አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መጠነ ሰፊ ውድመት ካደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ሸዋሮቢት ሲሆን፤ ከመሠረተ ልማት ተቋማት ውስጥ ደግሞ የህክምና አገልግሎት መስጫዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ የጤና ተቋማትን አውድሟል፤ የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችንም ዘርፏል። በዚህም በሁለቱም ክልሎች በርካታ ሕዝብ ከህክምና አገልግሎት ተቆራርጧል።
ሆኖም አሸባሪ ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊቱ፣ በአማራና አፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በተወሰደበት እርምጃ ከሁለቱ ክልሎች ተጠራርጎ ከወጣ በኋላ በመንግሥትና በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ድጋፍ የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራዎች በስፋት ሲከናወኑ ቆይተዋል። በዚህም በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ የህክምና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዜጎች ማቅረብ ተችሏል።
በዚሁ ጦርነት ምክንያት ከተቆራረጡ አገልግሎቶች ውስጥ ታዲያ አንዱ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ሲሆን አንዳንድ ጤና ጣቢያዎች ከጦርነቱ በኋላ ዳግም አገግመው አገልግሎቱን በማስጀመር ለሌሎች አርአያ መሆን ችለዋል። ከነዚህ ውስጥም አንዱ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ቀወት ወረዳ፣ ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው የሸዋሮቢት ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ነው።
ወይዘሮ ወርቋ ንጉሴ በሸዋሮቤት ከተማ ልዩ ስሙ ዜሮ ሁለት ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናት። የሦስት ልጆች እናት ስትሆን የዕለት ጉርሷን የምታገኘው ጉልት ውስጥ በከሰል ንግድ ነው። ሆኖም ያጋጠማት የልብ፣ ጉበትና የሳምባ ህመም ሥራዋን እንደልብ ሊያሠራት አልቻለም። የልብ ህመሟ እስካሁን ባይሻላትም ታዲያ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆኗ ካጋጠማት የጉበትና የሳምባ ህመም መዳን ችላለች።
‹‹የጤና መደህን አባል ባልሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ በሽታዎች ተደራርበውብኝ በሕይወት የመቆየት ዕድሌ እጅግ ዝቅተኛ ነበር›› የምትለው ወይዘሮ ወርቋ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ትላለች። በየዓመቱ በማዋጣው ገንዘብ ሳልሳቀቅ በፈለኩት ጊዜ የፈለኩትን የህክምና አገልግሎት እንዳገኝ ዕድል ሰጥቶኛልም ትላለች።
እስካሁን እንኳን ለህክምናዋ ከ400ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ይህም የተሸፈነው በጤና መድህን አባልነት መሆኑንም ትጠቁማለች። ከዚህ አንፃር ሰዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል ቢሆኑ ካላስፈላጊ የህክምና ወጪ እንደሚድኑና ገንዘብ ሳይኖራቸው በአነስተኛ መዋጮ ብቻ የህክምና አገልግሎት ስለሚያገኙ ዛሬ ነገ ሳይሉ አባል ሁኑ ስትልም ወይዘሮ ወርቋ ትመክራለች።
ወይዘሮ ቦጋለች ሽመልስም በተመሳሳይ የሸዋሮቢት ከተማ፣ ዜሮ ሁለት ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን በአነስተኛና ጥቃቅን የሻይ ዳቦ ንግድ ትተዳደራለች። የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆኗ ከምትኖርበት ሸዋሮቢት ከተማ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ የመጀመሪያ ልጇን የማሳከም ዕድል እንዳገኘች ትገልፃለች። አሁንም ሁለተኛ ልጇ ታሞ ለማሳከም ወደ ሸዋሮቢት ጤና ጣቢያ እንደመጣችና የጤና መድህን አባል ከሆነች ሁለት አመት እንደሆናት ትናገራለች።
‹‹ጤና መድህን ለእኛ የቁም እድራችን ነው›› የምትለው ወይዘሮ ቦጋለች እርሷን ጨምሮ መላው ቤተሰቧ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆኑ እፎይታን እንዳገኘች ትገልፃለች። ሌሎችም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል ቢሆኑ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንደማይሆኑ ትመክራለች።
የሸዋሮቢት ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ አስማረ ዘበነ እንደሚሉት ተቋሙ በወረራው ወቅት ኢላማ ከተደረጉትና ዝርፊያና ውድመት ከደረሰባቸው ውስጥ አንዱ ነበር። ሆኖም ወረራው ከተቀለበሰ በኋላ በመንግሥት፣ በተለያዩ አጋር ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ዳያስፖራዎች ድጋፍ የተለያዩ መድኃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን ለተቋሙ ማሟላት ተችሏል። በዚህም ተቋሙ አገግሞ የጤና መድህን አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል።
በዚህም ከሸዋሮቢት ከተማ በዘንድሮው ሁለት ሩብ አመታት ውስጥ 15ሺህ 372 ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋሙ መጥተው በጤና መድህን ተገልግለዋል። ከቀወት ወረዳ 1ሺህ 572፣ ከጣርማ በር ወረዳ 260 ታካሚዎች እንዲሁም ከኤፍራታ ግድም 568 ታካሚዎች በጤና መድህን የህክምና አገልግሎት በጤና ተቋሙ አግኝተዋል።
ይህ አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን ደግሞ ከሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር በዚህ ሁለት ሩብ ዓመት 937ሺህ 209 ብር በጤና መድህን ተጠቅመዋል። ከቀወት 900ሺህ 300 ብር፣ ከጣርማ በር 16ሺህ 67 ብር፤ እንዲሁም፣ ከኤፍራታ 27ሺህ 17 ብር በሁለቱ ሩብ አመታት በጤና መድህን የህክምና አገልግሎት ተጠቅመዋል።
በጣቢያው ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እጥረት ይታያል። 30 ከመቶ የሚሆኑ የመድኃኒት ዓይነቶችም በጤና ተቋሙ የሉም። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት መድኃኒቶችን ማግኘት አለመቻልና በውጪ የሚሸጡ መድኃኒቶች ውድ መሆናቸው ነው። ይሁንና በተቻለ አቅም ሁሉንም ዓይነት ጥረቶችን በመጠቀም መድኃኒቶችን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014