ሽብርተኛው ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ በከፈተው የጦርነት ምክንያት መላው ዜጎች ህልውናቸውን ለመጠበቅና አገራቸውን ከመፍረስ ለመታገል እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል። በዚህም የትህነግ ጋሻ ጃግሬዎችን አከርካሪ በመስበር ወደ ዳር እንዲያፈገፍግ አድርገውታል። ይሁን እንጂ ይህ ቡድን ጨርሶ ስጋት መሆኑ አላበቃም። ዋንኛ ምክንያቱ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ መመሸጉና አሜሪካና ምእራባውያኑ በሚያደርጉት ጫና ነው።
በዚህ ጦርነት መላው ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ጥቅል የህልውና ስጋት ውስጥ ገብተዋል። በተለይ ለልማትና እድገት መዋል የሚጠበቅበት የገንዘብና ጉልበት ለጦርነት በመዋሉ ምክንያት እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ ጫና በመፈጠሩ ዜጎች በዚህ ጫና ውስጥ እንዲያልፉ ተገደዋል። አሁንም የዚህ ጫና ሰለባ ሚሊዮኖች ናቸው።
ይህ አልበቃ ብሎ ምእራባውያን የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማእቀቦችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ እንኳን የኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ ለማፅደቅና ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ግብግብ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጫና ሳይንበረከኩ አገራቸውን ከመፍረስና ከመክሸፍ ለመታደግ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትና አሁንም የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በታሪክ መዝገብ የሰፈረ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የክርስትና እምነት የገናና ጥምቀት ክብረ በዓላት አስመልክቶ የቱሪዝምና ኢኮኖሚ ዘርፉን ለማነቃቃት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ባደረጉት መሰረት የታየው መተባበርና አመርቂ ውጤትም የርብርቡ አንድ አካል ተደርጎ የሚታይ ነበር። በተለይ በጦርነቱና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያገግም፣ በመዳረሻ ስፍራዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎችና አስጎብኚዎች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው የዚህ “ወደ አገራችሁ ግቡ” የሚለው ጥሪ ጉልህ ድርሻ ነበረው። ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይና ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩ አሳይተውበታል።
“ወደ አገራችሁ ግቡ” የሚለው ጥሪ ለመላው ዓለም በአንድነቱ የማይደራደር ሕዝብ መኖሩን ለዓለም ከማሳየቱም በዘለለ የኢትዮጵያ የሃይማኖት፣ የታሪክና የብዝሃ እሴቶች ባለቤት እንደሆነች ያሳየ ነበር። ታዲያ ይሄን እድል ህብረ ብሄራዊነትን ለማጉላት ከምንም በላይ እድል ፈጥሯል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ቆይታ የነበረውን ንቅናቄና የመጣውን ውጤት አንስተው መሰል ትብብር መቀጠል እንዳለበት አሳስበው ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ የብዝሃ ሃይማኖት መገኛ ከመሆኗ አንፃር በመጪው የእስልምና እምነት የታላቁ ረመዳን ፆም ፍቺንና ክብረ በዓሉን በማስመልከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ እስላማዊ ቅርሶችንና የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ “ኢትዮጵያ በዓለም እጅግ አስደናቂ እስላማዊ ታሪክና ቅርሶች ባለቤት እንደሆነች” ለቀሪው ዓለም እንዲያስመሰክሩና በተለይ እነዚህ እሴቶች ለአገር አንድነትና ህብረት ለዘመናት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አጉልተው እንዲያሳዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የዝግጅት ክፍላችንም ሙስሊም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ቢመጡ ሊመለከቷቸው የሚችሉትን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች እነሆ ለማለት ወድዷል። ለዛሬ ግን በልዩ ሁኔታ እስላማዊ ቅስሶችን እናስተዋውቃችኋለን። ከዚያ በፊት ግን በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቁ ረመዳን ፆም ተብሎ የሚጠራውን የሃይማኖቱን ምሰሶና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚከወኑ ስነስርዓቶች ምን እንደሚመስሉ በጥቂቱ ለማየት እንሞክር።
በተለይ በመንግሥት ጥሪ መሰረት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደሚወዱት አገር ቢመጡ አንድነታቸውንና ለጠላት የማይበገሩ መሆናቸውን ከማሳየታቸውም ባለፈ ይህን ታላቅ ፆምና የፍቺውን ቀናት ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የማሳለፍ እድሉን ያገኛሉ። ከዚህ ባለፈ የተዳከመውን ቱሪዝም ማነቃቃት ትኩረት ያላገኙ እስላማዊ ቅርሶች እንዲለምዱ፣ እንዲተዋወቁና በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ የበኩላቸውን አሻራ ማሳረፍ ይችላሉ።
የረመዳን ፆም
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ የረመዳን ፆም ከአንደበት፣ ከክፉ ሥራ እንዲሁም ከመሰል ድርጊቶች በመቆጠብ መልካም በማድረግ ለተራበ በማጉረስና የተጣላን በማስታረቅ ተግባር ውስጥ ሆኖ በታላቅ መንፈሳዊ አርምሞ የሚተገበር ፆም መሆኑንን በተለያዩ ጊዜዎች ይህ ለአንድ ወር የሚደረግ የታላቁ ረመዳን ፆም ሲገባ ለሕዝበ ሙስሊሙ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የረመዳን ፆም ሲገባ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከቤተሰብ ጋር የመጠያየቅ፣ አብሮ የማፍጠር ሰደቃ የመስጠት፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት መልካም ነገርን ማድረግ፣ ትንንሽ ኪታቦች፣ መፅሃፍት እና ሌሎች እስላማዊ ስጦታዎችን ማበርከት፣ ተራርቀው የሚገኙ ልጆችና ዘመዶች ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረግ እና ሌሎች መሰል ተግባራትን ማከናወን በዚህ በረመዳን ወቅት አስፈላጊ መሆኑን ሼኮችና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች ይመክራሉ።
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በቅዱስ ቁርአን “ከሰዎች አላህ ዘንድ በጣም ተወዳጁ ለሰዎች በጣም ጠቃሚ የሆነው ነው፤ አላህ ዘንድ በጣም ተወዳጁ ስራ ሙስሊምን ማስደሰት፣ ጭንቀቱን ማስወገድ፣ እዳውን መክፈልና አብልቶ ረሀቡን ማስወገድ ናቸው” የሚል መልዕክት ማግኘት ይቻላል።
ታዲያ በረመዳን ፆም መንግሥት ወደ አገራችሁ ግቡ የሚለውን መልዐክት ማስተላለፉን ተከትሎ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከላይ የጠቀስናቸውን አጋጣሚ አግኝተው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የሚተጋገዙበት እድል ያገኛሉ። በተለይ በአማራና በአፋር ክልል በደሴና በወሎ አካባቢ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ አካላትን ለማገዝ ይህ የረመዳን ወቅትና የመንግሥት ወደ አገራችሁ ግቡ የሚለው ጥሪ ከፍተኛ እድል ይሰጣል
እስላማዊ ቅርሶች
ኢትዮጵያ በርካታ የታሪክ፣ የቅርስና የባህል የእስልምና እሴቶች አሏት። ከሁሉም በላይ ተቻችሎ መኖር የሚችል የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚገኙባት አገርም ነች። ይሁን እንጂ እነዚህ እሴቶቿ በበቂ ተዋውቀዋል ተብሎ አይታሰብም። በዚህ ዓመት በምንይዘው የሮመዳን ፆም መንግሥትና ታላላቅ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች፣ ተፅእኖ ፈጣሪዎች የአገር አንድነትን ለማፅናትና የኢትዮጵያን ተወዳጅ ሃብቶች ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገራቸው የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ ጥሪ አድርገዋል። ለመሆኑ እነዚህ ዜጎች ወደ አገራቸው ሲገቡ በሚኖራቸው ቆይታ ምን አይነት እስላማዊ ቅርሶችን መመልከት ይችላሉ። የተፋዘዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በምን መልኩ የማነቃቃት እድል አላቸው። የሚከተሉት እስላማዊ ቅርሶች የሚገኙበት ስፍራና ሃብቶች መልስ አላቸው።
አርኪዮሎጂስ ሐሰን ሰ ኢድ (ዶ/ር) ‹‹እስላማዊ ቅርሶች ዓይነትና ስርጭት ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ›› በሚል በ2008 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ እንደገለፁት በአማራ ክልል አልዩ አምባ፣ አበዱል ረሱል፣ ጎዜ፣ ጎንዶሬ፣ ገታ፣ ጀማ ንጉሥ፣ ሾንኬ፣ ጠለሐ፣ ገዶ፣ ዶዶታ፣ ጡርሲና በተባሉ ቦታዎች የሚገኙ የእስላማዊ ቅርሶች ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ አሳይተዋል። እንዲሁም በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ የሚገኙ ገቸኔ፣ ጨኔ፣ ገበሮች፣ ካይር አምባ፣ አሊ ግምብና መጠቅለያ በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችም የጽሑፋቸው አካል ነበሩ። በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ ነገር ግን ያልታወቁ እስላማዊ መሠረት ካላቸው ቅርሶች በተቃራኒው በብዙኃኑ የሚታወቁ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ የሶፍ ዑመር ዋሻም ይገኙበታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ ውስጥም በታላላቅ ምሁራንና አርኪዎሎጂስት አማካኝነት የተዋቀረ እስላማዊ ቅርሶች የሚገኙበት ሙዚየም ይገኛል። ጎብኚዎች ወደዚህ ስፍራ ቢከትሙ ብዙ እውቀት መገብየት ይችላሉ። በአባ ጅፋር አገር ጅማም ቤተመንግስቱን ጨምሮ አያሌ እስላማዊ ሃብቶችን ማግኘት ይቻላል። ይህ ሃብት በተለይ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ማንነትና ባህል እንዲሁም እሴት ይግለፅ እንጂ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብት እንደሆነም ይታመናል።
ሌላው በ9ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ላይ በቅርስና ባህል ዘርፍ የ2013 የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ቢላሉል ሀበሺ ሙዝየም ነበር። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ስፍራ ቢሄዱና መጎብኘት ቢችሉ በብዙ ያተርፋሉ። ቢላሉል ሀበሺ ሙዝየም በ1992 ዓ.ም የተመሠረተ የማኅበረሰብ ሙዝየም ሲሆን የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችንም ይሠራል። ለኢስላማዊ ቅርሶች ልዩ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ የተቋቋመው በቅርስነት ሊያዙ የሚገቡ ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ እንዲታወቁና በአንድ ቦታ ተሰብስበው ለጥናትና ምርምር ጭምር እንዲውሉ ለማስቻል ነው።
ሌላው በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ እስላማዊ ቅርሶች መካከል ‹‹የመለሳይ አገር መስጊድ›› አንዱ ነው። የመለሳይ አገር መስጊድ ከፍታ ላይ የተመሠረተ ነው። መስጊዱ ስያሜውን ያገኘው ከኢማም አህመድ ጦር እንደሆነ ይነገራል። ወደ ጎን 24 ሜትር፣ ቁመቱ ደግሞ 3.3 ሜትር ከፍታ ያለው የመለሳይ መስጊድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር የአካባቢው አዛውንቶች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን የመለሳይ መስጊድ እንኳንስ ምዕመናን ሊያገለግል ራሱን ችሎ መቆምም ተስኖታል። ይህን ሃብት በስፍራው ተገኝቶ መጎብኘት እና ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግም ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ታላቅ አደራ ነው። በረመዳን ፆም በጎ ማድረግ መቻል ደግሞ የእምነቱ ዋንኛ ምሰሶ በመሆኑ ተግባሩ ለኢትዮጵያውያን አሁን ላይ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።
ከኢድ እስከ ኢድ ለምን?
‘’ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል ስያሜ ታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ከሰሞኑ በተሰጠ መግለጫ ሰምተናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታላቁ የረመዳን ወር በኢትዮጵያ ታላቁ የኢድ ሶላት እንዲደረግ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ “ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል ስያሜ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያን መርሃ ግብርን ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል።
የዝግጅቱ ብሔራዊ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደሚሉት ከኢድ እስከ ኢድ በሚል ስያሜ የሚካሄደው ታላቁ የኢትዮጵያንውያን ጉዞ ኢትዮጵያ በሃይማኖት፣ በታሪክ በባህል ያላትን እሴቶች ለዓለም የምታሳይበት እንደሆነ በመግለፅ ዜጎች ይህ ተግባር በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ መጠየቃቸው ይታወሳል።
የፈረንጆች አዲስ ዓመትን አስመልክቶ በነበረው ታላቁ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግስት አስታውቆ ነበር። በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በወሳኝ ወቅት ለአገራቸው ያላቸውን ድጋፍና ፍቅር በተግባር ያሳዩበትም ነበር።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ለዝግጅቱ 16 መንግስታዊ ተቋማትን ያቀፈ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል። ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በመሆን ነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅትና ሃላል ፕሮሞሽን የመርሃ ግብሩ ያስተናብሩታል። ኡስታዝ አቡበከር አህመድ “በዓሉ ኢትዮጵያ ያላትን ቱባ እስላማዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ እና በጎ ተፅዕኖን በወዳጅ አገራት ላይ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ይሰናዳል። ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የሚያግዙ ምቹ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ያስችላል” በማለት ይህ መሰናዶ ምን አይነት ይዘት እንደሚኖረውና በምን ምክንያት እንደተዘጋጀ አሳውቀዋል።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ በሃይማኖት፣ ባህል፣ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች የታቀፈችና በህብረ ብሔራዊነት የደመቀች አገር ነች። እንኳን ለሕዝቧ ለመላው ዓለም የሚተርፍ አስደናቂ እሴቶችን ይዛለች። ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት እነዚህን እሴቶቿን ለመናድና ለማፈራረስ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚፈጠሩ ጠላቶች አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራ ይደረጋሉ። ይሁን እንጂ በግዛት አንድነቷና በሰላሟ የማይደራደሩት ልጆቿ የተጋረጠባትን ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንድታልፍ በሃይማኖት፣ በብሔር ሳይለያዩ በብልህነት አንድነታቸውን አጠንክረው ዛሬም በርትታ እንድትቆም አስችለዋታል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከሰተው ችግርም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። ከመላው ዓለም የሚገኙ ዜጎቿ ብዙዎች ፊታቸውን ሲያዞሩ “አይዞን አለን” በማለት የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል። ዛሬም ልክ በገናና ጥምቀት በዓል ያየነውን አንድነት ለመድገም “ከኢድ እስከ ኢድ” ወደ አገር ቤት የሚል የአንድነት ማሰሪያ ሸማ ይዘው ተነስተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2014