በአገሪቱ ዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት በተለይም ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እየተቻለ አይደለም። ዛሬ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነገ ከነገ ወዲያ በእጥፍ ይጨምር እንደሆን እንጂ ሲወርድ አይስተዋልም።
አሁን አሁንማ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ወጥቶ የሚወርደው ባንዲራ ብቻ ነው›› በሚል ቀልድ አዘል ቁምነገር ሰው ምሬቱን ያጣቅስ ጀምሯል።
የኑሮ ውድነቱ ያልነካካው ዘርፍ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። መሽቶ በነጋ ቁጥር ሁሉም ነገር በአንድ ቃል ጨመረ፣ ጨመረ፣ ጨመረ… ብቻ ሆኗል ቋንቋው። እዚህ አገር ውስጥ አንድ ምርት ከገበያ ከጠፋ ወይም እጥረት መከሰቱ በተሰማ ማግስት ዋጋው በእጥፍ መጨመሩም የማይቀር ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። ለዚህ ሁሉ ታድያ በአገሪቱ ያለው የንግድ ሥርዓት ጤናማ አለመሆኑና ደላሎች ዋነኛ ችግሮች ስለመሆናቸው ባለሙያዎች ደግመው ደጋግመው ሲያነሱ ይደመጣል።
ይሁንና ጤናማ አይደለም የተባለው የንግድ ሥርዓት ጤናማ በሆነ የንግድ ሥርዓት እንዲቃኝና እሳት ከማጥፋት ባለፈ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት እምብዛም አይስተዋልም። እርግጥ ነው የምርት እጥረት ለዋጋ ንረት መከሰት ዋነኛ ምክንያት ነው። ለዚህም መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ መፍትሔ ለማምጣት የተለያዩ ሥራዎችን ቢሠራም ትርጉም ያለው ለውጥ ግን አልመጣም።
በአሁን ወቅት አልቀመስ ያለውን የሲሚንቶ እና የብረት ገበያ ለአብነት ብናነሳ ገበያው ፍጹም ባለመረጋጋት ውስጥ ሆኖ እነሆ ዓመታት ነጉደዋል። የገበያው መረበሽም በተለያየ መልኩ ችግር እየፈጠረ ያለ ሲሆን በተለይም ብረትን ጨምሮ ሲሚንቶ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በሲሚንቶ ገበያ ላይ የሚታየው ችግር ሲንከባለል የመጣ ቢሆንም ቅሉ በአሁን ወቅት ያለው የገበያ ችግር ካለፉት ጊዜያት በእጅጉ የተለየና የተጋነነ ለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።
የሲሚንቶ ዋጋ መናር ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ጥረት ያደረገ ቢሆንም፤ ዛሬም የሲሚንቶ ገበያ ሊረጋጋ አልቻለም። አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ ቀጥሏል። በዘርፉ የተሰማሩ አካላት እንደሚገልጹት በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ ከ800 እስከ 1000 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያትም የኮንስትራክሽን ዘርፉ በከባድ ረብሻ ውስጥ ነው።
የምግብ ሸቀጦችንም ስናስብ የሚነሱት ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው። ሰዎች በየዕለቱ በሚጨምረው የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ናላው እየዞረ ቢሆንም ከየትኛውም አካል መፍትሔ የሚሆን ጠብ ያለ ነገር አልተገኘም። ሸማቹ በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት እንኳን ሕገወጥ ነጋዴና ደላሎች የፈጠሩት ችግር ነው ከማለት ባለፈ የሸማቹን ልብ የሚያሳርፍ ነገር አልታየም።
በንግዱ ዘርፉ የተሰማሩ አካላት እንደሚሉት በአምራች እና በገዥ መካከል የሚንቀሳቀሱ ደላሎች የምርቶችን ዋጋ ከፍ እንዲል እያደረጉ ነው። ከአምራቾች ተረክበው መልሰው የሚሸጡ አየር በአየር ነጋዴዎች ለዋጋ ንረቱ አይነተኛ ሚና አላቸው።
የትኛውም ገበያ ጤናማ የሆነ የግብይት ሰንሰለትን መከተል ያልቻለው በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነትና አየር በአየር ነጋዴዎች ቢሆንም መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች እንዳሉም ይታመናል። ማንኛውንም ምርት በስፋት ማምረት ካልተቻለ እጥረት መፈጠሩ የሚታመን ቢሆንም የተፈጠረውን እጥረትም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከተፈጠረው እጥረት በላይ ገበያውን የሚረብሹ በርካታ የዘርፉ ተዋንያኖች አሉ።
መንግሥት በየዘርፉ ውስጥ ያለውን የገበያ ችግር ለመፍታት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የሲሚንቶ ምርት አንዱ ነው። ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች የመሸጫ ዋጋቸውን እንዲቀንሱ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብቻ ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉና ሌሎች እርምጃዎችንም ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይህ መፍትሔ ጊዜያዊ እፎይታን ሰጥቶ አልፏል እንጂ በዘላቂነት በገበያው ውስጥ ያለውን ቁስል ግን ሊያሽረው አልቻለም።
የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይም እንዲሁ ከታክስ ማግኘት የሚገባውን ገቢ አጥቶ የተመረጡ ምግቦችን ከቀረጥ ነጻ ሲያስገባ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁንና መንግሥት አማራጭ ያላቸውን መንገዶች ሁሉ ነጋዴውን ይበልጥ ፈርጣማ ከማድረግ ባለፈ የሸማቹን ሸክም ሲያቀል አልታየምና ዛሬም ሸማቹ በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ቀጥሏል።
ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ የንግድ ሥርዓቱ ጤናማ በሆነ መንገድ በሕግና በመመሪያ በዘላቂነት መቀጠል የሚችለው እንዴት ነው፤ በየጊዜው የሚፈጠረውና ከወጣ የማይወርደው የዋጋ ንረትን እንዴት መቆጣጠር ይቻል ይሆን፤ለዋጋ ንረት መባባስ ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የምርት እጥረት እንዴት ማሻሻል እንደሚቻልና ሕገወጥ ስግብግብ ነጋዴና ደላሎችስ እስከመቼ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ይሆናሉ ስንል ላነሳነው ጥያቄ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን የሚከተለውን ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚውን ከፖለቲካው ነጥሎ ብቻውን መተንተን አይቻልም። ኢኮኖሚውና ፖለቲካው የማይነጣጠሉና የጠበቀ ትስስር ያላቸው ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢኮኖሚውን ቀስፎ የያዘው ፖለቲካው ነው። ስለዚህ ፖለቲካው ሲታመም ኢኮኖሚው ይታወካል። ፖለቲካው ሰላም ሲሆን በተመሳሳይ ኢኮኖሚው ይረጋጋል።
ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማለት ሊህቃን የሚዘውሩትና እንዳሻቸው የሚያደርጉት ሀብት እንደማለት መሆኑን የጠቀሱት ተንታኙ፤ ይህን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመደበኛው አካሄድ ወደታች ለማውረድ ደግሞ ግፊት፣ ትግልና ሙግት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። በተለይም በመንግሥት ሚዲያዎች ወቅታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን አስመልክቶ የመንግሥት አካላት ባሉበት ባለሙያዎች የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ አለባቸው። መንግሥትም ከባለሙያዎች ለሚሰነዘሩ ሃሳብና አስተያየቶች ጆሮ ሰጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ካልቻለ በተለመደው አካሄድ ብቻ መጓዝ ችግሩን ካለመፍታት ባለፈ በእጅጉ አድካሚ ነው።
ማንኛውንም ሥራ በእጃችን ላይ ያለውን ነገር ተጠቅመን ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ሰጥተን ምርጡን ነገር መሥራት ትክክለኛነት ስለመሆኑ የ11ኛ ክፍል ኢኮኖሚክስ ያስተምራል የሚሉት ተንታኙ፤ ነገር ግን አሁን ላይ እየሆነ ያለው ከፈረሱ ጋሪው አይነት እሽቅድምድም ነው። በጦርነት ምክንያት ሚሊዮኖች ተፈናቅለውና ተርበው ባሉበት አገር በሌሎች ሥራዎች ላይ ማተኮር ፖለቲካል ኢኮኖሚውን ካለማወቅና ካለመረዳት የመጣ ነው በማለት ያስረዳሉ።
ስለዚህ በቅድሚያ እንዲህ አይነቱን ስህተት ማረምና ቅድሚያ መስጠት ለሚገባው ቅድሚያ መስጠት ከተቻለና መደማመጥ ካለ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። ለዚህም የፖለቲካ አመራሮች ዓላማቸውና ሥራቸው ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ሕዝቡ መኖር እስኪያቅተው ድረስ የኑሮ ውድነት ጠፍንጎ በያዘበት በዚህ ወቅት ባለስልጣናቱ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል ወይ ብሎም መሞገት ተገቢነት ያለው ጥያቄ ስለመሆኑም ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ያላትና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ አርሶ አደር ስለመሆኑ ያነሱት ተንታኙ፤ ከሰሞኑ ዘይት ጠፋ ተብሎ የበዛ ጫጫታ እንደነበር ያስታውሳሉ። ጫጫታው 80 በመቶ የሚሆነውን ገበሬ የሚወክል አይደለም። ኢትዮጵያን ሊወክላት የሚችለው ገበሬ ነው። ‹‹ዘይት ማባያ እንጂ ምግብ አይደለም›› በማለት ከዘይት ይልቅ ጤፍ እንዳይጠፋ ገበሬው ጋር ያለውን ሥራ አድምቶ መሥራት ተገቢ እንደሆነና የሁላችንም ጫጫታ ኢትዮጵያን የሚመስል መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
እርግጥ ነው ገበያው በአንድም በሌላ እየተረበሸ ነው። መረበሹ ደግሞ ጤናማ አይደለምና መስተካከል እንዳለበት ይታመናል። ነገር ግን ለገበያው መረበሽ ምክንያቱ ደላላ እና ሕገወጥ ነጋዴ እንደሆነ ይነገራል እንዲህ አይነቱ ምላሽ እስከመቼ ለሚለው ጥያቄ ተንታኙ ሲመልሱ ደላላው እራሱ ማነው በማለት ጥያቄን በጥያቄ መልሰው ያነሳሉ። ከላይ እስከ ታች በዘር የተደራጁ አመራሮች ስለመኖራቸው በማንሳት በ2000 ዓ.ም አካባቢ በባለሃብቶች ኪስ ውስጥ የገቡ ከተሞችና ወረዳዎች የነበሩ ስለመሆናቸው ለአብነት ጠቅሰዋል።
እነዚህ ባለሃብቶች ከባለስልጣን ጋር በነበራቸው የጥቅም ትስስር የፈለጉትን ያህል መሬት የሚሰጣቸው እንደሆነና የመንግሥትን መዋቅር በኪሳቸው ውስጥ ያስገቡ ባለሃብቶች ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። ባለፈው ሥርዓት የነበረው ብልሹ አሠራር አሁንም ያለ መሆኑን ሲያስረዱም በባለሃብቱና በሹማምንቱ መካከል የነበረው ያልተቀደሰ ጋብቻ አሁንም አልፈረሰም ውሸት ነው በማለት ደላላው ማን እንደሆነ ይጠቁማሉ።
በዚህ ምክንያት አሁንም ሕዝቡ ከገባበት የፍርሃት ቆፈን ያልወጣ እንደሆነና ከገባበት የፍርሃት ቆፈን መውጣት እንዳለበት ያስረዱት ተንታኙ፤ ዛሬም ሕዝቡ ስም ጠቅሶ ለመናገር እየፈራ ያለበት ጊዜ መሆኑንና ሸብቦ ከያዘው ቆፈን መውጣት እንዳለበት በማመን ችግሩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለ ስለመሆኑን መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
አገሪቱ አሁን ከገባችበት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ትርምስ ውስጥ መውጣት የምትችለው በተለይም የተረበሸውን ገበያ ማስተካከል የሚቻለው እያንዳንዱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል ግዴታውን መወጣት ሲችል ነው። ባለፈው ዓመት በወሎና ጎንደር አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ያመረቱት ሽንኩርትና ቲማቲም ገዢ በማጣቱ እንደበሰበሰ መሰማቱን አስታውሰው ለዚህ ችግር በአካባቢው የሚገኘው የግብርና ጽሕፈት ቤት ተጠያቂ መሆን አለበት። ጽሕፈት ቤቱ ሚናው ምንድን ነበር በማለት መጠየቅም ይገባል።
ጽሕፈት ቤቱ በአካባቢው የሚገኘው አርሶ አደር ያመረተውን ምርት በማስተዋወቅ ነጋዴውም ሆነ ሸማቹ ምርቱን ከአርሶ አደሩ መግዛት እንዲችል ማድረግ ነበረበት። ነገር ግን ይህን እጅግ ቀላል የሆነውን ሥራ ባለመሥራቱ የአርሶ አደሩ ልፋት ከንቱ መቅረቱንና ሸማቹም በምርት እጥረት ምክንያት በሚያጋጥመው የዋጋ ንረት መሰቃየቱን አስረድተው በዚህ አጋጣሚ ደግሞ በመሐል ቤት ያለው ደላላ ተጠቃሚ ይሆናል።
እንዲህ አይነት ቀላል ተግባራትን በመከወን በቀጥታ ሸማቹ ምርቱን ከገበሬ መግዛት እንዲችል ማድረግ ቢቻል በመሐል ያለውን ደላላ ቆርጦ መጣል የሚቻል መሆኑን እንደ መፍትሔ አንድ ያስቀመጡት ተንታኙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምም እንዲሁ ሁለተኛው መፍትሔ ማምጣት ይቻላል።
ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም 20 በመቶ የሚሆን የአንድ አገር ሕዝብ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ከሆነ ያ አገር አምባገነን የሆነ መንግሥትን ሊወጣበት ዕድል የሌለው ስለመሆኑ የግብጽን አብዮት በአብነት አንስተው በማኅበራዊ ሚዲያ የተቀጣጠለ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በርካታ ዕድሎች ባሉበት ዓለም አማራጮችን ተጠቅመን የተሻለ ፖለቲካል ኢኮኖሚን መገንባት ለምን አልቻልንም የሚለው ሊቆጨን ይገባል የሚሉት ተንታኙ፤ እነዚህንና መሰል ችግሮችን መፍታት የሚቻለው የመንግሥት ሹማምንቶች ከባለሙያዎች ጋር በጋራ ተቀምጠው መወያየት፣ መከራከርና ወደ መፍትሔ መምጣት ሲችሉ እንደሆነ ያምናሉ።
በተለይም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከአማካሪዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በሚያደርጉት ክርክር የአገሪቱን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማስተካከል ይቻላል። መንግሥት ያልታየውን ነገር ከባለሙያዎች ጋር በሚያደርገው ውይይት ማየትና መረዳት ይችላል።
በአሁን ወቅት በአገሪቱ ለሚስተዋለው የኢኮኖሚ ችግር የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የመፍትሔ አካል በመሆን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መስተጋብር ምን መምሰል እንዳለበት ለመንግሥት ስዕሉን ማሳየት እንችላለን። ለዚህም የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት የሚወያዩበት ዕድል ይፈጠር በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014