ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በዚህም የቻይና ኩባንያዎችም በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ቀዳሚ ተዋናዮች በመሆን 43 ቢሊዮን ብር ፈሰስ እያደረጉ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከቻይናና ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጨመሩን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን ፤ በኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርና ትስስር መፈጠሩን፤ ይህን ተከትሎ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸው የሁለቱ ሀገራት ትስስር እየጎለበተ መሆኑን አመላካች ነው።
በኢትዮጵያ ፈሰስ የተደረገውን የቻይናውያንን ኢንቨስትመንት ከሌሎች ሀገራት ጋር ስናነጻጽረው የላቀ ነው። በዚህም ኩባንያዎቹ በአገሪቱ ዕድገት ላይ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ያመለክታል። በተጨማሪም በርካታ ኩባንያዎች ከእስያ፣ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓና አውስትራሊያ ወደ አገሪቱ እየገቡ መሆኑን ያመላክታል። ነገር ግን በርካታዎቹ ኢንቨስተሮች ከቻይና የሚመጡ ሲሆኑ የዚህ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም መሆኑንም መረጃው ያመለክታል።
የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ባላት አዎንታዊ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ በምሥራቅ አፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ጠቅሷል። ከአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ኮንጎና ሞሮኮን በመከተል አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የመረጡበት ምክንያት አገሪቱ ምቹ የሆኑ የኢኮኖሚ መዳረሻዎች ያሏት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ ባለቤት ከመሆኗ ባለፈ ምቹ የሆነ የገበያ ዕድል ያለባት አገር በመሆኗ ነው። ከዚህ ባለፈ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጣም አስፈላጊ የሆነውን መሠረተ ልማት አሟልታ መያዟንም ተመራጭ ከሚያደርጓት ጉዳዮች መካከል ነው።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በቻይናውያን ኩባንያዎች ተይዘው ወደ ሥራ የገቡና በዝግጅት ላይ የሚገኙ አንድ ሺ 564 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮች ሲሆኑ በፕሮጀክት ቁጥርና በፋይናንስ አቅርቦት ቀዳሚ መሆናቸውንም መረጃው ያመላክታል።
ከላይ ባስቀመጥነው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተሮችን መሳቧ ምን ይጠቅማታል? ለህዝቡስ ምን ጠብ የሚል ነገር ያመጣል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። ይሄንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ይዘን የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ብርሃነ መዋን አነጋግረናል። እሳቸውም ሀገር በተስተካከለ የኢኮኖሚ መደላደል ላይ እንድትቀመጥ የማምረት አቅም ከአገልግሎቱ ዘርፍ መብለጥ ይኖርበታል። ስለዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሀገሪቱ መግባታቸው ክፋት የለውም ይላሉ።
መጀመሪያ ከመግዛት በፊት መስራት መፍጠር ለገበያ የሚቀርብ ነገር መኖር ይኖርበታል የሚሉት አቶ ብርሀነ፤ እንዳለመታደለ ሆኖ ሀገሪቱ በርካታ ፋብሪካዎች ከሚኖሯት ይልቅ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሞልተው ይገኛሉ። እነሱም ለአገልግሎታቸው የሚሆነውን ምርት በሀገር ውስጥ ገበያ ስለማያገኙ የውጭ ገበያን ማማተር ይኖርባቸዋል።
ለዚህም ደግሞ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት የግድ የሚል ይሆናል። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ጉዳይ ደግሞ በአብዛኛው በእርሻ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ካለው ውስን የውጭ ምንዛሪ ላይ አብዛኛውን የአገልግሎት ዘርፉ ከወሰደው ለእድገት ፤ ለቴክኖሎጂ በጣም አስፈላጊ ለሚባሉ ነገሮች የሚወጣ ገንዘብ አይኖርም። ስለዚህም ግብርናውንም ቢሆን እሴት ጨምሮ የተሻለ ምንዛሪ የሚያስገኝ የሀገር ውስጥን ፍላጎት በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች በተመረቱ ነገሮች ለመሸፈን ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸው ግድ የሚል መሆኑን ይናገራሉ።
የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ሲገቡ ትልቁ ነገር ካፒታል ይዘው መግባታቸው ነው። ፋብሪካቸውን አቋቁመው ስራ ሲጀምሩ በርካታ ሰዎችን መቅጠር፤ በግብር የሀገር ኢኮኖሚን መደገፍ ብሎም ምርታቸውን ወደ ውጭ ሀገር ሲልኩ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ማምጣት በኢንቨሰትመንቱ እናገኛቸዋለን ብለን ከምናስባቸው ጥቅሞች መካከል መሆናቸውን አቶ ብርሃነ ያብራራሉ።
ይህም ትክክለኛ የሆነ ፖሊሲ ማስቀመጥ ከተቻለ የሀገር ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር እንዲገቡ ከተደረገ ይዘውት የሚመጡት ቴክኖሎጂ ሀገር ልታሳካው የምትፈልገውን የኢኮኖሚ መደላድል ከመፍጠር አንፃር ጠቀሜታ አለው። ኢንቨስተሮቹ ስራቸውን ጨርሰው ለቀው የሚሄዱ ከሆነም ኢትዮጵያውያን በስራው ውስጥ ገብተው መስራት የሚችሉበት አቅም ቢፈጠርላቸው ውጤቱ የላቀ እንደሚሆን አቶ ብርሃነ ያስረዳሉ። ይህም እንዲሆን የውጭ ኢንቨስተሮች በአቋቋሟቸው ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች በቀጣይ ሊያሰራቸው የሚችል በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ስርአትም ሊኖር ይገባል።
የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ ሲገቡ በቴክኖሎጂ፤ በእውቀት ሽግግር ሀገሪቱ በቀጣይ ልትጠቀምበት የምትችለውን ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸት ሀገሪቱ ለምታልመው ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መደላድል ይፈጥራል። የውጭ ባለሃብቶች በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ካልተመቻቸ የሰሩትን ስራ ትርፍ ወደ ሀገራቸው ይዘውት መሄዳቸው የማይቀር መሆኑን በመረዳት ወደ ሀገር በመግባታቸው የሚገኘው ተጠቃሚነት እየቀነሰ እንዳይሄድ አግባብነት ባለው ፖሊሲ ዘርፉ መመራት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።
ይህም ሲባል የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ ሲገቡ በርካታ ስራ አጦችን የሚቀጥር ኩባንያ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህ በላይ ግን የሰራተኛ ቅጥሩ በደንብ የተጠናበት የሰራተኛውን መብት መጠበቅ ያለበት መሆኑን ይናገራሉ። የውጭ ምንዛሪን ለማምጣት ኤክስፖርት ገበያ ከታሰበ ሊመጣ ይችላል። በትኩረት መታየት ያለበት ጉዳይ ግን የውጭ ምንዛሪ ማምጣቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ያስወጣል ወይ የሚል ጥያቄ መጠየቅ አለበት። ምን ያህል ጥሬ እቃ ነው ከውጭ የሚያስገባው? የሀገር ውስጥ ምርትን እንደግብአት ይጠቀማል ወይ? ምርት ወደ ውጭ መሄዱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ የሚተርፍስ ይሆናል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆን ይኖርበታል። ይህ ሲባል የሀገር ውስጥ ህዝብ እየተራበ ወደ ውጭ ለውጭ ምንዛሪ ሲባል ከመላክ ለሀገር ውስጥም የሚተረፍ ነገር ሊኖር ይገባል። የሀገርን ጥቅም ያስቀደመ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፖሊስ ሊኖር እንደሚገባ አቶ ብርሃነ ያብራራሉ።
ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ እንደ ትልቅ ቁም ነገር መታየት ያለበት ኢትዮጵያ በማንኛውም አይነት የፍላጎት ምርቶች ራሷን መቻሏ ነው፤ ትልቁ ሀገርን በዘላቂነት የሚጠቅመው ይሄ ነው። በጊዜያዊነት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፣ ሰራተኛ ለመቅጠር ሊሆን ቢችልም ትልቁ ቁም ነገር የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ማረጋገጠ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ተጠናክሮ ኢኮኖሚውን መያዝ ሲችል ያኔ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መፍጠር የሚቻል በመሆኑ ዘርፉ ትኩረት ይሻል ይላሉ።
በውጭ ኢንቨስተሮች ላይ የሚንጠለጥል ኢኮኖሚ በቀላሉ የሚፍረከረክ ይሆናል። የአለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ መንጠልጠል እነሱ ባኮረፉ ቁጥር አንታዘዝም ባልን ቁጥር፣ እርዳታ እና ብድር እናቆማለን ከሚሉ ማስፈራሪያዎቻቸው ባሻገር ኢንቨስትመንታችንን እናወጣለን በማለት ይወጣሉ። በተለያዩ ጊዜያቶች የውጭ ኢንቨስትመት በፖለቲካ የሚጠለፍበት ሁኔታ መኖሩንም የሰሞኑ የሩስያና የዩኩሬን ጦርነት ታላቅ ምስክር መሆኑን ይናገራሉ። በአጠቃላይ የውጭ ኢንቨስተሮች መምጣታቸው ችግር ባይኖረውም በዘላቂነት ግን የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ቀዳሚ ሆኖ ሌሎቹ ተከታዮች መሆን ይገባል።
የውጭ ባለሃብት መሳብ ጥሩ ቢሆን የሚመጡበት ምክንያት ግን ግልፅ ሆኖ መቀመጥ አለበት። የሚመጡበት አለማ ግልፅ ይሁን ሲባል፤ ባለሀብቱ በመምጣቱ ሀገሪቱ የምታተርፈው ምንድነው የሚለው መታየት አለበት። የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መዋእለ ነዋያቸውን አፍስሰው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጠብ የሚል ነገር የሚያበርክቱ ከሆነ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።
አሁን ላይ የሚታየው በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶች በይበልጥ ለውጮቹ የበለጠ ድጋፍ መደረጉ ከላይ እንዳልነው ኢኮኖሚው የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲጠለጠል ያደርገዋል ማለት ነው። ስለዚህም ይዘው ለሚመጡት ነገር ተመጠጣኝ የሆነ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሀገርን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የተለየ ድጋፍ ሊደረግላቸው የማይገባ መሆኑን አቶ ብርሃነ ያስረዳሉ።
“ሀገሪቱ ውስጥ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ምን ይጎለዋል? ምን ቢደረግለት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይደርሳል? በሚል የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናት ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ብርሃነ፤ ጥናት ላይ ተሞርክዞ ትክክለኛ ጉድለቱ ከታወቀ በኋላ ፖሊሲው ጥናትን መነሻ አድርጎ የሚወጣ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። ጉድለቶች እየታዩ ለኢንዱስትሪዎቹ የተለያዩ ድጋፎች ሲደረጉ ሀገሪቱን የማይጎዳ ሌሎችንም በተለየ የማይጠቅም መሆን የሚኖርበት ሲሆን የግድ አስፈላጊ የሆኑ የሚባሉ ነገሮችን ግን በጥናት አይቶ መደረግ ያለበትን ማድረግ ይገባል የሚል ምክረሀሳብ አላቸው።
በአጠቃላይ ዘርፉ የታሰበውን ያህል ከፍ እንዳይል አሁን ሀገሪቱ ያለችበት የጸጥታ ችግር ነው የሚሉት አቶ ብርሃነ ፤ ይህ ማለት ሰው ገንዘቡን አፍስሶ ስራ ለመስራት የተመቻቸና ሰላም የሚሰጥ የስራ አካባቢ እንዲኖር መንግስት ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል።
“የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅጣጫ የውጭ ባለሀብትን ማስገባት ከሆነ እሱ ጥሩ ነው ፤ ሀገሪቱን በዘላቂነት ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልና በውጭ ላይ ያለን ጥገኝነት በመቀነስ በራስ መተማመን እንዲኖር ለማድረግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ለዚህም የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ የማበረታታት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።” ብለዋል።
በቅርቡ በሀገሪቱ በስንዴ እርሻ ላይ የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን የተናገሩት አቶ ብርሃነ፤ የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት በሀገር መሸፈን ከተቻለ መሰረታዊ ፍላጎቶቻችንን ከውጭ የማንፈልግ ከሆነ ለቴክኖሎጂና አዲስ ነገር ለማግኘት የውጭ ኢንቨስተሮች መጋበዝ ጉዳት አይኖረውም።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት ችግር ሲመጣ ወደ ውጭ ከማየት የሚያድን መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ ዘይት ችግር ሆኖ መነሳቱ በጣም ያሳዝናል። ከ20 አመታት በፊት በየአካባቢው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ያቀርቡ የነበሩትን ማስወገዱ ስህተት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥን አቅም ሊያሳድግ ይገባል ብለዋል።
ባጠቃላይ መንግስት በተለይ መሰረታዊ በሆኑ ፍጆታዎች ምርት ላይ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ቢያበረታታ በተጨማሪነት ግን ለተሻሉ ቴክኖሎጂዎች የሚያመጣ፤ ለበርካታ ስራ አጦች የስራ እድል የሚሰጥ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ ጠቀሜታቸው ከሚያስወጡን በላይ ከሆነ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ መግባታቸው የሚበረታታ ነው በማለት ቆይታችንን ቋጭተናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014