ከግማሽ ምእተአመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በረጅም አመታት ጉዞው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲካሄድ ቆይቷል። በአንድ አጋጣሚ ብቻ ከአዲስ አበባ ወጥቶ 2005 አ.ም ላይ በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም መም ላይ ተካሂዷል። በዚያ ቻምፒዮናም በአንድ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ብቻ ነበር የተሻሻለው። በተረፈ በተለያዩ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ክብረወሰኖች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተመዘገቡት አዲስ አበባ ላይ ነው።
ዘንድሮ የአዲስ አበባ አንጋፋው ስቴድየም በእድሳት ላይ መገኘቱ ከተማዋ ትልልቅ ውድድሮችን እንዳታስተናግድ እንቅፋት የመሆኑን ያህል ከአትሌቲክስ አንጻር ይዞት የመጣው መልካም አጋጣሚም አለ። ይህም 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለሁለተኛ ጊዜ በሌሎች ክልሎች እንዲካሄድ ማድረጉ ሲሆን ቻምፒዮናው በአትሌቲክስ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በሚረዳ የአየር ጸባይ እንዲካሄድና ለረጅም አመታት ሳይደፈሩ የቆዩ ክብረወሰኖች በብዛት እንዲሰበሩ አድርጓል።
ቻምፒዮናው ከባህር ጠለል ከ2ሺ ሜትር በላይ ልኬት ካላት ቀዝቃዛዋ አዲስ አበባ ወጥቶ ከባህር ጠለል ከ1500 ሜትር በላይ በምትገኘዋና ሞቃት የአየር ንብረት ባላት ሐዋሳ በመካሄዱ ለረጅም አመታት ያልተደፈሩ በርካታ ክብረወሰኖች ሊሻሻሉ ችለዋል። ሐዋሳም በቀደሙት አመታት በአዲስ አበባ ብቻ የተመዘገቡ በርካታ ክብረወሰኖች የተመዘገቡባት ከተማ በመሆን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የታሪክ ተጋሪ ለመሆን
በቅታለች። ከክብረወሰኖቹ ባሻገር በተለያዩ ውድድሮች በርካታ አትሌቶች ያስመዘገቧቸው ሰዓቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ የሚያስችላቸው እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። ይህም ኢትዮጵያ ኦሊምፒክን ጨምሮ ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አትሌቶችን ለሰዓት ማሟያ(ሚኒማ) ወደ ኔዘርላንድስ ሄንግሎ በመውሰድ የማጣሪያ ውድድሮችን እንዲያከናውኑ የሚደረገው የተለመደ አሠራር ጥናቶች ተደርገው በአገር ውስጥ ሊሆን እንደሚችል እንደ ሐዋሳ ያሉ የአየር ንብረቶች ፍንጭ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሰኞ በሦስት አዳዲስ ክብረወሰኖች ታጅቦ የተጀመረው ቻምፒዮና ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅም በክብረወሰኖች ታጅቦ ነው። በዚህ ቻምፒዮና ለ18አመታት ያልተሰበረው የስለሺ ስህን የወንዶች 10ሺ ሜትር ክብረወሰንን ጨምሮ ለ16 አመታት ያልተደፈረው የሴቶች መቶ ሜትር ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል። በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ጾታ፣ በዲስከስ ውርወራ በሁለቱም ጾታ፣ በ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር በሁለቱም ጾታ አዳዲስ ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል። የወንዶች ስሉስ ዝላይ፣ የሴቶች መቶ ሜትር፣ የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድሮችም አዲስ ክብረወሰን ያገኙ ሆነዋል።
በቻምፒዮናው ከአስር በላይ ክብረወሰኖች ሲመዘገቡ ከሁለቱ በስተቀር ቀሪዎቹ በአዳዲስ አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው። ሁለት አትሌቶች ብቻ የራሳቸውን ክብረወሰን ማሻሻል ችለዋል። በሴቶች አሎሎ ውርወራ ከሦስት አመት በፊት በ2011 ቻምፒዮና አዲስ አበባ ላይ በመከላከያዋ አትሌት ዙርጋ ኡስማን 13.55 ሜትር ሆኖ የተመዘገበው ክብረወሰን ዘንድሮ በራሷ በዙርጋ ኡስማን 13.56 ሜትር ሆኖ የተመዘገው ክብረወሰን አንዱ ነው። ሌላው የሴቶች 20ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር ሲሆን አትሌት የኋልዬ በለጠው በ2009 አ.ም ለፌዴራል ማረሚያ ቤት ስትወዳደር በነበረበት ወቅት ያስመዘገበችው 1:32:39 ክብረወሰን ዘንድሮ ራሷ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በመሮጥ ከሰባት ደቂቃ በበለጠ ጊዜ(1:25:50.2) በሆነ ሰዓት ባለፈው አርብ ተሻሽሏል።
ባለፉት በርካታ አመታት በተለያዩ እርከኖች በሚካሄዱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነት የነበራቸው መከላከያና ኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ በርካታ ተፎካካሪ መጥቶባቸዋል። በተለያዩ ውድድሮችም ሁለቱ የቻምፒዮናው አውራዎች ያስመዘግቡ የነበረው ድል ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው በቀረቡት እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ደቡብ ፖሊስ በመሳሰሉ ክለቦች ሲነጠቁ ታይቷል። ታላላቅ ዓለም አቀፍ ክብር የተሰጣቸው የዓለም ቻምፒዮኖች ጭምር በዚህ ቻምፒዮና በአዳዲስ ቻምፒዮኖች ሲሸነፉ ታይተዋል። በተለይም በመጨረሻው የቻምፒዮና ቀን ሙክታር ኢድሪስ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ጌትነት ዋለንና ሌሎችም የዓለም ቻምፒዮኖችና ትልቅ ስም ያላየው አትሌቶች በ5ሺ ሜትር ፍጻሜ ለአዲሱ ቻምፒዮን አሊ አብዱልመና እጅ መስጠታቸው ያልተጠበቀ ክስተት ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014