በርካታ አትሌቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮችና በስፖርቱ የስመጥርነት ማማ የሚያደርሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮን ዘንድሮ ለ51ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ከቀናት በኋላ በሃዋሳ ከተማ በሚካሄደው ቻምፒዮና ላይም በርካታ ስመጥርና ወጣት አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሃገራቸውን የሚወክሉ የብሄራዊ ቡድን አባላትም ይታጩበታል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊውና በስፖርቱ ቀዳሚው ብሄራዊ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው። ለ51ኛ ጊዜም በአጭር እና ረጅም ርቀት፣ በውርወራ፣ ዝላይ እና እርምጃ የውድድር ዘርፎችም አትሌቶችን ያወዳድራል።
በቻምፒዮናው ላይ 7 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች 24 ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት የሚፎካከሩ ሲሆን፤ እነርሱን ወክለውም 413 ሴት እና 620 ወንድ በድምሩ 1ሺ33 አትሌቶች በውድድሩ እንደሚካፈሉም ተረጋግጧል። ከመጪው ሰኞ መጋቢት 19-24/2014 ዓም ለስድስት ተከታታይ ቀናት የሚደረገው ውድድር ከመክፈቻው በቀር ሁሉም በጠዋት እንደሚካሄዱም ፌዴሬሽኑ ያወጣው መርሐግብር ይጠቁማል።
አትሌቶች፣ ክለቦች፣ ክልሎች፣ የአትሌቲክስ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች ዝግጅታቸውን የሚፈትሹበትና ያሉበትንም ደረጃ የሚገመግሙበት ውድድር በመሆኑ ቅድሚያ ይሰጡታል።
ትጉህና ውጤታማ የአትሌቲክስ አሰልጣኞች አትሌ ቶቻቸውን በትልልቅና ዓለም አቀፍ ውድድር ተመራጭ ብርሃን ፈይሳ እንዲሆኑ አዘጋጅተው የሚቀርቡበት መርሐ ግብርም ነው። ከስመጥር አትሌቶች ባሻገር በርካታ ተተኪና ወጣት አትሌቶችም የሚታዩበትና ሃገራቸውን ለመወከል እድል የሚያገኙበትን ሁኔታም ይፈጥራል። የተያዘው ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአሜሪካ ኦሬገን ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄድበት በመሆኑ በብሄራዊ ቡድኑ የሚታቀፉ አትሌቶች የሚለዩበት ውድድር መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ተመላክቷል።
በሞሪሽየስ በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቲክስን ጨምሮ በመምና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ሃገራቸውን ወክለው ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶች የሚመረጡበትም ነው። የ50ኛ ዓመት እዮቤልዩ በዓሉን ባከበረ ማግስት የሚካሄደው ይህ ውድድር በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚካሄድ ይሆናል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ ስታዲየሙ እድሳት ላይ በመሆኑ ምክንያት ማስተናገድ ባለመቻሉ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ እንዲካሄድ መወሰኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ይህ ቻምፒዮና ዓለምን ባስጨነቀው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በ2012 ዓም ብቻ ሳይካሄድ ቀረ እንጂ ከ1963ዓም በየዓመቱ ሳይቆራረጥ የሚካሄድ አንጋፋ ውድድር ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ውድድሩን በማዘመን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድና በውድድር ስፍራው መገኘት ያልቻለው የስፖርት ቤተሰብ በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት እንዲከታተል የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል።
ቻምፒዮናው በግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞው ሃገራቸውን በኦሊምፒክ አደባባይ በመወከል የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙ ጀግና አትሌቶችን ያስገኘ ነው። ፈር ቀዳጁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ሰለሞን ባረጋ የመሳሰሉት በወንዶቹ በኩል ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ የምትገኘው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ቲኪ ገላና እና አልማዝ አያናም በዚህ ቻምፒዮና ተካፍለው ያለፉ ሴት ስመጥር አትሌቶች ናቸው። ከኦሊምፒክ ባለድሎቹ ባለፈ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ኢብራሂም ጀይላን፣ መሃመድ አማን፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ማሬ ዲባባ፣ ሙክታር ኢድሪስ እንዲሁም ሌሊሳ ዴሲሳ ቻምፒዮናው ያፈራቸውና በስፖርቱ ከፍተኛ ስፍራ ከሚሰጣቸው አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በዚህ ቻምፒዮና ላይም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊና ታዋቂ የሆኑ በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። ያለምዘርፍ የኋላው፣ሀብታም አለሙ፣ እቴነሽ ዲሮ፣ አርያት ዲቦ፣ ሙክታር እድሪስ፣ ገመቹ ዲዳ፣ ሞገስ ጥኡማይ፣ ሚልኬሳ መንገሻ ጥቂቶቹ ናቸው።
ፌዴሬሽኑ በዚህ ውድድር በግልም ሆነ በቡድን አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች የሜዳሊያ፣ ዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 541ሺ ብር ለሽልማት ማዘጋጀቱንም አሳውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014