ሲሀም አየለ ትባላለች። ወጣቶችን ለሥራ ብቁ እና ተመራጭ እንዲሆኑ በማብቃት ሳታሰልስ በመሥራት ትታወቃለች። ሲሀም እንደ ብዙ አዲስ ተመራቂዎች የሥራ እድል በማጣት አልተንገላታችም። በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ሲሀም ሥራ ማግኘት የቻለችው ገና የሁለተኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆና ነው። እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ያጠናቀቀችው የሴቶች ብቻ በሆነው ናዝሬት ስኩል ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ አግኝታለች። ሦስት አሥርተ ዓመታት ባልደፈነው ለጋ ዕድሜዋ አፍሪካንና አውሮፓን ጨምሮ ወደ ስድስት የውጭ አገራት በመጓዝ ባካበተችው ግንኙነት የተመረቀችበትን ሙያ ሥራ ላይ አውላለች ።
ሲሀም በአሁኑ ወቅት የኢንፎማይንሰድ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማህበር አካል በሆነው “ደረጃዶትኮም” ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆና እየሠራች ትገኛለች። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች የቅጥር ዕድል እንዲያገኙ በሚያመቻቸው በዚህ ፕሮጀክት ከሚሠሩት 50 ሠራተኞች መካከልም 90 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው።
‹‹በአገራችን እየተስፋፋ የመጣው ሥራ አጥነት የዜጎችን በተለይም የሴት ተመራቂ ወጣቶችን ሥራ የማግኘት ዕድል አጥብቦታል›› የምትለው ወጣቷ ሲሀም እንዳወጋችን ለሥራ የሚያዘጋጅ ስልጠና መስጠት የጀመረችውም እነዚህን ክፍተቶች ከለየች በኋላ ነው። እንደ ጥናቷ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች ፈጥነው ሥራ የማያገኙባቸውም ምክንያቶች ፈርጀ ብዙ ናቸው። አንዱና ዋነኛው መረጃ እንደልብ ማግኘት አለመቻል ነው። ሁለተኛው በዚህ ምክንያት በቂ የሥራ ዕድል አለመኖር ሲሆን ሦስተኛው ዕድሉን ቢያገኙም የሥራ ቦታው ርቀት ያለው መሆኑ ነው። ‹‹ሥራ ሊገኝባቸው የሚችሉ አማራጮችን አለማወቅ ሴቶች ሥራ እንዳያገኙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው›› የምትለው ሲሀም ከሦስት ዓመት በፊት የተጠና ጥናት አንድ ተመራቂ ተማሪ ሥራ ለመፈለግ በትንሹ በቀን 20 ብር እንደሚያወጣ ማመልከቱን ትጠቅሳለች።
ታዲያ ሴቶች አማራጮቹን ቢያውቁም ከወንዶች ይልቅ ከትራንስፖርት ሣንቲም ጀምሮ ተሯሩጠው ሊፈልጉበት የሚያስችል ጥሪት በማጣትም ሥራ የማያገኙበት ሁኔታ እንዳለም ትገልፃለች። ሲሀም ለወጣት ሴቶች፣ በአጠቃላይም ለወጣት ተመራቂዎች እንዲሁም ለወጣቶች ሥራ ማጣት ምክንያት ናቸው ካለቻቸው ውስጥ ደፍሮ አለመሞከር፣ በራስ አለመተማመን፣ በዚህ የተነሳ በሥራ ፈተና ቃለ መጠይቅ ወቅት መፍራትና ለተጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ አለመስጠት፣ በኢኮኖሚም ሆነ ልምድ በማጣት ለአለባበሳቸው በሚፈለገው ልክ ዝግጅት አድርገው ለቃለ መጠየቅ አለመቅረብ ይጠቀሳሉ። ችግሮቹን ለመፍታት “ደረጃዶትኮም” የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
“ደረጃዶትኮም” ጾታ ሳይለይ ሁሉንም ተመራቂ ተማሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ቢሆንም ለሴት ተመራቂዎች የተለየ ትኩረት ይሰጣል። ትኩረቱ ከዚህ ቀደም ወጣቶች የትምህርት ዕድል አለማግኘታቸውንና አሁን ላይ ቢያገኙም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ተደራሽነቱ ዝቅተኛ መሆኑ፤ በዚህ ሁኔታ ለመመረቅ የበቁትን ደግፎ ማውጣት ግድ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህን መሠረት በማድረግም ተመራቂዎች ከመመረቃቸው በፊትና በኋላ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ ማድረግ ከተግባራቱ ቀዳሚው ነው።
ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮም ለ100ሺህ ያህል ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት አመራሮችን ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ሊደርሽፕ (የአመራርነት ስልጠና) የሚሰጥበት “መሪ ፕሮጀክት”ም አለው። መሪ ሥራውን የጀመረው በፈረንጆቹ 2018 ዓ.ም ሲሆን ከEaryan Solutions ጋር በትብብር ይሠራል። በየዓመቱ 30 የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሴት ተማሪዎች በስልጠናው የሚሳተፉ ሲሆን እስከ አሁን ባለው ሁኔታ 90 ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነውበታል። ሆኖም ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በክልል እንዲሰፋ እየተሠራ ነው።
‹‹ለአንድ ቤተሰብ ልጆቹን በተለይም ሴቶች ልጆቹን አስተምሮ ማስመረቅ፤ ተመርቀውም ሥራ በመያዝ ራሳቸውን ሲችሉ ማየት ትልቅ ስኬት ነው›› የምትለው ሲሀም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለች በዩኒቨርሲቲው የወሰደችው የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ስልጠና ወደ እዚህ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ወጣቶች ሥራ ማስገኘት የሚያስችል ተግባር መሠማራት እንዳስቻላትም ትናገራለች። እንዳጫወተችን እሷ በናዝሬት ስኩል የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቅቃና ጥሩ ውጤት አምጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ በምትገባበት ወቅት ወንድምና እህቶቿ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ባለማግኘታቸው በፍለጋ ይንከራተቱ ነበር።
በአዕምሮዋ “ለምን?” የሚል ጥያቄን የፈጠረባት ሲሆን ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ በምትወጣበት ሰዓት ምን ልትሆን እንደምትችልም ሰግታ ነበር። ስትገባ የመረጠችው ፖለቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን ሲሆን፤ ሥራ ሊያስገኝላት መቻል አለመቻሉን ሳታውቅ መምረጧ ያሳስባት ነበር። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ለዚህ የሚረዳ ምክር ወይም ዝግጅት እያገኙ መምጣት ይገባ እንደነበር የተገነዘበችውም በዛን ወቅት ነው።
ሲሀም የፖለቲካል ሳይንስ መስክን የመረጠችው 11ኛ ክፍል እያለች የተለያዩ መጻሕፍቶችን በማንበቧ ነበር። ይሄና የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆኗ “አገር እንዴት ነው የሚተዳደረው፣ ሕዝብስ፣ ድህነትስ ምንድነው?” የሚለውን በጥልቀት እንድትመረምር አድርጓታል። የበለጠ በኢኮኖሚና ቢዝነስ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩርም አስችሏታል። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፖለቲካል ሳይንስ ኢንተርናሽናል ሪሌሽን መሥራት የመረጠችበት ምክንያትም ይህ እንደሆነ ትናገራለች።
‹‹ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች አሉኝ። ለወላጆቼ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነኝ›› የምትለው ሲሀም የመጨረሻ ልጅ በመሆኗ ምክንያት አባቷ በጣም ያቀርቧትና ነፃነት ይሰጧት እንደበር ታወሳለች። ከቤት ውስጥ ሥራና ከማንኛውም ጫና ነፃ ሆና ትምህርቷ ላይ ትኩረት እንድታደርግና ሙሉ በሙሉ በራስ የመተማመን መንፈስ እንድታዳብር ያደርጉ እንደነበርም ትገልፃለች። አባታቸው ለሦስቱም ሴቶች ልጆቻቸው እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ቢሰጡም ለእሷ የሚያደርጉት ላቅ ያለና የተለየ እንደነበረም ታስታውሳለች ።
ሁኔታው ከታዳጊነት ዕድሜ ዘመኗ እስከ አሁን ከልቦለድ ጀምሮ ስለ አገርና ሕዝብ አስተዳደር፣ ስለ ውጪ ግንኙነቶች፣ ስለ ድህነት፣ ስለ ኢኮኖሚና የተለያዩ ጉዳዮች የሚተርኩ መጻሕፍትን ለማንበብ ሰፊ ዕድል የሰጣት መሆኑንም ትጠቅሳለች። ደፋር እንድትሆንና ከሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖራት ማድረግ አስችሏታል። በትምህርት ስኬታማ እንድትሆንና የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆና የወሰደችውን የሥራ ክሂሎት ስልጠና በመጠቀም ወደ ሥራ ዓለም ፈጥና እንድትገባ አግዟታል። ያለፈችበትን መንገድ ሁሉም ተመራቂ ወጣቶች በተለይም ተመራቂ ሴቶች እንዲጠቀሙበት አብዝታም ትፈልግ ነበር። ተማሪዎቹን በማብቃት ለሥራ የሚያዘጋጅ ስልጠና ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራውም ለዚህ ነው። በስልጠናው ሴቶች የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለአብነት ደረጃዶትኮም ወደ ሥራ በገባባቸው የመጀመሪያ ዓመታት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ላይ ይሄንኑ ብቃትን በማጎልበት ለሥራ የሚያዘጋጅ የቅድመ ሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥታ ነበር። በስልጠናው ከተሳተፉት ሁለት ሺህ ተማሪዎች መካከል ሴቶቹ አምስት እንኳን አይሞሉም። ‘‘ገርሞኝ ሴት ተማሪዎቹ የት እንዳሉ ጠየቅኩ’’ ትላለች። ስለ ስልጠናው መረጃ ያላቸው አለመሆኑና ዶርም መሆናቸው ተነገራት። ያኔ የዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆና እንዲህ ዓይነቱን ስልጠና ስትወስድ የስልጠናው አስተባባሪ ሴቶች ዶርም ድረስ መጥታ እሷና ጓደኞቿን በስልጠናው እንዲሳተፉ ማድረጓም ትዝ አላት። ወዲያው መረጃ አግኝተው የመጡት ሴት ተማሪዎችን በየአቅጣጫው በማሠማራት ዶርም ለቀሩት ሴት ተማሪዎች መረጃውን በማድረስ ቀስቅሰው እንዲያመጧቸው አደረገች። ከዚህ በኋላም በርካታ ሴቶች በስልጠናው ለመሳተፍ ቻሉ።
ስልጠናው ከስልክና ኮምፒውተር ጀምሮ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ያካትታል። ሁሉም ተመራቂ ተማሪዎች እንደተመረቁ ሥራ ከማያገኙባቸው ምክንያቶች አንዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክሂሎታቸው ላይ ክፍተት በመኖሩ ነው። ይህ ክፍተት ሴቶች በኢኮኖሚ ተጽእኖ ስለሚደርስባቸው ይበልጥ የሰፋ ነው። ስማርት ስልክ እንኳን የሌላቸው ብዙ ናቸው። ያላቸውም አጠቃቀሙን አያውቁትም።
ደረጃዶትኮም በአምስት ዓመት ቆይታው እዚህ ላይ ሁሉ ትኩረት አድርጎ በመሥራት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን አብቅቷል። ወደ ሥራ በመግባቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እንዲቋቋም ምክንያት ከመሆን ጀምሮ በመንግሥትም፣ በግል ቀጣሪ ድርጅቶችም የተመራቂ ተማሪዎች በተለይም የሴት ተመራቂዎች ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝና በልዩ መርሐ ግብር እንዲታገዝ አድርጓል።
በየገለጻዋ መካከል ‹‹ሴቶች ላይ መሥራት ማኅበረሰብና አገር ላይ መሥራት ነው›› የምትለው ሲሀም ‹‹እኛ ሴቶች ድፍር ብለን ስልጠና መውሰድና ቅጥር ላይ መሄድ አለብን›› ስትልም ምክሯን ትለግሳለች።
ደፍረው የሄዱትን ሴቶች አብነት በማድረግም በቀጣሪ ድርጅቶችም ከወንዶች ይልቅ ብቃት ያላቸውና ውጤታማ በመሆናቸው በእጅጉ ተፈላጊ እንደሆኑ ትገልፃለች። አብዛኞቹ ቀጣሪ ድርጅቶች ይሄንኑ እንደሚመሰክሩላቸውና ሴት ሠራተኞችን እንዲልኩላቸው የሚፈልጉና የሚጠይቁም መሆናቸውን ትናገራለች። እኛም የዛሬው ጽሑፋችንን በዚሁ፣ በሲሀም ሀሳብ እናጠቃልላለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014