የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለ51ኛ ጊዜ በሐዋሳ ከተማ ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል። የሻምፒዮናው ጅማሬም በሜዳ ተግባራትና ረጅም ርቀት ውድድሮች ክብረወሰን ደምቋል።
የሻምፒዮናው የመጀመሪያ ቀን ውሎ በበርካታ ውድድሮች የፍጻሜና የማጣሪያ ፉክክር የታጀበ ሲሆን ሁለት የሜዳ ተግባራትና አንድ የረጅም ርቀት ውድድሮች የኢትዮጵያ ክብረወሰን የተሰበረባቸው ሆነዋል።
የሴቶች አሎሎ ውርወራ ውድድር አዲስ ክብረወሰን የተሰበረበት የመጀመሪያው ፉክክር ነው። ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 ሻምፒዮና አዲስ አበባ ላይ በመከላከያዋ አትሌት ዙርጋ ኡስማን 13.55 ሜትር ሆኖ የተመዘገበው የኢትዮጵያ ሴቶች አሎሎ ውርወራ ክብረወሰን ዘንድሮ 13.56 ሜትር ሆኖ ተሻሽሏል።
ክብረወሰኑን ያሻሻለችውም የቀድሞዋ ባለክብረወሰን ራሷ ዙርጋ ኡስማን ናት። የመከላከያዋ አትሌት በክብረወሰኑ ታጅባ ያሸነፈችውን ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት መርሃዊት ጸጋዬ 12.24 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላኛዋ የመከላከያ አትሌት አመለ ይበልጣል ደግሞ 12.16 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ በመሆን አጠናቃለች።
የውድድሩን መክፈቻ በክብረወሰን ያደመቀው ሌላኛው ውድድር የወንዶች ስሉስ ዝላይ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌት የሆነው ክችማን ኡጅሉም የውድድሩ አዲሱ የኢትዮጵያ ባለክብረወሰን ነው። ክችማን 16.03 በመዝለል አዲስ ክብረወሰን ሲያስመዘግብ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አትሌት ዶል ማች 15.79 ሜትር በመዝለል የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
15.54 ሜትር የዘለለው የኦሮሚያ ክልል አትሌት በቀለ ጅሎ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ፈጽሟል። የቀድሞው የኢትዮጵያ የወንዶች ስሉስ ዝላይ ክብረወሰን በ2011 አዲስ አበባ ላይ እንደተመዘገበ የሚታወስ ሲሆን የመከላከያው አትሌት አዲር ጉር 15.88 ሜትር በመዝለል ነበር ያስመዘገበው።
በሻምፒዮናው ሳይጠበቅ የተሻሻለው ትልቅ ክብረወሰን የወንዶች አስር ሺ ሜትር ነው። ይህን ክብረወሰን ትልቅ ያደረገውም ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ሳይሰበር መቆየቱ ነው። በ1996 አም አዲስ አበባ ላይ ጀግናው አትሌት ስለሺ ስህን ለፌደራል ማረሚያ ቤት እየሮጠ ያስመዘገበው 28:16:23 ሰዓት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ሳይሰበር ቆይቷል።
ዘንድሮ ግን ይህን ክብረወሰን የሚደፍር አትሌት ከደቡብ ፖሊስ ክለብ ተገኝቷል። አትሌት ታደሰ ወርቁ የርቀቱ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ብቻም ሳይሆን ያስመዘገበው 28:11:92 ሰአት አዲስ ክብረወሰን መሆን ችሏል። ታደሰን ተከትሎ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ በአምስት ሺ ሜትር ብቸኛ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረው አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ 28:27:26 በሆነ ሰዓት ኦሮሚያ ክልልን የብር ሜዳሊያ ባለቤት አድርጓል። ገመቹ ዲዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ28:29:93 በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆኗል።
በተመሳሳይ አስር ሺ ሜትር ሴቶች ትናንት አዲስ የኢትዮጵያ ክብረወሰን መመዝገቡ የዘንድሮው ሻምፒዮና በክብረወሰን እንዲደምቅ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በርካታ የአገር ውስጥ ውድድሮችን በማሸነፍ አስደናቂ ብቃት እያሳየች የምትገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚያብሔር 31:21:48 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ የርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤትም ሆናለች።
ቀደም ሲል የርቀቱ ክብረወሰን በትራንስ ኢትዮጵያዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ2011 አም አዲስ አበባ ላይ የተመዘገበ ሲሆን ሰአቱም 32:10:13 ነበር። ባለክብረወሰኗ ግርማዊት ኮከብ በሆነችበት ውድድር የመከላከያዋ አትሌት ሃዊ ፈይሳ 31:21:48 በማጠናቀቅ የብር ባለቤት ስትሆን አበራሽ ማናስቦ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ32:10:74 ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።
የሻምፒዮናው ሁለተኛ ቀን በሌሎች ክብረወሰኖች ደምቆ ሲውልም የሴቶች ዲስከስ ውርወራ አዲስ ክብረወሰን ተመዝግቦበታል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት የሆነችው መርሃዊት ጸሐዬ 45.40 ሜትር በመወርወር የአዲሱ ክብረወሰን ባለቤት ሆናለች።
ከተመሳሳይ ክለብ አለሚቱ ተክለስላሴ 41.60 ሜትር ወርውራ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን፣ዙርጋ ኡስማን 40.14 ሜትር በመወርወር ለመከላከያ ነሐስ አስመዝግባለች። የውድድሩ የቀድሞ ክብረወሰን በ2007 አም በመከላከያዋ አትሌት አልማዝ ንጉስ በ42.83 ሜትር አዲስ አበባ ላይ እንደተመዘገበ ይታወሳል።
የሴቶች መቶ ሜትር ውድድርም አዲስ ክብረወሰን ያገኘ ርቀት ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት የአብስራ ጃርሶ ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት በሌላኛዋ የንግድ ባንክ አትሌት አታክልቲ ውብሸት በ1998 አዲስ አበባ ተይዞ የቆየውን 11.55 ሰከንድ አሻሽላዋለች።
የአብስራ አዲሱን ክብረወሰን በዘጠኝ ማይክሮ ሰከንዶች በማሻሻል 11.46 ሰከንድ የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ ባይቱላ አላዮ በ11.89 ሰከንድ ከደቡብ ፖሊስ የብር ሜዳሊያ አሸንፋለች። ራሄል ተስፋዬ ከመከላከያ በ11.90 ሰከንድ የነሐስ ሜዳሊያው ባለቤት ነች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014