ከአስር አመት በኋላ መኝታ ክፍሌ አልጋ ውስጥ ያስቀመጥኩትን የወረቀት ፋይል አገላብጣለሁ። ዩኒቨርሲቲ እያለሁ የማነባቸውን መጽሐፍቶች፣ የተማርኩባቸውን አንዳንድ ደብተሮች እያየሁ የትዝታ አለንጋ ገረፈኝ። ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ ጀምሮ እጄን ወደ አልጋዬ ሰድጄ አላውቅም። ዛሬ ምን ወደዛ እንደሰደደኝ አላውቅም፤ ትዝታዎቼ በአእምሮዬ ውስጥ እንጂ እንዲህ አካል ለብሰው ወረቀት ላይ አገኛቸዋለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር። አልጋዬ ስር ባስቀመጥኩት ትናንቴ ወደ ተውኩት አምና ተሰደድኩ።
የትዝታ ተጠቂ ነኝ፤ ትናንትና ምንም ይሁን ከነግሳንግሱ ይናፍቀኛል። ነገ የትናንትን ያህል ናፍቆኝ አያውቅም። ዘንድሮ ያምናን ያህል ብርቅ ሆኖብኝ አያውቅም። በእኔ ሕይወት ውስጥ ዛሬ ነገ ሲሆን ሁሉም ትዝታ ነው። ከሙዓለ ሕፃናት እስከ አሁን ድረስ ያለው ትናንት፣ ያለው አምና፣ ያለው ድሮ ናፍቆቴ ነው። ትናንትን አንቆ መግደል አቅቶኛል።
ብዙ ነገሮችን አየሁ፤ የረሳኋቸውን ብዙ ነገሮች አስታወስኩ። ደብተሬ ላይ የብዙ ጓደኞቼ የእጅ ጽሑፍ ነበር። ክፍል ውስጥ ማድመጥ እንጂ መጻፍ አልወድም ነበር፤ ለዚህም ክፍል ውስጥ እኔ ደብተር ላይ ያልጻፈ አንድም ተማሪ አልነበረም።
ትናንትናዬን ገለጥኩት፤ ዛሬም ድረስ የማይረሳኝን የመክሊትን የእጅ ጽሑፍ ደረስኩበት። መክሊት የክፍላችን ብቻ አይደለችም፤ የዩኒቨርሲቲያችን ብቸኛ ቆንጆ ተማሪ ነበረች። ዛሬም ድረስ የእሷን ዓይነት ቆንጆ ሴት አላየሁም። ድሮዊንግ አስተማሪያችን በእሷ ምክንያት ‹ኤፍ› እስከሰጠኝ ጊዜ ድረስ ተለያይተን አናውቅም ነበር።
አይ ቲቸር ሞገስ፤ ቲቸር ሞገስ ድሮዊንግ አስተማሪያችን ነው፤ ክፍል እንደገባ የመጀመሪያ ሥራው ወዳለችበት ተራምዶ አጠገቧ መቆም ነው። ከዚያ በኋላ ነው ጥቁር ሰሌዳው ላይ የሆነ ነገር ስሎ የሚያስተምረን። ከእኔ ኋላ ስለምትቀመጥ አጠገቧ ሲቆም ጥላው ያርፍብኛል። ዛሬም ድረስ የሚጠርነኝ ሽቶው ይሸተኛል። ሰማይ የተደፋብኝ ያህል ክብድ ይለኛል። ወንድነቱ ነፍሴ ላይ ያርፋል። ሰው እንዴት ያንን ያህል ይገዝፋል? ሳይናገር፣ ሳያወራ፣ ቃል ከአፉ ሳያወጣ የኔን ነፍስ ያስጨንቃታል።
እሱ ጎልያድን እኔ ደግሞ ዳዊትን ሆነን እዚያ ስፍራ ለአንድ አመት ተሰቃይቻለሁ። ከአጠገቤ እብስ ሲል እንደ ዳዊት በጠጠር ያባረርኩት ነበር የሚመስለኝ። በነጋታው አጠገቤ ጥላው አርፎብኝ ሳየው ጎልያድ ፊት እንደ ቆመው ኮሳሳው ዳዊት እኮስሳለሁ።
ቲቸር ሞገስ የመክሊትን ስም ሳይጠራ አስተምሮን አያውቅም። ዛሬም ድረስ ያልገባኝ ነገር የሴት ስም ለአንድ ድሮዊንግ ምሳሌ ሆኖ መቅረቡ ነው። አመት ሲያስተምረን ከመክሊት ስም ሌላ ምሳሌ ተጠቅሞ አያውቅም። እኛ ክፍል ኤክስና ዋይ የሚያርፉት በድሮዊንግ ክላስ በመክሊት ስም ነው።
ኤክስና ዋይ ነፍስ ቢኖራቸው ኖሮ መክሊትን የሚያመሰግኑ ይመስለኛል። ክላስ ውስጥ በእሷ ምክንያት ለሰባት ልጆች ‹ኤፍ› ሰጥቷል.፤ ከዚያ ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ። በአንድ ቆንጆ ሴት ምክንያት ምንም የማናውቅ የሰባት ወንዶች ህልም መደናቀፉ ዛሬም ድረስ ያናድደኛል። ቲቸር ሞገስ ለምን መምህር እንደሆነ አላውቅም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መክሊትን ፈራኋት፤ ግዝት እንዳለበት ሰው በመቶ ሜትር ነበር የምርቃት። እስከተመረቅንበት ጊዜ ድረስ አውርቻት አላውቅም። የምርቃታችን ጊዜ ከአዳራሽ ስወጣ ጠብቃ አንድ ነገር አለች፤ ‹ከእንግዲህ እኮ አንገናኝም፣ ነገ ለእኔና ለአንተ ሌላ ቀን ነው፤ ከአንተ ጋ አንድ ማስታወሻ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ አለችኝ።
ዝም ብዬ ፊቷ ቆምኩኝ፤ ያ ቀን ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቷ የቆምኩበት ቀን ነው። በደንብ አየኋት፤ እንደ ዛ ቀን ውብ ሆና አይቻት አላውቅም። ፊቷ ላይ ውበቷን ያደመቁ ብዙ ዓይነት ቀለሞች ይታዩኛል። ቅንድቧ በቀጭን ተቀንድቧል፣ ዓይኖቿ ዙሪያ ገባውን ተኩለዋል። ጉንጮቿ በወዛማ ቀለም ልመዋል። ከንፈሯ እንደምትወደው በማውቀው፣ ሰማይ ቤት ድረስ ይዛው በምትሄደው ቀይ ቀለም ደምቋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ዓይኖቿ ይስቃሉ፣ ጠንበለል አካሏ ይቁነጠነጣል።
‹ነገ ሲሆን ሁሉም ሌላ ነው…የአሁን ማለዳዎች በኋላ የሚመሹ ናቸው። ነገ በሚደበዝዙ አጋጣሚዎች ልትለያት አንድ ቀን የቀረህን ጓደኛህን አታሳዝናት› ስትል ሰማኋት። ልቤ አራራልህ አለኝ። በሕይወቴ ሁሉም ቦታ ያለች ሴት ሆና ግን ጨከንኩባት። የነፍሴ ቦታ ቢታይ..የልቤ ስፍራ ቢፈተሽ እሷ ብቻ ናት ግን ፊት ነሳኋት።
ዓይኖቿ ይማጸኑኛል…ዓይኖቼ ይሸሹዋታል። ከየት እንዳመጣሁት የማላውቀው እንቢ ልላት የሚያስችል ብዙ ኃይል ነበረኝ። ዕድሜ ለቲቸር ሞገስ እንደ አራስ ነበር እንድፈራት አድርጎኛል። በዚያ በመጨረሻ ሰዓት አንድ ፎቶ እንነሳ ብላ ከነጋዋኗ ፊቴ ስትቆም ትቻት ነበር የሄድኩት። ያ ቀን ሁሌም ይቆጨኛል። ምነው እሺ ባልኳት ስል አስባለሁ። ዛሬ ላይ ከእሷ ይልቅ እኔ ነበርኩ ያ ፎቶ የሚያስፈልገኝ እላለሁ። ከእሷ ጋር ለመታረቅ ያ ቀን ትክክለኛ ጊዜ ነበር። ያን ያህል ለምን እንደጠላኋት አላውቅም። በጣም የሚገርመው ደግሞ በሸሸኋት በነዛ ሁሉ ቀናት ውስጥ ልታናግረኝ ስትከተለኝ እንደነበረኝ አስታውሳለሁ።
አሁን ላይ ልቤ ይቅር ብሏት ቢሆን ኖሮ እላለሁ። አሁን ላይ አንድ አይደለም ከእሷ ጋር ለቁጥር የሚታክቱ ፎቶዎች ኖረውኝ ቢሆን እላለሁ። በተለያየንባቸው አስር አመታት ውስጥ ሳላስባት የቀረሁበት ጊዜ አልነበረም። እሷም ይሄን ስለምታውቅ ነው መሰለኝ ትናንትና ዛሬ አንድ ዓይነት አይደሉም ያለችኝ። ከሰው ልጅ ቀድሞ ሕይወት የገባት ሴት ትመስለኛለች።
ትናንት ላይ ሆና ዛሬዬን አይታልኛለች። ባሳለፍኩት አስር አመታት ውስጥ ነፍሴ እንደ እሷ የተራበችው ሰው የለም። እኔም በእሷ የተራቆትኩትን ያህል በምንም አልተራቆትኩም። አሁን የት እንዳለች አላውቅም፤ ይሄ ሁሉ ዘመን አልፎ እንኳን ከውስጤ አልደበዘዘችም፤ ፊቴ ቆማ አንድ ፎቶ እንነሳ እንዳለችኝ እኔም አንድ ቀን ፊቷ ቆሜ እባክሽ ፎቶ እንነሳ የምልበት ቀን ይመጣል እላለሁ።
ምድር ላይ ዳግም እኔና እሷ እዛ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ እዛ ክፍል፣ እዛ አዳራሽ በር ላይ ብንፈጠር እላለሁ። እዛ ክፍል በቲቸር ሞገስ ብንማር እላለሁ። ስለ እሷ የማይሆን ነገር አስባለሁ።.
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2014 ዓ.ም