የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው መልስ ወደ ኮሞሮስ አቅንተው ዛሬ በወዳጅነት ጨዋታ አቋማቸውን ይፈትሻሉ። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ኮሞሮስ ከማቅናቱ አንድ ቀን አስቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ቡድኑን ያበረታቱ ሲሆን የዋልያዎቹ የተከላካይ መስመር ተጫዋች አማኑኤል ዮሐንስ ሽልማት ተበርክቶለታል።
ቡድኑ ባረፈበት ጁፒተር ሆቴል በነበረው የሽኝት መርሃግብር አቶ ኢሳያስ ጅራና የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚዎች፣ ቡድኑ መልካም ጨዋታ እንዲያደርግ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው በማበረታታት ከቡድኑ ምን እንደሚጠበቅ፣ በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ በምን መልኩ መገንባት እንዳለበትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመቀጠል የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በወሰኑት መሰረት በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለነበራቸው የብሔራዊ ቡድን አባላት በቀጣይ በአዳማ የዕውቅና መስጠት መርሐ ግብር እንደሚከናወን የተገለፀ ሲሆን በቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ ላይ አስተዋፅኦ የነበረው እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫው ከቡርኪና ፋሶ ጋር በተደረገው ሦስተኛ የምድብ ግጥሚያ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ለተመረጠው አማኑኤል ዮሐንስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀለት የክሪስታል ዋንጫና 150 ሺህ ብር ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ደካማ እንቅስቃሴ በማሳየት ከውድድሩ በቀዳሚነት የተሰናበቱት ዋልያዎቹ ከሳምንት በፊት ለኮሞሮሱ የአቋም መፈተሻው ጨዋታ ዝግጅት መጀመራቸው ይታወቃል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉና የመጀመሪያ ቀን በአካል ብቃት ላይ ያተኮረ ልምምዳቸው ከሰሩ በኋላ ስድስት ተጨዋቾችን ከቡድኑ ቀንሰዋል። አሰልጣኙ ከ23 ተጫዋቾች ጋር የመጨረሻ ልምምድ በማድረግ ወደ ኮሞሮስ ሲያቀኑ ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ብቃት ማሳየት የቻለው አቤል ያለው በጉዳት ምክንያት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ለመሆን እንደተገደደ ይታወቃል።
ወደ ኮሞሮስ ካቀኑት የዋልያዎቹ አባላት መካከል ግብ ጠባቂዎች ተክለማሪያም ሻንቆ ከሲዳማ ቡና፣ ፋሲል ገብረሚካኤል ከባህር ዳር ከነማና አቤል ማሞ ኢትዮጵያ ቡና ተመራጭ ሆነዋል። በተከላካዮይ ስፍራ ሱሌማን ሀሚድ፣ ምኞት ደበበ፣ አስቻለው ታመነ፣ መናፍ አወል፣ ሚሊዮን ሰለሞን ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ረመዳን የሱፍ ከወልቂጤ ከነማ፣ አስራት ቱንጆ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ያሬድ ባዬ ከፋሲል ከነማ የተመረጡ ናቸው።
የአማካዮች ስፍራ ላይ ከተመረጡት ተጫዋቾች መካከል አማኑኤል ዮሐንስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ወንድማገኝ ኃይሉ ከሀዋሳ ከተማ፣ ሽመልስ በቀለ ከግብጹ ኤልጎውና፣ ሱራፌል ዳኛቸውና ይሁን እንዳሻው ከፋሲል ከነማ እንዲሁም ቢኒያም በላይ ከመከላከያ ናቸው። በአፍሪካ ዋንጫው ዋልያዎቹ ካስቆጠሩት ሁለት ግብ አንዱን በፍጹም ቅጣት ምት ቡርኪናፋሶ ላይ ያስቆጠረው የዋልያዎቹ የምንጊዜም ኮከብ ግብ አግቢ ጌታነህ ከበደ በዚህ የወዳጅነት ጨዋታ ያልተካተተ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነው። በአንጻሩ በአጥቂ መስመር አዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን የፋሲል ከነማው በረከት ደስታ አንዱ ነው። አቡበከር ናስርና ከነባሮቹ አጥቂዎች አንዱ ሲሆን ይገዙ ቦጋለ ከሲዳማ ቡና፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ዳዋ ሁቴሳ ከአዳማ ከተማና መስፍን ታፈሰ ከሐዋሳ ከተማ በአጥቂ መስመር የተካተቱ ተጫዋቾች ሆነዋል።
ከተቀነሱት ተጫዋቾች መካከል አብድልከሪም ወርቁ፣ በረከት ወልዴ፣ ዳንኤል ተሾመ፣ ፍፁም ጥላሁን፣ ዊሊያም ሰለሞንና ዓለም ብርሀን ይግዛው መሆናቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንደሚቀጥሉ በገለጸበት መድረክ ዋልያዎቹ ከዛሬው የወዳጅነት ጨዋታ አንስቶ የራሱ መገለጫ ያለው የጨዋታ ስልት እንዲኖረው እንደሚፈልግ መጠቆሙ የሚታወስ ነው። ቡድኑ በተለይም ኳስን በተቃራኒ ቡድን ክልል ውስጥ ተጭኖ በመጫወት ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት የሚከተል እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ መናገራቸው ይታወሳል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በዛሬው የወዳጅነት ጨዋታ አዳዲስና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በማዋሃድ ቡድኑ መለያው እንዲሆን በሚፈለገው የአጨዋወት ስልት ከወዲሁ ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግንባታውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዋልያዎቹ ተጋጣሚዎች ኮሞሮስ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሳተፍም ያልተጠበቀ አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ጋናን የመሳሰሉ ታላላቅ ቡድኖችን በማሸነፍ ጭምር ከምድብ ማጣሪያ ማለፉ አይዘነጋም።
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም