ከሁለት ወጣቶች አንዱ ጥንቃቄ በጎደለው የመስማት ችግር ምክንያት የመስማት ችሎታ ማጣት አደጋ እንደሚከሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያም ጥንቃቄ በጎደለው የመስማት ችግር ምክንያት ወጣቶች የመስማት ችሎታቸውን የማጣት አደጋ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ መረጃዎች አሉ። የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የመስማት ቀንም ‹‹የመስማት ችግርን በዘላቂነት ለማስወገድ በጥንቃቄ ያድምጡ›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ከሰሞኑ ተከብሯል።
ዶክተር አለነ መሸሻ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የጆሮ፣ አፍንጫና ጉሮሮ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪምና መምህር ናቸው። በጆሮና በመስማት እንክብካቤ ፕሮጀክት ደግሞ በአስተባባሪነት ይሰራሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የመስማት ችግርና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ጫና በጣም ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። ተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ሲወዳደርም ከፍተኛ ጫና በማሳደር አራተኛውን ደረጃ እንደሚይዝ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያም ከአንድ መቶ ሰዎች መካከል አምስቱ በተወሰነ ደረጃ ለመስማት እንደሚቸገሩም ይጠቅሳሉ።
ይሁን እንጂ ይህን ያህል ጫና ያለው የጤና ችግር በሚገባው መጠን የህክምና ተደራሽነት እንደሌለው ዶክተር አለነ ይናገራሉ። አብዛኛው ከመስማት ችግር ጋር የሚከሰተው የጤና ችግር ደግሞ በትንሽ ወጪና ግንዛቤ በማስጨበጥ መከላከል የሚቻል እንደሆነም የሚጠቁሙት ዶክተር አለነ፤ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ሰዎች ግንዛቤው ኖሯቸው የመስማት ችግርን አስቀድመው እንዲከላከሉ ዓለም አቀፍ የመስማት ቀን በየዓመቱ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ እንደሚከበርም ይገልፃሉ።
ዶክተር አለነ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ምን ያህሉ ሰው የመስማት ችግር እንዳለበት ለማወቅ ወደ ፊት በሚሰራው የዳሰሳ ጥናት እንጂ አሁን ባለው መረጃ መጥቀስ አይቻልም። አሁን እንደመረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውም የዓለም ጤና ድርጅት ለሀገራት ያስቀመጠው መረጃ ነው። በዚሁ መሰረት ከመቶ ሰዎች ውስጥ አምስቱ የመስማትና ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉባቸው መረጃው ያሳያል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
ከፅንሰት ጀምሮ የሚከሰቱ የመስማት ችግሮች አሉ። ከውልደት በኋላም በሚመጡ ኢንፌክሽኖች የሚከሰቱም የመስማት ችግሮች ይኖራሉ። በእድሜ የሚመጣ የጆሮ ነርቭ መድከም ችግርም ሌላኛው ከመስማት ችግር ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው ይላሉ። አብዛኛው ከስኳር፣ ደም ብዛትና ሌሎች የጤና ጉዳቶች ጋር በተገናኘ የሚከሰት ችግር ነውም ብለዋል።
በዚህ ዓመት በተለየ ሁኔታ ለሰዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ የተፈለገው ጥንቃቄ ከጎደለው መስማት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የመስማት ችግር ለመቀነስ እንደሆነ የሚያብራሩት ዶክተር አለነ፤ በርካታ ወጣቶች የጆሮ ማዳመጫዎችን ተጠቅመው ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ሙዚቃዎችንና ፊልሞችን ጮክ አድርጎ የመስማት ችግር ይታይባቸዋል።
ከፍተኛ የድምፅ ልቀት ባሉባቸው የመዝናኛ አካባቢዎች ላይም የማሳለፍ ዝንባሌ እንዳላቸው ይናገራሉ። በተመሳሳይ በግንባታ ቦታዎች ላይና በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የድምፅ ብክለት ይስተዋላል። ስለሆነም እነዚህ ጥንቃቄ የጎደላቸው መስማትና የድምፅ ብክለቶችን በቀላሉ መከላከል ስለሚቻልና እነዚህን መከላከል ካልተቻለ ደግሞ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት እንደተደረገ ያስረዳሉ።
የድምፅ ብክለትን በተመለከተ የቁጥጥር ሕግ መውጣቱ መልካም ቢሆንም የጤና ችግሩን አብሮ ለማየት ከጤና ስርዓቱ ጋር አብሮ መተሳሰር ይኖርበታል። የሕግ ማስከበሩ ተግባርም ከጤና ተያያዥ ጉዳቱ ጋር መያያዝ አለበት። በትስስር ሊሰራ የሚገባና ረጅም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራንም ይጠይቃል ብለዋል።
እንደ ዶክተር አለነ ገለፃ፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ካሉት የሶስተኛ ደረጃ ህክምና አገልግሎት ሰጪና ማስተማሪያ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የድህረ ምርቃ ተማሪዎችንና ከአንገት በላይ ህክምና ዘርፍ ሐኪሞችን ያሰለጥናል። እንደ ሀገር ደግሞ የመስማትና የጆሮ እንክብካቤ ፕሮጀክት መገኛም ነው።
በዚህም የተመላላሽ የጆሮ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ የአንገት በላይ ታማሚዎች ውስጥ ከሀምሳ እስከ ስልሳ የሚሆኑት የጆሮ ችግር ያለባቸው ናቸው። 893 ያህል የጆሮ ታምቡር ቀዶ ህክምናዎችም ተካሂደዋል። ሆኖም ችግሩ ከዚህም በላይ የሰፋ በመሆኑ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማስፋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። እየተማሩ ባሉ ስፔሽያሊስት ሐኪሞች ብቻ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ የአሰልጣኝ ስልጠናዎችም እየተሰጡ ይገኛሉ።
በተለይ ደግሞ አዘውትረው የሚከሰቱ የጆሮ ህመሞችን ማከም እንዲቻል የአሰልጣኞች ሥልጠናው በስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያስረዳሉ። የህክምና አገልግሎቱ ተደራሽ እንዳይሆን የጤና ተቋማት ብቃትና የህክምና ጥራት አለመኖር፣ የህክምና ባለሙያዎች በብዛት፣ በብቃት፣ በጥራትና በተለያየ የሙያ ስብጥር አለመገኘት፣ ለህክምና አገልግሎቱ የሚያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎች እንደልብ አለመገኘትና የመሳሰሉት አሉታዊ ተፅእኖ አሳድረዋል።
ከዚህ አኳያም በቀጣይ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡንና ተደራሽነቱን ለማሻሻል በቅድሚያ የመስማት ችግር በሀገሪቱ ውስጥ በትክክል በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ እንደሚገባ ይናገራሉ። በመቀጠል የዳሰሳ ጥናት ውጤት በመያዝም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ለረጂ ድርጅቶችና ውሳኔ ሰጪ አካላት ብሎም ፖሊሲ አውጪዎች ሰነዱን ማቅረብና ያለውን ጫና ማስረዳት ይሆናል።
በዛ ልክ የተቋማት ግንባታው፣ የሰው ኃይል ስልጠናው፣ የግብዓት አቅርቦቱ ከዛ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረግ፣ በእርዳታ የተጀመረው ፕሮጀክት በዚሁ ሊቀጥል የሚችል ባለመሆኑ መንግሥትና ተቋማት በቀጣይ የሚያስቀጥሉበትን ሁኔታና የራሳቸው የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ጠቅሰዋል። ህብረተሰቡም ከከፍተኛ ድምፅ ራሱን ማራቅና መጠበቅ ይኖርበታል።
በተለይ ደግሞ ወጣቶች ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ የድምፅ ማዳመጫዎችን በመጠቀም ሙዚቃዎችን፣ ፊልሞችና ሌሎችንም መስማት የለባቸውም። በመዝናኛ ቦታዎችም በተመሳሳይ ድምጽ ካለባቸው ቦታዎች ራቅ ማለትና ያለውን የድምፅ ልኬትም መቀነስ አለባቸው መልእክታቸው ነው።
የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ተጠቃሚዎችም የድምጽ ብክለት ጉዳት እንደሚያመጣ አውቀው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመዝናኛ ኢንዱስትሪው አካባቢዎች ያለውን የድምፅ መጠን ለመቀነስም ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋልም ሲሉ ይመክራሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014