በታላቋ አህጉር እስያ ለሁለተኛ ጊዜ፤ በዓረቡ ዓለም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የኳታር ዓለም ዋንጫ ሊካሄድ ወራት ብቻ ቀርተዋል። በዚህ የምድራችን ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር ላይም ተሳታፊ ከሚሆኑት 32 አገራት መካከል 29ኙ ተለይተዋል፤ የምድብ ድልድሉ ከትናንት በስቲያ ምሽት ታውቋል። የውድድሩ ባለቤት የሆነው ፊፋ ከአዘጋጅነት ምርጫው ጋር በረሃ ላይ የተመሰረተችው ዘመናዊቷ ሃገር ኳታር ደግሞ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱባቸው የቆየ ይሁን እንጂ፤ ለተቺዎቻቸው ጆሮ ባለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቆ የውድድሩ መጀመር በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።
የውድድሩ መጫወቻ ኳስ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራቹ አዲዳስ ያዘጋጀው መሆኑ ታውቋል። ከሰሞኑ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው ኳስ ‹‹አል ሪሃላ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ የዓረቦች ባህላዊ ልብስ የሆነው ነጭ ቀለም ከኳታር ባንዲራ ጋር ባጣመረ ቀለም የተዘጋጀም ነው። ‹‹ስፒድሼል›› የተባለ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ የተደረገበት መሆኑ የተነገረለት ኳሱ፤ ከፍተኛ ፍጥነትና የመተታጠፍ አቅም ያለው መሆኑ ታውቋል።
ዓለም ዋንጫው 32 አገራትን የማሳተፍ ምዕራፉ በዚህ ውድድር የሚዘጋ ሲሆን፤ ከአራት ዓመታት በኋላ በሚካሄደው ውድድር 48 አገራትን ለመጀመሪያ ጊዜ ይካፈላሉ። ይኸውም ባልተጠበቀና በአሳዛኝ ሁኔታ ከዓለም ዋንጫ ለሚቀሩ አገራት ተስፋን የሚያለመልም ሆኗል። ከሰሞኑ ተጠቃለው የታወቁት የውድድሩ ተሳታፊ አገራት ባሻገር አስደናቂ በሆነ መልኩ በመድረኩ የማይታዩ ቡድኖች ጉዳይ አነጋጋሪ ነበር። የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋና ዓለም ዋንጫን ለአራት ጊዜያት ያነሳችው ጣሊያን የዓለም ዋንጫ ተካፋይነት ጉዞዋ በማጣሪያው ተገቷል። ከዓለም ዋንጫው ስትርቅም ይህ ሁለተኛ ጊዜዋ ነው። ያለፈው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ የነበረችው ሩሲያ ደግሞ ከዩክሬን ጋር በገባችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት ከየትኛውም ውድድር የተገለለች አገር መሆኗ ይታወሳል።
በአምስት አገራት የምትወከለው አፍሪካ፤ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ እና ካሜሮን በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ትኬት መቁረጣቸውን እርግጠኛ ሆነዋል። በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ችሎታቸው የተሻሉ የሚባሉት እንደ ግብጽ፣ ኮትዲቯር፣ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ ያሉት አገራት አለማለፋቸው በእግር ኳስ ቤተሰቡ አስገራሚ ጉዳይ ነበር። ከሶስት ቡድኖች በቀር (ቡድኖቹ ባይታወቁም በምድብ 2፣ 4 እና 5 ተደልድለዋል) አብዛኛዎቹ ተሳታፊ አገራት መለየታቸውን ተከትሎም በተካሄደው የምድብ ድልድል አዘጋጇ አገር ኳታር በምድብ አንድ ከኢኳዶር ጋር የመክፈቻውን ጨዋታ እንደምታደርግ ታውቋል። ሴኔጋልና ሆላንድም በዚሁ ምድብ ተጠቃለዋል።
በምድብ ሁለት እንግሊዝ፣ ኢራን እና አሜሪካ ሲደለደሉ፤ በቀጣይ ከዩክሬን፣ ስኮትላንድ እና ዌልስ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ምድቡን ይቀላቀላል። የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ቻምፒዮናዋ የሜሲ አገር አርጀንቲና ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሜክሲኮ እና ፖላንድ ጋር በምድብ ሶስት ተገኝተዋል። ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ያነሳችው ፈረንሳይ ደግሞ ከዴንማርክ፣ ቱኒዚያ እንዲሁም እስካሁን ካልታወቀው ቡድን ጋር ተመድባለች። ምድብ አምስት የአራት ጊዜ ዓለም ዋንጫ ባለቤቷ ጀርመንን፣ ከስፔን፣ ጃፓን እና በቀጣይ ከሚታወቀው ቡድን ጋር አገናኝቷታል። በምድብ ስድስት ቤልጂየም፤ ከካናዳ፣ ሞሮኮ እና ክሮሺያ ጋር ተደልድላለች። የዓለም ዋንጫን ለአምስት ጊዜያት በመውሰድ አቻ ያልተገኘላት ብራዚል፤ በምድብ ሰባት ከሰርቢያ፣ ስዊዘርላንድ እና ካሜሮን ጋር ተሰልፋለች። የመጨረሻው ምድብ ላይ የሚገኙት አገራት ደግሞ ፖርቹጋል፣ ጋና፣ ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ መሆናቸው ታውቋል።
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ለሚካሄደው ውድድር ኳታር ዝግጅቷን አጠናቃለች። ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት በሌላው ዓለም ክረምት ይሁን እንጂ በኳታር ያለው ሙቀት አስቸጋሪ እንደሚሆን ከወዲሁ ይጠበቃል። ነገር ግን አገሪቷ ያዘጋጀቻቸው ስምንት ግዙፍ ስታዲየሞች እጅግ ዘመናዊና የአየር ሁኔታውንም መቆጣጠር የሚችል ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቃለች። 28ቀናትን በሚቆየው ውድድር ላይም 1ነጥብ5 ሚሊዮን የሚሆኑ ደጋፊዎች ይካፈላሉ በሚል ሲጠበቅ፤ ቁጥራቸው ከዚህ የሚልቁት ደግሞ ማረፊያቸውን በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አድርገው በ70 ደቂቃ የአየር በረራ ብቻ ጨዋታዎችን መመልከት እንደሚችሉም ተጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም