ምሥራቅ አፍሪካ፣ በአገሮች የድንበርና በእርስ በእርስ ግጭት እንደ ድርቅና ረሀብ የጎርፍ አደጋና የአንበጣ ወረራ በመሳሰሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚጠቃ አካባቢ ነው። አካባቢው በየጊዜው ግጭቶች ስለሚታዩበት ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጥሎ በጦርነት ተጠቃሽ ቦታ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ባሻገር የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ድርቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለ ክስተት ሲሆን፤ የዝናብ እጥረትና ተደጋጋሚ የበረሃ አንበጣ ክስተትም ሌሎች ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው። በዓለም ተከስቶ የነበረውና የአገራትን ምጣኔ ሀብት ያላሸቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝም አንዱ ችግር ነበር።
በያዝነው ዓመት የካቲት መባቻ ብቻ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያወጣው መረጃ በምሥራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ 13 ሚሊየን ሕዝብ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ እያንዣበባቸው መሆኑን ያስረዳል። በዚህም በያዝነው የፈረንጆቹ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከፍተኛ አደጋ ይሄው ሪፖርት ያሳየ ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅ እአአ ከ1981 ጀምሮ በተደጋጋሚ በመጠቃት ላይ ያለ አካባቢ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያሳያል።
በተለይ ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች የተከሰተው የዝናብ እጥረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ሰፊ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ይሄም የሰብል ምርት ለማምረት ካለማስቻሉም በላይ፤ በርካታ የቤት እንስሳትን ለመኖ እና ለመጠጥ ውሃ ችግር በማጋለጡ ሰፊ የእንስሳት ሃብት በድርቁ ምክንያት እንዲረግፉ ሆነዋል። አንዳንድ አርብቶ አደሮች ደግሞ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የውሃ እጥረት እና የግጦሽ ችግር ማጋጠሙን ተከትሎ ለከብቶቻቸው ውሃ እና የግጦሽ ሳር ፍለጋ እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል። ይሄም ሆኖ ሰዎች ከእንግልት፤ እንስሳቱም ከሞት ሊድኑ አልቻሉም።
በዚህ መሀል ደግሞ በአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ጎሳዎች መካከል በግጦሽ መስክ ምክንያት ግጭቶች ይጨመራሉ። ምክንያቱም የአርብቶ አደር ሕይወት ከአርሶ አደሩ የሚለየው ብዙ ከብቶች ይዞ ከቦታ ቦታ መኖ ፍለጋ የሚዘዋወር መሆኑ ነው። አንድ ቦታ ላይ ሊቆይ የሚችለው ከብቶቹ የሚፈልጉት የግጦሽ መስክና የመጠጥ ውሃ እስካለ ድረስ ብቻ ነው። ታዲያ አርብቶ አደሮቹ ለከብቶች መኖ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲኳትኑ በውሃና ግጦሽ ምክንያት በሄዱባቸው አካባቢዎች ላይ የመጋጨት አደጋዎች ያጋጥማሉ።
ይህ ሲሆን ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ ቀጣናዊ ዳይሬክተር እንዳሉትም፤ በእነዚህ ቦታዎች ድርቁን ለመቋቋም የተሰበሰቡ የእንስሳት መኖዎች ስለሚወድሙ የቁም ከብቶችን ሞት በሚፈለገው ልክ ማስቀረት አልተቻለም። በዚህና ተያያዥ ምክንያቶችም በተደጋጋሚ የተከሰቱት ድርቆች በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ይገኛል። በመሆኑም ክስተቱ አስቸኳይ ሰብዓዊ ምላሽ የሚሻና የተጎዱ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የመቋቋም ተግባራት በቀጣይነት መከወን ያስፈልጋል።
እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም መጀመርያ ድረስ በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታን እንደሚፈልጉ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ያወጣቸው የመረጃ ትንበያዎች ይጠቁማሉ። የዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በያዝነው ዓመት በኢትዮጵያ ደቡብ ምሥራቅና ደቡባዊ አካባቢዎች ማለትም በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው ድርቅ ሲሆን፤ በዚህም ለአብነት፣ በቦረና ዞን ብቻ አንድ አርብቶ አደር ከ300 ከብቶች በላይ በድርቁ ምክንያት የሞቱባቸው መሆኑ መገለጹ የአደጋውን አስከፊ ገጽ ያሳያል።
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ ምክንያት 3ነጥብ 5 ሚሊየን ሕዝብ ለአስቸኳይ እርዳታ የተጋለጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊየን በላይ እንስሳት መሞታቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ አስታውቋል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 6ነጥብ 8 ሚሊየን ሕዝብ ለአደጋ መጋለጣቸውን፤ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ደግሞ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች የውሃ እጥረት ያጋጠማቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የድርቅ አደጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች አብዛኞቹ በሚባል መልኩ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ያሉት አርብቶ አደሩ ወይም ደግሞ በከብት እርባታ የሚተዳደሩ ሰዎች ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ድርቅ ሲያጋጥማቸው ለከብቶቻቸው መኖ ፍለጋ ሲሰማሩም የተሻለ መኖ እና ውሃ ባለበት አካባቢ ዳሳቸውን ተክለው ይቆያሉ። የሚያስፈልገው መኖና ውሃ ሲጠፋ ደግሞ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሄዳሉ።በያዝነው ዓመት በደረሰው ድርቅ በቦረና ዞን ለከብቶቻቸው ውሃና መኖ ፍለጋ 200 ኪሎ ሜትር ርቀው በመሄድ ጭምር እንስሳቶቻቸውን ለመታደግ ቢሞክሩም ያልተሳካላቸው በርካቶች ናቸው።
በዚህም በየቦታው በመኖና ውሃ ችግር ምክንያቶች የሞቱ ከብቶች በየቦታው የሚታዩ ሲሆን፤ በቁም ያሉትም ቢሆን በቆዳ ብቻ የተሸፈነ አጥንታቸው የሚቆጠር ሆነው የሚታዩ፤ ሞታቸው የቀረባቸው የሆኑ ናቸው። ባጠቃላይ አርብቶ አደሮቹ ድርቁ ባመጣባቸው አደጋ ከብቶቻቸው በድርቅ አደጋ እየረገፉ፤ በየቦታው ወድቀው ቅሪተ አካላቸው የሚታዩ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለፈው ለፓርላማ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ስለ ድርቁ ጠቅሰዋል። ለድርቁ የአጭር ጊዜ መፍትሔው የዕለት ደራሽ ምግብ፣ አልሚ ምግብ፣ ክትባትና መሠረታዊ አቅርቦቶችን ለተጎጂዎች ማቅረብ ነው ማለታቸው ይታወሳል። በዘላቂነት ድርቁን ለመከላከል ደግሞ በውኃ አያያዝና አጠቃቀም ላይ መሥራት፣ የግብርና ምርቶችን የገበያ ትስስር ማጠናከር፣ እንዲሁም ደመናን በማጎልበት ሰው ሠራሽ ዝናብን ማሳደግ መሆኑን አስረድተው ነበር።
ሆኖም በኢትዮጵያ በየጊዜው ድርቅና ረሃብ አጋጠመ ሲባል እንደ መፍትሔ የሚነሱት የመስኖ ልማትና የውኃ አጠቃቀም ቢሆኑም፤ በዘላቂነት ሲተገበሩ አይታይም። ድርቅ ከመድረሱ በፊት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ችግሩ ከሚደርስባቸው አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ተያይዘው መሥራትን መልመድ አለባቸው።
በወረቀት የሚቀርቡ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚያስጨበጭቡና የሚስደንቁ ቢሆኑም፤ በጠረጴዛ ላይ ተደርድረው አደጋዎች እየተከሰቱ ደረት የሚስደልቁ እየሆኑብን ነው። በቆላማ አካባቢዎች ውሃ ማቆር ላይ ቢተኮር፤ ለከብቶች የመጠጥ ውሃ በማመንጨት ረገድ በትኩረት ቢሠራ፤ ከአርብቶ አደሮች ጋር ባለሀብቶች በቁም ከብት ንግድ የገበያ ትስስር የሚጥሩበት መንገድ ቢመቻች፤ በመንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርቅ አስመልክቶ የሚሰጡ የማስጠንቀቂያ ትንበያዎች ላይ ትኩረት ቢሰጥ፤ ቢያንስ አርብቶአደሩ ከብቶቹን በቶሎ ሊሸጥ የሚችልበትና ገንዘቡን ባንክ አስቀምጦ አደጋውን ሊቀንስለት ይችላል።
በእርግጥ ድርቅ በደረሰባቸው አካባቢዎች ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ችግሩን አስቀድሞ በመተንበይ ለመቀነስ እንደተቻለ ሰነዶች ያስረዳሉ፤ የግብርና ሚኒስቴር የደንና አካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአርብቶ አደር ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ ድርቁ የሚያስከትለውን አደጋ መቀነስ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ ማድረግም ችለዋል። ሆኖም ለችግሩ ግን ዘለቄታዊ መፍትሔ መሻትን የዘወትር ሥራ ማድረግ ይገባናል።
ድርቅ በመጣ ቁጥር የከብት መኖና ውሃ በመስጠት ችግሩን መቀነስ ቢቻልም ለዘለቄታው መፍታት የማይታሰብ ነው። ሁላችንም ለዘለቄታዊ መፍትሔ መረባረቡ ያዋጣናል። በረሃውን አልምተው ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ እየላኩ ከሚጠቀሙ አገሮች ተሞክሮ በመቀመር ጭምር ለውጥ ማምጣት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ከጊዜያዊ እርዳታ በሻገር ሊመለከቱ፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ባለሀብቶች፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በረዘመውም እቅድ መሳተፍ፤ ለአጭር ጊዜውም የምግብና የመኖ ድጋፍ በማድረግ ችግሩን በጊዚያዊነት መቀነስ ተገቢ ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም