የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት ለተመዘገበው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁንም እያደረገ ይገኛል። መንግሥት በመሠረተ ልማት እና በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ያፈሰሰው ከፍተኛ ሀብት አገሪቱን ከአህጉሪቱ ትላልቅ ኢኮኖሚዎች አንዱ እንድትሆን አስተዋጽኦ ማበርከቱን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ፈጣን የከተሞች መስፋፋት የተሻሻሉ የመሠረተ ልማት ሥርዓቶች አስፈላጊነት እንዲጨምር እና የመኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ እንዲበራከት ምክንያት መሆኑም ይነገራል ።
ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ የግንባታ ሥራዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥትና በግል አከናውናለች። በአሁኑ ወቅትም እያከናወነች ትገኛለች። የግንባታ ሥራዎች መበራከት በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማትና የቤት ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የዜጎችን ኑሮ ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
የመሰረተ ልማቶቹ እና የቤቶች ግንባታ መስፋፋት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከተጫወተው ሚና ባሻገር ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በተለይም በትላልቅ ከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ዛሬም እየፈጠረ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአገሪቱ ውስጥ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የተሰማራበት ዘርፍ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። በርካቶች በዚህ ዘርፍ በመሰማራት የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን የዕለት ጉርስና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ያሟላሉ።
ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ ከችግሮች የጸደ አይደለም። በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ ዘርፍ ነው። በዘርፉ ጎልተው ከሚነሱ ችግሮች መካከልም የግንባታ ግብዓት ችግር አንዱ ነው። የግንባታ ግብዓቶች እጥረትና ዋጋ መናር ለዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት ሆነዋል። በተለይም በሲሚንቶ ላይ የሚታየው የዋጋ መናር ዘርፉ እንዳይላወስ ያደረገው ሲሆን፤ በርካታ ግንባታዎች እንዲጓተቱም መንስኤ ሆኖ መቆየቱን የዘርፉ አካላት ያብራራሉ።
የሲሚንቶ ዋጋ መናር ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም፤ ዛሬም የሲሚንቶ ገበያ ሊረጋጋ አልቻለም። አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ ቀጥሏል። በዘርፉ የተሰማሩ አካላት እንደሚገልጹት በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ ከ800 እስከ 1000 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የግንባታ ዘርፍ ከባድ ችግር እያጋጠመው ይገኛል።
በዘርፉ የተሰማሩ አካላት እንደሚሉት በአምራች እና በገዥ መካከል የሚንቀሳቀሱ ደላሎች የሲሚንቶ ዋጋ ከፍ እንዲል እያደረጉ ነው። ከአምራቾች ተረክበው መልሰው የሚሸጡ አየር በአየር ነጋዴዎች ለሲሚንቶ ዋጋ መናር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ሊቀመንበር ኢንጂነር አመሃ ስሜ እንደሚሉት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ ቆይቷል። በሲሚንቶ ላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው የዋጋ ንረት የግንባታ ዘርፉን በእጅጉ ጎድቷል። በአሁኑ ወቅትም ዘርፉ ላይ ከባድ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
በርካታ የግንባታ ሥራዎች እየተስተጓጎለ ነው። የግንባታ ሥራዎች መስተጓጎል ደግሞ ዳፋው ብዙ ነው። መንግሥት የሲሚንቶ ገበያውን ለማረጋጋት በማሰብ በሲሚንቶ ምርት መሸጫ ዋጋ ላይ ተመን አውጥቶ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቀረፈም። አሁንም የሲሚንቶ ዋጋ መናር ከባድ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። የሲሚንቶ አየር በአየር ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት የሲሚንቶ ዋጋ እንዲንር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የሚያነሱት ኢንጂነር አመሃ፤ አየር በአየር ንግድ ላይ
የተሰማሩ አካላት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ እየሸጡ መሆኑን ይናገራሉ። መንግሥት እጁን በማስገባት ገበያውን ለማረጋጋትና የምርቱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። ሲሚንቶ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሆኖ መቆየቱን የሚያብራሩት ኢንጂነሩ፤ ገበያው ጥቂት ሰዎች የሚከብሩበትና የግንባታ ሥራ የሚበደልበት ሆኗል ይላሉ።
በርካቶች ሌሎች ሥራዎች ላይ ከመሰማራት ይልቅ የሲሚንቶ አየር በአየር ወደ መሸጥ እና ማሻሻጥ አዋጭ እየሆነለት በመምጣቱ በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። የሸማቾች እጅ ላይ ሳይደርስ ደላሎች ሲሚንቶ ገዝተው ዋጋ ጨምረው እየሸጡ ነው።
አየር በአየር ንግድ አዋጭ የሥራ እድል ተደርጎ እየታየ ነው። በዚህ ዙሪያ የአገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየተዘዋወረ ይገኛል። እነዚህ አካላት ከአምራቾች ጋር በመመሳጠር የራሳቸውን ኪስ እየሞሉበት ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ አገሪቱን ክፉኛ እየጎዳት ነው። ይህን ችግር መቅረፍ ለመንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ነው።
እየተስተዋለ ያለው ሰው ሰራሽ የሲሚንቶ እጥረት የግል እና የመንግሥት ግንባታዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። በአገራችን በመንግሥት እና በግል እየተገነቡ ያሉ የግንባታ ሥራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ እያደረጉ ካሉ ምክንያቶች አንዱ ነው።
ግንባታዎች ተጨማሪ በጀትና ጊዜ እንዲጠይቁ ምክንያት እየሆኑ ካሉ ችግሮች አንዱ ሆኗል። ግንባታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ግንባታዎችም አሉ። ይህ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በአጭር እና በረጅም ጊዜ ከፍተኛ መዘዝ የሚያስከትል ነው።
ከሌሎች ደባል ምክንያቶች ጋር በመዳመር አገሪቱ ቀደም ባሉት አስርት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው የምጣኔ ሀብት እድገት ቀጣይነት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆን ነው። እንደ ኢንጂነር አመሃ ማብራሪያ፤ የሲሚንቶ ዋጋ መናር የመንግሥትና የግል የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በዘርፉ ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችም ከሥራ ውጭ ሆነው የከፋ ችግር ውስጥ እንዲወድቁ መንስኤ እየሆነ መሆኑን ያብራራሉ። በተለይም በከተሞች አካባቢ በግንባታ ሥራ የሚተዳደሩ በርካቶች ችግር ውስጥ እንዲወድቁም አንዱ ምክንያት እየሆነ ነው።
አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች መንግሥት የሚያስተዳድራቸው እንደመሆኑ የሲሚንቶ ዋጋ መናር በግንባታ ዘርፍ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ባሻገር ለሌሎች ሸቀጦች ለዋጋ መናርም አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ከመሬት ንግድ ባልተናነሰ ሁኔታ ለኑሮ ውድነት የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በሲሚንቶ ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት የሚሉት ኢንጂነር አመሃ፤ ሲሚንቶ የሚያመርቱ ድርጅቶችና ተቋማት የማምረቻ ዋጋቸውን እና ለገበያ የሚያቀርብበት መንገድ መለወጥ አለበት። ይህ እጥረት የሚጀምረው ከማምረቻ ፋብሪካዎች ነው። አብዛኞቹ አምራቾች ከፍተኛ የአስተዳደር ችግር አለባቸው። አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አይደለም።
እነዚህ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ መደረግ አለበት። በሙሉ አቅማቸው ካመረቱ ችግሩን መቅረፍ አዳጋች ሊሆን አይችልም። በመሆኑም በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በሙሉ አቅማቸው ማምረት ከጀመሩ የሲሚንቶ ምርት ገበያው ውስጥ ይትረፈረፋል። እንደ ኢንጂነር አመሃ ማብራሪያ የሲሚንቶ ገበያ ላይ አንድም ችግር እየፈጠረ ያለው በገበያው ላይ ያለው የሲሚንቶ ገበያ ጥቅም ትስስር ፋብሪካዎቹ ድረስ ዘልቆ መግባቱ ነው።
ይህ ችግር እስካልተፈታ ድረስ ነገም በሲሚንቶ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ አይችሉም። ሰው ሰራሽ እጥረት የሲሚንቶ ገበያ ችግር ሆኖ ይቀጥላል። ስለዚህ ፋብሪካዎች አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው ።
በመሃል ላይ ገብተው አየር በአየር ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት ከገበያው ለማስወጣት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ይላሉ። ይህን ኃይል ከገበያው ማስወጣት ካልተቻለ የሲሚንቶ ገበያን ማረጋጋት የሚታሰብ አይደለም። ገበያው ላይ የምርት እጥረት በመፍጠር ሀብታም የሚኮንበት ሁኔታ ተፈጥሯል መንግሥት እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ከውጭ ሆኖ መቆጣጠር ይገባዋል።
በገበያው ላይ ያለው የሰው ሠራሽ ችግር እና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሩ መቀረፍ አለበት። መንግሥት ገበያ ውስጥ ገብቶ ሲሚንቶ ከመሸጥ ይልቅ ገበያውን ለማረጋጋት እና ለመቆጣጠር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መቻል አለበት። ይህ እስካልሆነ ድረስ ገበያው ይረጋጋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ያነሳሉ።
መንግሥት ምርት ባልተገባ መንገድ ደብቀው የሚይዙትን አካላት መቆጣጠር አለበት። ምርት ባልተገባ መንገድ ደብቀው የሚይዙ ኃይሎች በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ለሚስተዋለው ችግር የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙ ናቸው።
እውነተኛ የምርት እጥረት ቢኖር ገበያው ባዶ ይሆን ነበር። አሁን የተፈጠረው ምርት እያለ የዋጋ መጨመር ነው። ይህ ደግሞ የገበያ ሥርዓቱ እና የተቆጣጣሪ አካላት ድክመት ነው። የግንባታው ዘርፍ ከሚገባው በላይ አድጎ የተፈጠረ እጥረት አይደለም። እየተፈጠረ ያለው እጥረት ሰው ሠራሽ ነው ይላሉ።
በመሃል ገብተው ገበያውን እያመሰቃቀሉ ያሉ አካላትን ከማስወጣት ጎን ለጎን የሲሚንቶ ችግር ለመቅረፍ ከዚህ በፊት መንግሥት እንዲህ አይነት ችግር በተፈጠረበት ወቅት ከውጭ በግለሰቦች በመግባት እንዲያመርቱና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ችሎ ነበር።
ከውጭ የገቡ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መጀመራቸውን ተከትሎ የሲሚንቶ ዋጋ ተረጋግቶ ነበር።
አሁንም መንግሥት እንዲህ አይነት አማራጮችን ማማተር አለበት ።
በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የግንባታ ዘርፍ ተጠቅመው ራሳቸውን ጠቅመው ኢትዮጵያንም ሊጠቅሙ የሚችሉ ባለሃብቶችን መጋበዝ ያስፈልጋል።
እነዚህ ባለሃብቶች የተሻለ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ያላቸው እንደመሆናቸው በዘርፉ ያለውን ችግር በአጭር ጊዜ መቅረፍ ይችላሉ።
ከዚያ ጎን ለጎን የአገራችን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የፉክክር መንፈስ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል።
መንግሥት ደላሎችን ከማስወጣት እና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ከማድረግ ጎን ለጎን ጊዜያዊ መፍትሄዎችንም ማፈላለግ አለበት። የግንባታ ዘርፍ መጎዳት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ስብራት የሚያስከትል መሆኑ ከግምት በማስገባት እጥረት በሚኖርበት ወቅት መንግሥት ከውጭ ማስገባት አለበት።
መንግሥት ክፍተቱን ለመሙላት ከውጭ አገራት ማስገባት ቢጀምር አየር በአየር ንግድ ላይ ተሰማርተው ሰው ሰራሽ እጥረት እየፈጠሩ ያሉ አካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከገበያው ይወጣሉ።
እንደ ኢንጂነር አመሃ ማብራሪያ፤ ይህን ሰው ሰራሽ ችግር ለመፍታት መንግሥት ገበያውን ነጻ ማድረግ፤ ከውጭ ማስገባት የሚፈልግ አካል እንዲያስገባ መፍቀድ አለበት።
ይህ ቢደረግ መሃል ላይ ገብቶ በድለላ ላይ የተሰማራው ኃይልም አደብ ይገዛል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሲሚንቶ በጥቂት ግለሰቦች እጅ ውስጥ እየገባ ገበያው ወደ ኦሊጎፖሊ ሥርዓት ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ገበያው ሙሉ በሙሉ ኦሊጎፖሊ ውስጥ ከገባ መዘዙ ከባድ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014