ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን በዓለም አደባባይ ስሟ በክብር እንዲጠራ የሚያደርገው የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። በትውልድ ቅብብሎሽ ዘወትር ደምቀው የሚታዩት ብርቅዬ አትሌቶቿ ከታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ባሻገር በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናም ጎልቶ የሚጠቀስ ስኬት አላቸው። በውድድሩ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ ከአንድ ጊዜ በቀር በሁሉም መሳተፍ የቻለችው ኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ በሰርቢያ ቤልግሬድ ተካሂዶ ባለፈው እሁድ ፍጻሜውን ባገኘው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶ ሃያ ስድስት አገራት አንደኛ ሆና በማጠናቀቅ ትልቅ ክብር መቀዳጀቷ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ከስምንት መቶ ሜትር ውድድር ውጪ በሁለቱም ጾታ በሶስት እርቀቶች ብቻ ተሳትፋ 4 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከእግር ኳስ ውድድሮች በቀር በእያንዳንዱ የዓለም የስፖርት መድረኮች ቀዳሚ ሆና የማጠናቀቅ ባህል ያላትን ኃያሏን አሜሪካ አስከትላ ከዓለም ሀገራት መሪ በመሆን አኩሪ ታሪክ ተጽፎላታል። ለዚህ ደግሞ ሁሌም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ነጭ ላባቸውን አፍስሰው የሚያኮሯት ጀግኖች አትሌቶቿ ከምንም በላይ ተወዳሽ ናቸው።
በቤልግሬድ ቆይታው የሀገሩ ስምና ብሔራዊ መዝሙር በተደጋጋሚ ጎልቶ እንዲደመጥ ሰንደቅ ዓላማውም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በጀግንነት ተልእኮውን የተወጣው የጀግኖች ስብስብ ወደ አገሩ በሰላም ተመልሷል። ቡድኑ ወደ አገሩ ተመልሶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም በማርሽ ባንድ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ትናንት ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የደረሰው ቡድኑ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ፣ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አባላት፣ የአትሌቲክስ ስፖርት ሙያ ማህበራት ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አበርክተውላቸዋል።
በቀጣይም ጀግኖቹ አትሌቶች ለሕዝብ እይታ ክፍት በሆነ ተሽከርካሪ ተሳፍረው በክብ እጀባ በውጤቱ ለተደሰተባቸው ሕዝብ ሰላምታ እያቀረቡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተዘዋውረዋል። ጀግኖቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የክለብ መሪዎቻቸው በተገኙበትም ላስመዘገቡት ውጤት የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቁ አትሌቶች 40 ሺ ብር ሲያገኙ፤ የብር ሜዳሊያ ባለቤቶች 25 እንዲሁም የነሃስ ባለሜዳሊያዎች 15ሺ ብር ተሸልመዋል። አሰልጣኞች እንዳስገኙት የሜዳሊያ ብዛት እንዲሁም የቡድኑ አባላት እንደየተሳትፏቸው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፤ ስለተገኘው ድል የእንኳን ደስ አለን መልእክት አስተላልፈዋል። ጥረት፣ ህብረት እና በአንድነት መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ከዚህ ብሄራዊ ቡድን መመልከት ተችሏል። ሜዳሊያዎቹን ያስመዘገቡት ዘጠኝ አትሌቶች ይሁኑ እንጂ ድሉ ግን በቻምፒዮናው ላይ አገራቸውን የወከሉት 14 አትሌቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በመሆኑም ውጤታማ አትሌቶች ክብር እንደሚገባቸውና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በየትኛውም ጉዳይ ከጎናቸው እንደሚሆን ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም በተመሳሳይ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቷን በማስተላለፍ፣ ድሉ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና ያደረገችበት መሆኑን በፍጹም ደስታ ተሞልታ ተናግራለች። የጀግኖቹ ቡድን መሪ ወይዘሮ አበባ የሱፍ፤ የቡድኑ አባላት ከልምምድ እስከ ውድድር ከፍተኛ የቡድን ስሜት እንደነበረው ገልጸዋል። ከውድድሩ አስቀድሞ በእቅድ እንደተያዘውም አረንጓዴውን ጎርፍ ቡድኑ ማሳካቱን እንዲሁም በውድድሩ ከዓለም አንደኛ በመሆን አዲስ ታሪክ መጻፋቸው ያሳደረባቸውን የደስታ ስሜት አጋርተዋል።
በቻምፒዮናው ላይ አትሌቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡት አሰልጣኞች መካከል 2 የወርቅ፣ 1 የብር እና 1 የነሃስ ሜዳሊያ እንዲገኝ ምክንያት የሆኑት አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎም ደስታቸውን አንጸባርቀዋል። አሰልጣኙ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቁጭት እንደነበረባቸውና በሰሩት ልክ አስደሳች ውጤት በመገኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ውጤታማ በመሆን የአገራቸውን ስም ያስጠሩ አትሌቶችም ክብር እንደሚገባቸው አስታውሰዋል። የ3ሺ ሜትር አሰልጣኙ መላኩ ደረሰ በበኩሉ ድሉ በቤት ውስጥ ቻምፒዮናው ብቻም ሳይሆን፤ በዩጂኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ በመድገም ሕዝባቸውን እንደሚያስደስቱ ቃል ገብተዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነው አገራቸውን በማስቀደም ውድድሩን ያጠናቀቁት አትሌቶች ስላገኙት ክብርም የተሰማቸውን ደስታ አንጸባርቀዋል። ውጤቱ በመተባበር የተገኘ መሆኑንና በቀጣዩ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ውጤታማ ለመሆን ያላቸውን ተነሳሽነትም አሳይተዋል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ በ10 ሺ ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው እንቁው ወጣት አትሌት ሰለሞን ባረጋ፤ በቤልግሬዱ ቻምፒዮናው የ3ሺ ሜትር ባለድል መሆኑ ይታወቃል።
አትሌቱ ‹‹በሁለቱም ውድድሮች የተሳተፍኩባቸው ርቀቶች የዙር ብዛት እንጂ ስሜቱ ተመሳሳይ እንደሆነ ነው። ውጤታማ ለመሆኔ ምክንያትም ሥራዬን በትኩረት በመስራቴ ሲሆን፤ አገሬን ወክዬ በዓለም አደባባይ ስሟን በማስጠራቴም ደስ ብሎኛል›› ብሏል። አያይዞም የሴቶች ከ 20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አቀባበል ስላደረገላቸው መደሰቱን ጠቅሶ፤ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም