ውይይት ለአንድ ሀገርና ማህበረሰብ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ አሁን እነግራችኋለው። ልዩነትን ወደጎን ብሎ ለጋራ ጥቅም በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ያለውን ሀገራዊ በረከትም አወራችኋለው። የአንድ ሀገር የስልጣኔ ልክ ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ መነጋገር መቻል ነው እላለው። ይሄ በሕይወቴ ውስጥ ያወኩት አንዱና ትልቁ ጥበቤ ነው። መነጋገር ከዘመነ እና አርቆ ከሚያይ ጭንቅላት ውስጥ የሚመነጭ የመልካም እሳቤ ነጸብራቅ ነው። መነጋገር ለሀገር መጥፎ ነገሮችን እየጣሉ ለሀገር የሚጠቅሙ ምርጥ ነገሮችን የምንወስድበት የመጨረሻው የእውቀት ማሳያ እንዲህም ነው።
ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ ግን ይሄ ነገር ትርጉም ያለው ሆኖ አይታይም። ብዙዎቻችን ውይይት የምንጠላ፣ የምንፈልገውን ነገር በኃይልና በጉልበት የእኛ ለማድረግ የምንበረታ ነን። ለምን መነጋገር አቃተን? ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት ለምን ከበደን? ከትላንት እስከዛሬ ባለመነጋገራችን ብዙ ነገር አጥተናል እያጣንም ነው። ለምን እንደሆነ አላውቅም ደጆቻችን፣ ቢሮዎቻችን ለብዙ ነገር ክፍት ሆነው ለውይይት ሲሆን ግን የሚዘጉት ናቸው። ለምን እንደሆነ አላውቅም አብዛኛዎቹ ውይይቶቻችን ፍሬ ያላመጡ ጊዜና ገንዘብ ያባከኑ ሆነው ያለፉ ናቸው። ለየትኛውም የሰው ልጅ የስልጣኔ መሰረቱ ንግግር ነው። ውይይት ከስህተት የምንጸዳበት፣ ልክ ያልሆኑ ነገሮች ልክነት የሚያገኙበት የልዕልና ስፍራ ነው።
እንደ ሀገር ስልጣኔአችንን ውይይት ውስጥ መፈለግ ይኖርብናል። እስካሁን ድረስ ጠልፈውን የጣሉን ችግሮቻችን ከእኛ በላይ ስለገዘፉ ሳይሆን እኛ ለንግግር በሮቻችንን ስላልከፈተን ነው። በመሆኑም መከራዎቻችንን በምክረ ሀሳብ ማጽዳት ይኖርብናል። ጥሩ ነገር ፍለጋ ከመነሳታችሁ በፊት ውይይትን ባህል እናድርግ። አንድ ህዝብ በብዙ ልዩነት ውስጥ፣ በብዙ አለመግባባት ውስጥ ሆኖ ለስምምነት በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ ከቻለ እርሱ ስልጡን ህዝብ ነው። ብዙዎቻችን ችግሮቻችንን በጉልበትና በትግል ለመፍታት ስለምንሞክር የንግግርን ጥቅም አናውቀውም። ብዙዎቻችን የሀሳብ ልዩነታችንን ልማት በማፍረስና መንገድ በመዝጋት ስለምንጠይቅ የመነጋገርን ጥቅም አልደረስንበትም። ብዙዎቻችን ጥያቄዎቻችንን በአፈሙዝ ለመመለስ ስለምንሞክር የውይይትን ዋጋ አናውቀውም።
በአስተሳሰቡ የሰለጠነ ማህበረሰብ ሀገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ጎራዴ አይመዝም፤ ጦር አይሰብቅም። በአስተሳሰብ ስንሰለጥን በራችንን ለውይይት ክፍት እናደርጋለን። ውይይት የብዙ ችግሮች የብዙ አለመግ ባባቶች የመፍትሄ ቦታ ነው። ከመፍረስና ታሪክ ከማበላሸት ባለፈ በጥልና በክርክር፣ በጦርና በጎራዴ የምናመጣው ለውጥ፣ የምንመልሰው ጥያቄ የለም። ትውልድ ከመመረዝ ባለፈ በወቀሳና በትችት የምናመጣው ሀገራዊ ለውጥ የለም። እውነተኛ ለውጥ ያለው በመነጋገር ውስጥ ነው። እውነተኛ የሀገር ፍቅር ያለው ልዩነትን ወደ ጎን ብሎ ለጋራ ጥቅም በጋራ በመወያየት ውስጥ ነው።
ትላንትና እና ዛሬ የሀገራችን አንኳር ችግር ይሄ ነው። ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ለመስማማትና አንድ ለመሆን ቀላል ዘዴ እያለ መብት ለማስከበር ጫካ የምንገባ ነን። ለመስራት ለመለወጥ መነጋገርና መቀራረብ እየተቻለ በያዝነው የሀሳብ ልዩነት ብቻ እንደ ጠላት የምንተያይ ነን። አሁን ላይ ብዙ ነገራችን ስህተት ሆኖ ለማስተካከል የከበደን ከውይይት ይልቅ በኃይልና በጉልበት ለመስማማት የሞከርንበት ያለፈ ጥፋታችን የፈጠረው ነው እላለሁ። የዛሬ መልካችን በትላንት የተፈጠረ ነው እያልኩ ነው። ነጋችን እንዳይበላሽ ዛሬ ላይ በውይይት የሚያምን አዲስ ትውልድ መፍጠር ይኖርብናል። አላማችን ሀገር መገንባት ከሆነ ባለመስማማት ውስጥ መስማማትም እንችላለን።
አላማውን አንድ ሀገርና ህዝብ ያደረገ ትውልድ ሁሌም ቢሆን ለመነጋገር በሩን የከፈተ ነው። ዛሬ ላይ የፈጠርናቸውና ከትላንት ይዘናቸው የመጣነው ብዙ ሀገራዊ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት በመነጋገር ብቻ ነው። ብዙ ኃይል ብዙ ተከታይ ሊኖረን ይችላል፤ ሀገር ለመገንባት ግን እንደ መነጋገር የሚጠቅመን ነገር የለም። ብዙ እውቀት ብዙ ጥበብ ሊኖረን ይችላል፤ የመወያየትን ያክል ግን የሚበጀን የለም። ልዩነታችንን ትተን ወደ ፊት ለመሄድ በምናደርገው ትግል ውስጥ ኃይል ሆኖ የሚያግዘን ውይይት የታከለበት የህዝቦች ተሳትፎ ብቻ ነው። ለእድገት ውይይትን ብቸኛው አማራጫችሁ አድርጉ። ሌላው ሁሉ ከኋላ የሚከተላችሁ ነው።
እንወያይ…ተወያዩ። በውይይታችን ውስጥ አንድነታችን ያብባል። በመነጋገራችን ውስጥ ፍቅራችን ይጨምራል። ከእንግዲህ ላለችው ኢትዮጵያ የተባበረ የሀሳብ ልዕልና እንጂ ጦርና ጎራዴ አያሻትም። ከእንግዲህ ለምትፈጠረው የሀበሻ ምድር አንድነት እንጂ መለያየት አይጠቅማትም። ከእንግዲህ ለሚመጣው አዲስ ትውልድ እውነትን እንጂ ማስመሰልን አናወርሰውም። ሀገራችንን ለዘመናት ስንገላት ኖረናል። እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ኋላ ቀር አመለካከት ስናኮስሳት ኖረናል። ስር በሰደደ እኔነት ስናደማት ስናቆስላት ኖረናል። ስናጎድፋት ስንመርዛት ሰንብተናል። ከእንግዲህ ትንሳኤዋ እንዲሆን እፈልጋለው።
ከእንግዲህ የጎዳናትን ያክል የምንክስበት ዘመን እንዲሆን ሁላችሁም እመኑ። በፖለቲካው አለም የቆማችሁ እናተ ሀሳባችው አንድ ሀገርና አንድ ህዝብ ከሆነ ከእኔነት ወታችሁ ከነልዩነታችሁ ለውይይት መቀመጥን ልመዱ። የሀገራችሁ ነገ የሚያስጨንቃችሁ ወጣቶች ሀሳባችሁ ሀገርና ህዝብ ከሆነ ከማስመሰል ወጥታችሁ ለእውነት ቁሙ። አሁን ላይ አብዛኞቻችን መብታችንን ለማስከበር የምንሄድበት መንገድ ሁሉ ጊዜ ያለፈበት ነው። ለምንም ነገር ጠብመነጃ የምናነሳ ነን። ለምንም ነገር ጦርና ጎራዴ የምንታጠቅ ነን። ለምንም ነገር ተከታዮቻችንን የምናነሳሳ ነን።
ሆኖም በመነጋገር እንጂ በአፈሙዝ መብት አይከበርም። በአንድነትና በመተቃቀፍ እንጂ በልዩነት ውስጥ ሀገር አትለማም። እውነታችንን…ፍጻሜአችንን ፍቅር አድርጉት። መነሻና መድረሻችሁን ሀገርና ህዝብ አድርጉት። ሌሎች ላይ መጥፎ መሆን፣ በሌሎች ላይ የራስን የበላይነት መጫን ለዚህ ዘመን የሚመጥን አይደለም። እንደ ሀገር ለዘመኑ የሚመጥን ሀሳብና አመለካከትን ማራመድ ይኖርብናል። ነገ ላይ ትውልዱ ለሚጠይቀን ሀገራዊ ጥያቄ እብለት የሌለበት መልስ ማዘጋጀት አለብን። ይሄ የሚሆነው ደግሞ በመነጋገርና በመወያየት ብቻ ነው።
ሀገርና ማህበረሰብን ባላገናዘበ መልኩ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ውድቀት እንጂ ስኬት አይኖረውም። ከምንም በፊት ገዢና በላጭ ሀሳብ ያስፈልገናል። በዛ ገዢና በላጭ ሀሳብ ተረማምደን የቆምንለትን ህዝብ ማገልገል ይቀጥላል። መጀመሪያ ከምንም በፊት አንድነታችንን ለህዝብ ማሳየት ይኖርብናል። አላማችን ሀገርና ህዝብ ማሻገር እስከሆነ ድረስ ከመተቻቸትና ከመጠላላት ወጥተን በፍቅር ውስጥ፣ በመግባባት ውስጥ ራሳችንን ለህዝብ ግልጽ ማድረግ ይቻለናል እላለው። አንዱ አንዱን እየናቀ፣ አንዱ አንዱን አይረባም እያለ ልዕልናን ለማግኘት የሚደረግ የብኩርና ሩጫ አይገባኝም። ሁሉም ዜጋ በአስታራቂና በበላጭ ሀሳብ ኢትዮጵያን የማገልገል መብት አለው።
ይሄን ስናደርግ ለምን እንደምንሞት፣ ለምን እንደምንታገል ስንጠየቅ ለሀገርና ህዝብ የምንል ብዙዎች ነን። ይሁን እንጂ ሀገርና ህዝብ በመግባባት ውስጥ እንደሚፈጠር ገና አልገባንም። ዛሬም ድረስ ታሪኮቻችን ሁሉ ጦርነት ወለድ ናቸው። ባለመግባባት ውስጥ ያበላሸናቸው በርካታ ትላንትናዊ መልኮች አሉን። ዛሬን እንኳን ሰው እንሁን እስኪ፤ ዛሬን እንኳን በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ ሀገር እንፍጠር እስኪ። ለአንድ አላማ የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ ሲተቻቹና ሲናናቁ ማየት ራስን ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። ለአንድ አላማ የቆሙ ዜጎች መግባባት አቅቷቸው ሲገፋፉ እጅግ ያሳዝናል። አላማችን ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ ከነውር መውጣት ግድ ይለናል። በትችትና በወቀሳ ውስጥ ማሸነፍ የለም። እውነተኛ ማሸነፍ በመዋደድና በመከባበር ውስጥ ነው ያለው።
ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ፍቅርን እንልበስ፤ መጀመሪያ መከባበርን እንልመድ፤ ከዛ ወደ ህዝብ እንመልከት። አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ውይይት ብቸኛ መፍትሄዋ መሆኑን ተገንዝበን በየትኛውም ሁኔታ ላይ ብንሆን ራሳችንን ለውይይት እናዘጋጅ። የምንፈልገውን ነገር በኃይልና ባልተገባ መንገድ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ለውይይት መቀመጥ እጅግ ዋጋ ያለው ነገር ነው። ብዙዎቻችን ተምረናል እውቀታችንን ግን ጥቅም ላይ ስናውለው አንታይም። ተምረን ፊደል ቆጥረን ሀገር ከመጥቀም ይልቅ ሀገር የምንጎዳ ነን። በክብር በማዕረግ አንቱ ተብለን ለስህተት የተጋለጥን ነን። ዲግሪ ይዘን ከአውሮፓና ከኢሲያ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ዶክተር እና ፕሮፌሰርነት አግኝተን ከለውጥ ይልቅ ለነውጥ የበረታን ነን። ችግሮቻችንን በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ በሌላ ባልተገባ መንገድ ለመፍታት የምንበረታም ነን።
መማር ራስን ማሰልጠን ነው። መማር አእምሮን መግራት አስተሳሰብን ማረቅ ነው። መማር ከትላንት የተሻለ ነገን፣ ከአምና የላቀ ዘንድሮን መፍጠር ነው። መማር አዲስ ማንነትን መላበስ ነው። መማር መሰልጠን.. መለወጥ ነው። ይሄ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ ላይ የእኛ ሀገር ምሁራን ግን ለንግግር መቀመጥን እንደ ጉድ የሚፈሩ ናቸው። ሀገራችን ላይ እንዳለው የትምህርት ተቋም ቢሆን፣ እንደ ዩኒቨርሲቲ ብዛት ቢሆን፣ እንደ ተማረው የወጣት ቁጥር ቢሆን ዛሬ ላይ ችግሮቻችን ሁሉ ድራሽ አባታቸው በጠፉ ነበር።
አሁንም እላለው፣ ጦርና ጎራዴ ታጥቀን ጫካ ከመግባት ወጥተን ለችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥን ባህል እስካላደረግን ድረስ መማራችን ትርጉም አይኖረውም። እዚች ሀገር ላይ ለምንም ነገር ደም የሚፈስ ነው። እኛ ለመስማማት ሰው መሞት የለበትም። እኛ ለመታረቅ ደም መፍሰስ የለበትም። ያለምንም ደም መስማማት፣ አንድ መሆን እየቻልን የንጹሀን ደም የሚፈስበት ምንም ምክንያት አይታየኝም። ለመፍትሄ እንማር። ህዝብ ለመለወጥ ሀገር ለማሻገር ትምህርት ቤት እንግባ። መፍትሄ የሚያመጣ እውቀት ከሌለን በመማራችን ለሀገር ስጋት እንደሆንን ልናውቅ ይገባል። እውቀታችንን ወደ ተግባር በመቀየር እኛንም ሆነ ሌላውን መጥቀም አለብን። ውይይትን መልመድ አለብን። ለችግሮቻችን መፍትሄ ለማምጣት መነጋገር አለብን።
አሁን ላይ ብዙ ችግሮቻችን በተማሩ ሰዎች የመጡ ናቸው። መማር ራስንም ሆነ ሌላውን ከጉዳት የሚታደግ ካልሆነ መማራችን ትርጉም አይኖረውም። ከእኔነት የወጣ፣ እኛነትን የዋጀ ሁሉን አቃፊ እሳቤ ያስፈልገናል። ቀሪ ዘመናችንን ለኢትዮጵያ የምንተጋበት የከፍታ ዘመን እንዲሆንልን ሁላችንም መበርታት አለብን። ብዙ ችግሮች ሊኖሩብን ይችላሉ፣ መልስ የሚፈልጉ ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩን ይችላሉ ሁሉንም ግን በውይይት ለመፍታት መሞከር አለብን። በምክንያታዊነት የታጀበ ገዢ እውቀት ሊኖረን ይገባል። መጠቀም ከቻልን ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ አዎንታዊ ሀሳቦች ሀገራችን ውስጥ አሉ። ግን መነጋገርና መወያየትን ልማድ ስላላደረግን ያን መልካም ሀሳብ የምንጠቀምበት አጋጣሚ አላገኘንም። ለዚህም እኮ ነው ተምረን ግራ የተጋባነው። አውቀን ፊደል ቆጥረን ስህተት የምንሰራው።
ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ሀሳቦቻችንን የምናዋጣበት የጋራ መድረክ ያስፈልገናል። በእያንዳንዳችን ውስጥ ሀገር ሊለውጡ የሚችሉ ብዙ ተዐምረኛ ሀሳቦች አሉ። እነዛን ሀሳቦች ደግሞ ወደ አንድ በማምጣት ለምንፈልገው አላማ መጠቀም እንችላለን። ይሄ የሚሆነው ግን ከጥላቻና ከመለያየት ወጥተን ለድርድር አብረን መቀመጥ ስንችል ነው።
መወያየትንና መነጋገርን ባህል ያላደረገ ሀገርና ህዝብ ደግሞ ሁሌም ግራ እንደተጋባ ነው። ያልተነኩ ብዙ ሀሳቦች አሉን። የእኔ ሀሳብ ልክ ካልሆነ ልክ ሀሳብ ወዳለው በመሄድ፣ እኔ ልክ ከሆንኩ ደግሞ ልክ ያልሆኑት ከእኔ ሀሳብ ጋር በመቀናጀት ለሀገራችን ተዐምር መፍጠር እንችላለን እላለው። መጀመሪያ እንግባባ፣ መጀመሪያ አንድ እንሁን። አንድ ሀገርና ህዝብ ይዘን ተለያይተን መቆም የለብንም። ሀገር የምትገነባው በብዙ ሀሳቦች ነው። የእኔም የአንተም ሀሳብ ሀገር ለመገንባት አስተዋጽኦ አለው። የተለያየ አይነት አመለካከትን የምናራምድ ብዙ ሰዎች እንኖራለን፤ በመወያየት መግባባት እንደምንችል ማወቁም ተገቢ ነው።
ስልጣኔ በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ምርጡ ስልጣኔ ግን ራስን ለውይይት ማዘጋጀት ነው። መነጋገርን የመሰለ ስልጣኔ አላውቅም። እናንተም የተሻለው ይሄ ነው ላትሉኝ ትችላላችሁ። ስልጡን ማህበረሰብ በውይይት የሚፈጠር ነው። ስልጡን ሀገር የንግግር ውጤት ናት። በአስተሳሰብ፣ በትምህርት፣ በታሪክ በብዙ ነገር ከፊት ቀድመን ሊሆን ይችላል፤ የሁሉም ፈጣሪ ግን በልዩነት ውስጥ መስማማት ነው። ሳንስማማ..አንድ ሳንሆን የምናመጣው ቅንጣት ለውጥ የለም። ስለዚህም እንነጋገር እላለው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም