባሪው የሕወሓት ወረራ ነጻ ወጥቶ ፓርኩ ወደ ሥራ ሲመለስ ካምፓኒዎች ሠራተኞችን እንዲመልሱና በጦርነቱ ምክንያት ሳይከፈላቸው የቆየውን ደመወዝ እንዲከፍሉ ለማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን የሚጠቁሙት አቶ አሕመድ፤ ካምፓኒዎች በጦርነቱ የደረሰባቸውን የንብረት ጉዳት ከግምት በማስገባት የሚያገግሙበት ጊዜ ለመስጠት በማሰብ የሰባት ወራት የሼድ ኪራይ እፎይታ መሰጠቱን አመላክተዋል። ምንም እንኳን የሼዶቹ ኪራይ እፎይታ መሰጠት አገሪቱን በርካታ ገንዘብ የሚያሳጣት ቢሆንም ካምፓኒዎች በደረሰው ጉዳት ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ እንዳይመለሱና ሠራተኞችም እንዳይበተኑ የተወሰነ ውሳኔ ነው።
በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስባቸውም በቁጭት ወደ ሥራ መግባታቸውን በፓርኩ የሚገኙ ካምፓኒዎች ሲገልጹ፤ አብዛኛው ምርታቸውን በአጎዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ ገበያ ይልኩ የነበረና በአሁን ወቅት ደግሞ አገሪቱ ከአጎዋ ተጠቃሚነት መሰረዟ የገበያ ማጣት ስጋት ፈጥሮባቸዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሚገኙ አምራች ኩባንያዎች አንዱ የሴቶች የእጅ ቦርሳ እያመረተ ወደ ውጭ ገበያ የሚልከው የፑንግ ኩንግ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው።
የፋብሪካው የሰው ኃይልና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ያሬድ እንዳላማው እንደሚገልጹት፤ ፋብሪካው ከምርቱ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነውን ኢትዮጵያ የነበራትን ከኮታ እና ቀረጥ ነጻ የገበያ እድል ተጠቃሚነት በመጠቀም ወደ አሜሪካ ገበያ ሲልክ ቆይቷል። አሁን ግን አገሪቱ ከአጎዋ ተጠቃሚነት በመሰረዟ የገበያ እጦት ይገጥመናል የሚል ስጋት ገብቶናል ይላሉ።
ፋብሪካው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት ፓርኩ ላይ ውድመት እስካደረሰበት ጊዜ ድረስ አንድ ሺ አስራ ስድስት ሰራተኞች የነበሩት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ አሁን ላይ ስምንት መቶ ሰማኒያ የሚሆኑት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል። ሆኖም ግን አሁን ላይ ከገዢው ምንም አይነት የምርት ትዕዛዝ እየመጣ ባለመሆኑ ስጋት ገብቷቸዋል።
ፑንግ ኩንግ የሴቶች ቦርሳ አምራች ፋብሪካ በጦርነቱ ምክንያት ከአራት መቶ ሺ ዶላር በላይ አጠቃላይ ጉዳት እንደደረሰበት የሚናገሩት አቶ ያሬድ፤ የምርቱ ዋና ገዢ ማይክል ኮርስ ኩባንያ አሜሪካ ስለሚገኝ ድርጅቱ በጦርነቱ ከደረሰበት ጉዳት ባለፈ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ በመደረጉ አዲስ ትዕዛዝ እየተቀበለ አለመሆኑን ጠቅሷል። በአሁን ወቅትም ቀደም ሲል የተቀበሉትን ትዕዛዝ በማምረት ላይ እንደሚገኙና ተጨማሪ ትዕዛዝ ለማግኘትና ምርቱን ለመላክ የሚወጣውን ወጪ መጋራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከገዢው ጋር ድርድር እያደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል። ድርድሩ ውጤት የማያመጣ ከሆነ ግን ድርጅቱ የገበያ እጦት ሊገጥመው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አስረድተዋል።
የትራይባስ ብሪጅ ቴክስ ኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ማሞ እንደሚሉት ደግሞ፤ ፋብሪካው ሙሉ ልብሶችን በማምረት በአጎዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ ገበያ ሲልክ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ቀደም ብሎ ተቀብለውት በጦርነቱ ምክንያት የዘገዩ ትዕዛዞችን በማምረት ላይ የሚገኙና ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት በመሰረዟ ምክንያት አዲስ ትዕዛዝ እየተቀበሉ አለመሆኑን አንስተው በቀጣይ አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ለመፈለግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል።
አውሮፓ ላይ የገበያ እድሎች ቢኖሩም ፋብሪካው በግባትነት የሚጠቀማቸው ጥሬ እቃዎች ከውጭ ስለሚመጡ ያለውን ፉክክር ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል የዋጋ ተወዳዳሪነት መፍጠር ከባድ ነው። በአሁን ወቅትም ትራይባስ ብሪጅ ቴክስ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የሰላሳ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ቀጥተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን አቶ አዲሱ አስታውሰው በተጨማሪም በወቅቱ አምርተው መላክ ባለመቻላቸው ተቀብለውት የነበረው ትዕዛዝ ተሰርዟል። በዚህም ከአንድ ሺ በላይ ሠራተኞችን መቅጠር ያስችል የነበረው የማስፋፊያ ሥራን ለማቋረጥ ተገደዋል።
ፋብሪካው የተቋቋመው ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ በመሆኑ በመንግሥት በኩል መፍትሔዎች ካልተቀመጡ የፋብሪካው ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል አሁን ያሉትን ሠራተኞች ይዞ ለመቀጠል አዳጋች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይሁንና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሕመድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከኮታ እና ቀረጥ ነጻ የገበያ እድል ተጠቃሚነት ወይም አጎዋ መሰረዟን ተከትሎ የተፈጠረውን የምርት መዳረሻ ገበያ ማጣት ስጋትን ለመፍታት አማራጭ የገበያ እድሎች እየተፈለገ ነው። አብዛኞቹ የፓርኩ ባለሀብቶች ምርታቸውን በአብዛኛው የሚልኩት ወደ አሜሪካና አውሮፓ በመሆኑ የኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት መታገድ በአምራቾች ላይ ችግር ፈጥሯል። ነገር ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኩል አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየተሠራ ነው።
ለሦስት ሳምንት ያህል ዱባይ ኤክስፖ ላይ እየተሳተፉ እንደነበር ያስታወቁት አቶ አሕመድ፤ በቆይታቸውም ከዱባይ ባለሀብቶች ጋር ምክክር በማድረግ የገበያ እድል ለመፍጠር ጥረት መደረጉንም ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተወከለ ቡድን የገበያ አማራጮችን ለማየት በቅርቡ ወደ ሕንድ ማምራቱም ሌላኛው አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አንስተው ሙከራዎቹ ውጤት ያመጣሉ የሚል ተስፋ እንደተጣለባቸው አስታውሰዋል። አማራጮችን ለመፈለግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ተከትሎ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ካምፓኒዎች በሙከራ ደረጃ ምርቶችን ወደ አውሮፓ ለመላክ አማራጭ የሙከራ ምርቶችን እየሠሩ ይገኛሉ።
ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2017 የተገነባ ሲሆን፤ በጂቡቲ ወደብና በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ አቅራቢያ መገኘቱ ተመራጭነቱን ከፍ እንዳደረገው ተነግሯል። ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጠቃላይ አስር ሼዶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ ለባለሀብቶች የተላለፉ ስለመሆናቸው ከፓርኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንም እንኳን በርካታ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጦርነቱ የወደሙ ቢሆንም በአሁን ወቅት ጦርነቱ ካደረሰባቸው ጉዳት ማገገም እንዲችሉና በጦርነት ማግስት ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁንና ወደ ምርት የገቡ መሰል ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ በማገዝ በሙሉ አቅማቸው ማምረት እንዲችሉና ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ብሎም በቂ ትርፍ እንዲያስገኙ የገበያ መዳረሻዎች ማፈላለግና ማስፋት ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014