በየሁለት ዓመቱ ከሚካሄዱ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አንዱ ነው። የብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያም በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክና ዋናው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከገነባችው ስምና ስኬታማነት በላይ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ገናና ስምና ውጤት አላት። ዘንድሮ በሰርቢያ ቤልግሬድ ለ18ኛ ጊዜ ተካሂዶ ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀውን ቻምፒዮና ጨምሮ ኢትዮጵያ ለ17 ጊዜ ተሳትፋለች።
በዚህም 31 ወርቅ፣ 13ብር፣15 ነሐስ በአጠቃላይ 59 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሜሪካና ሩሲያን ተከትላ ከአለም ሶስተኛዋ አገር ነች። ኢትዮጵያ በዚህ ቻምፒዮና ይህን ታላቅ ደረጃ እንድትይዝም በርካታ እንቁ አትሌቶቿ በተለያየ ጊዜ አስደናቂ ድሎችን በማስመዝገብ የሜዳሊያ ቁጥሮችን ከፍ አድርገዋል። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም በዚህ ቻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ሁለት ኢትዮጵያውያን የምንጊዜም ጀግኖችን ገድል እንዳስሳለን።
የሁለት ኦሊምፒክና የበርካታ የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጀግና አትሌት መሰረት ደፋር ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን እንድትሰበስብና ከዓለም አሁን ያላትን ትልቅ ደረጃ እንድትይዝ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡ ከዋክብት መካከል ቀዳሚ ሆና ትጠቀሳለች።
መሰረት ደፋር በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ለ7 ጊዜያት በመሳተፍ ብቸኛዋ የኢትዮጵያ አትሌት ናት። በ3000 ሜትር 7 ሜዳልያዎችን (4 የወርቅ ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ) በመጎናፀፍ ደማቅ ታሪክ ያስመዘገበች ሲሆን በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ታሪክ በምንጊዜም ከፍተኛ ውጤት በ52 ነጥብ ከዓለም 6ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል። እኤአ 2003 በርሚንግሃም ላይ በ3ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ስኬቷን የጀመረችው መሰረት በቀጣዩ 2004 ቻምፒዮና ሃንጋሪ ቡዳፔስት ላይ በተመሳሳይ ርቀት ወደ ወርቅ ሜዳሊያ ተሸጋግራለች። በ2006 ሞስኮ፣2008 ቫሌንሲያ፣2010 ዶሃ በተካሄዱ ቻምፒዮናዎችም በተመሳሳይ ርቀቶች ወርቁን የነጠቃት የለም። 2012 ኢስታንቡልና 2016 ፖርትላንድ ላይም የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በቤት ውስጥ ቻምፒዮናዎች ደምቃለች።
በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ታሪክ መሰረትን ተከትሎ በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ትልቅ ስኬት ያለው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጀግናው ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። ኃይሌ እኤአ በ1997 ፓሪስ ላይ በ3ሺ ሜትር ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮናው ወርቅ ሲያጠልቅ፣ በ1999 ጃፓን ሜባሺ ላይ በ1500ና 3ሺ ሜትሮች ጥምር ድሎችን አጣጥሟል። እኤአ 2003 በርሚንግሃም ላይ በ3ሺ ሜትር ያጠለቀው ወርቅም በቻምፒዮናው ታሪክ በሜዳሊያ ብዛት ከመሰረት ቀጥሎ ስኬታማው ኢትዮጵያዊ አትሌት ያደርገዋል። መሰረትና ኃይሌ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቢሆኑም እንደ ገንዘቤ ዲባባ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሰለሞን ባረጋና ሌሎች አትሌቶች ሁለት ሁለት ወርቆችን በማጥለቅ ኢትዮጵያ አሁን ለያዘችው ትልቅ ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
መሰረትና ሃይሌ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርካታ ወርቆችን የተጎናጸፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ አይደሉም። በዓለም ደረጃም ስኬታቸው ቁንጮ ሆኖ ይጠቀሳል። በዚህ ቻምፒዮና ሰባት ወርቅ፣ አንድ ብርና አንድ ነሐስ በመሰብሰብ ታሪካዊቷን ሞዛምፒካዊት አትሌት ማሪያ ሞቶላን የሚስተካከል የለም። ሞቶላ ይህን ሁሉ ክብር የሰበሰበችው እኤአ ከ1993 እስከ 2008 ድረስ በስምንት መቶ ሜትር ውድድር ነበር። እሷን ተከትላ ሩሲያዊቷ አትሌት ናታልያ ናዛሮቫ በአራት መቶና አራት በአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል እኤአ ከ1999 እስከ 2008 ድረስ ሰባት ወርቅና አንድ ብር በማጥለቅ ትልቅ ታሪክ አላት። ከሁለቱ አትሌቶች ቀጥሎ በጎላ ስኬት ታሪክ የሚያስታውሳቸው ኩባዊው የርዝመት ዝላይ ተወዳዳሪ ኢቫን ፔድሮና ቡልጋሪያዊቷ ከፍታ ዘላይ ሴፍካ ኮስታዲኖቫ ናቸው። ፔድሮ እኤአ ከ1993 እስከ 2001 አምስት ወርቆችን ያጠለቀ አትሌት ሲሆን ኮስታዲኖቫም በተለያየ ጊዜ አምስት ወርቆችን ተጎናጽፋለች።
ከነዚህ አትሌቶች ቀጥሎ የሚቀመጡት ስኬታማ አትሌቶች ኢትዮጵያውያኑ የምንጊዜም ኮከቦች መሰረትና ኃይሌ ናቸው። በእርግጥ የመሰረትና ኃይሌን ታሪክ የሚጋሩ የሌሎች አገራት ጥቂት አትሌቶችም እንዳሉ ታሪክ አይዘነጋቸውም። በተለይም ታሪካዊው የዩክሬን አትሌት ሰርጌ ቡካ በምርኩዝ ዝላይ ያጠለቃቸው አራት ወርቆች ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። ሰርጌ ሶስቱን ወርቆች ያጠለቀው ሶቬት ህብረትን ወክሎ ሲሆን ቀሪውን ሶቬት ህብረት ተበትና ዩክሬን እንደ አገር ከቆመች ወዲህ ነበር። ኩባዊው ከፍታ ዘላይ ጃቪየር ሶቶማዮር አራት ወርቅና አንድ ነሐስ፣ ስዊድናዊው ከፍታ ዘላይ ስቲፋን ሆልም አራት ወርቅና ሩሲያዊው የ5ሺ ሜትር እርምጃ ተወዳዳሪ ሚክሄል ሽኒኮቭ አራት ወርቆችን በማጥለቅ ተመሳሳይ ታሪክ የሚጋሩ አትሌቶች ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2014