እንደኩላሊት ታታሪ የሆነ የሰውነት ክፍል የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ኩላሊት በሰውነት ውስጥ ያሉ ቆሻሻዎችንና ተጨማሪ ፈሳሾችን አጣርቶ በሽንት መልክ ስለሚያስወግድ ነው። ኩላሊት በሰውነት ሴሎች የሚመረቱ አሲዶችን በማስወገድ በሰውነት ውስጥ የተመጣጠነ ውሃ፣ ጨውና ሶዲየም፣ ካልሺየም፣ ፎስፈረስና ፖታሺየም የመሳሰሉ ሚኒራሎች እንዲኖሩም ያስችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ አእምሮ የተወሳሰበ የሰውነት ክፍል ሲሆን አስተሳሰብን፣ የማስታወስ ችሎታን፣ ስሜትን፣ ንክኪን፣ የሰውነት ጡንቻ የመንቀሳቀስ ችሎታን፣ ራዕይን፣ መተንፈስን፣ ሙቀትን፣ ረሃብን እና ሌሎች የሰውነት እንቅስቃሴ ሂደቶችን ይቆጣጠራል። ከዚህ አንፃር አእምሮ ወሳኝ የሰውነት ክፍል ሆኖ ይቆጠራል።
ሆኖም በዓለም አቀፍ ዙሪያ በርካቶች የኩላሊትና የአእምሮ ጤና ችግር አጋጠመን ሲሉ ይደመጣሉ። እነዚህ ሁለት ወሳኝ የሰውነት ክፍሎች በአግባቡ ሥራቸውን እንዲከውኑና ከበሽታም እንዲጠበቁ ለእነሱ የሚስማሙ ምግቦችን መመገብ ይጠይቃል።
በተለይ ደግሞ ተፈጥሯዊ ምግቦችን መመገብ የኩላሊትና የአእምሮ ጤናን በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የሥነ- ምግብ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ፈሊክሎድድ /fleekloadede.com/ ያወጣው መረጃ ደግሞ ከታች የተዘረዘሩት ሦስት ተፈጥሯዊ ምግቦች ለኩላሊትና አእምሮ ጤና ፍቱን መድኃኒት ናቸው ይላል።
1ኛ፡- ቱና እና ሳለሞን ዓሣዎች
እነዚህ የዓሣ ዝርያዎች በበርካታ ማዕድናት በተለይ ደግሞ የደም ግፊትን ለመቀነስ በሚረዱ ኦሜጋ-3 የበለፀጉ በመሆናቸው የኩላሊትዎንና የአእምሮውን ጤና መጠበቅ ከፈለጉ የዘወትር ምግብዎ ያድርጓቸው። ምን አልባት እንደነዚህ ዓይነት የዓሣ ዝርያዎችን ላያገኙ ቢችሉ እንኳን እዚሁ አገርዎ ያለውን ዓሣ የመመገብ ባህሉን ካዳበሩ የኩላሊትና የአእምሮ ጤናዎን በቀላሉ መጠበቅ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ የደም ግፊትዎ ከፍተኛ ከሆነ የኩላሊት
ህመም ሊኖርብዎት ስለሚችል ዓሣን አዘውትረው እንዲመገቡ በጤና ባለሞያዎች ይመከራሉ።
2ኛ፡- እንጆሪ
የኩላሊትዎንና የአእምርዎን ጤንነት ለመጠበቅ መመገብ ካለብዎ ምግቦች ውስጥ ሌላኛው የእንጆሪ ፍሬ ነው። እንጆሪ ሲባል ታዲያ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን
ሁሉንም የእንጆሪ ዓይነቶች ያካትታል። የእንጆሪ ፍሬ በአንቲኦክሲደንት የበለፀገ በመሆኑ በተለይ የኩላሊትዎን ጤና በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት ይህን ፍሬ አዘውትረው እንዲመገቡ ይመከራሉ።
3ኛ፡- ለውዝ
የአእምርዎን ጤንነት ከሚጠብቁ ምግቦች ውስጥ አንዱ ለውዝ ነው። ለውዝ በአንቲኦክሲደንት በተለይ ደግሞ በቫይታሚን ኢ የበለፀገ በመሆኑ በአእምሮ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ህመሞችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እርስዎም ለውዝ ለማግኘት እምበዛም ስለማይቸገሩ የዘወትር ምግብዎ ቢያደርጉት ያተርፋሉ እንጂ አይከስሩም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014