ምንድን ነው እየሆነ ያለው !? የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ የደቀነውን አደጋ በቅጡ አልተረዳነውም ማለት ነው፤ በዚሁ ከቀጠለ የህልውናችን፣ የሰላማችን፣ የደህንነታችንና የጸጥታችን ስጋት መሆኑስ አልተገለጠልንም ማለት ነው !? ስንት ዋጋ የከፈልንለትና እየከፈልንለት ላለው ለውጥ ፈተና እንደሆነ አልገባንም ማለት ነው !? የእንግሊዙ የግሎሪየስ ፣ የፈረንሳይ ፣ የራሽያው የጥቅምት ፣ የ1966ቱ የጸደይ አብዮቶች የተቀሰቀሱት በኢኮኖሚያዊ ቀውስ መሆኑን ዘነጋን ማለት ነው?፤ ነው አብዮት አማረን !?
አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ኢኮኖሚው ከሰንደቃችን ፣ ከዜግነታችን ፣ ከኢትዮጵያዊነታችን ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ የጋራ አካፋያችን መሆኑ እንደ ስፔስ ሳይንስ ከብዶናል ማለት ነው !? ከአገራዊ ምክክሩ ባልተናነሰ ለብሔራዊ እርቅና አገራዊ መግባባት መንገድ እንደሚያቀና አልታየንም ማለት ነው !? ምንድን ነው የነካን !? በዚህ ያልደነገጥን በምን ልንደነግጥ ነው !? ተሯሩጠንና እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት ለመነሳት ከዚህ ፈተና በላይ ምን ይምጣልን !?ነው ወይስ እኔን ያልገባኝ ነገር አለ !?
የኑሮ ውድነት ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ ስራ አጥነት ፣ ድህነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ብሔርና ሀይማኖት የላቸውም ። አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ሲዳማ ፣ ሱማሌ ፣ ትግሬ ፣ ወዘተረፈ አይደሉም ። ኦርቶዶክስ ፣ እስላም ፣ ክርስቲያን ፣ ዋቄ ፈና ፣ ወዘተረፈ አይደሉም ። ኢትዮጵያዊ ከፍ ሲልም ሰው ናቸው ። እነዚህ የኢኮኖሚ መሠረታዊ አላባውያን ጤናማ ከሆኑ ሕዝብን በአዎንታ ሳይነጋገር አንድ ያደርጋሉ ። ሕዝብን ለድጋፍ ለአንድነትና ለፍቅር ያነሳሳሉ ። በተቃራኒው እነዚህ መሠረታውያን ጤናማ ካልሆኑ ሕዝብን በአሉታ ማለትም ለተቃውሞና ለአመጽ በአንድነት ያነሳሳሉ ። ይህ ኢኮኖሚያዊ ስኬታችንም ሆነ ውድቀታችን ከፖለቲካው በላይ ጉልበት እንዳለው ያስረዳል ። ከፖለቲካችን በላይ ለኢኮኖሚያችን ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ የሚለው ለዚህ ነው ።
በኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ ሕልውናችን አደጋ ላይ እየደወደቀ ቢሆንም ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥን ፣ አጥጋቢና ወጥ አለመሆኑን ስመለከት ፤ ለዘላቂ መፍትሔ ተጨባጭ ፣ ግልጽና ተፈጻሚ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሳጣ ፤ የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ እየተመላለሱ ነው ። የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ከቀጠለ ከሕወሓትና ሸኔ በላይ የህልውናችን አደጋ ፤ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የመሆን አሉታዊ አቅሙን በቅጡ ተረድተነዋል !? ወላፈኑስ ያለ ልዩነት እኩል እየተሰማን ነው !? የመንግስት ባለስልጣናትስ የኑሮ ውድነት እንደ ተራው ሕዝብ ይሰማቸዋል !? ካልተሰማቸው እንዴት የመፍትሔው አካል ይሆናሉ !? እንዴትስ ለመፍትሔው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይችላል !? እያልሁ እብሰከሰካለሁ።
ሁለት አስር አመታትን ያስቆጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የዜጋውን ኑሮ በብርቱ እየፈተነው፤ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወደለየለት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስነት እንዳይባባስ እያሰጋ ይገኛል። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ኢኮኖሚው ለቀደሙት 27 አመታት የአንድ ቡድንና የጭፍራው መጠቀሚያ በመሆኑ በተከሰተው ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ አሻጥር፣ ጦርነትና አለመረጋጋት ተጨምሮበት ኑሮው አልቀመስ ብሏል።
በአናቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት፤ ከገበሬ ማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገ ደላላ፤ የገነገነ ሙስና፣ በግብይት ሰንሰለቱ የተንሰራፋው ስርዓት አልበኝነት፤ ዋጋን በአድማ መወሰን፤ ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር፤ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በመንግስት ዘንድ ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር፤ የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ አለመሆን፤ ወደብ አልባ በመሆናችን በየአመቱ ቢሊዮኖችን የምናወጣ እና ስለመብቱ የሚቆረቆርና የሚጠይቅ ሸማች አለመፈጠሩ እንደ ዚምባብዌና ቬኒዞላ ባይሆንም በሰዓታት ልዩነት ለሚተኮስ የዋጋ ግሽበት እንዲዳረግ መግፍኤ ሆኗል።
በየፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ግሽበትንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል። አምስት ሊትር የምግብ ዘይት 1200 መግባቱ ሳያንስ ከገበያ ጠፍቷል። የስንዴ ዱቄት በኪሎ 52 ብር ተተኩሷል። ዳቦ ከ4 እስከ 5 ብር ገብቷል። ጤፍ እንደዚሁ በኪሎ 52ና ከዚያ በላይ ገብቷል። ቡና በኪሎ ወደ 420 ብር አሻቅቧል። ሽንኩርት፣ ቲማቲም አጠቃላይ አትክልትና ፍራፍሬ አልቀመስ ብሏል። እህልና ጥራጥሬውም ብሶበታል።
በዚህ ሳቢያ በመዋቅራዊና በተቋማዊ ችግር የተነሳ ጽኑ ታማሚ ሆኖ ለኖረው ኢኮኖሚ ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። የለውጡ መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ያደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን አምኖ የአዲሱ መንግስት ቀዳሚ ተግባርም ይሄን ማስተካከል እንደሆነ ቃል ቢገባም፤ በሚፈለገው ፍጥነትና ቅንጅት እየሄደ አይደለም። እንዲያው ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ይገኛል።
ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በዚህ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው ችግሩን እንዳወሳሰበው ሰሞኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው መድረክ ይፋ ሆኗል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በተካሄደው ጨፌ ኦሮሚያ ስብሰባ ላይ ይሄን ሀቅ ደግመውታል። ከዚህ ውይይት በፊት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ክትትል መሠረት በየመካዝኑ ተከዝነውና ተደብቀው የሚገኙ የምግብ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመያዝ ሲንቀሳቀስ በየአካባቢው ያለ አመራር ለመተባበር እንዴት እግሩን ይጎትትና ለማደናቀፍም ይጥር እንደነበር መግለጹ የኮሚሽኑን ግኝት ተጨባጭ ያደርገዋል። መንግስት መዋቅሩን ካላጠራ ችግሩ ተባብሶ የስርዓቱም የአገሪቱም አደጋ መሆኑ አይቀርም።
ይሄን ስርዓት አልባ የግብይት አሰራር መንግስት በማያዳግም ሁኔታ በሕግ አግባብ ስርዓት ሊያሲዘው ካልቻለ፤ ከማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገውን ደላላ ከግብይት ሰንሰለቱ ካላስወጣ፤ በድጎማ ከውጭ የሚገባን ዘይትና ስንዴ ለነጋዴው 70 በመቶ፤ ለሸማቹ 30 በመቶ የነበረውን የስርጭት ቀመር ቀይሮ የተገላቢጦሽ ካላደረገ፤ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ተመንና የትርፍ ሕዳግ ካልተቀመጠ፤ ገበያውን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ካላደረገው ችግሩ ተባብሶ ተባብሶ ወደለየለት የጸጥታና የደህንነት ችግር እንዳይባባስ ያሰጋል።
የዋጋ ግሽበቱ ከ40 በመቶ በላይ ተተኩሶና በየቀኑ እየተባባሰ ባለበት፤ የኑሮ ውድነቱ ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑሮ የማይቀመስ ካደረገው፤ የስራ አጡ ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ እንዴት ስለኢኮኖሚያዊ ስኬት ማውራት ይቻላል?፤ እንዴት ስለብልጽግና ማለም እንችላለን?። መንግስትስ ከዚህ በላይ ምን አንገብጋቢ ጉዳይ አለው?፤ ይሄን ችግር ለመፍታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የማያሳየው ሕዝብ ሰልፍ እስኪ ወጣ፤ አመጽ እስኪቀሰቀስ እየጠበቀ ነው?። ጽዋው ሲሞላ ማጣፊያው እንደሚያጥር አያውቅም። ለምንድን ነው ይሄን አጉራ ዘለል የግብይት ስርዓት አደብ የማያሲዘው። መቼ ነው ከዘመቻና እሳት ከማጥፋት አሰራር የሚወጣው።
ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይሄን ኢኮኖሚያዊ ትብታብ አሁን ላለው መንግስት በእዳ የተላለፈለት እንጂ ለብቻው የፈጠረው አይደለም። ሆኖም ይሄን ትብታብ የመፍታት ኃላፊነት ትከሻው ላይ ወድቋል። እንደ ሰበብ/excuse/ ሊጠቀምበትም አይችልም። የጦርነቱ ጫናም ቀላል አይደለም። በባህሪው ገበያ ድንጉጥ ነው። አይደለም ጦርነትና የግጭት አዙሪት የተሳሳተ የገበያ ትንበያ/speculation/ ገበያን ያስበረግጋል። ይሄን ችግር ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ሸማቹ ሕዝብ የመንግስት ቁርጠኝነት በሙላት ሲገለጥ አለማየቱ ነው። በዚህ የተነሳ ከዛሬው ነገ እንዳይከፋ አስፈርቶታል። አስጨንቆታል ።
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም ግብርናን፤ የቆላ ስንዴን ፤ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት፤ የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ጥረት እያደረገ ነው። ሆኖም ምርት ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ብልሹው የግብይት ስርዓት ካልታረም፤ ደላላው ከገበያው ካልወጣ፤ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በሕግ ስርዓት ማስያዝ ካልተቻለ፤ ማህበራዊ ስብራታችን ካልታጀለ ምርታማነታችን የቱንም ያህል ቢያድግ ከዚህ አዙሪት መቼም ቢሆን ሰብረን መውጣት አንችልም ።
ሆኖም ይሄ ችግር በመንግስት የተናጠል ጥረት ብቻ አይፈታም። ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ያሉ ማህበራት፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ እንደ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ ተቋማት ይሄን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምር በማድረግ የፖሊሲ ሀሳብ ማመላከትና ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል።
ይሄን ሁሉ ተቋም ተሸክመን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዴት እንደ ስፔስ ሳይንስ እስከ መቼ እንደተወሳሰበብን ይቀጥላል። በእርግጥ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የተፈጠረው በምርት እጥረት ነው፣ በግብይት ስርዓት ችግር፣ እሴት በማይጨምር ደላላ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች፣ በዩክሬንና በራሽያ ጦርነት፣ ወዘተረፈ ነው !? መልሱን በጥናት ማግኘት የማያዳግም መፍትሔ ለማስቀመጥ ይረዳል። በተረፈ ችግሩንና ተጠያቂነቱን ያለአድራሻ ማስቀመጥና ጣት መቀሳሰር ከተዘፈቅንበት አረንቋ አያወጣንም።
የውጭ ንግዳችን ከአገር ውስጥ ገበያው ይልቅ የውጭ ምንዛሬ ማሳደድ ላይ መጠመዱ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል። የቅባት እህል ወደ ውጭ ልኮ የፓልም ድፍድፍ ገቢ ያደርጋል። አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ ልኮ መድሀኒት በውጭ ምንዛሬ ያስገባል። የውጭ ንግድ መሠረቱንና አይነቱን ማስፋት ሲገባው ከሸማቹ ጉሮሮ እየቀማ ወደ ውጭ ይልካል። ይሄ የተፋለሰና ወለፈንዲ የሆነ አሰራር በጥናት ተፈትሾ መስተካከል አለበት። የአገር ውስጥ ገበያን እያራቆቱ ምርትን ወደ ውጭ መላክ ለዜጋው አለማሰብ ነው።
መንግስት የግብይት ስርዓቱን ስድ መልቀቁ የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን አባብሶታል። ስለሆነም በሕግና በአደረጃጀት ነገ ዛሬ ሳይል ስርዓት ሊያሲዘውና የቁጥጥርና የክትትል አሰራር ሊዘረጋ ይገባል። የመኖሪያና የንግድ ቤት ኪራይ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ ችግሮች ዋናው ነውና ተመን ሊወጣለት ይገባል። በመሠረታዊ ሸቀጦች የትርፍ ሕዳግና የዋጋ ተመን ሊወጣ ግድ ይላል። ለሸማቾች ሲል ዘይት፣ ስንዴና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ቢያደርግም የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት ስለአልዘረጋ ገበያው ሊረጋጋ አልቻለም። መንግስት በዚህ ፖሊሲው ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ቢያጣም ለሸማቹ ጠብ ያለ ነገር የለም። ይህ ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሕግ ክፍተት መኖሩን ያሳያል። ስለሆነም በማያዳግም ሁኔታ ስርዓት ሊበጅለት ይገባል።
ትኩረት በኑሮ ውድነት አለንጋ እየተገረፈ ላለው ሸማች !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም